አዲስ ዘመን ድሮ

ታሪክን መሰነድ ብቻ ሳይሆን እራሱ ታሪክ የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በእስከ ዛሬው፣ ለምእተ ዓመት ጥቂት ቀሪ በሆነው የሕይወት ዘመን ጉዞው ያልዘገበውና ያልሰነደው ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ጉዳይ የለም። ያላናገራቸው ልሂቃን፤ ያልሞገታቸው ፖለቲከኞች፣ ያልደረሰላቸው ኅዙናን ወዘተ የሉም ማለት እስኪቻል ድረስ ያላስተናገደው አካል አለ ለማለት የሚቻል አይደለም። ከእነዛ ሁሉ የመረጃ ቋቶች የሚከተሉትን ለዛሬ መርጠናል። በተለይም ወቅቱ በሀገር፤ በተራዛሚውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለበትን አሁናዊ ይዞታ በመገንዘብ ምርጫችን በዚሁ ዙሪያ ያተኮረ ሆኗል። ከአዲስ አበባ እንጀምር። ከዚያም ውንብድና ወደ ተሞላበት የዚያ ዘመን ንግድ እንዝለቅ፤ በመጨረሻም ዘና በሚያደርግ አጭር ግጥም አማካኝነት የሰውን ልጅ መንታ ባህርያት (ከሥነምግባር አኳያ) እንመልከት።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ቤቶች ተመሳሳይ ቀለም እንዲቀቡ ትእዛዝ ተላለፈ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድና የሌላም ዓይነት ተግባር ማከናወኛ መደብሮች ከዚህ ወር ጀምሮ ለአካባቢው የሚስማማ ቀለም እንዲቀቡ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ክፍሎች ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት ክቡር ሚኒስትር ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ናቸው።

……

የሚቀቡትም ቀለም አልባሌ ሳይሆን በዓይነቱና በጥራቱ የተሻለ መሆን አለበት። የቀለሙንም ዓይነት በየክፍሉ የሚገኙ ማዘጋጃ ቤቶች ሊሰጡ ይችላሉ ሲል የማዘጋጃ ቤቱ የማስታወቂያና የሕዝብ ኅብረት ማስፋፊያ ክፍል በተለይ ለአዲስ ዘመን ገልጧል።

የአዲስ አበባ ከተማ በአየርና በከፍተኛ ሥፍራ ሆነው ሲያዩት አብዛኛውን ቤት ጣራው የቆሸሸ፤ ቀለሙ የዛገ ሆኖ ይታያል። ስለዚህ እንደ ባለቤቱ መራጭነት አረንጓዴ ወይም በቀይ ቡናማ ቀለም መቀባት አለበት የሚል ማሳሰቢያ ክቡር ከንቲባው መልእክት ውስጥ ይገኛል። ያረጀውም ጣሪያ እንዲለወጥ የክፍሉ ባለሥልጣኖች በጥብቅ ታዝዘዋል።

(አዲስ ዘመን፣ መስከረም 7 ቀን 1964 ዓ.ም)

ዕቃ የሚደብቁ ነጋዴዎች ፈቃድ ይወሰዳል

(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር 3ኛው ዙር የዋጋ ቁጥጥር መጀመሩን ገልጦ ዕቃ ደብቀው የሚገኙ ነጋዴዎች ፈቃዳቸው የሚወሰድባቸው መሆኑን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ሰሞኑን ባደረገው በሁለት ዙር የተከፈለ የቁጥጥር ዘመቻ አጥጋቢ ውጤት መገኘቱን ገልጧል።

በአዲስ አበባና በአካባቢው በሚገኙ የገበያ ሥፍራዎች፣ የንግድ መደብሮችና መናኸሪያዎች፤ እንዲሁም በየኬላውና በአዲስ አበባ አምስቱም በሮች እንስፔክተሮች ተሠማርተው ባልሆነ ቦታ ዕቃ በሚያቆዩና በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ማድረጋቸውን ገልጦ በዚሁ መሠረት የዕቃ እጥረትን እንዳይደርስ ዕቃ በሚደብቁ፣ ባልሆነ ቦታ በሚያቆዩና የንግድ መደብራቸው ከሚገኝበት ሥፍራ በቶሎ የማያደርሡ ነጋዴዎች በአስተዳደር ውሳኔ ብቻ የንግድ ፈቃዳቸው ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚያዝባቸው አስታውቋል።

(አዲስ ዘመን፣ መጋቢት 1 ቀን 1968 ዓ.ም)

ነጋዴዎች እንዲያውቁት ስኳር በቀድሞ ዋጋ እንዲሸጥ ማስገንዘቢያ ወጣ

(ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ)

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዋጋ መቆጣጠሪያ ክፍል እለታዊ ቁጥር ክፍል በሚያደርግበት ወቅት የስኳር ዋጋ ጨምሮ መገኘቱን ለመረዳት ስለቻለ ጉዳዩን ካጣራ በኋላ፤ የስኳር ሽያጭ እንደቀድሞው እንዲሆን ለፋብሪካ ነጋዴዎች ማስገንዘቢያ አወጣ።

ከንግድና ኢንዱስት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የተሰጠው ዜና እንደሚያመለክተው፤ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወደ ንግድና ኢንዱስትሪ ተጠርተው፤ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተደርጓል። የስኳር ዋጋም ስለጨመረበት ምክንያት ምክትል ሥራ አስኪጁ የሰጡት ማስረጃ አጥጋቢ ሆኖ ባለመገኘቱና ተገቢው የአሠራር ዘዴ ባለመከተሉ፤ ኩባንያው የቀድሞውን ዋጋ ሳይለውጥ እንዳይሸጥ ተገቢ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል።

ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ በላይ የተሰጠው መግለጫ የሚያፈርስ ሌላ ማሳሰቢያ እስከሚወጣበት ጊዜ ድረስ የስኳር ዋጋ ያለምንም ጭማሪ ለሕዝብ እንዲሸጥ የስኳር ነጋዴዎች ሁሉ እንዲያውቁት የሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤቱ ትናንት በሰጠው መግለጫ ላይ አስገነዘበ።

ወደፊትም ስለዋጋው ምናልባት ለውጥ ቢኖር፤ ጉዳዩን በደንበኛው አጥንቶ ውሳኔውን የሚሰጠው ይኸው የሚኒስቴር መ/ቤት መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህን ትዕዛዝ ባለማክበር፤ ማንኛውም የስኳር ነጋዴ ከተለመደው ዋጋ በላይ ስኳር ሲሸጥ ቢገኝ ተገቢው ርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ትናንት አስታውቋል።

(አዲስ ዘመን፣ ጥር 10 ቀን 1961 ዓ•ም)

ተቆጣጣሪ በመምሰል ያጭበረበረው ተቀጣ

ደሴ፣ (ኢዜአ) በደሴ ከተማ ውስጥ ምንም አይነት ሥልጣን ሳይኖረው የአሥር አለቃ ነኝ በማለት ከገጠር ወደ ከተማ የሚገባውንና የሚወጣውን እህል፣ ስኳርና ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጦች በመፈተሽ ሲያወናብድ የተገኘው ዓሊ መሐመድ በ3 ወር እስራት እንዲቀጣ የ 04-01-01 ቀበሌ ማኅበር የፍርድ ሸንጎ ከትናንት በስቲያ ወስኖበታል።

በተከሳሹ ላይ የእስራት ቅጣት ሊወሰንበት የቻለው ባልተሰጠው ሥልጣን በመንገድ ላይ እየጠበቀ ስኳርና ሸቀጥ ጭነው ወደ ገጠር የሚወጡትንና እህል ጭነው ወደ ከተማ የሚገቡትን መኪናዎች እያስቆመ በመፈተሽ የተመቸውን ጥቅም በመቀበል ሲለቅ ያልተመቸውን ደግሞ ወደ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ በማቅረብ አወናብዶ ለማስቀጣት ሞክሮ እንደነበር በማረጋገጡ ነው።

(አዲስ ዘመን፣ የካቲት 19 ቀን 1969 ዓ.ም)

የዓለም ፍሬ

አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ

ዓለም ስትወልጂ ሁሉም መንታ መንታ፣

አንደኛው ቅን ሲሆን አንደኛው ወስላታ።

አንደኛው ደግ መንፈስ ሌላው አመጸኛ፣

ወንድሙን ለመግደል ለሊት የማይተኛ፣

ሁለቱም ሲሆኑ የማህጸን ጓደኛ፣

ታዲያ ለምን ሆነ አንደኛው ምቀኛ።

ብዬ ብጠይቃት ዓለምን በመላ፣

እሷም ነገረችኝ መልሱን እንዲህ ብላ።

ወልጄ … ወልጄ … ሲቀር ሳይሟላ፣

ሐኪሙ መርምሮ ኋላ ይቀራላ!!!

ኃይለሚካኤል ዓባይ

(አዲስ ዘመን፣ መጋቢት 7 ቀን 1952 ዓ.ም)

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You