ብሔራዊ ምክክሩ የእርቅና የተግባቦት መድረክነው

የዓለም የሥልጣኔ መልኮች ከሆኑት ውስጥ በሃሳብ ፍጭት ሰላም ማውረድ አንዱ እና ዋነኛው ነው። ሥልጣኔ ብዙ መልኮች፣ ብዙ አረዳዶች ሊኖሩት ይችላሉ። ብዙ ፍልስፍናዎች፣ የተለያዩ መነሻዎች ሊኖሩት ይችላሉ ሰላም እንዳለበትና ለሰላም ዋጋ መክፈልን የመሰለ የልህቀትና የብርታት ጥግ ግን የለም። አንዳንድ ነገሮች እስኪገቡን ድረስ ዋጋ አስከፋዮቻችን ናቸው።

ባለፉት ዘመናት ስለ ነጻነት የተሻለ መረዳት ፈጥረን ለሌሎች የነጻነት መነቃቃት ሆነናል። በዚህ ዘመን ደግሞ ባለመደማመጥ ያልገባን ሆነን ከክብራችን ጎድለናል። ለእንዲህ ዓይነቱ ሀገራዊ ውጥንቅጥ እንደ መፍትሔ ሆኖ ከፊት የሚመጣው የሃሳብ ፍጭትን ያነገበ የእርቅና የተሀድሶ መድረክ ነው።

በሌሎች የዓለም ክፍሎች እንዳየነው የፖለቲካ ልዩነት፣ የሃሳብ፣ የፍላጎት አለመገጣጠም የትም ቦታ፣ በምንም መልኩ የሚነሳ ነው። ዋናውና ሊሰመርበት የሚገባው፣ የሥልጣኔን ምንነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳየን ለዚህ ልዩነት የምንሰጠው ግብረ መልስ ነው። ስልጣኔያቸውን ከሰላም የጀመሩት እነርሱ የሃሳብ ልዩነቶቻቸውን ለተሻለ በረከት በመጠቀም ለአዲስ እይታ ሲሰናዱ ሥልጣኔያችን ግጭትና እልኸኝነት የሆነው እኛ ደግሞ ዋጋ ለመክፈል እንጠቀምበታለን። ልዩነታችን ከዚህ የሚጀምር ነው።

አንድ ዓይነት ሰው የለም። አንድ ዓይነት ጭንቅላትና እኩል አረዳድ የለም። እንደ ልዩነታችን ልዩ ልዩ ነገር ለማሰብ በመገደድ ሰው የሆንን ነን። በልዩነት ወደ ጦርነት መግባትና በልዩነት አዲስ እይታን መተለም እጅግ ምርጡ የሥልጣኔ መልክ ነው። ትግላችን ወይም ደግሞ ብሔራዊ ምክክር ስንል የምናወራው በልዩነት ጦርነትን ሳይሆን አዲስ እይታን ለመለማመድ ነው።

በሃሳብ ልዩነት ወደ ጦርነት የሚገቡ ስለሀገር ቢያወሩ የማያምርባቸው፣ በቃል ካልሆነ በተግባር እዚህ ግቡ የማይባሉ፣ የሀገር ፍቅርን ጽንሰ ሃሳብ ያልተረዱ ናቸው። በተቃራኒው ልዩነትን ለእድገትና ለዝማኔ የሚጠቀሙ እነርሱ በሀገርና ሕዝብ ፊት የሚያጎነብሱ፣ ቅድሚያ ለሀገር በሚል ፈሊጥ የሚታወቁ ናቸው።

በፍጭት ውስጥ እንጂ በግጭት ውስጥ ሥልጣኔ የለም። ከእንስሳት ዓለም ጊንጥ ራሷን በራሷ መርዛ የምትገል እንስሳ ናት። ለምን ? መርዟ ራሷን እንደሚገላት ባልተረዳና ባልገባው ደመነፍስ ውስጥ ስለሆነች ነው። የእኛም ታሪክ እንደዚህ እየሆነ ነው። ማንም ሳይመጣብን፣ ማንም ሳይጠጋን እርስ በርስ ተመራርዘንና ተጨካክነን ለራሳችን አደጋ እየሆንን ነው።

ማንም አፈ ሙዝ ሳይደቅንብን እርስ በርስ እየተተኳኮስን ነው። ይሄ የሀገራችን ታሪክ፣ የፖለቲው ትርፍ መሆኑ አሳዛኝ ነው። ሀገራችን የምትታወቀው አስታራቂና የሰላም ባለቤት ሆና ነበር። ሕዝባችን በጋራ እሴት እና ትውፊት ተሳስሮና ተጋምዶ እንዳይለያይ ሆኖ ሲኖር ነበር።

መች ይሆን ሞተንና ገለን የሚበቃን? መች ይሆን ተቃቅፈንና ተደጋግፈን በአንድ የምንቆመው? መቼ ይሆን እንደክፉ ህልም የምንሰራው ሥራ መጥፎ እንደሆነ ገብቶን ድንገት የምንባንነው? በለው በሚልና ድንጋይ አቀባይ መሀል፣ አስታራቂና ዘካሪ በሌለበት ሁኔታ የምናፍቃራትን ኢትዮጵያ የምናየው ?።

የእልህ ፖለቲካ ለሀገርና ሕዝብ አንደ ጊንጧ መርዝ ነው። ማንንም የማይምርበት የሆነ ጊዜ ይመጣል። በዛ ጊዜ ላይ ሞትና መከራ የሕዝባችን የእለት ተእለት መልክ ሆኖ ይቀጥላል። በራሳችን ራሳችንን መርዘን ከማጥፋታችን በፊት ከፖለቲካው ላይ መርዙን ነቅለን፣ ከፖለቲከኞቻችን ላይ እንዲሁም ከሕዝብና ትውልድ ላይ እርግማንን አስወግደን ስለሰላም ዋጋ እንክፈል።

ስለሰላም ዋጋ ለመክፈል ደግሞ ከፉክክር ወደ ምክክር፣ ከጥላቻ ወደ እርቅ፣ ከግጭት ወደ ሃሳብ ፍጭት ልንሸጋገር ይገባል። ከምንም በላይ ደግሞ ልዩነቶቻችንን በብስለትና በብልሀት በማጤን ለጦርነት የሚያበቁ እንዳይደሉ መረዳት ግዝፈት ያለው የሰላም ምንጫችን ነው። በአንድ ዓይነት አቅጣጫ አንድ ዓይነት ድርጊትን እየከወኑ መኖር ባለድል አያደርግም።

እያደረግነው ያለው ነገር ጥቅም የሌለው ከሆነ የአቅጣጫ ለውጥ እጅግ አስፈላጊያችን ነው። ብሔራዊ ምክክር እንደ አቅጣጫ ለውጥ ለተሻለ ብሔራዊ ድል የመጣ የእርቅና የተግባቦት መድረክ ነው። ካለ እርባና በእልህ ፖለቲካ፣ በጥላቻ መንፈስ እያፈረስንና እያወደምን የመጣንበትን ጎዳና ለመጥረግ፣ ካለ ትርፍ እየገደልንና እየሞትን የመጣንበትን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት በሕዝብ የሃሳብ መዋጮ የቆመ የሰላም ዘብ ነው።

በጦርነት ሁሉንም ዓይነት መከራ አስተናግደናል የፈጠርነው አዲስ እውነት ግን የለንም። ምክንያቱም የአቅጣጫ ለውጥ ስላላደረግን ነው። እዚህ ጋ በቅቶን አዲስ ሀገርና ትውልድ፣ አዲስ ፖለቲካና ፖለቲከኛ የምንፈጥርበትን ምህዳር መፍጠር ስለሰላም ብቸኛው አማራጫችን ይሆናል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዓለም የሃሳብ ልዩነትን የተረዳበትን ሁኔታ ላስተዋውቃችሁ። በምድራችን በአራቱም አቅጣጫ የሃሳብ ልዩነት በሚፈለግበት ዘመን ላይ ነን። በሀገረ አሜሪካም ሆነ በአብዛኛው የአውሮፓ ሀገራት የእኛን ሀገር ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የሄዱ በርካታ ዜጎች ይገኛሉ።

ይሄ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ሥልጣኔና ዘመናዊነት በተመሳሳይ ሃሳብ ሳይሆን በተለያየ አረዳድ የሚጸና እንደሆነ ለማስረዳት ነው። የነዛ ዜጎች በአሜሪካም ሆነ በሌሎች ባዕድ ሀገራት መኖር ለሀገሪቱ ተጨማሪ ሀብት፣ ተጨማሪ ኃይል እንጂ ያጎደለው አንዳች ነገር የለም። አይኖርምም። ወንድም ከወንድሙ አይደለም ከሌላ ሀገር ሰው ጋር እንኳን ይኖራል።

አሜሪካ በዲቪም ሆነ በመሰል አማራጮች የዜጎቿ ሃሳብ አልበቃ ብሏት ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ሃሳብ ያላቸውን ዜጎች በበጎ ፍቃድና በብዙ ማማለያዎች እያስኮበለለች ትገኛለች። በካናዳ፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን በሌሎችም ሀገራት ተመሳሳይ ነው ያለው። የሃሳብ ልዩነት እኛ ሀገር እንጂ በሌላው ሀገር ሞትና ጉስቁልና ሆኖ አያውቅም። ይሄ እውነት እስካልገባንና ልዩነቶቻችንን ለልማት መጠቀም እስካልቻልን ድረስ ከድካማችን አናርፍም።

ሃሳብ የታከለበት ፖለቲካና በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ፖለቲከኛ ለሀገር ያለው ዋጋ በምንም የማይተካ ነው። በሃሳብ የዳበረ መድረክና ሃሳብ የሚንሸራሸርበት ሥርዓት ትውልድ በመቅረጽና ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ረገድ የትየሌለ ሚና ያለው ነው። ልክ እንደዚህ ሁሉ በፖለቲካውና በፖለቲከኞቻችን ውስጥ ሃሳብ ከሌለ ጥፋቱም የዛኑ ያህል የከፋ ነው። መቼም ይቺን ተራ እውነት ለመረዳት የሀገራችንን አሁናዊና ትላንትናዊ ትኩሳት ማየቱ ብቻ በቂ ነው።

“የዝሆኖች ጥል ሣሩን ነው የሚጎዳው” እንደሚባለው፤ በእኛ ሀገር የፖለቲካ ሽኩቻ ከሕዝብ፣ ከወጣቱ፣ ከሴቶች፣ ከሕጻናት፣ ከአረጋውያን በላይ የተጎዳ የለም። እነዚህ የጦርነት ሰለባዎች እንደ ሀገር የተሳሉ፣ እንደ ትውልድ፣ እንደ ታሪክ የተቀመጡ፣ እንደጋራ እሴት ምልክት የሆኑ ቅርሶች ነበሩ ባለመግባባት ግን ወድመዋል። እነዚህ የትንቅንቆቻችን ኪሳራዎች ናቸው።

የሀገር ሞት የግለሰብ ሞት ነው። ሰው ሲሞት ሀገር እየሞተ ነው፣ ትውልድ እየጎደለ ነው፣ ታሪክ እየተሸረፈ ነው። ሀገር ማለት ሰው የሚለው ብሂል በዚህ ካልሆነ በሌላ በምን ይገለጻል? ቢገለጽስ እንደምን ልክ ይሆናል? አንድ ነገር እንመን ፤ ስለሀገር እንዳልገባን.. ስለሀገር የገባን ቢሆን ኖሮ ይሄን ያክል በራሳችን ላይ ባልጨከንን ነበር።

ባለፈውና አሁን ላይ እየሆነ ባለው የእርስ በርስ ግፊያ የጋራ ታሪኮቻችንን ከማጠልሸት ባለፈ ለመጪው ትውልድ ቂምና በቀልን ከማሽቀመፅ ባለፈ ያተረፈን የለም። ከዚህ ይልቅ በእኛ ይብቃ ብለን ለትውልዱ የእርቅና የፍቅር ድልድይ ብንሰራለት ኖሮ፤ የዛሬው መልካችን በተቀየረ ነበር።

ይህ ሲሆን ግን አይታይም ዛሬም ፤ ጦርነቱን የጀመሩት ዝሆኖች ሣሩን ካደረቁና ካጎሳቆሉ በኋላ ለእርቅ የሚቀመጡ ናቸው። በሌላ ቋንቋ የጦርነቱ አስጀማሪዎች ሕዝብን ለመከራ ከጣሉ በኋላ በስተመጨረሻ የሚተቃቀፉ ናቸው። በዚህ ሃሳብ ላይ ሊነሳ የሚገባው ትልቁ ጥያቄው ዝሆኖቹ ሳይጣሉ፣ ሣሩም ሳይጠወልግ በሰላም እርቅ ማምጣት አይቻልም ነበር ? የሚል ነው። በምክክር ትኩሳቶቻችንን ማብረድ ከቻልን፣ ከነውጥ ወደ ለውጥ፣ ከግጭት ወደ ፍጭት አቅጣጫ ከቀየርን ይቻላል።

በድህነትና በኋላ ቀርነት ለሚታወቅ ማህበረሰብ አይደለም በኢኮኖሚያቸው እንዳይፈርሱ ሆነው ለቆሙትም ቢሆን ጦርነት አውዳሚ ነው። ባሳለፍነው ጦርነት ሳቢያ ብዙ ነገሮች ከስረውብን አሁን ላይ እነሱን በመተካት ላይ ነን። ባለን ላይ ከመጨመር ይልቅ ያጠፋናቸውን በመተካት ላይ ሳለን ለሌላ ጥፋት ራስን ማሰናዳት ምን ሊባል ይችላል። በዚህ ዘመን አይደለም በዛ የድንጋይ ዘመንም ቢሆን የጦርነት አስተሳሰቦች የእልቂትና ማንንም ፊተኛ የማያደርጉ የኋቀርነት መገለጫዎች ናቸው።

ዘመኑ የተግባቦት ዘመን ነው። ከውይይት በስተቀር በምንም በኩል መፍትሔ ማምጣት አንችልም። በአንድ ሀገር ላይ የጋራ ታሪክ ማጽናት እንጂ በብቻ ትርክት የጋራ ታሪክን መናድ ለማንም የማይበጅ የኋላ ኋላ ሁሉንም ዋጋ የሚያስከፍል ድርጊት ነው። እንደነዚህ ዓይነት ማንነት ለበስ ልምምዶች ጎጂ ከመሆናቸው በላይ ለማንም የሰላም መንገድ የማይከፍቱ የቂምና የጥላቻ ውርሶች ሆነው ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ ናቸው።

ግጭትና የሃሳብ ፍጭት በአንድ ሀገር ላይ፣ በአንድ ፖለቲካ ውስጥ እንዲሁም ባለውና በሚመጣው ትውልድ ላይ የራሳቸው የሆነ መልክና ቀለም አላቸው። መልክና ቀለማቸው በሞትና ሕይወት የተሳለ በሥልጣኔና በስይጥንና የሚጠሩ ናቸው። በእልህና በይዋጣልን ስለመጣን የሃሳብ ፍጭትን እምብዛም ዋጋውን አናውቀውም። ግጭት ግን የኖርንበት እና ብዙ ሀገራዊ ዋጋ የከፈልንበት ስለሆነ ዳፋውን በሚገባ እናውቀዋለን።

በኢትዮጵያ ምድር ጦርነት ግብአተ መሬቱ የሚፈጸምበት፤ ሰላም እና አብሮነት እንደ ሕዝብ ለከፈልነው መከራ ክፍያችን ሆኖ በእያንዳንዳችን ቤት የሚነግሰው መቼ ይሆን ? በግጭትና ባለመግባባት የከፈልናቸው ብዙ ዋጋዎች ስክነትና ውይይት ታክሎባቸው ቢሆን ፤ የለውጥና የእድገት መጠሪያ በሆኑን ነበር። ለሰላም የሚረፍድ ጊዜ የለም፤ አሁንም ቢሆን ነገሮችን በማስተካከል የተሃድሶ አቅጣጫን መተለም እንችላለን። ለዚህ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር አላማም ችግሮቻችን ላይ ተመካክረን ፤ ተሻግረናቸው የምንሄድበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ነው፤ በዚህም ሀገርን በአዲስ ጎዳና ማራመድ ነው። በሃሳብ የበላይነት የሚደረግን የሕዝብን፣ የወጣቱን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስምምነት ለሀገር ሁለንተናዊ ሰላም ማዋል ነው።

ሀገራዊ ውይይት ባለመግባባት ያጣናቸውን እድሎች በሃሳብ ፍጭት፣ ፖለቲካዊ አቅጣጫን ከማስቀየር ባለፈ ከሞትና ከግጭት እሳቤ ወደ ሰላም መር የሚያሸጋግር፣ እንደ ሀገር በላቀ እና ዋጋ ባለው ፋይዳ መሀል ትውልድን የሚያራምድ፣ ለሁለንተናዊ ተሀድሶ የሰላም መንገድ የሚከፍት፤ የእርቅና የተግባቦት መድረክ ነው። ቸር ሰንብቱ።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You