የሸማቾች ማህበራት ዝግጁነታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል !

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ባደረገችው የመጀመሪያው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የአሰር አመት መሪ እቅድ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ለውጦችን ማሳየት ችላለች። በግብርናው ዘርፍ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በቡና ልማትና ግብይት፤፣ በቱሪዝም ዘርፍ የቱሪስት መሠረተ ልማቶችን በመገንባት፤ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተኪ ምርት በማምረት፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በዲጂታል ኢኮኖሚ ትግበራ የታዩ ለውጦች ከተመዘገቡ ለውጦች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

በቀጣይም በእነዚህና በሌሎች ዘርፎች ለውጦችን ለማስመዝገብ መሠረት የሚጥሉ በርካታ አሠራሮች ተቀይሰው የእቅድ ትግበራው ገብተዋል። በቅርቡ ጸድቆ ወደ ትግበራ በገባው የሀገር በቀል አኮኖሚ ማሻሻያው ሁለተኛ ምእራፍ ትግበራም የበለጠ ለውጥ እንደሚመዘገብ ይጠበቃል።

ሀገሪቱ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ ያስገባችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምና እሱን ተከትሎ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ለእዚህ ሥራ ወሳኝ ፋይዳ እንዳላቸው ታምኖባቸዋል። ማሻሻያው መልካም እድሎችን ይዞ እንደመምጣቱም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሁለተኛ ምእራፍም ትላልቅ ለውጦች እንደሚመዘገቡ ይጠበቃል።

የማሻሻያውን መውጣት ተከትሎ ለኢትዮጵያ ለዓመታት ብድርና ርዳታ ከመስጠት ታቅበው የቆዩት የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ድርጅት ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር እስከ መፍቀድ ደርሰዋል። ይህ ብድር ልማቷን ለማሳለጥ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፈተና ሆኖባት ለቆየችው ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም ሊሆን እንደሚችል ማንም ይስተዋል ተብሎ አይታሰብም። የእነዚህን ተቋማት ርምጃ ሌሎች አበዳሪ ተቋማትና ለጋሽ ሀገሮች የሀገሪቱን ልማት ማሳለጥ የሚያስችል ድጋፍ ወደ ማድረግ እንደሚገቡ ሊያደርግም ይችላል ብሎ መገመት ስህተት አይሆንም።

ይህ ሁሉ በሁለተኛው ምእራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዋ ሰፋፊ የልማት እቅዶችን ለያዘችው ሀገር ትልቅ አቅም ነው። በዚህ ወሳኝ ወቅት ትላልቅ ግቦችን አስቀምጣ ለስኬታቸው እየሰራች ላለችው ሀገር ዓለም አቀፍ የፋይንናስ ተቋማት የውጭ ምንዛሬ ይዘው መምጣታቸው በቀላሉ ሊታይ የሚገባው አይደለም፤ ብዙ ተደክሞ ድርድር ሲካሄድ ቆይቶ ነው የተገኘው።

ማሻሻያው መልካም እድሎችን ብቻ ይዞ አለመምጣቱን መንግሥት አያይዞ አስታውቋል። ስጋቶች እንዳሉም አመልክቷል። እነዚህን ስጋቶች ስጋት በማይሆኑበት ደረጃ ለማስቀረትም ሆነ ጉዳት እንዳያደርሱ ለማድረግ ደግሞ የተለያዩ ተግባሮች እንደሚከናወኑ አያይዞ አመልክቷል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም እንዲሁ ርምጃውን የዘገየ እስከማለት ደርሰው፣ እነሱም ስጋት ያሉትንና መውጫውንም እየጠቆሙ ናቸው። መውጫ ባሉት ላይ ከመንግሥት ጋር ብዙ ልዩነት የለም። የምርት አቅርቦት እጥረት እንደሚፈጠር አስታውቀው በአቅርቦት ላይ በስፋት መሠራት እንዳለበት.፣ ሕገወጥ ነጋዴዎችን መቆጣጠር እንደሚገባ አስታውቀዋል። መንግሥትም ይህንኑ ብሏል።

ባለሙያዎቹ በውጭ ምንዛሬ ላይም ባንክ ውስጥ ያሉ ሕገወጦች ጭምር ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ አመልከተዋል። መንግሥትም በሕገወጦች ላይ ጥብቅ ርምጃ እንደሚወሰድ በተደጋጋሚ እያስገነዘበ ነው።

እንደተባለውም አንዳንድ ወገኖች ይህን መልካም እድል እንደ ጥፋት የቆጠሩበት ሁኔታ ታይቷል፤ የተገኘውን ድጋፍ እና በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ጭምር የሚኮንኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህ አካላት እነሱን ለሀገር አሳቢ መንግሥት ሀገር አፍራሽ አድርገው ቀርበዋል። ሃሳባቸውን እንደ ሃሳብ ማንጸባረቃቸው ችግር ባይኖረውም፤ ማሻሻያውን ለመገዳደር በሚል ሕገወጥ ተግባር መፈጸም ውስጥ መግባት ግን የለባቸውም።

ይሁንና የእነዚህ አካላት ጽንፍ የረገጠ ተቃውሞ በተቃውሞ ብቻ አላቆመም። ስግብግብ ነጋዴዎች ምርቶችን በመደበቅ፣ ዋጋ በማናር ተቃውሞውን ተቀላቅለውታል። ማሻሻያውን የሚገዳደር ድርጊት መፈጸም ማለት ተቃውሞ ነው።

ማሻሻያው በወጣ ማግስት ጥቂት የማይባሉ መደብሮች እንደ ዘይት ያሉትን ምርቶች ሲደብቁ ፣ ከፍተኛ ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ ታይተዋል። በማሻሻያው ከተጠቀሰው ስጋት አንዱም ይሄው ነው። አንዳንድ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ምርት መደበቅ፣ ዋጋ መጨመር፣ ጥራት ማጉደል ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ አስቀድሞም ተለይቷል፤ ሁሌም በአንድ አይነት ስሌት የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ሕገወጦች መሰል ርምጃዎች ሲወሰዱ ሲያደርጉ የኖሩትን ሕገወጥ ተግባር አሁንም ወደ መፈጸም ገብተዋል።

ለእዚህም መንግሥት እነዚህ ሃላፊነት የማይሰማቸው አካላት ከሕገወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠንካራ ርምጃ እንደሚወሰድ ባስታወቀው መሠረት ድርጊቱን ሲፈጽሙ በተገኙ መደብሮች ላይ የማሸግ ርምጃ መውሰድ ጀምሯል። ይህ ርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ስለመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ከትናንት በስቲያ በተካሄደ መድረክ ላይ አስገንዝበዋል።

ርምጃው ከእስከ አሁንም በላይ የተጠናከረ መሆን ይኖርበታል። ተመሳሳይ የፖሊሲና የመሳሰሉት ለውጦች ሲደረጉ ሕገወጥ ተግባር በመፈጸም የሚታወቁ አካላት በተደጋጋሚ ወደዚህ ተግባር የሚገቡት የሚወሰድባቸው ርምጃ የሚያም አይነት ባለመሆኑ ነው። አሁንም ይሄው ታውቆ የሚያም ርምጃ ለመውሰድ ብዙ ማሰብ አያስፈልግም።

ከእነዚህና መሰል የአቅርቦት ችግሮች ዜጎችን ለመታደግ እንደሚሠራ መንግሥት ማስታወቁ ይታወቃል። በሴፍቲኔት መርሀ ግብርና በመሳሰሉት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ገልጿል፤ የመሠረታዊ ምርቶች አቅርቦትን እንደሚደጉም፣ ዝግተኛ ደሞዝ ተከፋዮች የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

መንግሥት በመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ ሊከሰት የሚችለውን የአቅርቦት ክፍተት ለመሙላት እስከ አሁንም ሲያደርግ እንደቆየው እንደ ስኳር፣ ዘይት፣ የዳቦ ዱቄት የመሳሰሉት ምርቶች ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ የሚያደርገው በሸማቾች ማህበራት በኩል መሆኑ ይታወቃል።

እነዚህ ማህበራት ይህን መሰሉን ሃላፊነት በመወጣት ይታወቃሉ። በእዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወቅትም ይህን ሃላፊነቸውን ለመወጣት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ይገባዋቸዋል። ለእዚህም ራሳቸውን በፋይናንስ ማዘጋጀት፣ አሠራራቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል።

መንግሥትም ምርቶቹን በድጎማ ገዝቶ ከማቅረብ በተጨማሪ ምርቶችን እንደ አርሶ አደሮች ካሉት ላይ ለመግዛት የሚያስችላቸውን የፋይናንስ አቅርቦትን ጭምር ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህ ሲሆን ምርቶቹን በሚፈለገው ልክና በተሳለጠ መልኩ ማቅረብም ይችላሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ ወቅት ወደ ብዙ መቶ ሚሊዮን ብር ለማህበራቱ /በተዘዋዋሪ ፈንድ / ያቀረበበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል። ይህን አይነቱ ድጋፍ ካለ ማህበራቱ እህልና የመሳሰሉትን የሀገር ውስጥ ምርቶች በብዛት ገዝተው ለማኅበረሰቡ ማድረስ ይችላሉ።

የሸማቾች ማህበራት ከዚህ በኋዋላ መንግሥት በድጎማ የሚያቀርባቸው የፍጆታ ምርቶችንና የግብርና ምርቶችን ብቻ ለማቅረቡ ሥራ አይደለም መዘጋጀት ያለባቸው። ሌላ ዝግጁነታቸውን ማረጋገጥ ያለባቸው ጉዳይም ተከስቷል። የንግዱን ሥራ ነጻ ለማድረግ እየተሠራ ነው። መንግሥት በንግዱ ዘርፍ የሚታዩ የአቅርቦት፣ የዋጋ ፣ የጥራትና የመሳሰሉትን ችግሮች ለመፍታት ያግዛል ያለውን ርምጃ ለመውሰድ እየሠራ ነው።

የሀገሪቱን የንግድ ማህበረሰብ ለመጠበቅ በሚል እስከ አሁን የውጭ የንግድ ማህበረሰብ በጅምላም ሆነ በችርቻሮው ዘርፍ እንዳይሰማራ ሲያደርግ ቆይቷል። አሁን ነገሮች ተቀይረዋል። እነዚህ የጅምላና የችርቻሮ ንግዱን እንዳይቀላቀሉ የተደረጉ የውጭ ባለሀብቶች በእዚህ የንግድ ሥራ እንዲሠማሩ አዋጅ ወጥቶ ለትግበራው እየተሠራ ነው።

በቅርቡ ወደ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምና እሱን መሠረት አድርጎ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ለእነዚህ አካላት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑ ታምኖበታል። በቅርቡም ወደ ሀገሪቱ ገብተው በእዚህ ሥራ ሊሰማሩ ይችላሉ።

እነዚህ ባለሀብቶች ለሸማቹ ህብረተሰብ ሌላ አማራጭ ሆነው እንደሚመጡ ይጠበቃል። የምርት አቅርቦት፣ ስርጭት፣ ጥራትና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ በሚል ታስቧል።

የእነሱ ወደ ሀገር ውስጥ መግባትና እየተሰፋፉ መምጣት የሀገር ውስጥ የንግዱ ዘርፍ ጠቅልሎ ይዞት የቆየውንና እንዳሻው ሲያደርገው የኖረውን የንግድ እንቅስቃሴ ተወዳዳሪ ይገባበታል።

ይህ ተወዳዳሪነት የሸማቾች ማህበራት ጫፍ አይደርስም ተብሎ መታሰብ የለበትም። አሁን ሁለተኛ አማራጭ ሆነው ያሉበት ሁኔታ ሊገፋና ሥራ ሊያጡ የሚችሉበት ሁኔታ ሊከሰት ስለሚችል ማህበራቱን የሚመሩ አካላት የሀገሮች ተሞክሮን በመቃኘት ማህበራቱ የህብረተሰቡ አማራጭ ገበያ ሆነው ሊቀጥሉ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መሥራት ይኖርባቸዋል።

በተለይ የግብርናና የኢንዱስትሪ የፍጆታ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለማቅረብ መዘጋጀት፣ ለእዚህም ከኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ከእርሶ አደሮች ማህበራት ጋር በቅርበት መሥራት አለባቸው።

ይህ ወቅት ህብረተሰቡን ከዋጋ መናር ፣ ክምርት አቅርቦት እጦትና ከምርት ጥራት ችግሮች ለመታደግ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ተነሳሽነትና ብቃት መሥራትን የግድ የሚል ነው። ማህበራቱም ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁነት ላይ ማተኮር ፣ ወደ ትግበራ ሲገባም አቅርቦቱ ላይ ምንም አይነት ችግር ሳይፈጠር ለህብረተሰቡ እንዲደርስ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ለእዚህም ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት የፋይናንስ አቅም ማሳደግ እንዲሁም የአሠራር ዝግጁነትን በማጠናከር መንግሥት በአቅርቦት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ ይኖርባቸዋል።

እስመለአለም

አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You