የወርሃ ነሐሴ የሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ድምቀቶች

የበጋው ወር አልፎ ክረምት ሲገባ የኢትዮጵያ አርሶ አደር ከተፈጥሮ ጋር ያለው ወዳጅነት ይጠብቃል። ከጋራ ሸንተረሩ፣ ከሜዳ ጉድባው ጋር መነጋገር ይጀምራል። ከዝናቡ፣ ከማጡ፣ ከብርድና ቁሩ ጋር ይፋለማል፡፡

የሰብል እርሻውን አለስልሶ በዘር ይሸፍናል፣ የጓሮ አትክልቱን፣ የፍራፍሬ እፅዋቱን ይተክላል። የክረምት ወቅት ለኢትዮጵያ አርሶ አደር እጅጉን አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ለመላው ኢትዮጵያውያንም ልዩ ትርጉም አለው። የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ዋናው መሠረት የሆነው ይህ የግብርና ወቅት ከሀገሪቱ ዓመታዊ የግብርና ምርት አብዛኛው የሚመረትበት ነው፡፡

በሐምሌና ነሐሴ ከሚደረገው ጠንካራው የእርሻ ሥራ ጎን ለጎን ይህ ወቅት ደማቅ የኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶች የሚንፀባረቁበትም ነው። ጎብኚዎች ወደ ገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ቢያቀኑ ከማራኪ የግብርና ሥራው ባሻገር በክረምት ከሚገለጠው የተፈጥሮ ፀጋ ጋር ተገናኝተው የማይረሳ ትዝታን ሸምተው ይመለሳሉ።

ኢትዮጵያውያን ከመስከረም እስከ መስከረም በባሕላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት የሚደምቁ የዓለም ፈረጦች ናቸው። ሀገሪቱ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እና የብዝሀ ሃይማኖትና ባሕል መገኛ እንደመሆኗ መጠን የማህበረሰቡን እሴት የሚወክሉ፣ የመላውን ዓለም ቀልብ የሚስቡ ደማቅ ክብረ በዓላት ዓመቱን ሙሉ ይከናወኑባታል። ከእነዚህ በርካታ መስህቦችና ሀብቶች መካከል ደግሞ የክረምቱን ወር (በተለይ ነሐሴን) ጠብቀው የሚከበሩ ተወዳጅ ክብረ በዓላት ይገኛሉ።

በወረሃ ነሐሴ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሚያከብሩት ጾመ ፍልሰታ ተከትሎ ሁለት በዓላት በድምቀት ይካሄዳሉ። እነዚህ በዓላት በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል። በዓላቱ የደብረ ታቦር (ቡሄ) እና የልጃገረዶች በዓል የሆነው አሸንድዬ፣ አሸንዳና የሶለል ባሕላዊ ጨዋታዎች ናቸው።

የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ እንዲሁም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚጠቁሙት፤ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች የሚገኙበት የሻደይ/አሸንዳ ክብረ በዓል ‹‹የሴቶች የነፃነት በዓል እንደሆነ የሚታመን፤ በክብረ በዓሉ ወቅት በተለይ ልጃገረዶች እንደልባቸው በመሆን በነጻነት የሚጫወቱበትና በአደባባይ ደምቀው የሚታዩበት ነው›› በማለት ተወዳጁን ባሕላዊ ሥርዓት ይገልፁታል።

የዝግጅት ክፍላችንም በዓሉ ከፆመ ፍልሰታ ፍቺ ቀን አንስቶ እስከ መስከረም ወር እየተከበረ የሚቆይ ተወዳጅ መስህብ እንደመሆኑ መጠን የአከባበር ሥነ ሥርዓቱን፣ ለኢትዮጵያውያን ያለውን ትርጉም እንዲሁም የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በባሕላዊ ሥርዓቱ ላይ ያደረገውን ጥናታዊ ዳሰሳ ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎችን ለመቃኘት ወዷል፡፡

ወይዘሮ ነፊሳ አልማህዲ የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ ሥነ ጥበብ ፈጠራ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ናቸው። እርሳቸው የዘንድሮውን የአሸንድዬ፣ ሻደይ፣ አሸንዳና ሶለል ክብረ በዓላትን አስመልክተው አንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ እንደየ ብሔር ብረሰቦችና ሕዝቦች ባሕልና ወግ፣ የአኗኗር ሥርዓትና ፍልስፍና ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የምታስተናግድበት እምቅ የሆነ የባሕል ባለቤት ሀገር ነች።

ከነዚህም በዓላት መካከል የሴቶች የነፃነት ቀን እንደሆነ የሚነገርለት የአሸንድዬ፣ ሻደይ፣ አሸንዳና ሶለል የሴቶች በዓል አንዱ ሲሆን፣ ሴቶች በጉጉት፣ በናፍቆት፣ በፍቅርና በልዩ ዝግጅት የሚጠብቁትና በሚኖሩበት ማህበራዊ ሥርዓት ሥነልቦናዊ እርካታ የሚያገኙበት ደማቅ በዓል ነው። በበዓሉ ወቅት ሴቶች እውቀታቸውን፣ ፍላጎታቸውን፣ ፈጠራቸውን፣ ችሎታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ አመለካከታቸውን፣ እምነታቸውን፣ ፍልስፍናቸውን እንዲሁም መፃኢ ተስፋቸውን የሚያዩበትና የሀገር በቀል የምስጋና ባህርይ የሚስተዋልበት በዓል ጭምር ነው።

ሚኒስቴር ዴኤታዋ እንዳስረዱት፤ ሀገር በቀልና ጥንታዊ ባሕሎቻችን ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ በማንነቱ የሚኮራና ባሐላዊ ሀብቶቹን አውቆና ተረድቶ በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመፍጠር የአሸንድዬ፣ ሻደይ፣ አሸንዳና ሶለል የሴቶች በዓልን ጨምሮ በብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውስጥ ያሉ ቱባ ባሕሎችን ለመጠበቅ፣ ለማጥናት፣ ለማልማት፣ ለማደራጀትና ለማስተዋወቅ ሁሉም የየራሱን ድርሻ መወጣት ይገባዋል።

የሴቶች የነፃነት ባሕል ተደርጎ የሚቆጠረው በዓል ከሚከበርባቸው የሰሜኑ ክፍል አካባቢዎች አንዱ የሰቆጣ ከተማ ይገኝበታል። በአካባቢው የሚከበረው ይህ ባሕል ሻደይ የሚል ስያሜ አለው። የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ መላሽ ወርቃለም እንደሚገልፁት፤ ባሕላዊ ትውፊቱን፣ ወጉንና እሴቱን በጠበቀ መልኩ በዋግ ሹሞች መናገሻ በሰቆጣ ከተማ በድምቀት ለዘመናት ሲከበር ቆይቷል። ዘንድሮም በተመሳሳይ መልኩ እየተከበረ ይገኛል።

‹‹የሻደይ በዓል ምንም እንኳን የልጃገረዶች በዓል ቢሆንም እንደ ማህበረሰብ ብዙ ትርጉም አለው›› የሚሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ ከልጃገረዶች ባሕልና የነፃነት ቀን ባሻገርም ዘመድ ከዘመድ ጋር የሚጠያየቅበት፣ በዋግ ሕዝብ ውስጥ ትልቅ ማህበራዊ መስተጋብር የሚፈጥር ተወዳጅ በዓል መሆኑን አስታውቀዋል። ይህን የማህበረሰብ ባሕላዊ ሥርዓትም ከትውልድ ወደ ትውልድ ጠብቆ ለማሸጋገር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አባይ መንግሥቴ በበኩላቸው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በያዝነው በነሐሴ ወር ደማቅ ሥርዓትን የያዘው የሴቶች የነፃነት የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል በዓል እንዲሁም የቡሄ፣ እንግጫ ነቀላና ከሴ አጨዳ በዓል እንደ ከዚህ ቀደሙ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ነው።

የአማራ ክልል ከአስደማሚ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ በተጨማሪ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ዓመቱን ሙሉ የሚከበሩ በርካታ ባሕላዊ ክብረ በዓላት መኖራቸውን አቶ አባይ በመግለጫቸው አንስተዋል። ከእነዚህ ክብረ በዓላት መካከል በያዝነው የወርሀ ነሐሴ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በድምቀት የሚከበሩት የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ቡሄ፣ እንግጫ ነቀላና ከሴ አጨዳ ይገኙበታል ሲሉ እሳቸውም ተናግረዋል። ክብረ በዓላቱ በየአካባቢዎቹ እየተከበሩ እንደሚቀጥሉ የሚያነሱት አቶ አባይ፣ በተለይም ሻደይ በዋግ ኽምራ፣ አሸንድዬ በላስታ ላሊበላ፣ ሶለል በራያ ቆቦ፣ ከሴ አጨዳና እንግጫ ነቀላ በምስራቅ ጎጃም የሚከበሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሚከበረውን የልጃገረዶች በዓል በታላቅ ድምቀት ከሚያከብሩት መካከል የትግራይ ብሔረሰብ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በዓሉ በክልሉ አሸንዳ በሚል ይታወቃል። የዘንድሮው የአሸንዳ በዓልም ባሕላዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እየተከበረ መሆኑን የክልሉ መንግሥት ኮሚኒኬሽን እና መገናኛ ብዙሃን አሳውቀዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ‹‹የአሸንዳ በዓል በትግራይ፣ ዋግ ኽምራና ላስታ-ላሊበላ›› በሚል በጥናት መልክ ሰርቶ ይፋ ባደረገው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንደተመለከተው፤ በዓሉ በትግራይ አሸንዳ በሚል በየዓመቱ በወርሀ ነሐሴ በክልሉ ርዕሰ ከተማ በመቐለ፣ በእንደርታ፣ አዲግራት፣ ተምቤን ጨምሮ በልዩ ልዩ አካባቢዎች ይከበራል።

ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ያካሄደው ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚጠቁመው፤ የአሸንዳ በዓል በየዓመቱ ከነሐሴ 16 እስከ 21 ባለው ጊዜ ውስጥ ለአንድ ሳምንት ያህል ሲከበር የቆየና ዛሬም እየተከበረ የሚገኝ ነው፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በዓሉ የበለጠ እውቅና እንዲያገኝና የሁሉም በዓል ሆኖ እንዲከበር በመደረጉ በአደባባይ በፌስቲቫል መልክ ከነሐሴ 16-18 ባለው ጊዜ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በመቐለ፣ በዓብዓዲ/ተምቤን፣ በአዲግራት እንዲሁም በአክሱም ነሐሴ 24 ቀን በድምቀት እየተከበረ የሚገኝ ታላቅ ክብረ በዓል ነው፡፡

እንደ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ጥናታዊ ማብራሪያ፤ የአሸንዳ በዓል በሚከበርበት ወቅት ልጃገረዶች ተወዳጅ የሆነውን ጨዋታቸውን በባሕላዊ አልባሳት ደምቀው ይጫወታሉ። ልጃገረዶች እንደ የቡድናቸው አለባበሳቸውን፣ የአሸንዳ ቅጠል አስተሳሰራቸውን፣ የአንገት ጌጦቻቸውን፣ የጸጉር አሰራራቸውን ሁሉ እርስ በርስ አስተካክለው፣ አምረውና ተውበው ለጨዋታው ዝግጁ እንደሚሆኑም ይገልፃል፡፡

በዚህ መልኩ ዝግጅታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከተለያየ አቅጣጫ ግንባራቸውን በእጃቸው ያዝ ቀና እያደረጉ ለጨዋታው እንዲሰባሰቡ ከጓደኞቻቸው ጋር በዚህ ወቅት በሚደረግ የአጠራር ዘይቤ መሰረት በድምጽ ይጠራራሉ፡፡ ከበሯቸውን እየመቱና እየዘፈኑ ወደጋራ የመሰብሰቢያ ቦታቸው በመውጣት ክብ ሰርተው ጨዋታቸውን ይጀምራሉ፡፡ አሸንዳም በዚህ መልኩ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሮ ያልፋል። በዚህ መሰል ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ወደ ትግራይ ክልል እንደሚያቀኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በሰሜኑ በልዩ ድምቀት ከሚከበረው የልጃገረዶች በዓል ውስጥ ሻደይ አንዱ መሆኑን ጠቅሶ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ መሰረቱን እንዲህ እንደሚከተለው ያብራራል። የሻደይ ክብረ በዓል /ባሕላዊ ጨዋታ/ አከባበር የሚጀመረው በወርሃ ነሐሴ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ክብረ በዓሉ የፍልሰታ ጾም በሚፈታበት ነሐሴ 16 ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የሚከወን መሆኑን አብራርቶ፣ የአከባበር ሥርዓቱ በአለባበስ፣ በአጊያጌጥ፣ በቡድን ምስረታና በመሳሰሉት የራሱ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶችና ቅድመ ሥርዓቶች እንዳሉት ጠቁመዋል፡፡

ሻደይ የክረምት ወቅት /ወርሃ ነሐሴ/ ምድር ከከባድ ዝናብ መላቀቅ የሚጀምርበት፣ ሜዳው፣ ሸንተረሩ፣ ሸለቆና ተራራው በዓመት አንድ ጊዜ ብቅ በሚለው የአደይ አበባ የሚያጌጥበትና የምድር አዝዕርትም ፍሬ ማፍራት የሚጀምሩበትና የክረምቱ መልካምነት የሚረጋገጥበት ወቅት በመሆኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት በዓሉ መከበሩ አምላክ ከአለፈው ዘመን ወደ አዲሱ ዘመን በሰላም፣ በፍቅር፣ በጥጋብ ለመሸጋገሩ ምስጋና በብሔረሰቡ የሚቀርብበት እንደሆነ ይታመናል በማለት የበዓል አከባበሩን ዳራ ያስረዳል፡፡

በአማራ ክልል የልጃገረዶች በዓል አሸንድዬ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት እንደሚከበር የቅርስ ባለስልጣን ጥናታዊ ጽሑፍ ይጠቁማል። ክብረ በዓሉ ማህበረሰቡ ማንነቱን የሚገልጽበት የራሱ የሆነ ወግ፣ ቋንቋና ባሕል እንዳለው የሚያሳይበት መሆኑንም ያስረዳል።

የላስታ-ላሊበላ ሕዝብም በየደረሰበት የዘመን ምዕራፍ ሁሉ ደስታውንና ብሶቱን የሚገልጽባቸው የብርቅዬ ባሕሎች ባለቤት መሆኑን በመጥቀስም በየዓመቱ ከሚከናወኑ በርካታ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ጨዋታዎች መካከል ‹‹አሸንድዬ›› አንዱና ዋናው የአካባቢው ማህበረሰብ መገለጫ መሆኑን ያስረዳል፡፡

የአሸንድዬ ባሕላዊ ጨዋታ በአካባቢው ማህበረሰብ በየዓመቱ በጉጉት ተጠብቆ መከበሩ የአካባቢው ህብረተሰብ በራሱ ባሕል እንዲኮራ ከማስቻሉም በላይ ባሕላዊ ጨዋታው ታሪካዊነቱ እንዲጠበቅና ከትውልድ ወደትውልድ እንዲሸጋገር ያስቻለው መሆኑን መረጃ ያብራራል፡፡ ላስታ ላሊበላ ቱሪስት የሚጎርፍበት መካነ ቅርስ በመሆኑም ክብረ በዓሉ ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር የራሱ ድርሻ ያለው እሴት መሆኑንም ይጠቁማል።

እንደ መውጫ

እንደሚታወቀው የዓመቱ መገባደጃና የመስከረም መባቻ በሆነው ወርሀ ነሐሴ ላይ እንገኛለን። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ተወዳጅና ማራኪ የሆኑ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ሥርዓቶችን የምታከብርበት ማህበረሰቡም በባሕላዊ እሴቶቹ የሚደምቅበትና የሚዋብበት ነው። የደብረ ታቦርና አሸንዳ አሸንደዬ በዓላት ለመስከረም አቀባበል የሚያደርጉ፤ መጪውን ዘመን በብሩህ ተስፋ እንድንቀበል መሠረት የሚሆኑን ፈርጦችም ናቸው። ነገር ግን በዓላቱን ከዚያም በላይ ትርፍ አላቸው።

እነዚህ ተወዳጅ እሴቶች ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ላይ የማስተዋወቅ፤ በቱሪዝም ዘርፍ የኢኮኖሚና የሀገር መልካም ገፅታን የመገንባት እድል የሚፈጥሩ ናቸው። በመሆኑም በዓላቱ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ፣ እንዲለሙና ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸው አካላት ተግተው እንዲሰሩ የዝግጅት ክፍላችን ለማሳሰብ ይወዳል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You