የኢትዮጵያውያን ኅብረትና አንድነት የተገለጸበት – አረንጓዳ ዐሻራ

ሰዎች በተባበረና በአንድነት መንፈስ ከሠሩ የማይደረስበት የሚመስለውን ደርሰው፣ የማይጨበጠውን ጨብጠው፣ የማይቻለውን ችለውና አስችለው ለውጤት መብቃታቸው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ ሃሳቡ ከየትም ይምጣ ከየት፣ በሃሳቡ ሰዎች ተስማምተው ፣ አምነውበት ተቀብለውት የጋራ አድርገው ሲሳተፉበት ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንዲሉ አበው አንድነታቸውና መተባበራቸው ብርታትና ጥንካሬ ሆኗቸው የታለመው ግብ ይሳካል፡፡

የነገሩን ክብደት በማየት ይህ ግዙፍ ሥራ እንዴት ሆኖ ሊሳካ ይችላል፤ ኧረ በፍጹም አይቻልም ሊያውም በሌለ በጀትና የሰው አቅም እንዴት ሊሆን ይችላል ተብሎ ብዙዎች ተስፋ የቆረጡበት ነገር እንኳን ሳይቀር ብርታትና ጽናት በፈጠረው ሕዝባዊ አንድነትና መተባበር መንፈስ ተሳክቶ አይተናል፡፡

ለዚህ ደግሞ ብዙ ርቀን መጓዝ ሳያስፈልገን ኢትዮጵያና ሕዝባችንን መመልከት በቂ ነው፡፡ በዓድዋ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ በብዙ ቀድመዋል፣ ሰልጥነዋል የተባሉ ሀገራት ሳይቀሩ በቅኝ ገዢዎች እጅ ሲወድቁ ኢትዮጵያ ግን በቅኝ ገዥዎች አልደፈርም ባይነቷን፣ በሕዝቦቿ አንድነት በተባበረ ክንድ አረጋግጣለች፡፡ ዳር ድንበሯን ጥሰው የመጡ ጠላቶቿንም ድል አድርጋ ነጻነቷን አውጃ የአሸናፊነት ዋንጫ ያነሳች ብቸኛ ሀገር መሆን ችላለች። ይህም ከኢትዮጵያውያን መተባበር እና አንድነት የፈለቀ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህም የዓለም ሀገራት ዓይኖቻቸውን ከዚህች ደሃ ሀገር ላይ እንዳያነሱ ያደረገው ግዙፉ የዓባይ ግድብ ፕሮጀክትን በራስ አቅም ለመገንባት አቅዳ በቁርጠኝነት ስትነሳ የተሳለቁ ነበሩ፤ አንዳንዶች ደግሞ ይህ ግንባታ እንዳይሳካ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፤ አፍራሽ ተልእኳቸውን ለማስፈጸም ያልገቡበት ያልወጡበት አልነበረም፡፡

ግድቡ ግን ኢትዮጵያውያን እንዳሰቡት ሆኖ በየምእራፉ እየገዘፈ እየገዘፈ መጥቶ እነሆ በማጠናቀቂያ ምእራፍ ውስጥ ይገኛል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያውያን አሸናፊ ሆነው የወጡት በመተባበራቸውና አንድ ሆነው በመሥራታቸው ነው፡፡ ሕዝቡ ባለው ሀገራዊ ፍቅር በሚችለው አቅም የተሳተፈበትና ዐሻራውን ያኖረበት መሆኑ የግድቡን ስኬት ወደ ማጣጣም ገብቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን በዚህ ታላቅ ገድላቸው የቆየውን የአንድነት ተምሳሌትነታቸውን ደግመዋል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብን በራሷ አቅም ለመገደብ ግንባታውን ይፋ ባደረገችበት ወቅት ይሄ እንዴት ተደርጎ ሊቻላት፤ ኧረ በፍጹም አትችልም ፤ ህልም ነው ሲሉ የነበሩት አንዳንድ ሀገራት ተችሎና ግድቡ ሂደቱን ጠብቆ እየተጓዘ መሆኑን ሲመለከቱ ግራ ተጋብተው የተፋሰሱ ሀገራትን በማጯጯህ የግድቡ ግንባታ እንዳይካሄድ ጥረት ከማድረግ በዘለለ ቅናት አይሉት ምቀኝነት በየሚዲያው ዘመቻ ሲያደርጉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ይህን ትኩስ አጀንዳ አቀንቅነውና አራግበው ባይጨርሱም ሀገሪቱ ግን በሁሉም መስክ እየቀደመች ያሰበችውንና ያለመችውን ከግብ ማድረስ ችላለች፡፡

የኢትዮጵያውያኑ የአንድነትና መተባበር መንፈስ በእነዚህ ሥራዎች ብቻ አላበቃም፡፡ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የችግኝ ተከላም እየተሰለሰ ይገኛል፡፡ የዘንድሮውን ጨምሮ ለስድስት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ኢትዮጵያውያን ታሪክ መጻፋቸውን ቀጥለዋል።

የሀገሪቱ መንግሥት እየተመናመነ የመጣውን የሀገሪቱን የደን ሀብት ለመታደግ፣ የተፈጥሮ ሀብቷን ከአየር ንብረት ለውጦች ለመጠበቅ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፣ወዘተ በሚል አረንጓዴ ዐሻራን የህልውና ጉዳይ አድርጎ ይዞታል፤ ይህንንም በይቻላል መንፈስ እየሠራበት ይገኛል፡፡

ሕዝቡም በዚህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት በ2011 በተጀመረ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡ ልማቱን የራሱ ጉዳይ አድርጎ በመያዝ አልፎም ተርፎ ባህል በማድረግ በችግኝ ተከላና እንክብካቤ ላይ ርብርብ እያደረገ ነው፡፡

የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት በክረምቱ ወራት በተካሄደው የችግኝ ተከላ በመሳተፍ 32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ተክሏል፡፡ በዚህ ላይ ዘንድሮ የተተከሉት ችግኞች ብዛት ሲታከል ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አይከብድም፡፡ የችግኝ ተከላው ከእቅድ በላይ እየተፈጸመ የመጣ ሲሆን፤ ዘንድሮም ይሄው እንደሚፈጸም ይጠበቃል፡፡

በየዓመቱ የሚደረገው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበረ መጥቶ ሕዝቡ በራሱ ልምድና ባህል እያደረገ እየተሳተፈበት ይገኛል፡፡ የሕዝቡ የአንድነትና የተባበረ ክንድ በሁሉም መስክ እየተገለጸ ስለመሆኑም ሌላው ማመላከቻ ነው፡፡

በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች ብዛት ብቻ አይደለም እየጨመረ የመጣው፡፡ ሕዝቡ ሆ ብሎ በመውጣት በአንድ ጀንበር በሚተክላቸው ችግኞች ብዛትም ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ ይህም ለመትከል ታቅዶ ከነበረው 200 ሚሊዮን ችግኞች ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል ከፍተኛ ስለመሆኑ አሀዙ በራሱ ይናገራል፡፡

ይህ የአንድ የችግኝ ተከላ በ2015ዓ.ም ተካሂዶ ከ566 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ በአንድ ጀንበር መተከሉ ለሰሚው በእጅጉ አስደማሚ ቢሆንም እንኳን፤ ከሥራው አንጻር በሚፈለገው ልክ ሲነገርለት አይስተዋልም፡፡ ዘንድሮም በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በትናንቱ እለት ተከላው በመላው ኢትዮጵያ ሲካሄድ ውሏል፡፡

ኢትዮጵያውያንም ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ጀንበር ዐሻራችንን እናኑር ሲሉ ያስተላለፉትን ጥሪ በመቀበል ትናንት ከማለዳው 12 ሰዓት አንስቶ እስከ ምሽት 12 ሰዓት ድረስ የ600 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ እቅድን እንደተለመደው ለማሳካት ተረባርበዋል፡፡

በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላውም ሆነ በዘንድሮው የችግኝ ተከላ ኢትዮጵያውያን እንደተለመደው ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በየአካባቢያቸውና ከአካባቢያቸውም ራቅ ወደአለ ቦታ በመሄድ ጭምር ተከላውን አካሂደዋል፡፡ በዚህም በችግኝ ተከላ ያካበቱትን ልምድ በመጠቀም አስቀድሞ መሥራት ያለባቸውን በመሥራት በችግኝ ተከላው ቀን ችግኞችን ብቻ በመትከል በመርሀ ግብሩ የበለጠ ውጤታማ የሚሆኑበትን ተግባር ፈጽመዋል፡፡

በተለመደው ኅብረታቸው እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ መደጋገፍ በሚያስፈልግበት ስፍራ እየተደጋገፉ፣ የክረምቱ ዝናብ፣ ጭቃ፣ ብርድና ንፋስ ሳይበግራቸው ለእቅዳቸው ስኬት ብቻ ሳይሆን የለመዱትን ከእቅድ በላይ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ተረባርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራን ጉዳይ ከሀገራዊ አልፎ ክፍለ አህጉራዊ ለማድረግ እየሠራች ትገኛለች። ለጎረቤት ሀገሮች ችግኞችን በማቅረብ እንዲተክሉ አድርጋለች። ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ የሀገሮች አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ አባላት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጭምር በችግኝ ተከላው እንዲሳተፉ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ እነዚህ ዲፕሎማቶች ዘንድሮም ይህንኑ አድርገዋል፡፡ ይህ የሀገሪቱ ተግባር ዓለም አቀፍ ጉዳይ በሆነው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ምን ያህል አተኩራ እየሠራች ስለመሆኗ ለማመላከትም ያስችላል፡፡

በተባበረ ክንድና አንድነት የዓለማችን ትልቅ ችግር እየሆነ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሚያስችል ውጤታማ የሆነ የአረንጓዴ ልማት ሥራ ውስጥ እንደምትገኝ በተግባር እያሳየች ያለችበት ሁኔታ ለሌሎች ሀገሮችም ትምህርት ሊሆን ይችላል፡፡

መጪው ወቅት ደግሞ ለችግኞች እንክብካቤ የሚደረግበት ይሆናል፡፡ በመትከል የታየው መተባበርና አንድነት ችግኞችን በመንከባከብና በመጠበቅ መደገም ይኖርበታል፡፡ በእዚህም በኩል ቢሆን ለውጦች እየታዩ ናቸው፡፡ የችግኝ የጽድቀት መጠን ከ80 በመቶ ወደ 84 በመቶ የጨመረበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል። የጽድቀት መጠኑን መጨመርና ቀጣይ የእንክብካቤ ሥራዎችን ማካሄድ አሁንም ከኢትዮጵያውያን ይጠበቃል፡፡

ሕዝቡ በኅብረት ሆኖ ችግኞችን እንደተከለ ሁሉ የተከላቸውን ችግኞች የመንከባከብ ኃላፊነትም አለበት። ችግኞች መትከል አንድ ነገር ነው፤ መንከባከብና ለሚፈለገው ዓላማ ማድረስ ደግሞ ቀጥሎ የሚመጣው ተግባር እንደመሆኑ ችግኞቹ ለተፈለገው ዓላማ እስኪደርሱ የመንከባከቡ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በአጠቃላይ 32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ በዘንድሮው ተከላ ይህ አሀዝ 40 ቢሊዮን እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡ ይህ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ሀገሪቱ 50 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል የያዘችውን እቅድ ማሳካት ደግሞ ይጠበቃል፡፡ ለእዚህ ሁሉ የተለመደው የኢትዮጵያውያን አንድነትና ኅብረት ወሳኝ ነው፡፡

ትንሳኤ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You