በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛትነት ለመቀራመት ሲሉ በግዴታና በጫና ያሰመሯቸው የመልክዓ ምድራዊ ጠረፎች እውነተኛ የሆነ ድንበር ዘለል እንቅስቃሴ ሲደረግ ትርጉም ይኖራቸው ይሆን? እውነተኞቹ ድንበሮችስ የት ነው ያሉት? ሲል ካሉንዲ ሴሩማጋ ይጠይቃል። ካሉንዲ ሴሩማጋ ባሕላዊ አክቲቪስት፤ ጋዜጠኛና የፈጠራ ጸሐፊ ሲሆን የሚኖረው ኡጋንዳ ካምፓላ ነው።
ካሉንጊ ድንበሮች (ጠረፎች) ለአምባገነኖች ዋጋ አላቸው ይላል። አምባገነኖች ድንበሮችን የሚያዩት የእነሱ ሥልጣን በሚሠራበት መልኩ እንደሆነ አያጠያይቅም። አምባገነኖች የጠላቶቻቸውን ማንነት ገፈው ሊያጠፉ የሚፈልጉበት አንዱ ነጥብ ነው። በአፍሪካ የማንነት ጉዳይ በመጠኑም ቢሆን አወዛጋቢ ባሕርይ አለው። ለዚህም ምክንያቱ በሁለት ዘመናዊ በሆኑ ማንኛውም ብሔረሰቦች መካከል ያለው ልዩነት በገዘፈ መልኩ በአምባገነንነት መሞላቱ ነው ይላል ካሉንዲ።
ማሕበረሰቦች አንዳንዴም ራሱ ቤተሰብ ጭምር በአገሩ ውስጥ የሚገኙ የሌሎችን አገራት ዜጎች የሚያየው በ1885 (እ.ኤ.አ) በርሊን ጀርመን በተደረሰባቸው አፍሪካን የመቀራመት ስምምነቶችና በግዴታ በተጣሉት አዲስ የድንበር መስመሮች መነሻነት ነው።
በቅኝ ገዢዎች አንዱን አገር ከሌላው አገር ለመለያየት የተሰመረው ድንበር የማይገናኙ ነገሮች አሉት። አንድን ሕዝብ የተለያየ አገራት ውስጥ በግዴታ በመክተት የከፋፈለ ነው። አሁን ያሉት ድንበሮች ከዚህ ነጥብ መነሻነት ሲታዩ የሕዝቦቹን ማንነት በማዛባት በሁለት አገራት ድንበሮች ውስጥ እንዲኖሩ እንዲከለሉ ያስገደደ ነው።
የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ካጋሜ ሩዋንዳና ሩዋንዳውያንን ከኡጋንዳ ጎረቤቶቻቸው መለያየት ከፈለጉ ድንበሮቹን ከመዝጋታቸው በፊት በመጀመሪያ የአገራቸውን ድንበር ወደሰሜን ከ100 ኪሎሜትር በላይ ማስፋትና የጥንቷን የሩዋንዳን ኢምፓየር መጠየቅ አለባቸው። ፓውል ካጋሜ በመጋቢት መጀመሪያ በሩዋንዳ በኩል የሚገኘው ዋናው የሩዋንዳና የኡጋንዳ ድንበር ማቋረጫ እንዲዘጋ ትእዛዝ ሰጥተዋል።
ድንበሮች አምባገነኖች እንደሚፈልጓቸው ሁነው ጥቅምና አገልግሎት አይሰጡም። በአሁኑ ወቅት በኡጋንዳና በሩዋንዳ መካከል ድንበሩን አስመልክቶ የተፈጠረው ውዝግብ በሁለት ኮምፒዩተሮች መካከል በታይፕ መጻፊያው ባለቤትነት ላይ ያለ ክርክር ነው የሚመስለው። በአማራጭ ካጋሜ ምናልባትም ሩዋንዳን በጣም በጥልቀት ወደ ደቡብ ማሳነስ፤ መኖሪያቸውና አነስተኛ መንግሥቶቻቸው ጭምር በ1911 (እ.ኤ.አ) በግዴታና በኃይል በጀርመን ቅኝ ገዢዎች ሙሉ በሙሉ በአሁኗ ሩዋንዳ የተቀላቀሉትን ሕዝቦች የእኔ አይደሉም ማለትም ሊኖርባቸው ነው።፡
ሩዋንዳ ረዥም የስደተኞችና የስደት ታሪክ ያላት አገር ነች። ኡጋንዳ ደግሞ በሕዝቦቿ ላይ በአውሮፓውያን በግዴታ የተጣለባትን መሰረት የያዘ ቅራኔ ለመፍታት አዲስ መጤዎችን በብዛት ትጠቀማለች። እጅግ በጣም ብዙ የሩዋንዳ ስደተኞች በኡጋንዳ ኖረው አልፈዋል። በኡጋንዳ ፖለቲካ ውስጥም ትርጉም ያለው ተጽዕኖ ነበራቸው።
ይህ ሁኔታ ከሌላውም ዓለም የተለየ አይደለም። አርጀንቲናዊው ኤርኔስቶ ቼ ጉቬራ በኩባ ውስጥ በነበረው አብዮታዊ አስተዋጽኦ ይታወቃል። የቀድሞ ስሙ ኤርኔስቶ ጉቬራ ሊንች ነበር። ቼ በክፍለ ዘመናት የእንግሊዝ ቅኝ ግዛታዊ ተጽዕኖ በአይሪሾች ላይ በተፈፀመው የኢኮኖሚ ጥፋት ከተሰደዱት ብዙዎች የአይሪሽ ቤተሰቦች ዝርያ ውስጥ ነበር። በኋላም ግብጽና ሌሎችም ዓረብ አገራት የእሥራኤልን መንግሥት ወግተዋል።
አንድ ጊዜ አሚን አልዳዳህ (የቀድሞው የኡጋንዳ መሪ) ፕሬዚዳንት ከሆነ በኋላ ከእነዚህ አማጽያን (ስደተኞች) መካከል ጥቂቶቹ ለጀነራሉ የልዩ ኃይል ጥበቃ መስርተዋል። እነዚህ ሰዎች በደህንነት አገልግሎታቸው ልዩ ክብር ለማግኘት በቅተዋል። ብቻቸውንም አልነበሩም። የአሚን ኢንተለጀንስ (ደህንነት) አባላት የነበሩት የሩዋንዳ ስደተኞች እንዲሁም የብረት እናት በመባል የሚታወቁት ከጥቂት በላይ የሆኑ ፓለስቲኒያውያን አሚን ከምዕራቡ ዓለም ጫና በበረታበት ወቅትም ከጎኑ በመቆም አገልግለውታል።
የኡጋንዳ መንግሥት የተመሰረተው ከሌሎች አካባቢዎች በመጡ ሰዎች ነው። ሁለቱን ዋነኛ ተቀናቃኞች የቡንዮሮን ንጉሥ ካባላጋ እንዲሁም የቡጋንዳን ሙዋንጋ ለማንበርከክ የእንግሊዝ ቅኝ ገዢ ካፒቴን ፍሬድሪክ ሉጋርድ በዛሬ ኡጋንዳ ተብላ በምትጠራው ሰሜን ምዕራብ ውስጥ 1898 (እ.ኤ.አ) ረዥም ጉዞ በማድረግ በሱዳኑ ኮማንደር ሳሊም ቤይ ተነጥሎ በሚመራው ማዘዣ ጣቢያ ለመድረስ ተጉዟል።
ሳሊም ቤይ በወቅቱ ምሽጉን ይዞት የቆየው የአንግሎ ግብጽ ጦር ሰፈር አዛዥ ለነበረው ጀነራል ጎርደን ታማኝ መኮንን በመሆን ነበር። ቤይ በ1885 (እ.ኤ.አ) ካርቱም ውስጥ በእስላሚክ ሚሊታንቶች ተገድሎአል። ሉጋርድ በኋላ ላይ ወታደሮቹን ወደተያዘችው ቡጋንዳ መልሷቸዋል። በየቀኑ በሁለት የመመልከቻ ጣቢያዎች ሁኖ ሰንሰለት በመዘርጋት ሠራዊቱ በካባልጋ አንገት ዙሪያ እንዲጠመጠም አድርጓል።
ብዙዎቹ የኡጋንዳ እግረኛ ወታደሮች ከደቡብ ሱዳን፤ ከሰሜን ምዕራብ ኡጋንዳ አካባቢዎችና አሚን ራሱ ከተገኘበት አካባቢ ጭምር የተዋሀዱበት ምክንያት ይሄ ነው። ይሄ የመጀመሪያው የኡጋንዳ ሠራዊት ነው። በተለይ ቅኝ ግዛት ከተመሰረተ በኋላ ።
ለዚህ ሁነኛ መገለጫው እንዴት ጥቂትና ከፍተኛ የአሚን ዘመን የደሕንነት ሠራተኞች በጁባና በሌሎችም የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች ከሚገኙ በአሚን ላይ ተቃውሞ ካላቸው የኡጋንዳ ሴት ጓደኞቻቸው ጋር በመቀናጀት በ1979 (እ.ኤ.አ) ከታንዛኒያ ሠራዊት ጋር በማበር አሚንን ለመጣል የሄዱበትን መንገድ ማየት በቂ ነው።
የፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ መንግሥት በባህርይው የተለየ ነው። የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር መስራቾች ፓውል ካጋሜና ፍሬድ ሪዊጊይማ የኡጋንዳ ወታደራዊ ኢንተለጀንስ ምክትል ዳይሬክተርና የኡጋንዳ መከላከያ ምክትል ሚኒስትር ነበሩ። ሁለቱም ኃላፊነታቸውን ለቀው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባርን በመመስረት በኋላም ጦርነት ውስጥ በመግባትና በማሸነፍ በሂደት በኪጋሊ ሩዋንዳ የፖለቲካ ሥልጣኑን ተቆናጠዋል።
በእርግጥም በስም ተዘርዝረው የሚገለፁት ሩዋንዳውያን (አንዳንዶቹ አልፈዋል)። ዛሬ ርዕስ በርዕሳቸው የሚጣሉት እነዚህ ሰዎች የኡጋንዳ ማክሬሬ ዩነቨርሲቲ ተማሪዎችና የኡጋንዳ መንግሥት የቀድሞ ሠራተኞች የነበሩ ናቸው። እነዚሁ የሩዋንዳ ባለሥልጣናት በመገናኛ ብዙሃን ወጥተው ከኡጋንዳ ጋር ስለተፈጠረው አለመግባባት ሲናገሩ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ሳይሆን የኡጋንዳ ቅላፄ ባለው እንግሊዝኛ መናገራቸው በጣም አግራሞት ይፈጥራል። ያደጉት፤ የኖሩት፤ የተማሩት፤ ኃላፊነት ይዘው ይሠሩ የነበሩት በኡጋንዳ ውስጥ ነበርና።
የአፍሪካ የስደተኞች ሥርዓት በተለያዩ መልኮች ነው የሚሠራው። ለምሣሌ በቡጋንዳ የቅኝ ግዛት ስደት ከመጀመሩ በፊት ማህበረሰቦች የሚሰፍሩት ከ50ው የትውልድ ዝርያቸው በአንዱ ወይም በሌላው ተቆጥረው ነው። ሙሉ ዜጋም ይሆናሉ። ድንበሮች (ጠረፎች) የሚያገለግሉት ለገዢዎች ነው። የእኛ ድንበሮችና ጠረፎች ያሉት በተወላጅነት ተቋሞቻችን፤ በባህላችንና እነዚህን እንዲቀጥሉ በሚያደርገው የሰውኛ ዋጋችን ውስጥ ነው።
ከነዚህ ዛሬ ከዚህና ከዚያ በሚል በግድ በድንበር ተለይተው እንዲኖሩ የተፈረደባቸው ጎሳዎች ስደተኞቹ ከመጡበት አገርም አሉ። ይኖራሉ። ይሄ ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በጣም የተለመደ ነው። እኔ የተወለድኩበት ትውልዳዊው የኔቩቡ (ሂፖ) ጎሳ እስከ ደቡብ ቡጋንዳና ዚምባዌ ድረስ ይገኛል ይላል ካሉንዲ ሳራማጋ። ዛሬ ላይ ያለው ሁኔታ እነዚሀን ታሪኮች መመርኮዝ አለበት። ያለፈው ጊዜ ዋጋ አለው። ታሪክ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። አሁንም ቢሆን ፖለቲካ ነው።
ፕሬዚዳንት ካጋሜ ልጅ ስደተኛ ሁኖ ያቋረጠውን ድንበር፤ ቤተሰቦቹም ተሰደው ገብተው የኖሩበትን ትላንት ዜጋ ሆኖ ያገለገለበትን መንግሥት እንደገናም ወደ አገሩ ተመልሶ ሄዶ የሩዋንዳን መንግሥት አውርዶ ሥልጣን ከመያዙ በፊት የኖረባትን አገር ድንበር እንዲዘጋ መወሰኑ በጠንካራ ሁኔታ የሚያሳየው እኛን ብዙ እንደማያስጨንቀን ነው።
መሪዎች ድንበር ዘጉም አልዘጉ ዋናው በጥልቀት ያለው ለዘመናት የኖረውና ሥር የሰደደው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ በምንም መልኩ የማያቋርጥ መሆኑ ነው። አሁን የተፈጠረው አለመግባባት በአገራት መካከል ያለ ግጭት ወይንም በየአገራቱ ባሉ ሕዝቦች መካከል ያለ አይደለም። የሁለቱ አገራት መንግሥታት በታላቁ ሐይቅ አካባቢ ተመሳሳይ ፍላጎት ይዘው የሚያደርጉት የጥቅም ፉክክር ነው። ለተለያዩ ምዕራባውያን ኃይሎች እንዲሁም ሰፊ ለሆኑ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች የሚፈልጉትን ቁስ ለማቅረብ የሚደረግ የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ግብግብና ትንቅንቅ ነው ብሎአል ሳሩማጋ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2011
ወንድወሰን መኮንን