ታሪክ ሰርቶ የሚያልፍባቸው በርካታ አሁናዊ አጋጣሚዎች አሉት፡፡ ከነዚህ አጋጣሚዎች ውስጥ አንዱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ነው። እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ለአንድ ዓላማ በአንድ ከቆምንባቸው ታሪኮቻችን አንዱን ሆኖ የሚቀጥል፣ ኢትዮጵያንም የሚያስጠራ የአዲስ አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ ያለፉትን አምስት ዓመታት ዓለምን ባስደነቀ መልኩ ስለሰው ልጅ ግድ በሚለው የህልውና ጉዳይ ላይ ፊተኞች ሆነን ሰንብተናል፡፡ ዘንድሮም በተመሳሳይ መልኩ ካለፈው በበለጠና በላቀ ተሳትፎ ዐሻራችንን ልናሳርፍ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡
ከትናንት እስከዛሬ ለዓለም ህልውና አደጋ ሆነው ከታዩ ክስተቶች መሀል የአየር ንብረት ስጋት ዋነኛው ነው፡፡ መፍትሄ ሆኖ የተገኘው ደግሞ በአረንጓዴ ዐሻራ እሳቤ የተሰማራ መንግሥትና ማህበረሰብ ናቸው። አካል ቢታመም በመድሃኒት ይድናል፡፡ ራስ ወይም ሆድ ቢታወቅ በኪኒን አሊያም በመርፌ ይሽራል፡፡ ተፈጥሮ ከታመመ ግን ዛፍ ከመትከልና ለአረንጓዴ ዐሻራ ቅድሚያ ሰጥቶ ከመንቀሳቀስ ባለፈ መዳኛ የለም፡፡ ብዙ ጥናቶች ተፈጥሮን ከውድመት ለመታደግና የሰው ልጅን ከህልውና ስጋት ለመመለስ እንደፍቱን መድሃኒት ያስቀመጡት የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄን ነው፡፡
በዚህ ደግሞ እየተሳካላቸው ካሉ ሀገራት ተርታ ተሰልፈናል፡፡ ያለፉት አምስት ዓመታት ከልማትና ከአበይት ሀገራዊ ጉዳዮች ጎን ለጎን በአረንጓዴው ዐሻራም ተዐምር የሰራንበት እንደነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡ ከትላልቅ ፕሮጀክቶች እኩል በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተሠሩ ካሉ አበይት ሀገራዊ ክንዋኔዎች መካከል አንዱ ሆኖ በትግበራ ላይ ይገኛል፡፡
ከሊቅ እስከደቂቅ፣ ከባለሥልጣን እስከ መንግሥት ሠራተኛ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል አሳትፈን እንደህዳሴ ግድብና እንደዓድዋ ድል ታሪክ በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ ዘንድሮም ‹የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ› በሚል መነሻ ሃሳብ እንዳለፈው ጊዜ በጋራ ዘምተናል። ዘመቻው ዓለም አቀፍ መልክ ያለው፣ የሰው ልጆችን ሁሉ የማዳንና የመጠበቅ ተልዕኮ ያለው፤ ዓለምን ወደአንድ የአረንጓዴ ዐሻራ አስተሳሰብ ለማምጣት እንደአርዐያ የሚታይ ነው፡፡
ግሎባላይዜሽን ዓለምን ለአንድ ዓላማና ተልዕኮ ወደአንድ መንደር የማሰባሰብ ሂደት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በአረንጓዴ ዐሻራም እንደዚሁ ለአንድ ዓላማና ተልዕኮ በጋራ ሠርተን በጋራ ህልውናችንን ለማረጋገጥ የጀመርነው እንቅስቃሴ አንድ አካል ነው፡፡ ዘላቂ ህልውናን ታሳቢ ባላደረገ መልኩ ብንሰለጥን በዘመናዊነት ብንራቀቅ ትርጉም የለውም። የዓለም ሥልጣኔ እለት በእለት ሲዘምንና ሲመነደግ በአየር ንብረት ለውጥ ግን ምድርንና የሰው ልጆችን ወደሞት እየሰደደ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን በትላልቅ ታሪኮች ለዓለም ስምና ክብር፣ ነጻነትና ፍትህ ስትሆን እናውቃለን። በዓድዋ ለመላው የሰው ልጅ የነጻነት ችቦን ለኩሰናል፣ መላውን ጥቁር ሕዝብ ከሰው እንዲቆጠር እስከሞት የደረሰ ዋጋ ከፍለናል፡፡ በህዳሴ ግድብም አንዳንድ ጠላት ሀገራት ያለበሱንን አይችሉም የሚለውን ያረጀ የክፋት ስም በይቻላል ቀይረን ማንነታችንን አሳይተናል፡፡ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርም ማንም ባላደረገውና ባልሞከረው ሕዝባዊ ተሳትፎ ሽልማትና የክብር ስምን ከመቀዳጀት አንስቶ ብዙዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት መሪ ተዋናይ ሆነናል፡፡
ክረምት ለእኛ ብዙ ትርጉም ያለው ወቅት ነው፡፡ የጀርባ አጥንት የሆነው የግብርና ሥራችን ክረምትን ታኮ ነፍስ እንደሚዘራ፣ ለአረንጓዴ ዐሻራም የማይተካ ሚናን እየተጫወተ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ባሳተፈ መልኩ በየአመቱ የክረምት ወቅትን ታሳቢ በማድረግ የሚተከሉ ችግኞች ከላይ ላነሳሁት ሃሳብ ምስክሮች ናቸው፡፡
በየአመቱ በተለያየ አንቂና አሳታፊ መሪ ሃሳብ ተክለናል.. አጽድቀናል፡፡ ለአንድ ዓላማ፣ ለጋራ ክብር በክተት አዋጅ ተመርተን ስምና ዐሻራ አስቀምጠናል፡፡ ያለፈውን አመት ‹ነገን ዛሬ እንትከል› በሚል መሪ ቃል አጀአብ በሚያሰኝ የሕዝብ ማዕበል ታሪክ ሠርተን አልፈናል። ዘንድሮም ‹የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ› ስንል ታጥቀን በመነሳት እንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን።
ነገ ዛሬ ነው የሚሠራው፡፡ ራሱን የሚያ ፈቅር፣ ለትውልዱ ግድ የሚለው መንግሥትና ማህበረሰብ የነገ ህልሙን ከዛሬ ነው የሚጀምረው፡፡ ዓድዋ ትናንትና በአባቶቻችን ተሰርቶ ዛሬ ስማችን፣ ክብራችን፣ መጠሪያችን ሆኗል፡፡ የህዳሴ ግድብን ዛሬ ላይ ገድበን ነገ ላይ ልጆቻችን በኩራት የሚኖሩበትን የህብረብሄራዊነት ሀውልት ተክለንላቸዋል፡፡ አረንጓዴ ዐሻራም እንደዚሁ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የክብርና የይቻላል ስማችን ነው፡፡ እንደዐድዋ ነገ ላይ የዚህ ትውልድ መጠሪያ ስም ሆኖ ይቀመጣል፡፡
እንደዓድዋና የህዳሴ ግድብ አረንጓዴ ዐሻራም የህብረብሄራዊነት አርማችን ነው። የሚያስተሳስረን፣ የሚያስተቃቅፈን የጋራ ትርክታችን ነው፡፡ ዛፍ ስንተክል የጋራ ትርክት እየፈጠርን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በንቃት ስንሳተፍ የአብሮነት ትርክት እያበጀን ነው። በአንድነት ለአንድነት ሥንሰራ አስታራቂና አስማሚ ዐሻራ እያስቀመጥን ነው። አረንጓዴ ዐሻራ ከሚሰጠን ዘርፈ ብዙ በረከቱ ጎን ለጎን ኢትዮጵያዊነታችንን የምንቀልምበት በጎ አጋጣሚያችም ጭምር ነው፡፡
የጋራ ትርክት ከብቻ ትርክት ማምለጫ የማርያም መንገዳችን ነው፡፡ ስንተክል፣ ስናጸድቅ፣ ለአብሮነት ስንለፋ ከብቻ ትርክት እየራቅን የአብሮነት ታሪክ እየጻፍን ነው፣ በዚህም ነጋችንን እየሠራን ነው፡፡ የምትተክል ሀገር የሚያጸድቅ ትውልድ የሚለው መነሻ ሃሳብም ነገን ዛሬ ከመሥራት ጋር የተሳሳመ ሃሳብ ነው፡፡ በዚህ መነሻ ሃሳብ ላይ ሀገር ማለት ብዙሃኑ ማህበረሰብ ነው። ሀገር ማለት በእኔና እናተ ማዕቀፍ ስር የሚገለጽ ነው። ‹የሚያጸድቅ ትውልድ› እኛና መጪውን ትውልድ የተሳሰረበት ገለጻ ነው። በሀገር ስም እኛ እንተክላለን እንደትውልድም የተከልንውን እናጸድቃለን፡፡ መጪው ዘመን ለመጪው ትውልድ መልካም እንዲሆን አብሮነትን እንናገራለን፡፡
የአፍሪካ መዲና ሽቅርቅሯን አዲስ አበባ ጨምሮ ሁሉም የክልክ ከተሞች እስከ ወረዳ ድረስ በሚደርስ የተቀናጀ ሥራ አረንጓዴ ዐሻራን እየተገበሩ ይገኛል፡፡ ጅማሮአችን አዋጪና ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ያለፉትን ሶስትና አራት ዓመታት ማጤኑ ብቻ በቂ ነው፡፡ ለውጥ ካመጣንባቸው በዓለም አቀፍ ሚዲያ መነጋገሪያ ከሆንባቸው ሁነቶች መሀል አንዱ ሆኖ ታሪክ መዝግቦታል፡፡ በአንድ ጀምበር ብዙ ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ዓላማችንን ከሀገር ፈቀቅ አድርገን ዓለምአቀፋዊ ይዘትን አላብሰነዋል፡፡
ችግኝ መትከል ሕይወታችን ነው፡፡ አረንጓዴ ዐሻራ ደግሞ ከትላልቅ ስያሜዎቻችን ጎን አብሮ የሚጠራ መታወቂያችን ሆኖ ይቀጥላል። በተወካዮች ምክርቤት በጀት ጸድቆለት በአዲስ ዝግጅት ሊጀመር እንደሆነ ስንሰማ ደግሞ አብሮን የት ድረስ ሊጓዝ እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ከሚሰጠን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞቹ ጎን ለጎን እንደገቢ ምንጭና እንደየእለት ፍጆታ በማገልገል በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍነቱን እያሳየን ይገኛል፡፡ አመት አመት እያደገ የመጣው የመትከል ሞራላችን ውጤት እያሳዩ የሚፈለገውን ዓላማ እያመጡ ይገኛል። በአረንጓዴ ቀለም የዳበረ የህብረብሄራዊነት ዐሻራ ትውልዱን የሚያስተሳስርና የነገ የመኖር ዋስትናውን የሚያረጋግጥለት ተግባር ነው፡፡
አረንጓዴ ቀለም የሕይወት መልክ ነው። መኖር የሚሉት ብርቅ ነገር ይሄን ቀለም ለብሶ ህላዊ እንዲያገኝ የተፈጥሮ አስገዳጅነት ወድቆበታል። ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናልብሳት ብለን ስንነሳ በብዙ ምክንያት ቢሆንም ከፊታችን የተደቀነውን የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ለመመለስ ጭምር ነው። አረንጓዴ ቀለም በየትኛውም ሀገርና ማህበረሰብ አንድ አይነት ዓላማ ያለው ነው፡፡ የአየር መዛባትን ማስተካከል፣ ድርቅና በርሃማነትን መጠበቅ፣ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ እንዲመጣ ማድረግ፣ የአካባቢ ምህዳር ሚዛንን መጠበቅ የመሳሰሉ በረከቶች አሉት፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የእኔ የአንተ የሌለው ሁሉንም የዓለም ማህበረሰብ የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ ከመፍትሄው አኳያ ከድሃ ሀገራት ይልቅ የበለጸጉ ሀገራት የተሻለ አቅም ቢኖራቸውም በቴክኖሎጂው ዘመናዊነታቸውን ከማሳየት ባለፈ የፈየዱት ግን የለም፡፡ እንዳውም ችግር ፈጣሪና የስጋት ምንጭ በመሆን ጣት የሚቀሰርባቸው ናቸው፡፡ እነሱ በለኮሱት የዘመናዊነት እድፍ ድሃ ሀገራት የችግሩ ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ችግር ፈጣሪነታቸው ደግሞ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የካሳ ጥያቄ በመቅረብ ላይ ይገኛል፡፡
ዓለም ከአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ውጪ ለብዙ ችግሮቿ መፍትሄ አላት፡፡ ከትናንት እስከዛሬ አነጋጋሪና ወቅታዊ አጀንዳ በመሆን የመጣ ነው፡፡ የዓለም ሙቀት እለት በእለት እየጨመረ ብዙዎችን ለሞት የዳረገበትን የቅርብ ጊዜ ክስተት ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው። ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ መንግሥት ይሄን ተገንዝቦ እያደረገ ያለው የቅድመ መከላከል ተግባር እጅጉን የሚደነቅ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ሌሎች ሀገራትም ፈለጋችንን በመከተል ወደአረንጓዴ ዐሻራ እሳቤ በመምጣት ከፊታችን የተጋረጠውን የህልውና ፈተና ለመቀልበስ የመፍትሄው አካል የሆነውን ተሳትፎ በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ምድር ወደሲኦልነት የምትቀየርበት የቀስ በቀስ ሂደት ነው፡፡ የዓለም የሙቀት መጨመር እሳት የሚዘንብበት ክስተት ነው፡፡ እንዲህ ብለን ስንናገር ቀላል ሊመስል ይችላል ግን አይደለም፡፡ እንደ ዓለም ፍጻሜ ቅድመ ምልክቶች በርካታ ምልክቶች እያየን ነው፡፡ በሀገራችንም ሆነ በሌሎች የዓለም ክፍል እያየንውና እየሰማንው ያለው የሞት ዜና የዚህ ክስተት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ እያደረግን ያለነው ምድርን ከሲኦል እሳት የማውጣት ያክል የሚደነቅ እንቅስቃሴን ነው፡፡
በአረንጓዴ ቀለም ታሪክ እየጻፍን፣ ታሪክ እያስተላለፍን ነው፡፡ ዛፍ በመትከል፣ በማጽደቅና በመንከባከብ ሥነምህዳሩን በማስጠበቅ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን። አረንጓዴ ዐሻራ ከትላልቅ ጉዳዮቻችን እኩል የሚጠራ፣ የማንነታችን አንዱ ቀለም ሆኖ ከትውልድ ትውልድ ይተላለፋል። በሰላማዊ አካባቢ የመኖር ዋስትናችንን በማረጋገጥ፣ መርካቶና አትክልት ተራ ሳንሄድ ያማረንን ከጓሯችን እየበላን የመትከልና የማጽደቅ ግባችንን እናሳካለን። ቸር ሰንብቱ፡፡
ቴልጌልቴል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም