ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል። ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ ጉዳዮች የሚያደርጉት ዲፕሎማሲዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት አሁን ይበልጥ እየጠነከረ መጥቷል። ከኢኮኖሚያው እንቅስቃሴ አንጻርም፤ ባለፉት አስር ዓመታት ከነዳጅ ውጭ በሁለቱ ሀገራት የሚደረገው የገበያ ትስስር ይበልጥ እያደገ እንደሆነ ይስተዋላል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ ምርት መዳረሻ ከሆኑ ቀዳሚ አምስት ሀገራት አንዷናት። ቡናን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶች ከኢትዮጵያ ታስገባለች። ሀገሪቱ ለግብርና አመቺ የሆነ የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳር ስለሌላት ከኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን ትገዛለች።
የተለያዩ የአረብ ኤምሬትስ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በአልሙኒየም፣ በመጠጥ ምርቶች እና በሌሎች ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛል።ኢትዮጵያም ነዳጅና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶች በርካታ ሚሊዮን ዶላር አውጥታ ከአረብ ኤምሬትስ ወደ ሀገር ቤት ታስገባለች።
ሁለቱ ሀገራት አንዳቸው ካንዳቸው የሚፈልጉት ነገር እንደመኖሩ፤ የሁለቱ ሀገራት የንግድ እንቅስቃሴ እያደገ መጥቷል። ከዚህ አንጻርም ሰሞኑን ሁለቱ ሀገራት በራሳቸው መገበያያ ገንዘብ ለመገበያየት በየራሳቸው ብሔራዊ ባንክ ገዥ አማካኝነት ስምምነት ተፈራርመዋል።
በሁለቱ ሀገራት በተደረገው ስምምነት መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሶስት ቢሊዮን ድርሀም በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ ይኖረዋል። የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ በተቃራኒው 46 ቢሊዮን ብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ እንደሚኖረው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የኢትዮጵያ አንዷ የንግድ አጋርና የውጪ ኢንቨስትመንት ምንጭ መሆኗንን በመግለጽ፤ ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።
የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ብሔራዊ ባንክ ገዥ ካሊድ ሞሃመድ ባላማ በበኩላቸው ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነታቸው እየተጠናከረ መምጣቱን እንደሚያሳይ አመላክተዋል።
በዚህ ረገድ ስምምነት መደረጉ ያለው የኢኮኖሚ ፋይዳ ምንድነው በሚለው ዙሪያ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ከዘርፉ ምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር መዚድ ናስር (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ የመጣ ቢሆንም፤ አሁን ባለው መንግሥት በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚው እና በሌሎች ጉዳዮች በጣም እየጠበቀ መጥቷል።
ሀገራቱ በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት መስማማታቸው እስካሁን ካደረጓቸው ግንኙነቶች አንጻር የሚጋነን ባይሆንም፤ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የኢኮኖሚ ሁኔታ አንጻር እምርታዊ የሆነ ድጋፍ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
ሁለት ሀገራት በራሳቸው ምንዛሬ ለመገበያየት የሚስማሙበት ሁኔታ የተጀመረው፤ እ.አ.አ በ1983 ነው የሚሉት ዶክተር መዚድ፤ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ዶላር ስትበደር የወለድ መጠኑ ስምንት ነጥብ አምስት በመቶ ነው። የድርሃም ደግሞ አምስት በመቶ ነው በማለት ይገልጻሉ።
ስለዚህ ኢትዮጵያ ድርሃም ተበድራ በዶላር መቀየር ትችላለች። በመሆኑም የዚህ የገንዘብ ስምምነት አንዱ ጠቀሜታ ብድርን በዝቅተኛ ወለድ መክፈል መቻል ነው። ኢንቨስትመንትን ለማበረታት ትልቅ እድል እንዳለውም ይገልጻሉ።
እንደ ሀገር ይህን ስምምነት ማድረጋችን እቃዎችን ለመግዛት ተጨማሪ ምንዛሪ የሚፈልጉ ነገሮች እየቀነሱ ለመሄድ ያስችላል። ስለዚህ በስምምነቱ መሠረት ተጨማሪ 817 ሚሊዮን ዶላር አገኘን ብሎ መውሰድ ይቻላል ይላሉ።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለሀብቶችም ኢትዮጵያ ውስጥ እያለሙ እንደሚገኝ በማስታወስ፤ ይህ ስምምነት ከባንኮች ጋር የሚያደርጉትን አሰራር እና የንግድ ሥርዓቱ የተሳለጠ እንዲሆንላቸው ያስችላል ሲሉ ያስረዳሉ።
ዶክተር መዚድ ኢትዮጵያ ከአረብ ኤምሬትስ 220 ሚሊዮን ዶላር አውጥታ ነዳጅ ታስገባለች፣ ስምምነቱ ሲደረግ ኢትዮጵያ በራሷ ገንዘብ የምትከፈል ይሆናል። የሕክምና እቃዎችን ጨምሮ የተለያዩ አስፈላጊ እቃዎችም እንደዛው።
በሌላ በኩል ደግሞ የአረብ ኤምሬት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ፣ በካፒታል ገበያው ለመግባት መፈለጋቸው አይቀርም። ስለዚህ የራሳቸውን ገንዘብ ይዘው ሳይመጡ በኢትዮጵያ ገንዘብ ይገበያያሉ ማለት ነው በማለት ያስረዳሉ።
ስለዚህ ይህ ስምምነት ቀጣይነት ያለው ዓይነት ስለሆነ ሊቋረጥ የሚችልበት መንገድ አይኖርም የሚሉት ባለሙያው፤ ነገር ግን የአረብ ዲፕሎማሲ የሚቀያየር ስለሆነ፤ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲ ጠንካራ አድርጎ ከመዝለቅ ረገድ የበለጠ መሰራት አለበት ይላሉ።
በሲቪል ሰርቪስ የዩኒቨርሲቲ የልማት ምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ አቶ ዘካሪያስ ሚኖታ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ሀገራት በውጭ ምንዛሪ በሚገበያዩበት ሰዓት፤ ምንዛሪው በሀገሪቱ ቁጥጥር ስር አይሆንም።
በዚህም አንድ ሀገር በገንዘብ ረገድ አቅርቦትን እና ፈላጎትን ለማጣጣም የሚነደፉ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ቁጥጥር ለማድረግ ስልጣን አይኖረውም ይላሉ።
ነገር ግን አንድ ሀገር በራሱ ምንዛሬ በሚገበያይበት ወቅት የገበያውንና የኢኮኖሚውን ሁኔታ በማጥናት፤ ፍላጎትን እና አቅርቦትን አመቻችቶ ለመሄድ ሙሉ ስልጣን ይኖረዋል በማለት ይገልጻሉ።
አቶ ዘካሪያስ እንደሚናገሩት፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሲሆን ኢትዮጵያ ከ123 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ10 እጥፍ በላይ ብልጫ አለው።
በቆዳ ስፋትም ኢትዮጵያ ከአረብ ኤምሬትስ ጋር ስትነጻጸር ትልቅ ብልጫ እንዳላት በመግለጽ፤ አረብ ኤምሬትስ ገቢ ትልቁን ገቢ የምታገኘው ነዳጅ በመላክ ነው። ግብርና ምርት በተመለከተ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ከውጭ ሀገራት ነው የምታስገባው ሲሉ ያስረዳሉ።
አረብ ኤምሬትስ ካደጉት ሀገራት ተርታ የምትሰለፍ ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ከታዳጊ ሀገራት ትመደባለች፤ በሁለቱ ሀገራት ከድህነት ወለል በታች ያለውን ሕዝብ ቁጥር ሲታይ፤ አረብ ኤምሬትስ ምንም የላትም። ኢትዮጵያ ከ30 በመቶ በላይ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች እንዳላት መረጃዎች ይገልጻሉ በማለት ያስረዳሉ።
በመሆኑ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ መመዘኛዎች አረብ ኤምሬትስ ጠንካራ የምትባል ሀገር እንደመሆኗ፤ ይህ ስምምነት መደረጉ ጠቃሚነቱ የጎላ መሆኑን ይገልጻሉ።
የሚደረገው ስምምነት ለሕዝብ ግልጽ የሆነ፣ ዓለም አቀፍ አሰራሮችን በተከተለ መልኩ፣ በፓርላማ እንዲጸድቅ ተደርጎ ከተሰራበት እና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ የሚሄድ ከሆነ ውጤታማ ስለሚሆን እነዚህን ነገሮች ባለሟላ መልኩ መሰራት አለበት ይላሉ።
ሁሉም ሀገር ለራሱ ተጠቃሚ የሚሰራ ስለሆነ ሀገራዊ የሆኑ እና ወታደራዊ ጉዳዮች አሳልፎ አለመስጠት አስፈላጊ ነው። በዛ ደረጃ ተሳትፎ የሚያደርጉ ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል በማለት አያይዘው ይገልጻሉ።
መሰል ስምምነቶች ሲደረጉ የምዕራባዊያን ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ነገር ግን አጠቃላይ እንደ አፍሪካ ሆነ እንደ ኢትዮጵያ ከምንዛሬ ጫና ለመውጣት ጠንካራ የሚባል እቅድ እየተነደፈ ከውጭ ምንዛሬ ጫና ለመውጣት መንገድ መፈለግ የሚደገፍ ነው ይላሉ።
እስካሁን በተሄደበት መንገድ ለውጥ አልታየም የሚሉት ተመራማሪው፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ ድህነት ለማስተላለፍ ምክንያት ሆኗል። የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የሚደገፍና ለአንድ ጊዜ መስዋዕትነት ከፍሎ ለትውልድ የሚጠቅም ወዳጅነት ማየቱ አስፈላጊ ነገር በማለት ይገልጻሉ።
ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት አማራጮች ሲደረጉ ብልህነት በተሞላ መልኩ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ የንግድም ሆነ፤ የኢኮኖሚ ወዳጅነት መፈጸም ይኖርበታል በማለት ምክራቸውን ያስቀምጣሉ።
በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ባለሙያ ዳዊት ተሻለ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ሁለቱ ሀገራት ቀደም ብሎ የጠበቀ የኢኮኖሚና እና የፖለቲካ ትስስር እንዳላቸው ይታወቃል። አሁን በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት መፈራረማቸው የነበረውን ግንኙነት በአንድ ርምጃ ከፍ ያደርገዋል።
የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ የገንዘብ ዘርፉን፣ ኢንቨስትመንትን እና በሁለቱ ሀገራት ያለውን የንግድ ለውውጥ እንደሚያጠናክር ያስረዳሉ።
ዶክተር ዳዊት እንዳብራሩት ፤ ከወጪ ንግድ አንጻር፤ አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ ምርት መዳረሻ ከሆኑ አስር ቀዳሚ ሀገራት አንዷ ናት። የ2015 ዓ.ም መረጃ ሲታይ ከ18 በመቶ በላይ ድርሻ ያለው ምርት ከኢትዮጵያ ወደ አረብ ኤምሬትስ ተልኳል። ይህም በገንዘብ ሲታይ ከ781 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ነው ይላሉ።
በተመሳሳይ ዓመት ኢትዮጵያ ከአረብ ኤምሬትስ ያስገባቸው ምርት ሶስት ነጥብ አራት በመቶ ነው። በገንዘብ 564 ሚሊዮን ዶላር ነው። በራስ ገንዘብ መገበያያቱ የምንዛሪ ጫና ይቀንሳል ሲሉ ያስረዳሉ።
በስምምነቱ መሠረት ከተባበሩት አረብ የምናስገባው እቃ በኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ ካስገባን፤ ከዚህ በፊት ከሀገሪቱ እቃ ለማስገባት የምናወጣውን ዶላር ለሌላ ነገር ማዋል እንችላለን ሲሉ ይናገራሉ።
መድኃኒት፣ ማዳበሪያ እና ሌሎች ሊቀሩ የማይችሉ ነገሮች ከውጭ ሀገራት በዶላር ነው የሚገባው። ስለዚህ በእንደዚህ ዓይነት ነገሮች ላይ ልናውለው እንችላለን ሲሉ ያስረዳሉ።
ባለሙያው እንደሚናገሩት፤ በሁለቱ ሀገራት በሚደረገው የንግድ ልውውጥ ኢትዮጵያ የምትልካቸው እቃዎች ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብልጫ ስላለው ምናልባት መጀመሪያ አካባቢ ለአጭር ጊዜ የዶላር እጥረት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን አረብ ኤምሬትስ አሁን ላይ የበርካታ ሀገራት ምርቶችና አገልግሎቶች መዳረሻ እየሆነች ያለች ሀገር እንደመሆኗ፤ ከሌሎች ሀገራት የሚገቡ ምርቶችን ከእነሱ በመግዛት ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል ሲሉ ያስረዳሉ።
የተባበሩት አረብ ኤምሬት ባለሀብቶች በሀገሪቱ ትላልቅ ኢንቨስትመንቶችን ይዘው እየሰሩ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ በሪል እስቴት ገበያ እንኳን ብናይ በቡልጋሪያ ማዞሪያ ወደ ቄራ በሚወስደው መንገድ እና ለገሀር አካባቢ ትላልቅ የሪል እስቴት ኢንቨስትሜንቶችን ይዘው እየሰሩ ይገኛል ሲሉ በማሳያነት ያነሳሉ።
የተባበሩት አረብ ኤምሬት አቅም ያላት እንደመሆኗ ከኢትዮጵያ ጋር የገንዘብ ለውውጥ ስምምነት ማድረጓ ሌሎች ሀገራት በተመሳሳይ መንገድ እንዲመጡ መንገድ ይከፍታል። የኢኮኖሚ እና የባንክ ሥርጭትን የተሳለጠ ያደርጋል። የቴክኖሎጂ ልውውጥንም ያሳድጋል።
ስለዚህ ስምምነቱን ውጤታማ ለማድረግ በተለይም ከኢትዮጵያ በኩል ከገንዘብ ማስተላለፍ ጋር ተያይዞ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ለማዘመን መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ።
ንግዱ መጀመሪያም መስመር ላይ ስላለ፤ የተገኘውን እድል ለመጠቀም ፈጠን ብሎ ወደ ሥራ መግባት አስፈላጊ ነው። በተጨማሪ ንግድ እንደመሆኑ አለመግባባቶች ሊፈጠሩ ስለሚችል፤ ይህን ችግር መፍታት የሚያስችሉ ደንቦችን እና አገልጋይ መድረኮችን መቅረጽ ያስፈልጋል ይላሉ።
ዶክተር ዳዊት፤ ሁለቱ ሀገራት ባደረጉት ስምምነት ከሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ እና ሌሎች ተቋማት ሊኖር ከሚችል ጫና ጋር አያይዘው ባነሱት ሃሳብ፤ ኢትዮጵያ ቀደም ብላ ብሪክስን መቀላቀሏ ይታወሳል ነገር ግን እስካሁን የደረሰባት ተጽዕኖ የለም ሲሉ አንስተዋል።
ሁለት ሀገራት ችግር ውስጥ በሚገቡበት ወቅት በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት ስምምነት መፈጸማቸው የተለመደ ነገር ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ምንም ላይፈጠር የሚችል ቢሆንም ቀስ እያሉ የሚደርሱ ተጽዕኖችን ለመቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂ መንደፍ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል የሆነችበት አንዱ ምክንያት የዶላርን ጫና ለመቀነስ ነው። ስለዚህ አሁን ከአረብ ኤምሬትስ ጋር የተደረገውን ስምምነት ከቻይና፣ ከኬንያ እና ከሌሎች ሀገራት ጋር በማድረግ እያሰፉ መሄድ ያስፈልጋል በማለት ምክራቸውን ያስቀምጣሉ።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም