ለሀገር የተከፈለ መስዋዕትነት

በነበራቸው የሥራ ሥነ ምግባር ፣ በሚከተሉት የሕይወት መርህ የተግባር ሰው መሆናቸውን በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ይመሰክሩላቸዋል። ትምህርት ወዳድ በመሆናቸው የቀለም ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ በተጓዙበት መንገድ የተሰጣቸው ኃላፊነት ጥንቀቅ አድርገው መወጣትን አሳይተዋል። ከፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ እስከ ኢትዮ- ሶማሊያ ጦርነት እንዲሁም በአስመራ መድፈኛ ሆነው አገልግለዋል፤ በአስተዳደር ሥራ ውስጥም ጭምር ተሳትፈዋል። ሀገር ከፖለቲካ ልዩነትም ሆነ ከጥቅም የጸዳ ስሜት መሆን ይገባዋል ብለው ያምናሉ፤ ሻለቃ ቡሎ ኢፋ። በዛሬው የሕይወት ገጻችን ወደ ኋላ መለስ ብለው ለሌሎች አርአያ የሚሆኑበትን የሕይወት ጉዟቸውን አጫውተውናል። መልካም ንባብ …

ሻለቃ እና ልጅነት

ትውልዳቸው በሸዋ ክፍለ ሀገር ወሊሶ ነው። እናታቸው አንጋቱ ሶቦቃ ሲባሉ አባታቸው ኢፋ ሁሉቃ በኦሮሞ የገዳ ሥርዓት በጊዜው ይመሩ የነበሩ ሲሆን በአካባቢውም የሚታወቁ ናቸው። የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉበት ቤታቸው በወሊሶ ጨፎ በምትባል ቦታ የቀድሞው አርበኛ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ቤት ፊት ለፊት እንደሆነ በምናብ ያስታውሳሉ።

ለወላጆቻቸው የመጨረሻ ልጅ ሲሆኑ ኑሯቸውን በግብርና ከሚመሩት ቤተሰብ የተገኙት ሻለቃ ቡሎ ልጅነታቸው ከእርሻ ይልቅ ለቀለም ትምህርት ቦታ የሰጠ ነበር። በወቅቱ በቤተሰባቸው ዘንድ ወደ ትምህርት የገቡ ጥቂት ቢሆኑም በልጅነት አዕምሯቸው ትምህርትን በዚህ ልክ የመውደዳቸውን ምክንያትም ሲያስረዱ ‹‹ ቤተሰቦቼ ባለመማራቸው ለአንዳንድ ጉዳዮች ውል ሲያጽፉ ገንዘብ ይከፍላሉ፤ መጻፍ የሚችለው ሰውም ቀጠሮ ሲያበዛባቸው በጣም ይከነክነኝ ነበር። ›› በማለት ለመማር ጉጉት እና ቁጭት እንዳደረባቸው ይገልጻሉ።

ሻለቃ ቡሎ በወሊሶ ከተማ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ትምህርታቸውንም ለመከታተል ችለዋል። ወቅቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ እዚህም እዚያም የሚቀሰቀስበት ነበርና በሚማሩበት ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበሩ ተማሪዎች ባነሱት አመጽ ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜ ከትምህርት እንዲታገዱ ተደረገ። ታዲያ ታዳጊው ቡሎ ይህንን አንድ ዓመት ቤታቸው ተቀምጠው እርሻ ማረስን አልፈለጉምና ትምህርታቸውን ለመቀጠል ጉዟቸውን ወደ አዲስ አበባ አደረጉ።

ጉዞ ወደ አዲስ አበባ

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ተስፋ ያደረጉት በአዲስ አበባ የሚገኙ ዘመዶቻቸውን ነበር። ነገር ግን እነርሱ የሚሰሩት በፋብሪካ ውስጥ በመሆኑ ያላቸው ገቢ ይህንን ለማድረግ እንዳልፈቀደላቸው ሻለቃ ቡሎ ያስታውሳሉ። ታዲያ በአንድ ቀን ወደ ክቡር ዘበኛ እንዲገቡ በሬዲዮ የተላለፈውን ጥሪ ያደምጣሉ። ‹‹ወደ ፖለቲካ የመግባት ምንም ፍላጎት አልነበረኝም። ነገር ግን መማር ስለምፈልግ ሠራዊቱ ውስጥ ገብቼ መማር እችላለሁ ብዬ ስላሰብኩ ክቡር ዘበኛ ውስጥ ለመቀጠር ወሰንኩ እና ወደ ጃንሜዳ ሄድኩ። ›› ይላሉ።

ሻለቃ ቡሎ በማንኛውም አጋጣሚ የትምህርት ፍላጎታቸውን እውን አድርገው በቀለም ትምህርታቸው መቀጠል ይሻሉ። የክቡር ዘበኛ ምዝገባቸውን አጠናቀው ሲመለሱ በጊዜው አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ የፖሊስ ሠራዊት እየቀጠረ በመግቢያው ላይ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው ይመለከታሉ፤ ጉዳዩን ለማጣራት ጠጋ ያሉት ቡሎ የነበራቸው ወጣትነትና ቁመናቸው ፖሊስ ለመሆን የሚጠይቀውን ቅድመ ሁኔታ የሚያሟላ ነበርና በአንድ የፖሊስ አመራር እይታ ውስጥ ገቡ። ከክቡር ዘበኛ ይልቅ በዚያ መቆየትን መረጡ በፖሊስ ጣቢያውም የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሆነው ተቀጠሩ።

ወደ አዲስ አበባ የመጡት ለትምህርት ቢሆንም ነገር ግን ፖሊስ የመሆናቸው ነገር ለቤተሰቦቻቸው ለማሳመን በየጊዜው እየተመላለሱ እንደሚጠይቋቸው እና የሥራ ስምሪታቸው በተወለዱበት ቦታ ሊሆን እንደሚችል ነገሯቸው ያን ያህልም ተቃውሞ አልገጠማቸውም። በፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሆነው ትምህርታቸውንም አስረኛ ክፍል ደርሰው መማራቸውን ቀጠሉ። ትምህርታቸውን ለመማር የመረጡት የሥራ ዘርፍ ያን ያህል የተመቸም አልነበረም። በፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ውስጥ ሳሉ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር በገጠማት ጦርነት ወደ ሶማሊያ እንዲላኩ ትእዛዝ ተሰጠ።

ወደ ሶማሊያ ጦርነት ሲላኩ

ሻለቃ ቡሎ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን በኦጋዴን የአስረኛ ሻለቃ ፈጥኖ ደራሽ አባል ሆነው የሶማሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስነው ዳር ድንበር ላይ የሚያደርገውን ትንኮሳ እና ጥቃት ለመከላከል ፤ በኦጋዴን ጎግቲ ፣ ተፈሪ በር ፤ ቶጎ ጫሌ የሚሰኙ ቦታዎች ላይ በወር ተራ እየተዘዋወሩ ድንበር የማስከበር ሥራ ከአባሎቻቸው ጋር መሥራት ጀመሩ። ‹‹ ሶማሊያ ውጊያውን የከፈተችው ሐምሌ አምስት 1969 ዓ.ም በቶገ ጫሌ ላይ ነበር። ከዚያ በፊት በሰርጎ ገቦች የተለያዩ ውጊያዎች ነበሩ። ውጊያውን በመድፍ፣ በአየር በሜካናይዝድ ጦር ከፍተኛ ውጊያ አድርገዋል። ›› በማለት ጊዜውን ያስታውሳሉ

ውጊያውን ለመከላከል በቦታው የነበረው የእነ ሻለቃ ቡሎ ጦር የአስረኛ ብርጌድ እና የሶስተኛ ክፍለ ጦር አካል የነበረው ኃይል ውስን በመሆኑ ወደ ጂግጂጋ ተመልሶ በዚያ የመከላከል ሥራውን መሥራት ቀጠለ። ነገር ግን በጊዜው ከሶማሊያ ጦር ጋር የነበረው የኃይል መመጣጠን እጅግ አነስተኛ እንደነበር የሚያነሱት ሻለቃ ቡሎ ሆኖም ግን በሠራዊቱ ውስጥ የነበረው ወኔና ሞራል ሞት አልያም ሀገር ብለው በፍጹም ጀግንነት ሲዋጉ እንደነበር ያስታውሳሉ።

‹‹እኛ በጊዜው የታጠቅነው የአሜሪካን የጦር መሳሪያ ነበር። የሶማሊያው ጦር ደግሞ የራሺያን ዘመናዊ ጦር በመሆኑ የማረክነውን መድፍ ወደራሳችን ቦታ ለመውሰድ ከብዶን ነበር። ›› ይላሉ መድፉንም የማረኩት ከጅግጅጋ ወጣ ብሎ በሚገኝ ሃሮሬሳ የሚባል ቦታ ላይ ነበር። ሻለቃ ቡሎ ጦርነቱ በይፋ ተጀምሮ ቶጎ ጫሌ ላይ ውጊያውን ሲቀላቀሉ የያዙት ላውንቸር ብቻ ነበር። ሻለቃ ቡሎ በሚዋጉበት ጦርነቱ የተጀመረው ንጋት እየተቃረበ በመጣበት ሌሊት 11 ሰዓት በኋላ በተደረገ ውጊያ ሻለቃ ቡሎ እዚያው ቶጎ ጫሌ ላይ አንድ ታንክ ማቃጠላቸውን፤ የተቃጠለው ታንክም አሁንም ድረስ እዚያው ቶጎ ጫሌ ላይ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።

ውጊያውን ከበላይ አለቆቻቸው ጋር በመናበብና በሚሰጣቸው ትእዛዝ የሚያደርጉት ሲሆን በተሰጣቸው ትእዛዝ የነበሩበትን ምሽግ ጥለው ሲወጡ የቆሰሉ እና የተጎዱ የትግል ጓዶቻቸውን በዚያው ትተው በእጃቸው ላይ የቀረውን ቦንብ ሰጥተዋቸው ነበር ከምሽጋቸው የወጡት።

የሶማሊያ ጦር ኃይሉን አሰባስቦ ከአንድም ሁለት ጊዜ ከተማዋን ሲቆጣጠር የሻለቃ ቡሎ ጦር በካራማራ ላይ ሆኖ ይከላከል ነበር። በወቅቱ በካራማራ የምስራቅ አፍሪካን መቆጣጠር የሚያስቸል ራዳር እንዳይመታ ይጠብቁ እና ይከላከሉ ነበር። ከዚያም ሁኔታው አስጊ መሆኑን ሲያውቁ በአየር ኃይል ሙያተኞች እንዲወርድ ተደረገ ይላሉ ሻለቃ ቡሎ።

‹‹በዛ ጦርነት ብዙ ዜጎቻችን አልቀዋል ፣ ነገር ግን ጓደኛዬ አረፈ፤ ወገኔ ሞተ ብሎ ወደ ኋላ የሚል አልነበረም። በከፍተኛ ወኔ ነበር የምንዋጋው። ››

በማለት የነበረውን ሞራልም እንኳን ሠራዊታችን ይዋጋል መሬታችን የሚለውን መፈክር ጭምር ያስታውሳሉ። ሻለቃ ቡሎ ወጣትነታቸው ድፍረት ፣ ለሀገር ዋጋ ለመክፈል ወደኋላ አለማለት የታጀበበት ነበር። በሶማሊያ ጦርነት ያሳለፉትን ከባድ ጊዜ ግን አሁንም ድረስ ያስታውሱታል። ‹‹ ቆሬ የሚባል ቦታ ላይ ከጓደኛዬ ጋር የቀበሮ ጉድጓድ ወይንም ምሽግ እየቆፈርን ነበር። ምሽግ የሚቆፈረው ከአንገት በታች የሚቀብር ሲሆን ሶማሊያ ደግሞ በጣም በመድፍ ጥቃት በማድረስ ምሽግ ውስጥ ሆነን እንዳናየቸው ያደርጋሉ። እኛም ደግሞ የጥንቃቄ ሄልሜት አድርገን ነበር የምንቆፍረው። ሄልሜታችን ምግብ የምንሰራበት፣ ውሀ የምንጠጣበት፣ ራሳችንን ከጥይት የምንከላከልበት ነው። ምሽግ ስንቆፍር ደግሞ አፈር እንዳይበንብን እንዳንታይ የምንጠቀምበት ነው። ታዲያ በዚህ ሰዓት ድንገት የመጣ ሞርተር ጓደኛዬን ነጠቀኝ። ›› በማለት ከአሳዛኝ ገጠመኛቸው አንዱን ያነሳሉ።

ከካራ ማራ በኋላም ቆሬ የምትባል ቦታ ላይ በተደረገ ከፍተኛ መከላከል የጠላት ጦር ሰብሮ እንዳይገባ አድርገዋል። በመጨረሻም በተደረገ የኃይል ጭማሪ ካራማራን ሰብረው በመግባት የሶማሊያን ጦር ከኢትዮጵያ ምድር ማስወጣት መቻሉን ያስታውሳሉ ።

የሀገር ጥሪ በአስመራ

ሻለቃ ቡሎ ቀደም ሲል በነበራቸው ሥራ በፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ውስጥ ያገለግሉ ነበር። ከዚያም በደረሳቸው የሀገር ጥሪ በኦጋዴን ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ባደረገችው ጦርነት ላይ ተሳትፈዋል። ታዲያ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ባደረገችው ጦርነት ያገኘቸውን ድል ወደ ሰሜኑ ለመድገም በሚል ወደ አስመራ እንዲጓዙ ትእዛዝ ተሰጠ። ሻለቃ ቡሎ የሀገር ጥሪው ይመለከታቸው ነበርና በአዋሽ አርባ ማሰልጠኛ ውስጥ ለተወሰኑ ወራት ቆይተው የሶስተኛ እግረኛ ክፍለ ጦር ተደራቢ የ508 ስምንት ግብረ ኃይል አካል በመሆን ወደ አስመራ አቀኑ። ወደ አስመራ በሚያደርጉት ጉዞም ጎንደር ትክል ድንጋይ ፣ ሑመራ፣ ገርገፍ፣ ጋሉች ሰብደራት የሚባሉ ቦታዎችን አቆራርጠው ባሬንቱን አልፈው ከረን የሚባሉ ቦታዎችን በእግር ማለፍ ይገባቸው ነበር። በጊዜው 147ተኛ መድፈኛ የ14ተኛ እግረኛ ክፍለ ጦር ሻለቃ ነበሩ።

ሻለቃ ቡሎ በነበሩበት ቦታ የሠራዊቱ ትጥቅ መደራጀት አለበት በሚል በትምህርታቸው ጥሩ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ሠራዊት ውስጥ በመምረጥ መድፈኛው እንዲደራጅ ተደረገ። በዚህም ይላሉ ሻለቃ ቡሎ ከራሺያ ሀገር የመጣ 122 ሀውቲዘር መድፍ እንዲታጠቁ ተደርጎ በውጊያው እግረኛውን እያገዙ ቆዩ። ከረን ላይ የተገናኘው ሁለት ግብረ ኃይልም በመግፋት እና በማገዝ ወደ ናቅፋ አመራ። ረጅም ጊዜ ውጊያ የተደረገበት የቀይ ኮከብ እና የባህረ ነጋሽ ዘመቻ የተካሄደበት ውጊያም ጭምር ነበር። በእነዚህ የውጊያ ጊዜያት ሠራዊቱ ከፍተኛ የሆነ የመከላከል እና የማጥቃት ሥራን የሰራው በአልጌና እና በናቅፋ ግንባር እንደነበርም ያስታውሳሉ።

ሻለቃ ቡሎ ቅጥራቸው ፈጥኖ ደራሽ ቢሆንም ከዚያ ውስጥ ለመድፈኛነት ተመርጠው የመኮንንነት ኮርስ ስልጠና በ1972 ዓ.ም በሀረር አካዳሚ ከወሰዱ በኋላ ተመልሰው በሶስተኛ እግረኛ ክፍለ ጦር 37ተኛ መድፈኛ ከነበሩበት ስልጠናውን ጨርሰው ወደ አስመራ ሲመለሱ የ147ተኛ መድፈኛ ሻለቃ እንዲመደቡ ተደረገ። ውጊያው እስካበቃበት ጊዜ የሻለቃ ማዕረግ እድገትን አግኝተው የአራተኛ መድፈኛ ብርጌድ የሎጀስቲክ ኃላፊ ሆኑ። በጊዜው አራተኛ ብርጌድ ማለት አስመራ የሚገኘው የሁለተኛ አብዮታዊ ሠራዊት መድፈኛ ብርጌድ ነበር።

በገጠማቸው የሀገር ጥሪ ወደ አስመራ ሲያቀኑ በተሰጣቸው ኃላፊነት ውስጥም የጀመሩትን ትምህርት በዚያም አልተውትም ነበር። በጊዜው የነበረው ሥርዓተ ትምህርት ተቀይሮ ነበርና ተስፋ ሳይቁርጡ እንደገና ከስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን መማር ጀመሩ። በጥሩ ውጤትም የስምንተኛ ክፍልን አጠናቀቁ። የዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን በአስመራ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት እየተማሩ ጉብዝናቸውን ያዩ መምህር በጊዜው የሚሰጠውን ማትሪክ ፈተና እንዲወስዱ ያበረታቷቸው ነበር።

ሻለቃ ቡሎ 147ተኛ መድፈኛ ሻለቃ ውስጥ በተሰጣቸው ኃላፊነት በብዙ የሥራ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ይሰሩ ነበር። በባትሪ አዛዥነት ማለትም አራት መድፎች የያዘ አንድ ባትሪ ተብሎ ሲጠራ የዚያ አራት መድፎች የያዘ አንድ ባትሪ ተብሎ ሲጠራ የዚያ አዛዥ ሆነው ይሰሩ ነበር። ከዚያም በቅርብ አለቃቸው ኮሎኔል ከበደ አማካኝነት የነበራቸውን በሳል የመሪነት ችሎታ ተገንዝበው በአስተዳደር ሥራ ላይ ሊሾሟቸው እንደሚፈልጉ ነገሯቸው።

ሻለቃ ቡሎ ግን ወጣትነታቸው ለውጊያ ለድል ያሰለጠኑትን ሠራዊት ድል ማየትን ይመኙ ነበርና ፍቃደኛ አልነበሩም። ነገር ግን የአለቃቸውን ትእዛዝ መሻር አልቻሉም ነበርና በአስመራ ጸጸራት የጦር ካምፕ ውስጥ የሚገኙ የሠራዊቱን ቤተሰብ እንዲያስተዳድሩ የሎጀስቲክስ ኃላፊ ሆነው ተሾሙ። የጦር ሰፈሩ መድፈኛ ሻለቃ መጥቶ የሚያርፍበት ተሽከርካሪዎች እና የጦር መሳሪያዎች ሲበላሹ ጥገና የሚያደርግበት እና የጦር ሠራዊት ቤተሰቡም የሚኖርበት ነው።

‹‹በጦር ካምፕ ውስጥ በግንባር ያለው ሠራዊት ስለ ቤተሰቦቻቸው በማሰብ እንዳይሰናከሉ ምክር መስጠት ፣ የወታደር ሚስቶች ወደኋላ እንዲመለሱ የሚያደርግ ደብዳቤ እንዳይጽፉላቸው መቆጣጠር እና የሠራዊቱን ልጆች መንከባከብ፣ ትምህርት እንዲማሩ ፣ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው እናደርጋለን። የተለያዩ የኳስ ትጥቆችን ገዝተን እንዲጫወቱ እናደርጋለን። ›› በማለት በጦር ካምፕ ውስጥ የነበረውን የቤተሰባዊነት ጊዜ ያስታውሳሉ። ወታደሮቹም ፍቃድ አግኝተው ቤተሰቦቻቸውን እንዲጎበኙም ጭምር ያደርጋሉ። በአስመራም ከጸጸራት የጦር ሰፈር በተጨማሪ ቃኘው የጦር ሰፈር ፣ ፎርቶ መጋላ የጦር ሰፈር የሚባሉ ነበሩ።

ቤተሰብ መመስረት

‹‹ስፖርተኛ ነበርኩ፤ ለምንም ነገር አልሳሳም፤ ደፋር ነበርኩ›› ሲሉ የወጣትነት ጊዜቸውን የሚያስታውሱት ሻለቃ ቡሎ የትዳር ሕይወትን የመሰረቱት በአስመራ ነበር። በአስመራ ካሉ የጦር ካምፖች ውስጥ በጸጸራት የጦር ካምፕ ውስጥ የሎጀስቲክስ ኃላፊ ሆነው ከሰሩ በኋላም በኪራይ ቤቶች በዚያው አካባቢ ይኖሩ ነበር። የትዳር አጋራቸው ወላጅ አባት የምድር ባቡር ኦፕሬተር ሆነው በአስመራ ከስልሳ አመት በላይ ቆይተዋል። ሻለቃ ቡሎም ከእሳቸው ልጅ ወይዘሮ በየነች በ1977 ዓ.ም ትዳር መስርተዋል። በአስመራ በቆዩባቸው ዓመታትም ሶስት ልጆችን አፍርተዋል። ሻለቃ ለተወሰኑ ዓመታት በአስመራ ቆይተው ሥራቸውን እየሰሩ፣ የሚወዱትን ትምህርት እየተማሩ እና ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ ቢኖሩም ነገር ግን ሌላ ፈተና ሳይገጥማቸው አልቀረም።

በ1983 ዓ.ም በሀገሪቱ በነበረው የኃይል ለውጥ አስመራን ለቀው ወደ ሱዳን መጓዝ የግድ ሲሆን ሲያቀኑ ቤተሰቦቻቸውን በዚያ ጥለው ነበር የሄዱት። ታዲያ ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው ጋር በድጋሚ መገናኘት የቻሉት በቀይ መስቀል አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ነበር።

ከአስመራ ወደ ሱዳን

በጊዜው የኃይል ለውጥ በመኖሩ እና ከአቅም በላይ በመሆኑ በ1983 ዓ.ም ወደ ሱዳን ሲጓዙ ቤተሰባቸውን ትምህርታቸውን ሁሉ ትተው በቦታው ከነበሩ እና በሕይወት ከተረፉ የትግል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን ነበር።

ጦሩም ሆነ የሠራዊቱ ቤተሰብ ይገኝበት የነበረው የጸጸራት ካምፕ ብዙውን ጊዜ የጠላት ኢላማ ውስጥ ይገባ እንደነበር የሚያስታውሱት ሻለቃ የጦር ሠራዊቱ ቤተሰቦች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ትልቅ ምሽግ በመቆፈር እና ቤተሰቡን በማሰልጠን ጥቃት ሲፈጸም ወደዚያ ምሽግ ከእነልጆቻቸው በመግባት ሊተርፉ ችለዋል።

በ1983 ሻዕቢያ የጦር የበላይነትን ይዞ ወደ አስመራ ሲጠጋ የአራተኛ መድፈኛ ብርጌድ የሎጀስቲክ ኃላፊ የሆኑት ሻለቃ ቡሎ ከፍተኛ የጥይት ዲፖ የነበረበትን ቦታ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እና ጥይት ለማንሳት ቢሞከርም ሙለ ሙሉ ለማንሳት ግን አልተቻለም። በፍጹም ጠላት እጅ መግባት የለበትም የሚሉት ሻለቃ ቡሎ በወሰዱት አፋጣኝ ርምጃ በቲኤንቲ ከፍተኛ ፈንጂ በጠቅላላ እንዲወድም አድርገዋል። ጦርነቱን ለማሸነፍ በጊዜው ከእስራኤል ሀገር የመጣ የድምጽ ቅኝት መሳሪያ እንደነበር የሚያስታውሱት ሻለቃ ‹‹መሳሪያው የመጣው በስውር ነበር። 46 የመኪና ባትሪ ነበር የሚያንቀሳቅሰው። ባትሪዎቹን የሚሞላ ሁለት የራሱ ጄኔሬተር ያለው እና የራሱ ሪሞት ኮንትሮልም ነበረው። ሲመጣም ከአውሮፕላን የተቀበልኩት እኔ ነበርኩ። መድፍ ከየት እንደተተኮሰ የሚነግር ጨረር የሚለቅ ነበር። ጠላት እጅ እንዳይገባ ከእስራኤል ሀገር በሚስጥር ነበር የመጣው›› መሳሪያውን ለመጠቀም ከምድር ጦር እና ከአየር ኃይል ተመርጠው ወደ እስራኤል ሀገር ሄደው ስልጠናውንም ወስደዋል።

በኋላም መሳሪያውን ለመጠቀመው የሚያስችለውን ሪሞት የተላከው በአንድ ባለሙያ በኩል ከእስራኤል ሀገር ወደ ምድር ጦር ነበር። ‹‹መሳሪያውን ኦፕሬት ለማድረግ የሰለጠነው ባለሙያውም ሪሞቱን ለማምጣት ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ተላከ። ሪሞቱን ይዞ ወደ አስመራ መምጣት ነበረበት። ግን ከአሜሪካ የመጣች እህቱ ተመልሰህ ወደ ውጊያ አትገባም በማለት ይዛው ከሀገር ወጣች። ›› በማለት የሚያስታውሱት ሻለቃ ቡሎ መሳሪያው በአስመራ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት አጠገብ የነበረ ራዳር ቦታ ላይ ቆሞ ነበር።

ውጊያው እልባት የሚያገኝበት የመጨረሻ ሰዓት ነበርና መሳሪያውን መጠቀም ባለመቻሉ ሻለቃ ቡሎ ይህ መሳሪያ በፍጹም ጠላት እጅ አይገባም በማለት በዚያው ቦታ እንዲወድም አደረጉት። ያጊዜም የጦርነቱ ማብቂያ ነበርና ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ሱዳን ጉዟቸውን አደረጉ። ቤተሰቦቻቸውን ትተው ለባለቤታቸውም ‹‹ቻው ደህና ሁኚ በሕይወት ከቆየሁ እንገናኛለን ፤ ካልተገናኘንም ልጆቼን አደራ ›› የሚለው ቃላቸው ነበር።

ከአስመራ ወደ ሱዳን በእግራቸው ሲያቀኑ የሎጀስቲክስ ኃላፊ ነበሩና የጥገና ክህሎትም ነበራቸው። ታዲያ በአስመራ ባዶሮ የሚባል ቦታ ላይ ያገኙትን የተበላሸ መኪና አስተካክለው የተወሰነ ጉዞ አድርገው ወደ ሱዳን ከሚሄደው ጦር ጋር መቀላቀል ቻሉ። በእግር ባደረጉት ረጅም ጉዞ ከረን ከደረሱ በኋላ ከዚያም አቆርደት ላይ ጦሩ ተሰባስቦ በጊዜው በነበሩ የሥራ ኃላፊዎች አቀናጅተው ነዳጅ ያላቸውን መኪኖች የጦር መሳሪያዎችን እየያዙ ነዳጅ ያለቀባቸውን ደግሞ የማቃጠል ትእዛዝ ተሰጠ።

ሻለቃ ቡሎ የመድፈኛው ብርጌድ ትእዛዝ ተሰጥቷቸው መሪዎችን እያጀቡ እና ጥቃት እንዳይደርስባቸው እየተከላከሉ ተሰኔ ከዚያም አሊግደር አንድ ቀን አደሩ። በዚያ ቆይታቸው አዲስ አበባ ከሚገኙት ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ነዳጅ እና ቀለብ እንዲላክላቸው ጠየቁ። የተሰጣቸውን መልስ ግን ባላቸው ሠራዊት ባላችሁ ነዳጅ እንደምንም ሆናችሁ ወደ ሀገራችሁ ግቡ የሚል ነበር። ነገር ግን የነበራቸው ትጥቅ እና አቅም ወደ ሀገራቸው የሚያደርስ አልነበረምና በቦታው በነበሩ ጄኔራሎች ባደረጉት ውይይት ወደ ሱዳን እንዲገቡ የሚጠይቅ ልዑክ ተላከ።

‹‹ከሱዳን መንግሥት ጋር በመደራደር መሳሪያችንን ጥለን መድፎች ወደኋላ ታንኮች ቱሬታቸውን ወደኋላ አዙረው ያለንን መሳሪያ እያስቀመጥን እንድንገባ ትእዛዝ ተሰጠን። ከዚያም ሱዳን ከሰላ አቦ ጊመል የሚባል ቦታ ላይ እንድንገባ ተፈቀደልን። ›› ወደ ሱዳን ለመግባት በተፈቀደላቸው ጊዜ መሳሪያቸውን እንዳራገፉ የተከሰተው ክስተት ሲያነሱ አሁንም ድረስ ስሜታቸው ይረበሻል። ‹‹ መሳሪያችንን ጥለን ወደ ሱዳን ስንገባ የሻዕቢያ ጦር ተዘጋጅቶ ነበርና መሳሪያቸውን ባወረዱ ጦረኛ ተዋጊዎች ላይ ኃይሉን ማሳየት ጀመረ። ምንም መሳሪያ ባልያዘ ወታደር ላይ ሠራዊቱን ረሸኑ፤ የቀረውም ሠራዊት ሕይወቱን ለማትረፍ ወደ ሱዳን ገባ። ›› በማለት በፍጹም ሊደረግ የማይገባው ተግባር እንደነበር ያነሳሉ።

በፖርት ሱዳን ወደ 460 የሚጠጉ መኮንኖች ቆይተው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጥያቄ አቅርበው በተደረገ ውይይት ከሶስት ወራት ቆይታ በኋላ ሀምሌ 27 ቀን ወደ አዲስ አበባ ገቡ።

በድጋሚ ቤተሰባዊነትን ስለመቀጠል

የሻለቃ ቡሎ ባለቤት ባላቸው የት እንዳለ እና እንደደረሰ አያውቁምና የአንድ ዓመት፣ የአምስት ዓመት የሰባት ዓመት ህጻናት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ ልጆቻቸውንና የባለቤታቸውን ፎቶ ይዘው የሻለቃ ቡሎ ወላጆች ወሊሶ አቅንተው የልጅ ልጆቻቸውን አስተዋወቁ። ነገር ግን በጊዜው የሻለቃ ቡሎ ወላጆች የልጃቸውን በሕይወት መኖር አልያም ማረፍ ማወቅ አልቻሉም ነበር።

በሱዳን ያረፈው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከዛሬ ነገ ወደ ሀገር ቤት ይመለሳል የሚል ዜና በቴሌቭዥን ጣቢያ ይተላለፍ ነበርና የሻለቃ ቡሎ ባለቤት የሌሎች ሠራዊት ቤተሰቦች በየቀኑ ወደ አየር ማረፊያ በመሄድ ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ይጠባበቁ ነበር። ‹‹ ወደ ሀገሬ እንደገባሁ ባለቤቴ ልጆቼ የት እንዳሉ አላውቅም ነበር። እናም አየር ማረፊያ እንደደረስኩ ስሜ ሲጠራ ባለቤቴ እና ልጆቼን ሳያቸው ፍጹም ስላልጠበቅኩ ቃላት ለማውጣት እንኳን ተቸግሬ ነበር። ›› ሲሉ ሻለቃ ቡሎ ያን ጊዜ ያስታውሱታል።

ሻለቃ ቡሎም ወደ ሀገራቸው ገብተው ወደ ጦላይ ማሰልጠኛ እንዲሄዱ ሲደረግ በፊት እግረ መንገዳቸውን በሕይወት መኖራቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለቤተሰቦቻቸው ሲጽፉ ባለቤታቸው መጥተው እንደጠየቋቸው እና የልጅ ልጆቻቸውን መተዋወቃቸውን ከወላጆቻቸው መልዕክት ሲደርሳቸው የደስታ እና የሀዘን ስሜት በእኩል ሰዓት ያስተናገዱበት ጊዜ እንደነበር ሻለቃ ያነሳሉ።

ተሀድሶ ኮሚሽን

ሻለቃ ቡሎ ወደ ሀገራቸው እንደገቡ ወቅቱ የኃይል ለውጥ ተደርጎ ሀገሪቱን ይመራ የነበረው የኢህአዴግ መንግሥት ነበርና የተሀድሶ ስልጠና ለመውሰድ ወደ ጦላይ ማሰልጠኛ እንዲገቡ ተደረገ። ሻለቃ ቡሎ ይህንን ስልጠና ከመውሰዳቸው አስቀድሞ ከአጼ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ጀምሮ ሀገራቸውን በውትድርና ለ20 ዓመታት ያህል አገልግለዋል። በጦላይ የተሀድሶ ስልጠና ሲወስዱ የሁለተኛ አብዮታዊ ሠራዊት አስተዳደር ኃላፊ አድርገው መረጧቸው። የተሀድሶ ስልጠናቸውን ከጨረሱ በኋላ በሠራዊቱ ውስጥ እንዲቀጥሉ ጥያቄ ቀረበላቸው። ሻለቃ ቡሎ ግን የሲቪል ሕይወትን መቀላቀል መረጡ ‹‹ በሶማሊያ ጦርነት በጣም ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፈያለሁ፣ ወጣትነቴን ሰጥቻለሁ፤ በልጅነቴ ያፈራሁትን ሀብት ጭምር አጥቻለሁ፤ እድሜዬም እየገፋ በመሄዱ መቀጠልን አልፈለኩም ነበር። ›› የሚሉት ሻለቃ ቡሎ በወጣትነታቸው የነበራቸውን ደፋርነት በሶማሊያ ጦርነት ያሳለፉት ሰቆቃ ፊታቸውን ላይ ድቅን እንደሚል ይገልጻሉ።

ሌላ የሕይወት ምዕራፍ

ከፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ጀምረው ወጣትነታቸውን ወኔቸውን የሰጡለት ሙያ የሀገር ሠራዊትን የተቀላቀሉበት ወቅት የተሳተፉበት ጦርነት ለሀገር ትልቅ ውለታን የዋለ የውትድርና ሥራ ሙያ ውስጥ ለ20 ዓመታት አገልግለዋል። በጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት እና ቀላል የማይባሉ በጊዜ ሂደት እንኳን ሊረሱ የማይችሉ ከባድ እና የጀግንነት ጊዜን አሳልፈዋል። በወጣትነት ጊዜያቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ሲመሩ ሻለቃ የሚል ማዕረግን አግኝተው መልካም የሥራ ጊዜን አሳልፈዋል።

ሻለቃ ቡሎ የሲቪል ሕይወትን ከመረጡ በኋላ የተሰማሩት በታክሲ ሥራ ላይ ነበር። ወታደር በባህሪው ካለው የልብስ መለዮ ጨምሮ የራሱ ግርማ ሞገስ በህብረተሰቡም ዘንድ የሚሰጠው ቦታ ከፍ ያለ ነውና እንዴት የታክሲ ሥራን መረጡ ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ስለሥራ ክቡርነት ያላቸውን ሃሳብ በዚህ መልኩ ገልጸውልናል። ‹‹አንድ የማምንበት ነገር በክረምት ወቅት የሠርግ ጥሪ ቢኖር ወደ ተጠራበት ቦታ ጸኣዳ ልብስ ለብሶ የሚሄድ ሰው ድንገት ጭቃ ላይ ቢወድቅ እዛው አይቀርም።

ልብሱን እንደምንም አጽድቶ ወደ ተጠራበት ሠርግ ይሄዳል። ›› የሚሉት ሻለቃ ቡሎ ለዓመታት የቆዩበት የውትድርና ሕይወት ያስተማራቸው ጥንካሬን በሥራ ክቡርነት እንዲያምኑ ዝቅ ብሎ መሥራት ምንም ማለት እንዳልሆነ ኃላፊነትን እስከ መጨረሻው መወጣት ምን እንደሚመስል ያሳዩበት ነው።

የሲቪል ሕይወትን ሲቀላቀሉ የጀመሩት የታክሲ ሥራ ለስድስት ዓመት ያህል ከሰሩ በኋላ ሥራው በሚያሳድረው ጫና በገጠማቸው የኩላሊት ህመም አማካኝነት ሥራቸውን አቁመው ወደሌላ የግል ሥራ ገቡ። ይህም ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር እና እሳቸውን መርጣ ወላጆቿን ጥላ በጋራ ያፈሯቸውን ልጆች ለምታሳድግ ሚስት እና እናት እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው አባትና አባወራ ለቤተሰባቸው ሊከፍሉት በደስታ የተቀበሉት መስዋዕትነት እንደነበር ሻለቃ ቡሎ ይገልጻሉ። ‹‹ምንም ጤናዬ ቢጎዳም ልጆቼን አሳድጊያለሁ፤ አስተምሬያለሁ፤ በሰራሁት ሠራም ረክቻለሁ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም። ›› ይላሉ። ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ካላቸው ፍላጎት የተነሳም ትምህርታቸውን ትተው ሕይወትን ማሸነፍ ለቤተሰብ መኖር ላይ አተኩረዋል ።

የታክሲ ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላም በሌላ የግል ድርጅት ውስጥ በሱፐርቫይዘር ፣ ሳይት ጥናት ስምሪት እና በአስተዳደር ሥራ ለ12 ዓመት ያህል ሰርተዋል። በቤተሰብ ሕይወታቸውም አምስት ልጆችን የወለዱ ሲሆን የልጅ ልጅም አይተዋል።

እድሜ የሚያስተምረው

ባሳለፉት ሕይወት በነበራቸው ስብዕናና እና የሥራ ሥነ-ምግባር ጓደኞቻቸው ምሳሌ እንደሚያደርጓቸው ይናገራሉ። በውትድርና ዓለም ውስጥ ትልቁ መርህ ሁል ጊዜም ዝግጁ መሆን እና ጽናት መሆኑን የሚያነሱት ሻለቃ ቡሎ ኢፋ አሁን ላይ እድሜያቸው ሰባ ዓመት ሲሆን ይህ ትውልድ መማር ያለበት ይላሉ።

‹‹ የዛሬ ልጆች አንድ ችግር ሲገጥማቸው ቶሎ ይበሳጫሉ። ችግርን እንዴት ማለፍ እንዳለባቸው አያውቁም። የሥራ – ሥነ ምግባር፣ ዝቅ ብሎ መሥራት እና ረጋ ማለትን ማወቅ አለባቸው። ምክንያቱም ነገም ሌላ ቀን ነው። ይሄ ለልጆቼም ጭምር ሁሌ የምላቸው ነው። ›› በማለት ወጣቱ በትንሽ በትልቁ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት ይመክራሉ።

ሻለቃ ቡሎ ይህን የሚሉት በበረሀ በውጊያ ላይ ሳሉ ከቤተሰቦቻቸው ከልጆቻቸው መራቃቸው ጎድቷቸው ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ራሳቸውን ያጠፉ እንዳሉ በማስታወስም ጭምር ነው።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You