የተዘነጋው የኤች አይ ቪ ኤድስ አሳሳቢነት

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ የዓለም ሕዝቦች ከኤች አይቪ ኤድስ ጋር ይኖራሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ደግሞ የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። ከነዚህ መካከል ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናት ከኤች አይ ቪ ኤድስ ጋር እንደሚኖሩና በቫይረሱ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከሚሞትባቸው አህጉራት ውስጥም አፍሪካ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡

ከአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ለተጓዳኝ በሽታዎች በማጋለጥ የአንጎል ህዋሶች በአግባቡ ሥራቸውን እንዳያከናውኑ በማድረግ የመርሳት ህመምን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተጨማሪም ኤች አይ ቪ በሽታን በተመለከተ የተለያዩ የጤና ድረ-ገፆች ላይ የሰፈሩ ፅሁፎች እንደሚያብራሩት፤ ትኩሳት የመጀመሪያው የኤ.አር ሲ ምልክት ሲሆን፤ ከጉሮሮ ህመም፣ ከሊምፍ (በደም ውስጥ የሚገኝ ፈሳሽ ንጥረ ነገር) አመላላሽ ቱቦዎች እብጠት እና ከድካም ጋር ይያያዛል። ሌላኛው የበሽታው ምልክት ከፍተኛ የድካም ስሜት ሲሆን፤ ሰውነት በኢንፌክሽን (ማመርቀዝ) ሲዳከም የመቆጣት ምላሽ ይሰጣል። ይህም ለህመሞች የሚሰጠው ምላሽ ከፍተኛ የድካም ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል።

የመገጣጠሚያ አጥንቶች ህመም፣ የጉሮሮ ህመም እና ከፍተኛ የራስ ምታት፣ የቆዳ መንደብደብ፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ እና ተቅማጥ ከ30 እስከ 60 በመቶ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የተቅማጥ በሽታ ያጋጥማቸዋል። ክብደት መቀነስ፣ ደረቅ ሳል፣ ለሳምንታት የዘለቀ ደረቅ ሳልም በቫይረሱ መያዝን ሊያመላክት ይችላል። የሳንባ ኢንፌክሽንም ከምልክቶቹ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ግማሽ የሚሆኑት ከኤች አይ.ቪ ኤድስ ጋር የሚኖሩ ሰዎች በሌሊት ላብ ይጠመቃሉ። ይህም ከመኝታ ክፍሎች ሙቀት ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። የጥፍር ቀለም እና ቅርፅ መቀየር፣ የጥፍሮች መታጠፍ እና መጥቆር ቫይረሱ ወደ ሰውነታችን እንደገባ ሊያሳዩ ይችላሉ። የመተንፈሻ እና የመራቢያ አካላት ህመም፣ ብሎም የእጅ እና እግር ጡንቻዎች አቅም ማጣት ወይም መንቀጥቀጥ ለኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ብቻም ሳይሆን ለስኳር በሽታ መጋለጥንም ሊያሳይ ይችላል።

ተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ የተሰኘውና ኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ የሚሠራው ድርጅት በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ባጋራው ሰፋ ያለ መረጃ፤ ‹‹የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ምልክቶች አንዳንድ ጊዜ ሳይታወቁ ለረጅም ጊዜ ሊደበቁ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ቫይረሱ ወደ ሰውነት ከገባ ከአንድ እስከ ሁለት ወራት ባሉት ጊዜያት ውስጥ 50 በመቶ የኤች አይ ቪ ኤድስ ተጠቂዎች በቅድሚያ የሚገጥማቸው የህመም ምልክቶች (አኪዩት ሪትሮቫይራል ሲንድረም)›› የሚታይ ይሆናል።

እነዚህ የህመም ምልክቶች ከታዩ ታዲያ ኤች አይ ቪ ኤድስ በደም ውስጥ ስለመኖሩ ጠቋሚ ሊሆን ስለሚችል ወደ ህክምና ተቋማት ማምራት ተገቢ ነው። ኤ አር ሲ (አኪዩት ሪትሮቫይራል ሲንድረም) ሰውነት የተለያዩ ባክቴሪያዎችን እና ቫይረሶችን ለመቋቋም የሚያስችለውን ‹‹አንቲቦዲስ›› ከማምረቱ በፊት የሚከሰቱ የመጀመሪያ የህመም ስሜቶች ናቸው።

ኤች አይ ቪ ኤድስ ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ የደም ንክኪ፣ ስለታማ ነገሮችን በመጋራት እንዲሁም በእርግዝና ወቅት ከእናት ወደ ልጅ እንደሚተላለፍ ይታወቃል። በርካቶችም ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ ነው የሚባል ባይሆንም፤ አሁንም ግንዛቤው የሌላቸው ሰዎች እንዳሉና በይቫረሱ የሚያዙ ሰዎች ብዙ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለቫይረሱ መጋለጣቸውንም ቸል በማለት በወቅቱ ተመርምረው መድሃኒት ባለመጀመራቸው ለሞት ሊዳርጉ እንደሚችሉ ሐኪሞች ያስገነዝባሉ፡፡

አቶ ተመስገን ካሴ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ እና ምክር አገልግሎት ቢሮ ቴክኒካል አማካሪ ሲሆኑ፤ በሽታው በአሁኑ ወቅትም አሳሳቢ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ የበሽታው መተላለፊያ መንገዶች የሚታወቁ ቢሆንም በማህበረሰቡ ዘንድ መዘናጋት እንደሚስተዋል ጠቁመዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚሁ በሽታ የሚጠቁ ሲሆን፤ በተለይም ደግሞ በታዳጊ ሀገራት ያለው ሁኔታ የተባባሰ ነው፡፡ በበሽታው የሚያዙም ሆነ ምርመራ በማድረግ ረገድም በታዳጊ ሀገራት ያለው አሃዝ (ከፍ) ያለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአፍሪካ ከፍተኛው ቁጥር ይይዛል፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ ደግሞ የስርጭቱ መጠን የቀነሰ (0 ነጥብ 84 በመቶ) ቢሆንም በከተሞች ከፍተኛ ስርጭት መኖሩን እና አሁንም ድረስ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ስለመሆኑም ያብራራሉ፡፡

 

እንደ አቶ ተመስገን ገለፃ፤ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራን በተመለከተ ገና ብዙ መሠራት አለበት፡፡ በተለይም ሰዎች ተጋላጭ መሆናቸውን ከጠረጠሩ ስለራሳቸው የጤና ሁኔታ ለማወቅ ምርመራ ቢያደርጉ ይመከራል። በአዲስ አበባ ከ 171 ማዕከሎች በላይ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሽታው አሳሳቢ የጤና ችግር ሲሆን እንደ አዲስ አበባ ስርጭቱ 3 ነጥብ 2 በመቶ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ደግሞ በርካታ ዜጎች ቫይረሱ ደማቸው ውስጥ ይገኛል፡፡ ስርጭቱም 0 ነጥብ 84 በመቶ ደርሷል፡፡

አማካሪው እንደሚሉት፤ የበሽታው ስርጭት በአካባቢ (በጂኦግራፊ) ሲከፋፈል ግን አዲስ አበባ ከጋምቤላ ቀጥሎ እንደ ሀገር በሁለተኛ ደረጃ የምትገኝ ናት፡፡ ይህም በከተማ ከፍተኛ ስርጭት መኖሩን ይጠቁማል፡፡ በዚያው ልክ በሽታው በሴቶች፣ ህፃናት፣ አዛውንቶች፣ ወጣቶችና ላይ የስርጭት ደረጃው ይለያያል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ያለው ሁኔታም የበለጠ መትጋት እና በሽታውን መከላከል ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ የሚሳይ ነው፡፡

የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ችግሩ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊም ጭምር ነው፡፡ ይህም እንደ ሀገር ጉዳቱ ከፍተኛ ሲሆን ዘርፈ ብዙ ችግሮችንም ያስከትላል፡፡ በተለይም ደግሞ አምራቹን የማህረሰብ ክፍል ወይንም ወጣቶች በበሽታው በሰፊው የመጠቃት ዕድል ያላቸው በመሆኑ በአንድ ሀገር የምጣኔ ሀብት ዕድገት ወይንም ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ ይህ በመሆኑም በሽታውን ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር አስቻይ ምህዳር መፍጠር ይገባል፡፡

እንደ አቶ ተመስገን ገለፃ፤ በሽታውን ለመከላከል ከሁሉም በቀደመ መልኩ የባህሪ ለውጥ ላይ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በተደጋጋሚ መረጃዎችን በማሰራጨት እና በማንኛውም የተግባቦት ስልት በመጠቀም ግንዛቤ በመፍጠር ላይ ለውጥ መምጣት አለበት። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከማንኛው በላይ መገናኛ ብዙሃን በኃላፊነት ሊሠሩ እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን በሽታውን ለመከላከል እና ስርጭት ለመግታት ስልታዊ መዋቅር ‹‹ስትራቴጂካል ስትራክቸር›› መፈጠር እንዳለበትም ያብራራሉ፡፡

በየሥራ ባህሪ ለበሽታው የመጋለጥ ሁኔታዎች እንደሚለያዩ የሚናገሩት አቶ ተመስገን፤ ፆታዊ ጥቃቶች በብዛት ለበሽታው መስፋፋት ቀዳሚውን ሚና እንደሚወስዱ ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩት ሴቶች ለበሽታው በመጋለጥ ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን 19 በመቶ የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ ይገመታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለበሽታው የሚጋለጡት ደግሞ በሽታው ወደ ሌሎች የመተላለፍ ዕድሉንም ያሰፋዋል፡፡

አማካሪው እንደሚሉት፤ የረዥም ወይንም ሀገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች 4 ነጥብ 6 በመቶ በቫይረሱ ተጠቂ ናቸው፡፡ የትዳር አጋራቸው የሞቱባቸው 11 በመቶ ብሎም ፍቺ የፈፀሙ ደግሞ እስከ 2 ነጥብ 9 ስርጭቱ በመቶ የሚገኝባቸው ወይንም የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ከዚህም በዘለለ ሜጋ ፕሮጀክት አካባቢ የሚሠሩ ዜጎች ለበሽታው የመጋለጥ ዕድል 1 ነጥብ 3 በመቶ ነው፡፡ ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች ደግሞ 1 ነጥብ2 በመቶ የመጋለጥ ዕድል አላቸው፡፡ አካል ጉዳተኞች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና ወጣቶች እንዲሁም ጎልማሶች የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፋ ያለ ነው፡፡

እንደ ሀገር ለበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሆኑት 265 ወረዳዎች ሲኖሩ፤ ከእነዚህ ውስጥ 48 ወረዳዎች መገኛቸው አዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ እነዚህ አሃዞች በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ማሳያ ናቸው ይላሉ፡፡

በመሆኑም በከተማ ደረጃ ያለው የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ በሽታው በመጀመሪዎቹ ወቅቶች አሳሳቢም አስፈሪም ተደርጎ ይወሰድ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን መዘናጋቶች እንደሚስተዋሉ ያብራራሉ። የቫይረሱ ስርጭት አሁን ያለበት ደረጃ የሚያዘናጋ ሳይሆን ይልቁንም ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በሥራ ባህሪያቸው ለቫይረሱ የመጋለጥ ዕድል ያላቸው ዜጎች ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራ ቢያካሂዱ ይመከራል ይላሉ፡፡

በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ምርመራ እና ህክምና ዙሪያ በከፍተኛ ትኩረት በየሁለት ሳምንቱ በቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና በበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክተር እየተመራ ከክፍለ ከተማ እና ከጤና ተቋማት አመራሮች ጋር እየተገመገመ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ቢሆንም ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችን (የሴክሽዋል አጋራቸውን እና ከ19 ዓመት በታች ያሉ ልጆቻቸውን) አምጥተው ማስመርመር ላይ ክፍተት ስለሚስተዋል ኃላፊነታቸውን ቢወጡ ይመከራል፡፡ ይህም የራሳቸውን ብሎም በዙሪያቻው ያሉትን ሰዎች ጤና ለመታደግ ብሎም ከጥርጣሬ ለመዳን ፋይዳው የጎላ መሆኑን አቶ ተመስገን አስገንዝበዋል፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You