የተዛባ አየር፣ የተራቆተ ምድር ለትውልድ ላለማትረፍ በታላቁ ቀን በጋራ እንሳተፍ

ፕሮፌሰር ጃሬድ ዳይመንድ፣ ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸውና የተፈጥሮ ሀብትን የሚመለከቱ መጻሕፍትን በመፃፍ ይታወቃሉ። በተለይ ‹‹ Collapse–: How Societies Choose to Fail or Succeed›› በሚል ያሳተሙት መጽሐፋቸው በበርካቶች አድናቆት የተቸረው ነው።

አሜሪካዊ ፕሮፌሰሩ እኤአ በ2005 ባሳተሙት በዚህ መጽሐፍ ‹‹የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን በተገቢው መንገድ የማይዙና ጥቅም ላይ የማያውሉ ሕዝቦች ላልታሰበ ሥርዓተ ምህዳራዊ አጥፍቶ የመጥፋት አደጋ ይጋለጣሉ›› በማለት ተፈጥሮን መንከባከብና በአግባቡ መጠቀም የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ። የሰው ልጆችም ከተፈጥሮ ጋር መታረቅና ጥበቃ ማድረግ ግድ እንደሚላቸው ያትታሉ።

እንደ ፕሮፌሰሩ ሁሉ የተለያዩ ምሁራንና የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ሳይንሳዊ ትንታኔን ተመርኩዘው የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር መታረቅ እንዳለበት በተደጋጋሚ ቢወተውቱም ሰሚ ጆሮ ያገኙ ግን አይመስሉም። የሰው ልጅ ተፈጥሮን እየተንከባከበ ለማቆየት ዳተኝነቱን ዛሬም እንደቀጠለ ነው።

የሰው ልጆች ከተፈጥሮ ጋር በገጠሙት ጦርነት አለማችን ለመኖሪያነት የነበራትን ምቹነት እያጣች ትገኛለች። ሰዎች በተለያየ መንገድ ተፈጥሮን እያራቆቱ መሄዳቸው እየዋለ ሲያድር በየፈርጁ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል። ቀውሱም ድሃም ሆኑ ሀብታም የሚባሉ ሀገራትን ሳይለይ የጥፋት በትሩን ሁሉም ላይ እያሳረፈ ይገኛል።

በሰው ልጅ ኑሮን ለማዘመን በካይ የአኗኗር ዘይቤን በመከተሉ ሳቢያ የምድራችን የሙቀት መጠን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው። የተለያዩ ከተሞች በከፍተኛ ሙቀት እየተቃጠሉ ናቸው። አንዳንድ ሥፍራዎች ወደ በረሃነት እየተቀየሩ፣ በየቦታው ድርቅ እየታየ ነው። ሚሊዮኖች በድርቅ ምክንያት በረሃብና ቸነፈር እየተገረፉ ናቸው።

ግግር በረዶዎች ሲቀልጡ፣ ጥቅጥቅ ደኖች በእሳት ነበልባል ሲበሉ፣ ወንዞች ደርቀው ወደ ሜዳነት ሲቀየሩ መመልከት የተለመደ ሆኗል። በሌላ በኩል በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አንዳንድ ሀገራት ከፍተኛ የዝናብ መጠን ማስተናገድ ግድ ብሏቸዋል። በከባዱ ዝናብና ቅፅበታዊ ጎርፍ ምክንያት ዜጎቻቸውንና ኢኮኖሚያቸውን እየተነጠቁም ናቸው።

በዓለም ላይ እየበረታና እየተስፋፋ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ የሰው ልጆችን ጨምሮ በምድር ላይ ሕይወት ያላቸውን ፍጥረታት ሁሉ የህልውና አደጋ ሆኖ ቀጥሏል። በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች የችግሮቹ ገፈት ቀማሽ በመሆን የጉዳታቸው መጠን ከዓመት ዓመት እየበረታ ይገኛል።

እርግጥ በአየር ንብረት ለውጡ እሳት የበላቸውም ሆነ ቀጣዩ ቀውስ የሚያሰጋቸው የተለያዩ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራትና አጀንዳው ብሎም የፖሊሲያቸው አካል አድርገው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። ሁሉም በየፊናቸው የዓለም ስጋት ለሆነው ቀውስ መፍትሔ የሚሉትን እየከወኑም ናቸው። ጥረታቸው ከውጤት መነፅር ሲታይ ግን ብዙ መድከም እንደሚጠበቅባቸው በግልፅ የሚያስታውቅ ነው።

‹‹የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከተፈለገ ከሁሉም በላይ ያለ ደን ልማት አይታሰብም›› የሚሉት ፕሮፌሰር ጃሬድ ዳይመንድን የመሳሰሉና ሌሎችም የዘርፉ ምሁራንም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመቀነስ ረገድ የደን ሽፋኑን በከፍተኛ መጠን ማሳደግ ግድ እንደሚል ደጋግመው በመናገር ላይ ተጠምደዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ላለው ተፅዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ናት። ጊዜ እየቆጠረ የሚከሰተው ድርቅ የሚያሳድረውን ጫናም ሆነ የአየር ንብረት ለውጡን የሚቋቋም አቅም የላትም። የሀገሬው ሕዝብም ተፈጥሮን መንከባከብን ደን በመትከል የሚታማ አይደለም። ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዛፍ ችግኞችን የመትከል ልማድ እንደነበረው የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ።

ይሁንና እያደር የዛፎች ጭፍጨፋ እየጎለበተ መምጣትና በሚጨፈጨፈው ምጣኔ ልክ የመተካት ጥረቱ ዝቅተኛ መሆን የሀገሪቱ የደን ሽፋን በየጊዜው እየተመናመነ፣ መራቆት በሚባል ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረጉም የማይካድ ሃቅ ነው።

ይህንን ምስል ለመለወጥ ዓለም አቀፍ ችግር በመከላከልና በመቋቋም ረገድ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርሃ- ግብር ነድፋ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። ሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገቷን በዘላቂነት ለማስቀጠል የምታደርገው ግብ ግብ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል ጋር የተዛመደ ነው። የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂው የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ዝቅተኛ የካርበን ልቀት መጠን እንዲኖር የሚያደርግ አብዮት ነው።

ደኖች ለአፈርና ውኃ ጥበቃ፣ የካርበን ልቀትን ለመምጠጥ፣ ለብዝሀ ሕይወት ጥበቃ፣ ለመሬት ምርታማነትና ለሰው ልጅ ጤንነት፣ ለማኅበራዊ ኢኮኖሚው ከፍተኛ አበርክቶ አላቸው። ኢትዮጵያም የኢኮኖሚ ዕድገቷን በዘላቂነት ለማስቀጠል የምታደርገው ግብ ግብ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል ጋር የተዛመደ እንደመሆኑም በተለይ ለደን ልማት የሰጠችው ትኩረት ትልቅ ራዕይን ያነገበ ነው።

ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት ከ30 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የራሷን አስተዋጽኦ ከማበርከቷም በተጨማሪ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን ዓለምን ከካርቦን ልቀት ለመታደግ ለተያዘው ዓለም አቀፍ ጥረትም ጉልህ ፋይዳ እያበረከተች ትገኛለች። የደን ማልማት ሥራዎችም በአየር ንብረት ሥርዓቱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ከማምጣት ባሻገር የኢትዮጵያ የደን ሽፋን እንዲጨምርና ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ቶን ካርበን ማከማቸት ስለመቻሉም የሚታወቅ ነው።

ዘንድሮም ይህን ጥረት ለማስቀጠል ከክረምቱ ወራት ጅማሮ አንስቶ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ተካሂደዋል። በተለያዩ አካባቢዎችም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል። ይህ ተሳትፎ በአንድ ላይ በመሰብሰብ ሌላ ታሪክ ለመፃፍም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም 600 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር የመትከል ጥሪ አቅርበዋል። ይህን ተከትሎም እንደ ወትሮ ሁሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለማለት በሚያስደፍር መልኩም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የወል እውነት እንደሆነ ተረድቶ በመርሃ ግብሩ ላይ የራሱን ዐሻራ እንደሚያሳርፍ ጥርጥር የለውም።

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት መላው ሕዝብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እናቶችና አባቶች እንዲሁም ሕፃናት በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ ታሪክ ሰሪ መሆናቸውን በግልፅ በአደባባይ ማስመስከር ችለዋል።

ከዚህ አንፃር ጥቂቶች በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማትና የገጽታ ግንባታ ሥራ ላይ መሳተፍ ሀገር ሳይሆን መንግሥትን ከመደገፍ ጋር ሲያቆራኙት አስተውለናል። ችግኝ መትከልን ከሀገር ጥቅም ወደ መንግሥት ጥቅም አውርዶ የመንግሥትን እድሜ እንደማስቀጠል የሚመለከቱና ፖለቲካዊ ትርጓሜ የሚሰጡትንም ታዝበናል።

ይሁንና ይህ እሳቤ ፍፁም ስህተት ነው። ሊታወቅ የሚገባው ጥሬ አቅም፣ ችግኝ ከመትከል ጋር ተያይዞ የፖለቲካ ልዩነት ፣ የወቅታዊ አጀንዳዎች ፣ የእምነት ጉዳይ ፣ የጾታ ጉዳይ ፣ የሀብት ጉዳይ ሁሉ ትርጉም እንደሌለው ነው። ችግኝ የምንተክለው ለህልውናችን ቀጣይነት ነው። ከዛሬ ባለፈ ለነገ ትውልድ ምቹ ሀገር ብሎም ዓለምን ለማስረከብ ነው።

ይህን የወል ሃቅ በመገንዘብ መላው የሀገሪቱ ሕዝብ በዘንድሮም የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመሳተፍ ታሪክ ሰሪ ትውልድ መሆኑን ዳግም በተግባር ለዓለም ማስመስከር ይኖርበታል። የተዛባ አየር፣ የተራቆተ ምድር ለትውልድ ላለማትረፍም በታላቁ ቀን በጋራ ሊሳተፍና ትላንት የተሰራው ድል ዛሬም ሊደግም ይገባል።

ከዚህ ባሻገር የችግኝ ተከላ የአንድ ወቅት ተግባር ብቻ ሳይሆን ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል። ተከላውን ማከናወን ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ለቁም ነገር ማብቃት ከሁላችንም የሚጠበቅ ኃላፊነት ሊሆን የግድ ይላል። ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን ሰላምና አንድነታችን ማስጠበቅንም መቼውንም መዘንጋት አይኖርብንም።

ኢትዮጵያ ሕዝቦቿን በማስተባበር የዓለምን ችግር ለመፍታት የራሷን ድርሻ እየተወጣች መቀጠለም አድናቆት ሊቸራት ብሎም ሊያስመሰግናት ይገባል። ከሁሉም በላይ የሀገሪቱ ትጋት ይበልጥ ፍሬ እንዲያፈራ ከእውቅናም ባለፈ አስፈላጊ ገንዘብን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች ሊደረግላት ይገባል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር የሚፈለገውን ግብ እንዲመታ ከተፈለገም በተለይ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ምዕራባውያን ሀገራት እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ሀገራት ጋር በቅርበት መሥራት የግድ ይላቸዋል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You