አረንጓዴ ዐሻራ – ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር …

ምድራችን በተፈጥሮ ከተቸሯት ድንቅ በረከቶች ጋር በክብር ትኖር ዘንድ ልዩ ትኩረትን ትሻለች።የሰው ልጆችን ጨምሮ ፍጥረታት በሙሉ ህይወታቸው በድንቅ ጸጋዋ ላይ ተመስርቷል። ይህች ምድር ለዘመናት ያላትን ተፈጥሯዊ ሀብት እስትንፋስ ላላቸው ሁሉ ያለስስት ስትለግስ፣ ስትቸር ኖራለች።

ጥቅጥቅ ደኖች፣ ጥልቅ ባህሮች ፣ ግዙፍ ተራሮች፣ አረንጓዴ መስኮችና እልፍ ይሏቸው ብዝሀ ህይወቶች የምድራችን በረከቶች ሆነው ዘመናትን ተሻግረዋል። እነዚህ ተዝቀው፣ ተቆጥረው አያልቁ የሚመስሉ የተፈጥሮ ጸጋዎች ግን ዛሬ ላይ እንደጥንቱ ላይሆኑ መልካቸው ተቀይሯል፣ በረከታቸው ተገፏል።

የሰው ልጅ ፍላጎትን ጨምሮ፣ ዕድገት ስልጣኔው ማቆጥቆጥ ሲይዝ ቀዳሚ የለውጥ ማራመጃው የሆኑት እነዚህ በተፈጥሮ የተገኙ ጸጋዎች ናቸው።እስከዛሬ በነበሩ እውነታዎች ለፍላጎትና ጥቅም ሲባል ደኖች ተጨፍጭፈዋል፤ ተራሮች ተንደዋል፣ ጥልቅ ባህራት ያለምንም ገደብ ከጥቅም ውለዋል።

ይህ ለዘመናት ተፈጥሮን ያራቆተ ድርጊትም ውሎ አድሮ የሰው ልጅን መልሶ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።ዛሬ ላይ ዓለማችን በከፍተኛ የሙቀት መጠን፣ በከባድ የበረዶ ግግር መቅለጥ፣ በሚያሰጋ የመሬት መናድና መንሸራተት፣ በውሃ ሙላት፣ በሰደድ እሳትና መሰል ችግሮች ስትፈተን ትውላለች።.

አሁን የዓለማችን ቀዳሚ መልኮች በፍጥነት መቀያየር ይዘዋል። ትናንት ነፋሻማ የነበሩ ቦታዎች ዛሬ በከባድ ሀሩር እየተመቱ ነው ።የዝናብ በረከት ሲያረሰርሳቸው የኖሩ ስፍራዎችም በዘመናችን በረሃማነትን ተሹመዋል። ጥቅጥቅ ደኖች ተራቁተው፣ ለምለም መስኮች አረንጓዴ መጎናጸፊያቸው ተገፏል።

ይህ አይደበቄ ሀቅ የተከሰተው የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ባለመስማማት በሚያደርሰው የማያቋርጥ በደል ነው።ሰው ይሉት ፍጡር ትናንት በእጁ ያለውን ወርቅ በወጉ አለማክበሩ ዛሬን በመራቆት ዓለም ውስጥ እንዲኖር አስገድዶታል። በገዛ እጁ ባደረሳቸው ጉዳቶችም የተፈጥሮ ጸጋዎች እንዲወድሙ፣ አራዊት እንስሳ እንዲሰደዱና ምድር ነባር በረከቷን እንድትነጠቅ አድርጓል።

ይህ እውነታ በሌሎች ዓለማት ብቻ ተወስኖ የሚተው አይደለም። በሀገራችን ጭምር መሰል መገለጫ ከሆነብን ዘመናት ተቆጥረዋል። በእኛይቱ ድንቅ ሀገር ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበራት ተፈጥሮአዊ ማንነት ተጠብቆ አብሯት አልዘለቀም። ኢትዮጵያ ለዘመናት ስለ ነፋሻማ አየሯ፣ ጋራ ተራራዋ፣ ወንዝ ሸንተረሯ፣ ሲዜም፣ ሲዘፈንላት ቆይቷል።

ቀን ከሌት ክረምት ከበጋ ያለማቋረጥ የሚፈሱ ወንዞቿ ስለ ማንነቷ ድንቅ ተምሳሌት ሆነው ዘመናትን ተሻግረዋል። ተስማሚ አየሯን ሽተው ባህር አቋርጠው የሚመጡ በርካቶችም ተለይቶ የተቸራትን ተፈጥሮ መቼም፣ ከማንም የሚያወዳድሩት አልነበረም። ይህች ሀገር ግን ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታዋን በበርካታ ምክንያቶች ስታጣ፣ ስትነጠቅ ቆይታለች።

ዛፍን ያህል ታላቅ ጸጋና በረከት ገንድሶ ችግኝ መትከል ባልተለመደበት ባህል እስካዛሬ በርካታ ጥቅጥቅ ደኖች የስል መጥረቢያ ሰለባዎች ሆነዋል። የደኖች መጨፍጨፍን ተከትሎ የአፈር መሸርሸር በሚያደርሰው ጉዳትም ምድር ስትራቆት ድርቅና በረሃማነት ሲያሳድዱን ቆይተዋል።

እንዲያም ሆኖ ከእንቅልፋችን የነቃነው ዘግይተን ነበር። የአንድ ጀንበር በረከት ደርሶ ምድራችን በአረንጓዴ አሻራ መታተም እስክትጀምር የነበር ታሪካችንን ስናወሳ በሀዘን እንጉርጉሮ ስንተርከው ኖረናል።

እነሆ ! ዛሬ ትናንትና ስላጣነው የሀገራችን ድንቅ ተፈጥሮ እያሰብን የምንተክዝበት አይደለም። አሁን የቆሸሹ እጆቻችን የአፈር ጓል በያዙ ችግኞች ተሞልተዋል። የተራቆተው መሬታችን እንደ አምና ካቻምናው በእልፍ በረከቶች ሊሸፈን፣ በድንቅ ልምላሜ ሊሞላ ነው።

በእርግጥም ፊሽካው፣ መለኮቱ ተነፍቶ የተግባር ነጋሪቱ ተጎሽሟል። መሬት አረንጓዴ ሸማዋን ልትላበስ፣ የጥቁር አፈር ሽታ እያወደ ነው። ይህ አይነቱ ዕውነት ደግሞ ለእኛ ለኢትዮጵያውያኖቹ ብርቃችን አልሆነም። ሁሌም የአሮጌው ዓመት ሽኝት፣ የአዲሱ ዓመት ብስራት በአረንጓዴው አሻራ እንደታተመ ቀጥሏል።

በየዓመቱ የሚተባበሩ ክንዶች፣ የሚፈላለጉ ዓይኖች ትኩረት ዓላማቸው በአንድ የታሰረ ነው። ክረምት ሊያባራ ሰው ልምላሜን በሚሻው መሬት ላይ የተስፋን ህይወት ያኖራሉ። ልክ እንደ አምና፣ ካቻምናው ሁሉ በቆሙበት ስፍራ ሲገናኙ ለከርሞው ቀጠሮ ቀን አይስቱም። የሚያዩት ፍሬ ዳግም ስለነገው ዓለም አደራ ፣ ቃላቸው ይሆናል።

ነሀሴ 17 ቀን 2016 ዓም። እነሆ! የዚህች ዕለት ጀንበር ከሌሎች ቀናት ትለያለች። ሺዎች ስለእሷ መንጋት ጓጉተው፣ ማልደው ነቅተውባታል።ይህች ቀን ከምንጊዜውም ይበልጥ የኢትዮጵያን ምድር በአረንጓዴ ሸማ የምታለብስ፣ ምድርን በበረከት የምትሸፍን ናት። የተባበሩ ክንዶች በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ሊተክሉ ጉድጓዶችን ምሰዋል።

ችግኞቹ እንደሌሎቹ ቀናት ስያሜ ብቻ አይደሉም። በውስጣቸው ህይወትን ይዘዋል። ቅጠል ስሮቻቸው ለሰው ልጆች መኖር አጋርና እስትንፋስ ናቸው። በእነሱ መብቀል ትናንት የደረቁ፣ ምንጮች ወንዝ ሆነው ይጎርፋሉ።ቀድሞ የጠፉ ዛፎች ደን ሆነው አዕዋፍ አራዊትን ይጣራሉ። እናት መሬት ለብዝሀ ህይወቷ ፣ ለመልክዓ ምድሯ በረከት ልምላሜዋ ይሰፋል።

በየዓመቱ ቁጥሩ እየጨመረ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ እንደ ሁልጊዜው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ የላቀ ነው። እያንዳንዱ በህይወቱ፣ በማንነቱ፣በትውልዱ ላይ የሚያሳርፈው አሻራም ቀለሙ እንዳይለቅ ሆኖ ማንነቱ ተመዝግቧል። ይህ አኩሪ ተግባር የትውልዳችን ማህተም፣ የታሪካችን ድንቅ ዓርማ ነው። በማንነታችን ሰርጾ ዘመናትን በለውጥ ድልድይ ያሻገራል። በአንድ ጀንበር ጥረት የዘመናት ስንፍናን ይሽራል።

በአንዳንድ ሀገራት የዛፍ መትከል ተሞክሮ በቁም ነገር የታሰረ ነው። አባቶች ስለነገ መኖር ዛሬን ቆመው ያስባሉ፣ ለመጪው ትውልድ ህልውናም በሩቁ አሻግረው ያቅዳሉ። በጽኑ ድካምና ልፋት የሚተክሏቸው ዛፎች በእነሱ እድሜ የሚደርሱ አሁናዊ አይደሉም። እንዲያም ሆኖ ፈጽሞ ከተግባራቸው አይታቀቡም። ዛፉ ነገ ደርሶ እንደማይጠቅማቸው እያወቁ ችግኝ መትከል፣ማብቀላቸውን ይቀጥላሉ።

እነሱ ዛሬን እየኖሩ ነገን ማለማቸው ያለምክንያት አይደለም። በላብ በወዛቸው፣ በጉልበታቸው ድካም መጪውን ትውልድ ይታደጋሉ። የእነሱ ተተኪ ወደፊት በሚቆምበት ሌላ ዘመንም ይህ ታሪክ ጠንካራ ሰንሰለት ሆኖ በርካታ ትውልድን ይሻገራል።

እነሆ! በኢትዮጵያ ሀገራችን በአንድ ጀንበር የሚከወነው የ600 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ ትውልድን የመታደግ፣ ሀገርን ከችግር የማውጣት ዓላማን ሰንቋል። በሚሊዮኖች በረከት እልፍ ጸጋን አላብሶ ፣ ታሪክን በአረንጓዴ አሻራ የማድመቅ ታላቅ እሴትን ይዟልና።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You