ዶቃን ከማሰሪያው

 

ዶቃ ከምን? ካሉ…ዶቃ ከማሰሪያው ነው። በኢትዮጵያ ሲኒማ ላይ ውበትን ደርቦ ከአንገት እንደ ጌጥ ፈርጥ የተንጠለጠለው “ዶቃ” ፊልም አሁን ደግሞ ከሌላ ደማቅ የማሰሪያ ክር ጋር ለመታየት በቅቷል። ጥንቱን ዶቃ የሀገሬው ልጃገረድ ሁሉ መድመቂያው ጌጥ ነበር። አሁን ደግሞ ዶቃ ፊልም የሀገርኛውን ውበት ይዞ ከአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ማሰሪያው ጋር ብቅ ብሏል።

ስለ አሁናዊው ዶቃ ስለታሰረበት የቴክኖሎጂ አንገት ከማንሳታችን በፊት የማሰሪያውን አመጣጥ ጥቂት ከመንገዱ ላይ እንመልከተው። መንገዱም ወደ ሰሞነ ኮቪድ ያመለክተናል። የሰው ልጆችን የገጽ ለገጽ ግንኙነት በመንፈግ እንኳንስ ከሌላው ሰውና ከገዛ አካላችንም አራርቆ እንዳሰነበተን አንዘነጋውም። በዚህም ሳቢያ ሰው ተርበው ከቆዩ ስፍራዎች አንደኛው ሲኒማ ቤት ነበር። “ችግር ብልሀትን ይወልዳል” እንደሚሉት ሁሉ በሀገራችን ባይሆንም በሌላ ዓለማት ውስጥ ሲኒማ ቤቱን የሚተኩና የቴክኖሎጂ ውላጅ የሆኑ መተግበሪያዎች በርከት ብለው ወጥተዋል። ለሲኒማ አፍቃሪዎችም ሲኒማው እቤታቸው ድረስ ሲግተለተል መጣ።

ይሁንና እንደኛ ሀገር ቴክኖሎጂው አንገቱን አውጥቶ ብቅ ባለማለቱ ሲኒማ ቤቶች እንደተዘጉ፤ ሲኒማውም እንደተዘነጋ ነበር። ሀገራችንን ጨምሮ እንደ ዓለም አቀፍ እይታ ከኮቪድ በኋላም የሲኒማ ቤትና የሲኒማው ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ ቀጠለ። እንደ እነርሱ የቴክኖሎጂውን አማራጭ ስለያዙና አዲሱ ልምምድ ስለተመቻቸው ነበር። እንደ እኛ ግን ከሲኒማ ቤት ደጃፍ የሚያስቀር የያዝነው ምንም አልነበረም። ነገርየው “እንኳን ዘንቦብሽ ድሮም ጤዛ ነሽ” የሚያስብል ነበር።

ሲኒማ ቤቶች ማዶ ለማዶ ቆመው እንደተፋጠጡና ሲኒማው እንደተፋዘዘ መጥቶ አሁን ካለንበት ደርሷል። ሲኒማ ቤቱንም ሆነ የሀገራችንን የፊልም ኢንዱስትሪ ደግፎ ለማቆም የሚችል፣ በውጪዎቹ ዘንድ እንዳለው ዓይነት የቴክኖሎጂ ማኅደረ ሲኒማ መኖር እንዳለበት የቆረጡ ተነስተውም በቅርቡ አብስረውናል። እንግዲህ በሰሞኑ የ“ዶቃ” ፊልምን አንጠልጥሎ የታየው የቴክኖሎጂ አንገትም ይኼው ነው።

ለሀገራችን የቴክኖሎጂ ማኅደረ ሲኒማ ግንባር ቀደም አሳላጭ የሆነው ኤግል ላይን የተሰኘው የፋይናንስ ተቋም ነው። ተቋሙም የተነሳበትን ቴክኖሎጂ መር ሲኒማውን የመፍጠር ግቡን ለማሳካት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመቀናጀት በቴሌ ቲቪ ተገናኝተዋል። በዚህ ቴክኖሎጂም ከሰኔ 27/2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲሠሩ ቆይተዋል። እስከ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ሁለት የሲኒማ ፊልሞችን በቴክኖሎጂው አንገት ላይ ለማሰር ችለዋል። እነዚህም የመጀመሪያው ፈር ቀዳጅ “6 ሰዓት ከሌሊቱ” ሲሆን፤ ሌላኛውና ሁለተኛው ደግሞ “ትዝታ” የተሰኘው ፊልም ነው።

ለእይታ ከቀረቡ በኋላ በሁለቱም ፊልሞች የተንጸባረቀው ነገር አስደሳችና ይበል የሚያሰኝ ነበር። ለሦስተኛ ጊዜ አጋርነቱን በይበልጥ ከፍ አድርጎ በተሻለ ሁኔታ ለመቀጠል ማሰባቸውም ለዚሁ ነው። ለሦስተኛ ጊዜም ከሰሞኑ ከዚሁ አንገት ላይ ዶቃ አስረዋል። የ“ዶቃ” እዚህ መታየት ላለፈው እንደ ስኬት፣ ለሚመጣው ደግሞ እንደ ብስራት የሚቆጠር ነበር። ለዚህም ይመስላል በሚያካሄዱት የጋራ ስምምነት ወቅት ሚዲያው ሦስተኛ አካል ሆኖ በስፍራው እንዲገኝላቸው መፈለጋቸው። ፊሽካው የተነፋበት ያ ዕለትም ያሳለፍነው ሳምንት ነሐሴ 11 ቀን ነበር።

የሚዲያ ጋዜጠኞች በተኮለኮሉበት በዚያ የነሐሴ 11 ቀን የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይም ከሁለቱም ወገን ተገኝተው ግብራቸውን ፈጽመዋል። ከወደ መተግበሪያው የኤግል ላይን መስራችና ሥራ አስኪያጅ የሆነው በርሱፈቃድ ጌታቸው፣ የዶቃ ፊልምን በመወከል ደግሞ ተዋናይትና ፕሮዲዩሰር ማህደር አሰፋ ስምምነታቸውን አጽድቀውታል። ለኤግልም ሆነ ለዶቃ ፊልም ባለቤቶች ትልቁና ወሳኙ ይሆናል። ምክንያቱም በሦስተኛው የጋራ ግብራቸው ለማሳየት የተስማሙት በሲኒማ አፍቃሪው ዘንድ ሁሉ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን “ዶቃ” የተሰኘው ፊልም በመሆኑ ነው።

ፊልሙ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገራት ድረስ ሲዘዋወርና ሽልማቶችን ሁሉ ጥርግርግ! ሲያደርግ ከርሞ አሁን ደግሞ በቴክኖሎጂው ሰረገላ እየተጎተተ ለሁሉም ተመልካች ቅርብ በሆነ መተግበሪያ ብቅ ብሏል። በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ ሲኒማ አንድ ርምጃ ወደፊት ያለበት አቅም ነው። የሲኒማ ቤቶችን ደጅ መርገጥ እንደ ዓይነጥላ ለሆነበት የሀገር ውስጥ ተመልካች መድኃኒት ነው።

በሀገር ውስጥ ሳይገደብ ባህር ተሻግሮ ዓለም አቀፉንም ተመልካች የሚያካልል በመሆኑ ለኢንዱስትሪው ደግሞ አዟዙሩ የሚመለከትበትን ሌላ ዓይን ይጨምርለታል። ከዚህ ቀደም በቴክኖሎጂው ለመታየት የበቁትን ሁለት ፊልሞችና ሦስተኛው የዶቃ ፊልም ለአዲሱ ልምምድ ፈር ቀዳጅና በር ከፋች ናቸው እንጂ በእነርሱ ብቻ የሚያቆም አይደለም። ምናልባትም ቀጥሎ ላለው ጊዜ ሁኔታዎች ሁሉ የሚጠቁሙት ወዲዚያው ነው።

ታዲያ የመጣው አዲስ ቴክኖሎጂ ለሲኒማው ብስራት ወይንስ ስብራት? ምናልባትም ጉዳዩ አንዳንዶችን ያነጋግርና ያከራክር ይሆናል። በመጀመሪያ አንድ መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር እኛ ኢትዮጵያውያን ካለን የእርስ በርስ መስተጋብራና የማኅበራዊ ሕይወት የኑሮ ዘዬ ያለን ከመሆናችን አንጻር፣ እንዲሁም ከቴክኖሎጂዎች ጋር ያለን ቅርበትም እዚህ ግባ የሚባል ከመሆኑ የተነሳ ሲኒማ ቤቶች ተመራጭ ናቸው። ታዲያ ፊልሞች በዚህ የቴክኖሎጂ መንገድ መምጣታቸው ሲኒማ ቤቶችን ያዘጋል ማለት አይደለም። የመጣው ቴክኖሎጂ ሙሉ ሙሉ ሲኒማ ቤቶችን የሚተካ ሳይሆን እንደ ሁለተኛ አማራጭ በአጋዥነት የሚደግፍ ነው።

ለነገሩ አዲስና ከዚህ ቀደም ተሞክሮዎች የሌሉን በመሆኑ የሲኒማ ቤቱ ስጋት ይገባን ይሆናል። ነገር ግን ስጋቱን ማግዘፍም ሆነ መናቅ የለብንም። ሁለቱንም እንደ አስፈላጊነቱ አስታርቀን መሄድ ካልቻልን ስጋቱ እውን የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም። ይሁንና ሞት አለ ተብሎ ሳይንቀላፋ አይታደርም። ብንመርጥም ባንመርጥም እየመጣ ያለው የዓለማችን መንኩራኩር ያለ ቴክኖሎጂው የማያሳፍር ነውና ልንለማመደው የግድ ነው። ለኛ ካልሆነ በስተቀር ትልልቅ የፊልም ኢንዱስትሪ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ነገርዬው የተለመደ ነገር ነው።

ለአብነትም “ኔትፍሊክስ” የተሰኘውን የፊልም መተግበሪያ ብንመለከት ስሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገነነ ከመሆኑም በላይ ከዓለም አቀፉ ተመልካች የሚያስገኘው ረብጣ ረብጣ ገንዘብ ተዝቆ የሚያልቅ አይደለም። ዓለም አቀፍ የፊልም ባለሙያዎችም ምኞትና ትጋታቸው ፊልሞቻቸው በዚሁ የቴሌቪዠን መተግበሪያ እንዲታይላቸው ነው። ቀጣዩ የዓለማችን የፊልም ኢንዱስትሪ ትንቅንቅም በእነዚሁ የቴክኖሎጂ ሲኒማዎች መሆኑ አይቀሬ ነው።

እንደ ፊልም ኢንዱስትሪው የዚህ አዲስ ነገር መከሰት ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው። ፊልሞች ተሠርተው ለኪሳራ ከሚዳረጉበት ስርቆት ቀጥሎ ሁለተኛው ነገር የተመልካች እጦት ነው። የወለደውን ሲስሙለት፣ የሠራውንም ሲበሉለት ሰው ደስ ይለዋል፤ የሚባል ነገር ቢኖርም ነገር ግን ስመውለትም ሆነ በልተውለት “እግዜር ይስጥልኝ…በወጣ ይተካ” ተብሎ እንደሚኬድበት ዝክር አይደለም። ከዚህ ሁሉ በኋላ ፊልም ሠሪው ከፊልም ተመልካቹ ገንዘብ ይፈልጋል። ተመልካች ከሌለም ገንዘብ የለም ማለት ነው። ገንዘቡ ከሌለ ደግሞ በኪሳራው ፊልም ሠሪው ቀጥሎም የፊልም ኢንዱስትሪው ተያይዘው ይወድቃሉ።

እናም የፊልሞቹ ከቴክኖሎጂ ጋር ብቅ ማለት ከሲኒማው በተሻለ፣ ከሰመረለት ደግሞ ሊነጻጸር በማይችል መልኩ ገቢን ያስገኛል። የፊልም ባለቤቶችን ብቻም ሳይሆን የተራበውን ኢንዱስትሪም ማጥገቡ አይቀርም።

እንግዲህ ይህንን ሁሉ ስንል ለመዘንጋት የማይገባን አንድ ነገር አለ። ይኼውም የዶቃ ፊልም ስለቀረበበት የዶቃው ማሰሪያ ወይንም ስለ ቴሌ ቲቪ መተግበሪያ ነው። የፊልም ኢንዱስትሪውም ሆነ ተመልካቹ ገና ከጅምሩ ትልቅ ተስፋ ጥለውበታል። ለባለሙያውም እፎይታን የሰጠ ሆኗል። መተግበሪያውን በመጠቀም “ዶቃ”ንም ሆነ ሌላውን ፊልም ለመመልከት ለሚሻ መልዕክቱን እንዳናጎድል ከተሰጠው መግለጫ ላይ ባለቤቶቹ እንዳሉት ከማለት ያሉትን ከአንደበታቸው እንደወረደ መስማቱ ይበጃልና እንዲህ ነበር፤ “ፊልሙን ገዝተውም ሆነ ተከራይተው ለመመልከት ለሚፈልጉ ተጠቃሚዎች በኢንተርናሽናልም በሎካልም የክፍያ አማራጮች ቀርቧል።

ቴሌ ብርን በመጠቀም በአራቱም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ተመልካቾች ቪዛ፣ ማስተር ካርድ እንዲሁም አሜሪካን ኤክስፕረስን በመጠቀም ፊልሙን ከቴሌ ቲቪ ድህረ ገጽ ላይ መከራየት ይችላሉ። ለጊዜው ፊልሙን ማግኘት የሚችሉት ከዚሁ መተግበሪያ ላይ ብቻ ነው። በሀገር ውስጥ ያሉ የአንድሮይድ ስልክ ተጠቃሚዎች ደግሞ በቴሌ ብር መተግበሪያ ክፍያውን በመፈጸም እዚያው ላይ በቴሌ ቲቪ ለመመልከት ይችላሉ።

ለአፕል ስልክ ተጠቃ ሚዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በተጣለው የአፕል ፖሊሲ መሠረት አፕል ፔይን መጠቀም በመሆኑና አፕል ፔይ ደግሞ በሀገራችን ውስጥ የማይሠራ መሆኑን ተከትሎ ፊልሙን ለመግዛት አይችሉም። ነገር ግን፤ ለማግኘት የአፕልን የቴሌ ብር ሱፐር አፕ መተግበሪያን በመጠቀም ለመከራየት ይችላሉ። በአማራጭነት ደግሞ የቴሌ ቲቪን ድህረ ገጽ(teletv.et) በመጠቀም ካሉበት ሁሉ ሆነው መመልከት ይችላሉ” የሚል አንክሮተ መልዕክቱን አስተላልፏል። ከዚሁ ጋር ክፍያውን በተመለከተም ለሁለቱም ተመልካቾች በዋጋ ተሰፍሮላቸዋል።

በዚህ መሠረትም ለሀገር ውስጥ ተመልካች 1 መቶ ብር ሲሆን ለውጭ ሀገር ተመልካቾች ደግሞ 5 ዶላር ብቻ በመክፈል የቁጥር ግምት የማይወጣለትን ፊልም ለመመልከት ይችላሉ።

የ“ዶቃ” ፊልምን የቀጣዩ አዲስ መዳረሻን ተከትሎ በነበረው የማብሰሪያ ዕለት ሌላ አንድ አዲስ ነገርም አስመልክቶን ነበር። በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ ገነው ከታዩ ወጣት ሴት ተዋንያን መካከል የሆነችው ማህደር አሰፋ ለረዥም ጊዜያት ከፊልሙም ሆነ ከሌላ ጠፍታ መቆየቷ ይታወቃልና የዶቃው ማሰሪያ መልሶ አምጥቷታል። በዚህ ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት በመሥራት የገዘፈ አድናቆትን ከተቸሩት አንዷም ናት። ማህደር በ“ዶቃ” ተዋናይት ብቻ ሳትሆን የፊልሙ ፕሮዲዩሰርም ጭምር ናት።

“ፊልሙ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ እይታን እንዲያገኝ ከመጀመሪያው ጀምሮ እያንዳንዳችን ስንደክም ነበር። በፊልሙ እስከ ዛሬም በጣም ብዙ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ወስደናል። ገና የምንወስዳቸውም አሉ” የሚል ተስፋና የስኬት ሀሳቧን አጋርታም ነበር። በ“ዶቃ” ፊልም ውስጥ ከእርሷ ጋር ሌላኛዋ የዚህ ፊልም የጀርባ አጥንት ደግሞ ቅድስት ይልማ ናት። ከዚህ ቀደምም በርካታ ፊልሞችን በመድረስና ዳይሬክት በማድረግ ለቁጥር የሚታክቱ ሽልማቶችን ሰብስባለች። አሁን ደግሞ በእጥፍ በዶቃ ውስጥ ታሪክ ሠርታለች። “ዶቃ” ፊልም ከሀገር ተሻግሮ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሽልማቶችን ሁሉ ጥርግርግ አድርጎ የበላ ተአምረኛም ጭምር ነው።

“ዶቃ” ከነቃጭሉ ፊልሙና በፊልሙ ዙሪያ ለማኮብኮብ ያህል …ፊልሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ ከበቃበት አንስቶ በርካታ የፊልም አፍቃሪያን ጉጉታቸው እስከ ዶቃ ማሰሪያቸው ደርሶ “ዶቃን” ሲናፍቁና ሲያደንቁ ቆይተዋል። አሁንም የፊልሙን ታላቅነት እያነሱ በየማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሳይቀር ያወጋሉ። አንድ የኢትዮጵያ ፊልም በዚህ ያህል ደረጃ ሲያነጋግር መመልከቱ ደስታን የሚሰጥ መሆኑ እንዳለም የመጀመሪያውም ነው ለማለት ይቻላል። በሰሞኑ ደግሞ ለሁሉም የቅርብ ሆኖ ለመታየት በመጣበት መንገድ ውስጥ ይበልጥ መግነኑ አይቀርም።

ከማንም ይሁን ማን በርግጥም ይህን ፊልም በተመለከተ አድናቆትን ሲቸሩት ማየትና መስማት የተለመደ ነው። ምክንያቱም ደግሞ የዚህ ፊልም ልዕልና እጅግ ከፍ ያለና ዓለም አቀፍ ከፍታዎችን አሻቅበው እየተመለከቱ የሠሩት ፊልም በመሆኑ ነው። አንድ ለሲኒማው የተበረከተ ፊልም ብቻም አይደለም። ብዙዎችን ያስማማ እውነተኛ ገሀዳዊ ለውጥን ማሳየት የቻለ ታላቅ ፊልም ነው። ለፊልም አፍቃሪው ሀሴትን አጎናጽፏል። መቼ ይሆን የኢትዮጵያ ሲኒማ ከትልቅና ድንቅ ፊልም ጋር ቆሞ የሚያልፍለት ለሚለውም ማሳያ ነው።

በሌላ አቅጣጫ ክፉ ለሚመኘውም አፍ ማዘጊያ የሚሆን ፊልም ነው። በአጋጣሚዎች የተመለከቱት ዛሬም ድረስ ያጨበጭቡለታል። ያላዩትም የሚያዩበትን አጋጣሚ በጉጉት ሲጠባበቁ ሰንብተዋል። አሁን ግን ለሁሉም እንደ ምኞትና ፍላጎቱ በሆነ መልኩ ተከስቷል። ለሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ዛሬ ድረስ የናፈቀውን ብዙ አዲስ ነገሮችን አብርክቷል። ሀገርና ባሕልን በማንጸባረቅ፣ ሀገር በቀል የፊልም ጥበብን ዐሻራ በማኖር ደረጃ የተዋጣለት ነበር ለማለት ይቻላል። የተመልካቹን የፊልም ጥም በማርካትም ወደር አልባ ሆኖ ተገኝቷል። ከበረሀው መሀል እንደተገኘ ትንሽዬ የምንጭ ኩሬ ነበር። ከጊዜያት በኋላ ጊዜ ቆጥሮ ደርሷል።

በፊልም ጥበብ ሙያ ደረጃ እውቆቹ ሁሉ ሲያመሰግኑትና ሲያሞግሱት እንጂ ስለ ፊልሙ ሲተቹ አልተሰማም። ከዚህ ቀደም በፊልሞቻችን ውስጥ እንደ ችግር የሚወሱ ጉዳዮች ሁሉ በዶቃ ውስጥ የመታሰሪያ ልካቸውን አግኝተዋል። ከ6 ሺህ በላይ ሰው በተሳተፈበት ይህ ፊልም የጥራት ደረጃውንም እንዲሁ ከፍ ያደረገ ነበር። ከኢትዮጵያዊነት ወደ ምርጥ ኢትዮጵያዊነት ተጉዟል። “ዶቃ ፊልም የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቤት የሚያንኳኳ ስለሆነ ፊልሙን እንዴትስ አድርገን ወደሁሉም ተመልካች እናድርሰው የሚለው ነገር በጣም ጨንቆን ነበር” የፊልሙ ባለቤቶች እንዲህ ማለታቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊመለከተው የሚገባ ፊልም መሆኑን ለመጠቆምም ጭምር ነበር። በርግጥም ሊታይ የሚገባውም ዓይነት ነው። በሀገር ውስጥ የእይታ አድማሱን ማስፋት የሚኖርበት እንደመሆኑ የቋንቋው ጉዳይም መላ እየተበጃጀለት ይገኛል። ሁሉም ካለበት በቴክኖሎጂው አማካይነት የሚደርስ እንደመሆኑ ፊልሙ ከተሠራበት የአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ የጽሑፍ ትርጉም መካተት ነበረበትና እንደ መጀመሪያ የኦሮምኛ ቋንቋ ታክሎበታል። በቀጣይም በሌሎች ቋንቋዎችም የሚቀጥል መሆኑ ተነግሯል።

ከዚሁ የዶቃ ሰንሰለታማ ተራራ ላይ ስንጎራደድ ልንመለከታቸው ከሚገቡን መሀል ጥቂቱን እናክል… ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው የፊልሙ ታሪክና ጭብጥ ከትናንት ዛሬ ያለውን የሀገራችንን ገሀድ ፍንትው አድርጎ ያስመለክተናል። ከቁስ ጀምሮ በፊልሙ ውስጥ የሚታዩና የተካተቱ ነገሮች በሙሉ ከቱባ ባሕልና ሥርዓታችን ጋር ተሳስሮ እንደጌጥ ይታያል።

ሀገርና የሀገር ፍቅር ውበቱ በአንገት ላይ እንደታሰረው ዶቃ ነው። ዘረኝነት ግን እንደ ምላጭ ነው። በአንገት ላይ የታሰረውን የዶቃ ማሰሪያ በጥሶ ዶቃውን ያረግፋል። ዶቃ ፊልም የዚህን ምላጭ መጨረሻ ያሳየናል። “ዶቃ” በውብ ማሰሪያው እንደተንጠለጠለ ድንቅ የሆነውን የፊልም ጥበብ ከሀገርና ሀገራዊነትን ጋር አጊጦበታልና ግብዣው ለሁላችንም ነው።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You