አረንጓዴ ዐሻራን ለምግብ ዋስትና ማረጋገጫ

ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለድርቅ፣ ለጎርፍ፣ ለመሬት መሸራተት፣ ለአውሎ ነፍስ፣ ለሰደድ እሳት፣ ለከፍተኛ ሙቀት እና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ እየሆነች ትገኛለች። ለአየር ንብረት ለውጡ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከእነዚህም መካከል የተፈጥሮ ሀብት መራቆት እንዲሁም የደን መመናመንና መጨፍጨፍ አንዱ ነው።

ችግሩ አሳሳቢ እየሆነ መጥቶ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ እስከ መሆን ከደረሰም በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ ድንበር ዘለል ችግር በአንድ ሀገር ጥረት ብቻ ሊፈታ የማይችል መሆኑ ታምኖበት የዓለም ሀገሮች ችግሩን ለመፍታት ያስችላሉ የተባሉ ርምጃዎችን ለመውሰድ በተደጋጋሚ መክረውበት ውሳኔዎች አሳልፈዋል።

ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር ለመፍታት ከሚያስችሉት መንገዶች አንዱ የተመናመነውን የደን ሀብት መተካትና የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ሲሆን፣ በዚህም በተለይ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ትኩረት ተሰጥቶታል።

ኢትዮጵያም ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ትኩረት በመስጠት በምትከተለው የልማት አቅጣጫ የኃይል ልማቷን ጭምር አካባቢን የማይበክሉ ታዳሽ የኃይል አማራጮች እንዲሆኑ አድርጋለች። በዚህም የውሃ፣ የንፋስ፣ የፀሐይ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨትም ትታወቃለች።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የተመናመነባት የደን ሽፋን መለሶ እንዲያገግም ለማድረግ፣ የምግብ ዋስትናን ጭምር ለማረጋገጥ በተለይ ከ2011 ዓ.ም ወዲህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላን በመተግበር ትገኛለች። በሀገር አቀፍ ደረጃ በተጀመረው በዚህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ 32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 40 በመቶ ያህል ነው፤ ይህ የደን ሽፋን እየተመናመነ መጥቶ ሶስት በመቶ ደርሶም ነበር። ይህን ለመቀልበስ በተሰሩ ሥራዎች የደን ሽፋኑን ከመመናመን መታደግ የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ትግበራ በገባው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የችግኝ ተከላ የደን ሽፋኑን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17ነጥብ2 በመቶ ወደ 23ነጥብ6 በመቶ ከፍ ማድረግ የተቻለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል።

ይህ በመላው ሀገሪቱ እየተተገበረ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የሚሳተፍበት ነው። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበትና ባሕል እስከመሆን የደረሰም ሆኗል።

ሀገሪቱ በየዓመቱ የምትተከለው የችግኝ መጠን እየጨመረ መጥቷል። አራት ቢሊየን ችግኞችን በመትከል የተጀመረው መርሀ ግብሩ የሚተከሉት ችግኞች ብዛት በቢሊዮኖች እየጨመረ መጥቶ ዘንድሮ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊየን ችግኞች የሚተከሉበት መሆን ችሏል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩ በየዓመቱ የሚተከሉት ችግኞች ብዛት ብቻ አይደለም እየጨመረ የመጣው። በአንድ ጀንበር የሚተከሉ ችግኞች ብዛትም እንዲሁ እየጨመረ ይገኛል። በ2011 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 350 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ባለፈው ዓመትም እንዲሁ 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 566ሚሊየን ችግኞች ተተክለዋል። በዛሬው ዕለት 600ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል በተያዘው እቅድ መሠረት ተከላው በማለዳ ተጀምሯል።

በኢትዮጵያ እስካሁን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው። መርሃ ግብሩ ለፍራፍሬ፣ ለመኖና ለአፈር ለምነት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የተተከሉበት ሲሆን፤ እነዚህ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና ለግብርና ዘርፍ ካላቸው ጠቀሜታ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ታምኖባቸዋል።

የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ በመርሀ ግብሩ የችግኞች ተከላ እቅድ የነበረው 40/60 የመትከል ዘዴን በመጠቀም መትከል ነው። ይህም ማለት ከ40 በመቶ ያህል ደንና ተያያዥ ችግኞች ፤ 60 በመቶ ያህሉ ደግሞ የምግብና የፍራፍሬ ችግኞች ለመትከል ያለመ ነው።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ የምግብና የፍራፍሬ ችግኞች መትከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። እነዚህ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በዘለለ ወደ ውጭ ተልከው የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው። በተጨማሪም ለእንስሳት መኖነት የሚውሉ በመሆናቸው እንደዚህ ዓይነት ችግኞች እየተተከሉ ይገኛሉ። እነዚህ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በተለይ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ታይቶ በየዓመቱ እንዲተከሉ እየተደረገ ነው።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በየዓመቱ የምግብ ዋስትና የሚያረጋገጡ በርካታ ችግኞች እየተተከሉ ናቸው የሚሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ በየዓመቱ የሚተከሉት ችግኞች ቁጥርም ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሆኑን ይገልጻሉ።

ዘንድሮ ለመትከል ታቅዶ ከነበረው 7ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ 56 በመቶ ያህሉ የምግብና የፍራፍሬ ችግኞች እንዲሆኑ መደረጉን ጠቅሰዋል፤ የተቀሩት 44 በመቶ ያህሉ ደግሞ የደንና የቀረከሃ ችግኞች መሆናቸው ይገልጻሉ።

ከእነዚህ የምግብ ዋስትናን ሊያረጋገጡ ከሚችሉ ችግኞች መካከል የአቡካዶ፣ ዘይቱን፣ ብርቱካን ፣ ማንጎ ችግኞች ይጠቀሳሉ። ችግኞቹም እንደ የሥነ-ምህዳሩ ዓይነት እየታዩ ይተከላሉ። የችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከተተከሉት የምግብና የፍራፍሬ ችግኞች መካከል የአቡካዶ ምርት ለውጭ ገበያ እየተላከ ያለበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቅሰዋል። የተቀሩት ግን ለሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ እየዋሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ እስካሁን ኤክስፖርት የሚደረጉበት ደረጃ ላይ አይደሉም ሲሉ ተናግረዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገርም ለግብርናው ዘርፍ የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው የሚሉት አቶ ፋኖሴ፤ የአፈር ጤንነትና ለምነት ከማረጋገጥ አኳያ ከፍ ያለው ጠቀሜታ አላቸው ይላሉ። አሁን ላይ ከፍተኛ ዝናብ በሚጥልባቸው አካባቢዎች የአፈር መሸርሸር እንደሚከሰት ጠቅሰው፣ የአፈር መሸርሸር ደግሞ የአፈር ንጥረ ነገሮች በጎርፍ የሚሄዱበትን ሁኔታ እንደሚያስከትል አስታውቀዋል። ይህን ችግር ለመከላከል ችግኝ መትከል ያስፈልጋል ብለዋል።

ቀደም ሲል የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው በየዓመቱ ነጥረ ነገሮችን የያዘ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር አፈር በጎርፍ ተጠርጎ ወደ ወንዝ ይገባል። እነዚህ ወደ ወንዝ የሚገቡ የአፈር ንጥረ ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባው የአፈር ማዳበሪያም ጭምር በጎርፍ ይወሰዳል። ይሄ ደግሞ የአፈር አሲዳማነት እንዲባባስ ያደርጋል ሲሉ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ 4ሚሊዮን ሄክታር መሬት በከፍተኛ አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን ለእዚህ በአብነት አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከመተግበር አኳያ ይህን ችግር ለመቅረፍ ዋና መፍትሔ የሆነው ችግኝ መትከል በመሆኑ በየዓመቱ ችግኞችን በመትከል የአፈር ጤንነትን እና ለምነትን ማረጋገጥ ይቻላል። የአፈር ጤንነትን እና ለምነትን መጠበቅ ከተቻለ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚረጋገጥበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህ ደግሞ ለሰብል ብቻ ሳይሆን የእንስሳት መኖ ለማግኘት አፈሩ ጤናማነት መሆን አለበት። የችግኝ ተከላ ለግብርናው ዘርፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ምርትና ምርታማነት ከመጨመር አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

ችግኞችን መትከል የሥራ እድል ከመፍጠር አኳያም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ይገልጻሉ። በተለይ በለሙ ተፋሰሶች ላይ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መተግበር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ነው። ይህም ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎች የየአካባቢው ነዋሪዎች ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑበትን እድል ይፈጥራል። በንብ ማነብ፣ ከብቶች በማደለብ እና በመሰል ሥራ መስኮች ላይ ሊሰማሩ ይችላሉ። በተጨማሪ በየችግኝ ጣቢያዎቹ ችግኝ በመንከባከብ ብዙ ሰዎች ሊሳተፉበት የሚችሉት ሥራ በመሆኑ ለብዙዎች የሥራ እድልን ይፈጠራል።

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተግባራዊ ማድረጓ በሁሉም ረገድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንድታገኝ ያደርጓታል የሚሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፣ የመጀመሪያው ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ነው ይላሉ። ምርትና ምርታማነት አደገ ስንል ከውጭ የሚገባውን ምርት መተካትን ፣ የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ እና የአየር ንብረት የሚቋቋም ችግኞችን መትከልን ይጠይቃል። በአጠቃላይ ችግኝ መትከል ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ እየተሰራበት ይገኛል ይላሉ።

መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንዳብራሩት፤ ዘንድሮ 7ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቀዶ ተከላው ሲካሄድ ቆይቷል። ዛሬ ማለዳ ደግሞ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከሉ ሥራ ተጀምሯል። ችግኞቹ በወቅቱ በተከላ ቦታዎች ላይ እንዲደርሱ የማድረግ ሥራዎች አስቀድሞ ተሰርተዋል። በዕለቱም ችግኞቹ ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ርቀታቸውን በመጠበቅ ሥራቸው እንዳይታጠፍ አድርጎ መትከል ከሁሉም ዜጋ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

ችግኞችን ከመትከል ባሻገር የተተከሉትን ችግኞች መንከባከብ ሌላው ከሕዝቡ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ጠቅሰው፣ ችግኞችን የመንከባከቡ ሥራ ቀደም ባሉት ጊዜያት እምብዛም ትኩረት እንዳልተሰጠው ይናገራሉ። ችግኝ በመንከባከብ ረገድ ከባለፉት ዓመታት ልምዶች በመውስድ በርካታ ሥራዎች መሥራታችውንም ይገልጻሉ። የህብረተሰቡ ችግኞችን የመትከል ልምድ እየዳበረና እያደገ ችግኝ መትከልን ባሕል እያደረገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እያገኘ በመሆኑ ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻሎች እየታዩና ለውጦች እንዲመጡ አድርጓል ይላሉ።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያለው የችግኞች የጽድቀት መጠን እየጨመረ መምጣቱን መሪ ሥራ አስፈጻሚው አመላክተዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ የነበረው ችግኝ ተከላ የጽድቀት መጠን 80 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ የ2015 ዓ.ም የጽድቀት መጠን ስንመለከት ግን 84 በመቶ ያህል ነው። በ2016 ዓ.ም ደግሞ ከእነዚህ ዓመታት የተሻለ የጽድቀት መጠን እንደሚመዘገብ ይጠበቃል።

ለዚህም ምክንያት ሲገልጹ አንደኛው ህብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ ያገኘበት ሁኔታ መኖሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ቀደም ሲል ከነበሩት ጊዜያት የጽድቀት መጠን የሚጨመሩ የተሻሻሉ ሥራዎች መሰራታቸው ነው፤ ከእነዚህም መካከል የተከላ ጉድጓዶችን ቀድሞ ማዘጋጀት አንዱ ነው።

በሌላ በኩልም ዘንድሮም በችግኝ ተከላው ላይ ለውጦች ተደርገዋል። ከእነዚህ አንደኛው የተፋሰስ ልማቱ በበጋ በሚሰራበት ወቅት የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች አብረው የተዘጋጁበት ሁኔታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሥነ ምህዳርን መሰረት ያደረገ ተከላ እንዲከናወን ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ምክንያቱም ሥነ ምህዳሩን የጠበቀ ተከላ ሲደርግ በዚያው ልክ የጽድቀት መጠኑም ይጨምራል። እነዚህና መሰል ሥራዎች ቀደም ተብሎ በስፋት ተሰርተዋል፤ በዚህም የ2016 ዓ.ም የጽደቀት መጠን የተሻለ ተብሎ ይጠበቃል።

የደን ተመራማሪው ፕሮፌሰር ለገሰ ነጋሽ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአረንጓዴ ዐሻራ ችግኞች በመትከል ረገድ እያደረጉ ያሉትን ጥረት እንደሚያደንቁ ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ እንደ ፖለቲከኛ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ችግኞች የመትከል ጥረት አሁን በሚታየው ልክ ማንም አድርጎት አያውቅም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን እያደረጉት ነው። ኢትዮጵያ የምትፈልገው ይሄንን ነው። የተፈጥሮ ጉዳይ የሰው አእምሮ ላይ ይንጸባረቃልና ችግኝ መከተል ከምንመገበው ምግብ እና ከምንጠጣው ውሃ ጋር ይያያዛል። ይህንን ሁሉ የምናሟላበት ነው። በመሆኑም ችግኝ ተከላ በትልቁ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ችግኝ ተከላ የምግብ፣ የአፈርና እና የውሃ ዋስትናንም የምናረጋጥበት ከመሆኑ በዘለለ የሁሉም ነገሮች በሚባል ደረጃ መሠረት መሆኑ እሙን ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ይህንን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ችግኝ ተከላ ደግሞ እንዲሁ በቀላሉ መታየት እንደሌለበት አስገንዝበዋል፤ የዘርፉን ምሁራን ባሳተፈ መልኩ ሙያዊ አስተያየቶችን በመሰብሰብ ጭምር ሊተገበር ይገባል ሲሉ መክረዋል፡

እንደ ማውጫ

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ የህልውና ጉዳይ አድርጋ እአአ 2026 ድረስ 50 ቢሊዮን ያህል ችግኞች ለመትከል እቅድ እየተንቀሳቀሰች ነው። ባለፉት ዓመታት 32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኖች ተተክለዋል። በዚህ ዓመት 7ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ሲተገበር ቆይቷል፤ እስከ አሁንም አብዛኛው የችግኝ ተከላ ተጠናቋል። ዘንድሮ እስከ አሁን የተተከሉ ችግኞች ብዛት 40 ቢሊየን እንደሚሆን ይጠበቃል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዱ ተከላው እየተከናወነ ነው። ይህ እንዲሳካ ደግሞ በሀገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለው ሕዝብ ሁሉም በሚባል ደረጃ ወጥቶ ሊሳተፍበትና ዐሻራውን በማኖር ሀገርን በመገንባት የነገን ትውልድ ሊያስቀጥል ይገባል እንላለን።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You