አቶ ማህመድ አባ መጫ በግብርና ሙያ ነው የሚተዳደሩት፡፡ የትውልድ አካባቢያቸው በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን አጋሮ ነው፡፡ በተለይ አርሶ አደሩ ቡና አምራች ናቸው፡፡ በዓመትም ከ100 ኩንታል ያላነሰ የቡና ምርት ያመርታሉ፡፡ ሆኖም የቡና ምርቱን ከአጋሮ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መንገዱ ችግር ሲፈጥርባቸው እንደቆየ ይናገራሉ፡፡
በተለይ ደግሞ «ክረምት ክረምት ጭቃው ስለሚያስቸግር ትራንስፖርት በቀላሉ ማግኘት አይታሰብም። ምርታችንን ገበያ ለማቅረብ ረጅም ጊዜ ይወስድብናል። እንዲሁም ነፍሰጡሮችን ወይም ህመምተኞችን በፍጥነት ወደ ተሻለ ህክምና ለማድረስ እንቸገራለን። አሁን ግን መንገዱ በአስፓልት ደረጃ ሊሰራ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ በቀላሉ ትራንስፖርት ከማግኘታችን ባለፈ ምርታችንን ገበያ ማቅረብ ያስችለናል» ይላሉ።
በመንገዱ አስቸጋሪነት የተነሳ ከቡና ምርታቸው ተገቢውን ዋጋ እንደማያገኙ የሚገልጹት አርሶ አደር አህመድ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የጅማ-አጋሮ-ዴዴሳ ወንዝ መንገድ ሊሰራ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ የረጅም ጊዜ ጥያቄያችን መቋጫ አገኘ በሚል ደስታ ተሰምቶናል ይላሉ፡፡
በተለይ ከግቤ ወንዝ ጀምሮ እስከ ዴዴሳ ያለው መንገድ ለጉዞ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የቡና ምርት በቀላሉ ለገበያ እንዳናቀርብ ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከአጋሮ አካባቢ ብቻ በዓመት 10 ሺ ቶን የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ቢቀርብም መንገዱ የተበላሸና በክረምት ደግሞ ይበልጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ያጋጥማል ነው የሚሉት፤ ከአጋሮ እስከ ጅማ ድረስ ርቀቱ 45 ኪሎ ሜትር በመሆኑ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ቢኖር ኖሮ ከ30 እስከ 40 ደቂቃ ብቻ ነው የሚወስደው፡፡ ሆኖም አሁን መንገዱ በጣም የተበላሸ በመሆኑ ከሁለት ሰዓት በላይ ነው የሚፈጀው ብለዋል፡፡
በዚህ ምክንያትም አርሶ አደሩ ምርቱን በአነስተኛ ዋጋ እንዲሸጥ ይገደዳል። አርሶ አደሩም በገበያ ችግር ሳቢያ ባመረተው ልክ ተጠቃሚ አልሆነም፡፡ አሁን ግን መንገዱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ሁኔታዎች ይለወጣሉ የሚል እምነት አላቸው። እሳቸው የሚያመርቱትን ጨምሮ በአካባቢው የሚመረተውን ቡና በመሰብሰብ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ አላቸው፡፡
እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ፤ የመንገዱ መገንባት እኛ አርሶ አደሮች በአጭር ጊዜ፤ ያለምንም መንገላታት ምርታችንን ገበያ አውጥተን የምንሸጥበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልናል። ይህም ለኑሯችን መለወጥ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። እናም እኔም ሆንኩ የአካባቢው ህብረተሰብ የመንገዱን መጠናቀቅ በጉጉት እንጠብቀዋለን።
ዴዴሳ አካባቢ ተወልደው ያደጉት ሼህ አልብዱልቀድር ኢብራሂም የሃይማኖት አባት ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጅማ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ሁሌም ቢሆን ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ዴዴሳ ያቀናሉ፡፡ መንገዱ በጣም ተበላሽቷል፡፡ በተለይ ቱባ፣ ዳበሳና ዴዴሳ አካባቢ መንገዱ በጣም ተጎድቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ተሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ ለብልሽትና ለአደጋ እንደሚጋለጡ በአይናቸው ተመልክተዋል፡፡
‹‹በአደጋውም የብዙ ሰዎች ህይወት ያልፋል፡፡ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል፡፡ እኛም ቢሆን ከጅማ ወደ ዴዴሳ ወይም ከዴዴሳ ወደ ጅማ ስንሄድ ሁሌም በስጋት ነው የምንጓዘው፡፡ ተመልሰን ወደ ቤታችን እንገባለን ብለን አስበን አናውቅም›› እናም መንገዱን ለመስራት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ እንዳስደሰታቸውና የቆየ ችግራቸው ሊፈታ መቃረቡን ማብሰሪያ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡
በንግድ ሙያ የሚተዳደሩት አቶ ሰርሞሎ ሼህ ሀሰን በአጋሮ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ጤፍ ባቄላ፣ ምስርና በቆሎ ይነግዳሉ፡፡ ሆኖም የመንገድ ችግር ለንግድ ስራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ነው የሚናገሩት፤ ‹‹አጋሮ ቡና አምራች ናት፡፡ ይሁን እንጂ በልማት ወደ ኋላ የቀረች ደባ የተፈጸመባት ከተማ ናት፡፡ ምክንያቱም በአካባቢው ትልልቅ የመንግስት የቡና ልማት ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መንግስት በየዓመቱ ብዙ ገንዘብ ቢያገኝም ገንዘብ ከማሳደድ ውጭ ለአካባቢው ልማት ደንታ አልነበረውም፤ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡን ፡፡
መንግስት በአሁኑ ጊዜ ለአካባቢው ትኩረት ሰጥቶ የመንገዱን ግንባታ ማስጀመሩ ለነዋሪው ህይወት መሻሻል ተስፋ፤ ለከተማ ዕድገት ደግሞ ብርታት ይሆናል ብለን እንጠብቃለን ይላሉ፡፡ ምክንያቱም መንገዱ ወደ ጋምቤላና ወደአዲስ አበባ የሚያዘልቅ ነው፡፡ መንገዱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በአስፓልት ከተሰራ የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴ ያፋጥናል፤ ከተሞች እንዲስፋፉ ያደርጋል፡፡ ምርትን ለገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
የመንገዱ ግንባታ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብም እንዲጠናቀቅ እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ህብረተሰብ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግ ነግረውናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ፣ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽርና የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ በጋራ የጅማ-አጋሮ-ዴዴሳ ወንዝን መንገድ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ‹‹መንገዱ መጀመሩ ጥሩ ቢሆንም ፍሬውን አይተን ለመደሰት ብዙ ስራ ከፊታችን ይጠብቀናል›› ብለዋል፡፡
የጅማ-አጋሮ-ዴዴሳ ወንዝ መንገድ እጅግ የተጎዳና ጠባብ ነው፡፡ ይኸው መንገድ አምስት ሜትር ስፋት ሲኖረው ከ50 ዓመት በላይም አገልግሏል፡፡ በዚህ ምክንያት መንገዱ የተጎዳና ለተሽከርካሪም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለትራፊክ አደጋም ያጋልጣል፡፡ እንግልቱ የበዛበት ህዝብም እንደሌሎች መንገዶች ሁሉ የጅማ-አጋሮ -ደዴሳ ወንዝ መንገድም እንደ አዲስ እንዲሰራ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ያወሳል፡፡
የጅማ – አጋሮ- ዴዴሳ ወንዝ ድልድይ መንገድ በአዲስ መልክ መገንባቱ ለኢኮኖሚውም ሆነ ለማህበራዊው እንቅስቃሴ መጎልበት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ግንባታው መጀመሩንም ጠቅሷል፡፡ ይህ ፕሮጀክት የአገሪቱን ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ክፍሎች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ የመንገድ መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የሚያስችል ነው፡፡ መንገዱ 79 ነጥብ 07 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው፤ ከአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ ነው፡፡
ግንባታውን የሚያከናውነው የቻይና ሬል ዌይ 21ኛ ቢሮ ግሩፕ የተባለ ዓለም አቀፍ የስራ ተቋራጭ ድርጅት ነው፡፡ የምህድስናና የማማከር ስራውን በጋራ የሚያከናውኑት ደግሞ ኦሜጋ ኮንሰልቲንግ ኢንጅነሪንግና ፕሮሜ ኮንሰልታንት ናቸው፡፡ በመንገድ ግንባታው ከሚካተቱት ዋና ዋና ስራዎች መካከል የአፈር ቆረጣና ሙሌት፣ ነባሩን የዴዴሳ ወንዝ ድልድይ የመጠገንና ማጠናከር፤ እንዲሁም የትልልቅና አነስተኛ መፋሰሻ ቱቦዎች ግንባታ ይገኙበታል፡፡
የመንገዱ መሰራት በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን የሚገኙ ሶስት ወረዳዎችን፤ ማለትም የማና፣ ጎማና ጉማይ ወረዳዎችን ደረጃውን በጠበቀ የመንገድ መሰረተ ልማት ለማገናኘት የሚያስችል ነው፡፡ እንዲሁም፤ ከቡኖ በደሌ ዞን ጋርም ለማስተሳሰር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
መንገዱ ሰንጥቆ የሚያልፍባቸው አካባቢዎች የደጋ፣ ወይና ደጋና ቆላማ የአየር ጠባይ ያላቸው ናቸው፡፡ በአካባቢውም ቡና፣ በቆሎ፣ ስንዴና ምስር ይመረቱበታል፡፡ በኮንትራት ውሉ መሰረት የመንገዱ ግንባታ በሶስት ዓመት ከአምስት ወር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡ የሚገነባው መንገድ ስፋቱ በከተሞች የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 22 ነጥብ 5 ሜትር ሲሆን በገጠር ደግሞ 10 ሜትር ነው፡፡ የመንገዱ ግንባታ ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው፡፡
የመንገዱ ግንባታ በሚካሄድባቸው መስመሮች ላይ የሚገኙ የመስተዳድር አካላት፣ የአካባቢው ህብረተሰብ መንገዱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
የመንገዱ መገንባትም ለአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል ይፈጥራል፣ ለተሽከርካሪዎችም ጊዜ ይቆጥባል፤ እንግልትም ያስቀራል፡፡ በአካባቢው የሚመረቱ ምርቶችን በቀላሉ ወደ ገበያ ማውጣት ያስችላል፡፡ በተለይ የቡናን ምርት በፍጥነት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የመንገዱ መስራት ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ የህዝብ ለህዝብ ትስስርንም ያጠናክራል፡፡ ይህም የነዋሪውን ገቢ በማሳደግ ኑሮውን እንዲያሻሽል ያደርጋል፡፡
ከዴዴሳ ወንዝ እስከ መቱ የሚዘልቀው መንገድ በአስፋልት ኮንክሪት ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ መንገድ ለህዝቡ ህይወት መለወጥና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ድርሻ አለው። የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ወደ አርሶ አደሩ አካባቢ ለማድረስም ሆነ ያመረተውን ምርት ለገበያ ለማቅረብ መንገድ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ፍሰትም እንዲፋጠን ያስችላል። መንገድ ለከተሞች ዕድገት መፋጠንም ትልቅ ድርሻ እንዳለው መንገድ ያላቸውንና የሌላቸውን ከተሞች በንፅፅር ማየቱ በቂ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 3/2011
ጌትነት ምህረቴ