የክፍያው ጦስ

አብሮ አደግ ናቸው፡፡ አብረው ከማደግ አልፈው ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሔድም አብረው እስከመኖር ደርሰዋል፡፡ አብረው ይጠጣሉ፤ አብረው ይበላሉ፡፡ አብረው የእግር ኳስ ጨወታዎችን ያያሉ፤ በእግራቸው ይጓዛሉ፤ አንዱ ሌላው ቤት ያድራል፡፡ አንዱ ገንዘብ ካለው ሌላው ባይኖረው ችግር የለም፡፡ አንዱ ሌላውን ይጋብዛል፡፡ ከሶስት አንዳቸው ገንዘብ ካላቸው በቂ ነው፡፡ የማነህ ክንፈ፣ ተስፋ ወልዳይ እና ተስፋሁን ተክላይ የማይለያዩ ጓደኛሞች ናቸው፡፡ በዚህ አብሮነታቸው በጨርቆስ የማያውቃቸው የለም፡፡

ጊዜው ልክ እንደአሁኑ ከበድ ያለ ክረምት ነበር። በተደጋጋሚ ያለማቋረጥ ዝናቡ ይወርዳል፡፡ ዝናብ ሲዘንብ በእግራቸው ብዙ መጓዝ ስለማይችሉ ተሰብስበው አንደኛው ቤት ተቀምጠው ያወራሉ። አንዳቸው ገንዘብ ካላቸው መሸታ ቤት ገብተው አልኮል ይጠጣሉ፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታ ካለም አብረው ይመለከታሉ፡፡ ከበጋ ይልቅ ክረምትን የሚያሳልፉት ሳይለያዩ አብረው ነው፡፡

በ2015 ዓ.ም የክረምት መግቢያ ላይ ተስፋሁን እና ተስፋ መሃል መሻከር ተፈጠረ፡፡ አብረው ዘመናትን ቢያስቆጥሩም ተስፋ አመረረ፡፡ ለወትሮ የእንግሊዝ ፕሪሚርሊግን የሚያዩት አብረው ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መነጣጠል ጀምረዋል፡፡ ተስፋ ራሱን ገንጠል ከማድረግ አልፎ ብቻውን የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ማየት ቀጥሏል፡፡ የሚያነጋግረውም የማነህን ብቻ ነው። ተስፋሁንን ጭራሽ ማየት አይፈልገም፡፡

ተስፋሁን በበኩሉ ከተስፋ ጋር መለያየት አልፈለገም። በሌላ በኩሉ የማነህ ሁለቱን ለማስታረቅ ፈልጓል፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን መሻከር ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ቢጀምርም አልተሳካለትም፡፡ ጭራሽ እስከ መጠፋፋት ማሰብ ጀመሩ፡፡ በተለይ ተስፋ በትንሽ ነገር እየተበሳጨ መሻከሩን ይበልጥ ማሳደጉን ቀጠለ፡፡ ‹‹እንዳይጠጋኝ፤ አብሮኝ እንዳያድር፤ አብሮኝ እንዳይጠጣ›› ማለትን የየዕለት ቃሉ አደረገው፡፡ የማነህ ተጨነቀ፤ ለማንኛው እንደሚሆን ግራ ገባው፡፡ ተስፋሁን አንዳንድ ጊዜ ቱግ ቢልም እንደተስፋ አላመረረም፡፡ ታረቅ ቢባል ለመታረቅ ዝግጁ ነው፡፡ ነገር ግን ተስፋ በማምረሩ መታረቅ አልቻሉም፡፡

ግብዣው

በሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም የማነህ ተስፋ ጋር ደውሎ ‹‹የት ነህ?›› የሚል ጥያቄ አቀረበለት፡፡ የማነህ ብቻውን የእንግሊዝ ፕሪሚርሊግ እያየ ነበር፡፡ የአርሰናል እና የቶትነሃምን የእግር ኳስ ግጥሚያ እያየ መሆኑን ነገረው። የማነህ ‹‹እሺ በቃ እይ›› ብሎ ስልኩን ዘጋው። ተስፋ የኳስ ጨዋታው ሲያልቅ ወደ የማነህ ደወለ። የማነህ ግን ስልክ አላነሳም፡፡ ደጋግሞ ቢደውልም የማነህ ምላሽ አልሰጠውም፤ በዛው ዝም ብሎ ቆየ፡፡ ተስፋ ወደ ቤቱ እየሔደ መንገድ ላይ የማነህ ደወለለት።

ተስፋ ለየማነህ ‹‹ለምን ስልክ አላነሳህልኝም?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ‹‹ ለቅሶ ቤት ነበርኩ፡፡ አሁን ና ቢራ እንጠጣ፡፡›› አለው፡፡ ተስፋ በበኩሉ፤ ‹‹ብር የለኝም። ካለህ እና ከከፈልክልኝ እመጣለሁ፡፡›› የሚል ምላሽ ሰጠው፡፡ ተስፋ ይህንን ሲል በኪሱ ብር አልነበረውም። የማነህም ብር ላይኖረው ይችላል የሚል ስጋት ነበረበት።

ተስፋ እየተጠራጠረ ዘወትር ወደሚጠጡበት ቤት ሔደ፡፡ እዛ ሲደርስ ግን የማነህ ብቻውን አልነበረም። አብሮት ተስፋሁን ተክላይ ነበር፡፡ ተስፋ ተስፋሁንን ሲያይ ቅር አለው፡፡ ተስፋ አስቀድሞ ተስፋሁንም አለ ብሎ ቢነግረው አይመጣም ነበር፡፡ እርሱም ተቀምጦ አንድ ቢራ አዘዘ፡፡ እነርሱ እየደጋገሙ ሲጠጡ እርሱ ግን ከአንድ ቢራ በላይ አልጠጣም፡፡ ሰዓቱ መሸ፡፡ አራት ሰዓት ሲሆን፤ የመጠጥ ቤቱ ባለቤት ‹‹አስተናጋጅ ሊቀየር ስለሆነ ለአስተናጋጁ የጠጣችሁበትን ክፈሉ›› አለ፡፡

ተስፋሁን ለመክፈል ብር አወጣ፡፡ የማነህ ምንም እንኳ ለተስፋ እከፍልልሃለሁ ና ልጋብዝህ ቢለውም ለመክፈል አልሞከረም፡፡ ተስፋም ገንዘብ ስለሌለው መክፈል አልቻለም፡፡ ተስፋሁን ‹‹የሁላችንንም እኔ እከፍላለሁ፡፡›› ብሎ ገንዘብ ከኪሱ ሲያወጣ፤ ተስፋ በበኩሉ፤ ‹‹እርሱ እንዲከፍልልኝ አልፈልግም፡፡›› አለ። ተስፋሁን የተስፋ መመፃደቅ እያስገረመው፤ ‹‹ለምን እኔ አልከፍልም? ›› እያለ ከመጠየቅ አልፎ በጠጣ ምላሱ መደንፋት ጀመረ፡፡

ተስፋ በተስፋሁን ንግግር በጣም ተበሳጨ፡፡ የማነህ ገንዘብ ስለሌለው ለመክፈል አልሞከረም፡፡ ተስፋም ገንዘብ አልነበረውም፡፡ ተስፋ የማነህ ገንዘብ ሳይኖረው ስለጠራው ይበልጥ ተናደደ፡፡ ተስፋሁን መልሶ፤ ‹‹እንደውም አልከፍልላችሁም የምከፍለው ለራሴ ብቻ ነው፡፡›› ሲል፤ ተስፋ ‹‹አትለፍልፍ›› ብሎ ከመጠጥ ቤቱ ወጣ፡፡ በዝናብ በመንገዱ ላይ በብስጭት ብዙ ተጓዘ፡፡

የክፍያው ጣጣ

የማነህ ተጨንቆ ተስፋሁንን ለምኖ የጠጡበትን እንደምንም አስከፈለው፡፡ ‹‹ተስፋ ቤት እንሂድና እንደከፈልክ እንንገረው በዛውም ታረቁ፡፡›› አለው። እልህ እና ትዕቢቱ ታገስ ያለለት ተስፋሁን በየማነህ ሃሳብ ተስማምቶ ተስፋ ቤት ሔዱ፡፡ አብረው ተስፋ ቤት ሆነው ቢጠብቁትም ተስፋ በጊዜ አልመጣም፡፡

ተስፋ በካፊያ መልክ የሚወርደው ዝናብ አበሰበሰው፡፡ ነገር ግን ዝናብ እና ቅዝቃዜው ንዴቱን አላበረዱለትም፡፡ ምሽቱ እየገፋ ሄደ፡፡ ስልኩን ሲያይ አምስት ሰዓት መሆኑን አወቀ፡፡ ወደቤት ለመመለስ ወሰነ፡፡ ቅዝቃዜው እያንቀጠቀጠው ቤቱ ሲደርስ 5 ሰዓት ከ30 ሆኖ ነበር፡፡ ጊቢውን አልፎ ቤቱ ሲገባ ቤቱ ውስጥ ሰው አለ፡፡ አልጋው ላይ ተስፋሁን እና የማነህ ተኝተዋል፡፡ ተመልሶ ብልጭ አለበት፤ ሮጦ የሽንኩርት ቢላዋ አንስቶ ተስፋሁንን ከእንብርቱ በታች ወጋው። ተስፋሁን ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶት ስለነበር ለመከላከል አልሞከረም፡፡

የማነህ ግን ተነሳና ተስፋን ያዘው፡፡ ተስፋ የማነህን ወርውሮ ጣለው፡፡ ተስፋ ‹‹ቢላዋውን እንደያዘ ምናባታችሁ ልትሠሩ ቤቴ መጣችሁ?›› ብሎ አፈጠጠ፡፡ የማነህ ቢላዋውን እያየ፤ ‹‹የጠጣንበትን ከፍሎልናል እኮ›› ብሎ ምላሽ ሰጠው፡፡ ተስፋ የማነህን አላስጨረሰውም፤ በቦክስ ጉንጩን መታው፡፡ አሁንም ንዴቱ አልበረደለትም፤ ተስፋሁን አለመነሳቱን ሲያይ ተስፋ በድጋሚ የማነህን በቴስታ ግንባሩን ብሎ ጣለው። የማነህ መሬት እንደወደቀ፡፡ ተስፋ መለስ ብሎ ተስፋሁንን ሲያየው ተስፋሁን እንዳሸለበ ደሙ እየፈሰሰ ነው፡፡

ተስፋ ‹‹የራሳችሁ ጉዳይ ከቤቴ በአስቸኳይ ውጡ›› ብሎ ቆመ፡፡ ቢጠብቅ ሁለቱም ከቤቱ አልወጡም። ተስፋሁን አልጋ ላይ ተንጋሎ ደሙ ይፈሳል፡፡ የማነህም መሬት እንደወደቀ ነው፡፡ ተስፋ ምንም እንኳ በተስፋሁን በጣም ቢበሳጭም ድጋሚ ሊወጋው አልፈለገም። የማነህንም አይቶ በቢላዋው ሊወጋው አላሰበም፡፡ ሁለቱንም ባሉበት ሁኔታ ጥሏቸው ወጣ፡፡

የማነህ ሁኔታውን ሲያይ ተስፋሁን ሕይወቱ ሊያልፍ እንደሚችል ገምቶ መጮህ ጀመረ፡፡ ሰዎች ተሰበሰቡ፡፡ ሁሉም በየተራ ተስፋሁንን ተመለከተው። ተስፋሁን በዛችው ቅፅበት ሕይወቱ አለፈ፡፡ ሴቶች ነጠላ እያዘቀዘቁ መጯጯህ ጀመሩ፡፡ ጎረቤት ተጠራራ፤ ለፖሊስ ስልክ ተደወለ፡፡ የዕለቱ ተረኛ ፖሊስ ወዲያው ደረሰ፡፡ የፖሊስ የምርመራ ቡድን መጣና አስክሬኑ ተነሳ፡፡

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ ባካሄደው ምርመራ ተስፋ ወልዳይ የተባለው የ31 ዓመት ዕድሜ ያለው ሰው በሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ሰው ለመግደል በማሰብ ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ30 በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ጨርቆስ ሃያ ሁለት በተባለው አካባቢ ተስፋሁን ተክላይን እንደገደለ መረጃዎችን አሰባሰበ፡፡

የተከሳሽ ተስፋ ወልዳይን ቃል ከመቀበል በተጨማሪ የሶስት ምስክሮችን ቃል ተቀብሎ አደራጀ። ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ በመስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም የተፃፈውን የአስክሬን ምርመራ ውጤት ሰነድ አደራጀ፡፡ ወንጀሉን የሚያመለክት የሟች ገፅታን የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ አያይዞ ለአቃቤ ሕግ አቀረበ፡፡

የክሱ ዝርዝር

የማነህ ክንፈ፣ ተስፋ ወልዳይ እና ተስፋሁን ተክላይ አብረው የሚያድሩ ጓደኛሞች ቢሆኑም፤ ተስፋ ወልዳይ ‹‹ከቤቴ ውጡ›› በማለት ሟች ተስፋሁን ተክላይ ተኝቶ በነበረበት በቀኝ በኩል ከእንብርቱ በታች ስለታም በሆነ ቁስ አካል አንድ ጊዜ የመብሳት ጉዳት አድርሶበታል። በደረሰበት ጉዳት ተስፋሁን ተክላይ ሕይወቱ ያለፈ በመሆኑ፤ ተከሳሽ ተስፋ ወልዳይ የተባለው የ31 ዓመት ዕድሜ ያለው ሰው በፈፀመው ተራ የሰው መግደል ወንጀል መከሰስ አለበት ብሏል፡፡

ተስፋ በሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ሰው ለመግደል በማሰብ ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ30 በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ጨርቆስ ሃያ ሁለት በተባለው አካባቢ ተስፋሁን ተክላይን ከመግደል በተጨማሪ የማነህ ክንፈንም በቦክስ እና በቴስታ ግንባሩን የመታ በመሆኑ በፈፀመው ቀላል የአካል ጉዳት ወንጀል ተከሷል ሲል ዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝሩን ለፍርድ ቤት አቀረበ፡፡

አያይዞም ሶስት የሰው ምስክር፣ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ በመስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም የተፃፈውን የአስክሬን ምርመራ ውጤት ሰነድ አደራጅቶ ለዳኞች ሠጠ፡፡ በተጨማሪ የወንጀሉን አፈፃፀም ይበልጥ ለማስረዳት ያመቻል በሚል፤ የሟች ገፅታን የሚያመለክት ፎቶ ግራፍ ለፍርድ ቤት አሳየ፡ ፡ በተጨማሪ ወንጀሉ በተፈፀመበት ዕለት ለሊት ተከሳሽ ተስፋ ለፖሊስ የሠጠውን የእምነት ክህደት ቃልም በእማኝነት ቀረበ፡፡ በመጨረሻም ተከሳሽ ተስፋ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 540ን በመተላለፉ ቅጣት ይገባዋል ሲል ለፍርድ ቤቱ ሃሳብ ሰጠ፡፡

 

                                                                                                 –ውሳኔ

በከሳሽ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ ተስፋ ወልዳይ ገብረ መድህን መካከል በተፈጠረው ሰው የመግደል ወንጀል ዙሪያ በክርክር ላይ የነበረ ጉዳይ መቋጫ አገኘ፡፡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ በሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ጥፋተኛውን ያርማል ህብረተሰቡን ያስተምራል ብሎ በሰጠው ውሳኔ ተከሳሽ ስምንት ዓመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ በማለት ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ምህረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You