ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር፤ የቀጣናው ወሣኝ ሀገር ናት። ወሣኝ መሆኗ ደግሞ ለራሷ ብቻ ሣይሆን በዓለም ፖለቲካ ቁልፍ ሚና ያላቸው ሀገራት የሚገነዘቡት ነው። ለምዕራባውያን ሆነ ለዓረቡ ዓለም በመልክዓ ምድር አቀማመጧ፣ ባላት የተፈጥሮ ሃብት ብሎም በዓለም ስትራቴጂክ እይታዎች አኳያ ቁልፍ ቦታ ላይ የምትገኝ፤ የችግር ቀን ፈውስ ናት።
የዲፕሎማሲ እና የዓለም የፖለቲካ ቢሆኖችን በአግባቡ የሚረዱ አካላት የኢትዮጵያን ሚና አግዝፈው ይመለከታሉ። ይህም በመሆኑ ይህችን ሀገር ሳይዙ በቀጣናው ላይ ወታደራዊም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን መሞከር ትርፉ ልፋት ብቻ እንደሚሆን ብዙዎች ይስማማሉ።
አካባቢው ከሕንድ ውቅያኖስ እና ከቀይ ባሕር ጋር የሚገናኝ ነው፤ በተለይም ቀይ ባሕር የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እና የኤዥያ አሕጉራትን የሚያገናኝ ትልቅ የንግድ አካባቢ ነው። የፈረጠመ አቅም ማሳያ ትልቁ ቀጣናም ነው። በመሆኑም በዚህ ቀጣና ሀገራት ኢትዮጵያን የሚጠጉት ሆነ የሚወዳጁት ለብሔራዊ ጥቅማቸው ነው።
በአሁኑ ወቅት ዓረቡ ዓለም ኢትዮጵያን ከምንጊዜም በላይ የሚፈልግበት ወቅት ላይ ነው። በነዳጅ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆኖ መቀጠል እንደማይቻል የተረዱት ይመስላል። ይህንን ተከትሎም የዓረቡ ዓለም ባለ ታላላቅ ኢኮኖሚ ባለቤት ሀገራት ለየት ያለ የኢኮኖሚ እይታ እየያዙ ነው።
በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትም በባሕል ውርርስም ሆነ በመልክዓ ምድራዊ ቅርርቦሽ ለእነዚህ ሀገራት ቅርብ መሆናቸው ስትራቴጂክ ተጠቃሚ የመሆን ዕድላቸውን አስፍቶታል። አሁን ላይ ያለው ጥያቄ ግን ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ይህን መልከ ብዙ እና ሰፋ ያለ ፍላጎት ማን ያሟላል የሚለው ነው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ እና ተመራጭ ሀገር ናት።
በኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ 12 ወንዞችን ከለምለም አፈር ጋር ማገናኘት ይፈልጋሉ። ይህ የሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ደግሞ ዓረቦቹ ካላቸው አሁናዊ ካፒታል አኳያ ‹‹ኢምንት›› ነው። ይህ ለዓረቡ ዓለም እፎይታን የሚሰጣቸው፤ ኢትዮጵያን ስትራቴጂክ አጋር አድርጎ ለመቀጠልም የሚያነሳሳቸው ነው።
ሀገራችን በተፈጥሮ ሃብት አቅም እንዳላት፤ በርካታ ምሑራን የሚስማሙበት እና ዓለም የሚያውቀው ሐቅ አለ። ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ሃብት፣ መልክዓ ምድር ስፋትና የሕዝብ ብዛት ሀገራት ትኩረታቸውን እንዲጥሉባት አድርጓል። የሀገሪቱ አየር ፀባይና የአየር ንብረት ባሕሪ በሌሎቹ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ሕዝብም ትልቅ ሃብት ነው፤ በተለይ ደግሞ በነፃነት የኖረ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም ወሳኝ ስለመሆኑም ምሑራን ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ከማሕፀኗ የሚወጡ 12 ወንዞችን ወደ ጎረቤት ሀገራት ይፈሳሉ። ሸበሌ ወንዝ ወደ ሶማሊያ፣ ኦሞ ወንዝ ወደ ኬኒያ፣ ገናሌ ወንዝ ወደ ኬኒያ እና ሶማሊያ፣ ዓባይ ወንዝ ደግሞ በርካታ ሀገራትን እየነካካ የሚያልፍ ነው። እነዚህን የተፈጥሮ ትሩፋቶች በቅርብ ርቀት የሚመለከቱት የዓረቡ ዓለም ሀገራት የትሩፋቱ ተካፋይ ለመሆን ያላቸው የኢኮኖሚ አቅም ይፈቅድላቸዋል።
ሌላኛው ጉዳይ በዓለም ላይ ስጋት እየሆነ የመጣው የሽብርተኝት ስጋት ምዕራባውያን በቀጣናው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። ስጋታቸውን ለማርገብ በቅድሚያ ስትራቴጂክ አጋር አድርገው የወሰዱት ኢትዮጵያ ነው። ከዚህ አኳያ በሶማሊያ የአሸባሪን አልሽባብ ሴል ለመበጣጠስ በቀዳሚነት ኃላፊነቱን የወሰደው እና ትልቅ ውጤት ያስመዘገበው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው።
በዚህ ረገድ ደግሞ ሰፋ ባለ ሁኔታ የቀይ ባሕር ቀጣና ሠላማዊ ሆኖ እንዲዘልቅ ኢትዮጵያን የመሰሉ ጠንካራ የሠራዊት አደረጃጀት ያላቸው ሀገራት በአሜሪካውያን እና በምዕራባውያን ተመራጭ ናቸው። ሀገራቱ ብሔራዊ ጥቅማቸውን በማስከበር ሂደትም የኢትዮጵያ ሚና ወሳኝ ነው።
እነዚህ የተፈጥሮ ፀጋዎችና ስትራቴጂክ ሁኔታዎች ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጣና አይተኬ ሚና እንዳላት ቢያመለከትም፤ ይህን እውነታ በአንድም ይሁን በሌላ በራሳቸው ይሁን በሌሎች ተፅዕኖ መቀበል የማይፈልጉ ሀገራት መኖራቸውን ማወቅ ተገቢ እና እንደ ሀገር አሁን ላይ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች ለመሻገር ግድ የሚል ነው።
ለአብነትም ኢትዮጵያ በሶማሌ ላንድ የባሕር በር ለመጠቀም እያደረገች ያለውን ሠላማዊ ሂደት ሞቃዲሾ እየተቃወመች ነው። ከባለጉዳይዋ ኢትዮጵያ ይልቅ ወደ ግብፅ በመመላለስ አቤቱታ እያቀረበች ነው። እውነታው ‹‹ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያሥራል›› እንደሚባለው እየሆነ ነው።
ግብፅም ሞቃዲሾ አይዞሽ ለማለት የተጋችው አትራፊ ስለምትሆን አሊያም ጉዳዩ በቀጥታ ስለሚመለከታት ሳይሆን የ‹‹ጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› በሚለው ያረጀ ያፈጀ እሳቤ ነው። ይህ ከበርካቶች ውስጥ የሚጠቀስ ነጠላ ጉዳይ እንጂ፤ የኢትዮጵያ ፈተና ከዚህ በላይ ነው።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ታስፈልጋለች ከሚለው ነባራዊ ሁኔታ በዘለለ ኢትዮጵያም በዚህ ቀጣና ከሌለች ቀይ ባሕር ዘላቂ በሆነ መንገድ ሠላም የመሆን ዕድል የለውም። የዓለም የፖለቲካ ፍኖታ ካርታ በየዕለቱ እየተቀያየረ ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያም ከዚህ ቀጣና ማራቅ አይቻልም። ወዳጅ የበለጠ እንዲበዛ፣ ጠላትም አንገቱን እንዲደፋ በዚህ አካባቢ ቀዳሚ ሆኖ መገኘት ተገቢ ነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።
እነዚህ ነገሮች ሁሉ እንዲሳኩ ከምኞት በዘለለ መሬት ላይ ምን መሠራት አለበት የሚለው ግን አፅንዖት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው። በተለይም ደግሞ በሁሉም ዘርፍ ዲፕሎማሲን ማዕከል ያደረገ ጠንካራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። በዚህ ዘመን የበርካቶች ቀልብ እየገዛ የመጣውን የዲጂታል ዲፕሎማሲ በተጠና መንገድ በሁለንተናዊ መልኩ መተግበር ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከዓለም የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ መድረኮች ላይ ሐሳቧን የምትሸጥበት እና ቀጣናው ላይ አስፈላጊነቷን የምታጎላበት መድረኮችን በአግባቡ እና በተጠና ሁኔታ መጠቀም አለባት። ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት መፍጠር እና መንቀሳቀስ ደግሞ ዘመኑ የሚጠይቀው ዕውቀትና ሁኔታዎችም የግድ የሚያስብሉ ናቸው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም