ከከፍተኛ አመራሮቹ እና ከአባላቱ እንዲሁም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተገቢውን ሂደት የተከተለ አይደለም የተባለው፤ በሕወሓት ሊቀመንበር እና ምክትል በሚመሩ የድርጅቱ አባላት መካከል ክፍፍልን የፈጠረው የፓርቲው 14ኛ ጉባኤ በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የሕወሓት ጠቅላላ ጉባኤ መካሄድ መጀመሩን ተከትሎ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ድርጊቱን የሁለት ዓመቱን ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን የሚጥስ ነው የሚል ጽሑፍ በግል የፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
“ሕወሓት ደጋግሞ እንደመሸሸጊያ የሚያነሳው የፕሪቶሪያ ስምምነት የፌዴራል ተቋማትን አሠራሮች፣ ሕጎች እና አካሄዶችን በጥብቅ ሊያከብር ግዴታ ጥሎበታል” በማለት የገባውን ግዴታ በተጨባጭ “ደምስሶታል” ሲሉ ከሰዋል።
ድርጊቱ ከጦርነቱ መቆም በኋላ የትግራይ ሕዝብ ያገኘውን “አንጻራዊ ሰላም እንደመንጠቅ ይቆጠራል” ያሉት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ ሕወሓት ተመሳሳይ እና ተደጋጋሚ ስህተት በመፈጸም ወደ ጥፋት እያመራ ነው በማለት “ለዚህ ደግሞ ብቸኛው ተጠያቂ እራሱ ሕወሓት ይሆናል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ፤ ሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ ከማድረጉ ከ21 ቀን በፊት ለቦርዱ ማሳወቅና ፓርቲው በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባዔ የቦርዱ ታዛቢዎች መገኘት እንደሚኖርባቸው አመልክቷል። ይህን ሳያደርግ የሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ሕገ ወጥ እንደሆነ አብራርቷል። ሕጋዊ እውቅናም እንደማይኖረው አሳውቋል።
ጠቅላላ ጉባዔው ከቦርዱ ፍቃድ ውጭ ከተካሄደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዚህ ጉባዔም ሆነ በጉባዔዎቹ ላይ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ ዕውቅና የማይሰጥ መሆኑንም ገልጿል።
ይህን የሕወሓት ድርጊትንም ምክትል ሊቀመንበሩ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሜቴ አባላት ተቃውመውታል። ሌሎች የተለያዩ አካላትም ድርጊቱ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ መሆኑን እየገለጹ ነው።
እንደሚታወቀው፤ ለሁለት ዓመታት ያህል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 በፕሪቶሪያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን እና ብሔራዊ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ዕልባት ማግኘቱ ይታወሳል ።
የተደረሰው ስምምነት ከሁሉም በላይ፤ ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም፣ ዕርዳታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማስጀመርና የሀገሪቱን የድንበርና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲከበር የማድረግ አላማ ያዘለ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት እንዲሁም ይህንን ተከትሎ በኬንያ ናይሮቢ የተፈረመው ባለ 12 ነጥብ የማስፈጸሚያ ሰነድ የሚከተሉትን መሠረታዊ ነጥቦች የያዘ ነው።
የመጀመሪያው ጉዳይ ሕግ መንግሥታዊ ሥርዓትን መስከበር ነው። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሚመነጭ ነው። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነጻና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲካሄድ የማድረግ ስልጣን ያለው የምርጫ ቦርድ እንደሆነ በግልጽ ተደንግጓል።
ሕወሓት ቀደም ሲል፤ ከዚህ ድንጋጌ በተቃረነ መልኩ በትግራይ ክልል ‹‹ምርጫ ›› ተካሂዷል በሚል የትግራይ መንግሥት መቋቋሙን ለማወጅ መሞከሩ የሚታወስ ነው። በወቅቱም የፌዴራል መንግሥት በትግራይ የተካሄደውን ‹‹ምርጫ›› እንዳልተካሄደ የሚቆጠር መሆኑን በመግለጽ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቆ ነበር።
ይህንኑ ሃሳብ የሚያጸና ውሳኔ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደው ስምምነትም ስፍሮ እናገኘዋለን። ምርጫው ሕገ ወጥ በመሆኑም በትግራይ የሽግግር መንግሥት ይቋቋማል፤ በሂደትም ምርጫ ተካሂዶ ክልሉን የሚያስተዳድር መንግሥት እንደሚሰይም ያመለክታል። ይህም ስምምነቱን ተከትሎ ተግባራዊ ሆኗል። በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተሰይሞ እየተንቀሳቀሰ ነው።
ሌላኛው የፕሪቶሪያው ስምምነት በግልጽ የተቀመጠው። በአንድ ሀገር ውስጥ አንድ መከላከያ ሠራዊት ብቻ መኖር አለበት የሚለው ነጥብ ነው። በስምምነቱ ላይ ዋነኛ ጉዳይ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ ነው። በፕሪቶሪያው ስምምነትም ሆነ በናይሮቢው የማስፈጸሚያ ሰነድ መሠረት ስምምነቱን ወደ ተግባር ከመለወጥ ውጭ ሊቀመጥ የሚገባ ቅድመ ሁኔታ አይኖርም።
በፕሪቶሪያው ስምምነት የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ከተስማሙባቸው ጉዳዮች ሌላው፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን የማስጠበቅ ስልጣን የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ መሆኑ ነው። በተለይም ከውጭው ዓለም ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችና ስምምነቶች ሁሉ ሊከናወኑ የሚችሉት በፌዴራል መንግሥት ብቻ መሆኑ ነው። ይህው ሃሳብ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 51 ንኡስ አንቀጽ 8 ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል።
በአጠቃላይ የፕሪቶሪያው ስምምነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚያጸናና የዜጎችን ሰቆቃ የሚቀርፍ ስምምነት በመሆኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚተገበር ነው። ስምምነቱ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ከማጽናቱም ባሻገር በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ የነበሩትን የትግራይ፤ የአማራና የአፋር ሕዝቦችን እፎይታ አጎናጽፏል።
በስምምነቱ የተገኘውን ሰላም መጠበቅና መንከባከብ ካልተቻለ መልሶ በጦርነት አዙሪት ውስጥ የመግባት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ዘመናትን በጦርነት ውስጥ ለቆየ ሀገር ዘላቂ የሆነ የጦርነት ማስወገጃ ስልት መንደፍ ከመንግሥት የሚጠበቅ ቢሆንም ዋነኛው የሰላሙ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን የተገኘውን ሰላም ጠብቆ የማቆየት ግዴታ አለበት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በየዘመናቱ በሚነሱ ጦርነቶችና ግጭቶች ሰለባ ሲሆን የቆየ ነው። ሕዝቡ ከእንግዲህ ወዲህ ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ባሻገር ጦርነት ጊዜው ያለፈበት አማራጭ መሆኑን ማመላከት አለበት፤ አሻፈርኝ የሚሉትንም አንቅሮ ሊተፋቸው ይገባል።
በሕዝብ ተቀባይነት የሌለው አካል ያለመውን እኩይ ሃሳብ ማስፈጸም አይችልምና የጦርነትና የግጭት እሳቤ ያላቸው አካላት ከእንግዲህ ወዲህ በኢትዮጵያ ምድር ስፍራ ሊኖራቸው አይገባም።
ዛሬም ከጦርነት አባዜ የለውጡ ግለሰቦች እና አልፍ ሲልም ቡድኖች በረባ ባልረባው ወደ ጦርነት እና ግጭት የሚገፋፉ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ይታያሉ። ከሰሞኑ በሕወሓት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች ያደረጉትም ይህንኑ ነው።
እነዚህ ግለሰቦች ከሕገ መንግሥቱና ከፕሪቶሪያው ድንጋጌ ውጭ የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል። ምርጫ ቦርድ ያልፈቀደውን ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተው ፤ ጉባኤ እያካሄዱ ነው። ይህ ደግሞ መልሶ ወደ አለመግባባት እና ግጭት የሚወስድ የጥፋት መንገድ ነው።
በርግጥ የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ነፃነት መስዋዕትነት የከፈለ ኩሩ ሕዝብ ነው። በየዘመናቱ የመጡ ወራሪዎችን አሳፍሮ ሲመልስ የቆየና ለሀገሩ ነፃነትና ሉዓላዊነት ሲዋደቅ የኖረ ነው። ያለ ትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያን ማሰበ አይቻልም፤ ኢትዮጵያም ሆነ ኢትዮጵያዊነት ሙሉ አይሆኑም።
የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ፍላጎት ከተቀረው ወገኑ ጋር በሰላም፤ በእኩልነትና በፍትሃዊነት መኖር ነው። የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው። የትግራይ ሕዝብ ምኞት ኃላቀርነትና ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ ነው።
የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ምኞት ንጹህ የመጠጥ ውሃ፤ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፤ መንገድና መሰል የመሠረተ ልማቶች መስፋፋት ነው። ከእነዚህ መሠረታዊ ፍላጎቱ በተቃራኒ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ሕዝቡን ለሰቆቃ ከመዳረግ ውጭ ያመጡት ፋይዳ እንደሌለ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
መንግሥት የሕዝቡን ፍላጎት /ምኞቱ እውን እንዲሆን የፕሪቶሪውን ስምምነት በግንባር ቀደምነት ከመፈረም ጀምሮ፤ በጦርነቱ በእጅጉ የተጎዳውን የትግራይ ሕዝብ መልሶ ለማቋቋምና ጦርነቱ ያሳረፈበትን ሥነ ልቦና ለማከም በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የጥላቻውን ጉም በመግፈፍ ወደ ትግራይ በግንባር ቀደምትነት የተጓዘው በአፈ ጉባዔው የተመራው የፌዴራል መንግሥቱ ልዑክ ነበር። ይህ ልዑክ ከተጓዘ በኋላ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክና የአውሮፕላን አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀምሩ ተደርገዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት እንዲያዞር ተደርጓል።
የግብርና ሥራውን ለማገዝ የሚመለከተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በክልል ደረጃ ከሚጠበቅበት በላይ ሠርቷል። ዩኒቨርሲቲዎችንና ትምህርት ቤቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የትምህርት ሚኒስቴር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።
በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት እንዲጀመር ከማድረግ ባሻገር ከሁለት ዓመታት በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል።
የሰላም ስምምነቱን እንደ ዕድል በመጠቀም ሕዝብን ከችግር በማዳን፣ መንግሥታዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስመጀር ኃላፊነቱን ተወጥቷል። ከፌዴራል መንግሥቱም አልፎ ክልሎች ከአነስተኛ በጀታቸውና ገቢያቸው በመቀነስ የትግራይ ክልልን ደግፈዋል።
ይህም ሆኖ ግን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሆነ ከመንግሥት በኩል የተደረገውን ያህል የሚመጥን ምላሽ ከሕወሓት በኩል አልተገኘም። በሰበብ አስባቡ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጋፉ ድርጊቶችና አሉታዊ ሃሳቦች ጭምር በየጊዜው ሲደመጡና ሲታዩ ሁለት ዓመታት አልፈዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት የሰላም ስምምነቱን የፈረሙ አካላት ከአሉታዊ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲታቀቡ የሚያስገድዳቸው ቢሆንም ከመንግሥት ውጭ ያሉት አካላት ስምምነቱን የሚጥሱ ድርጊቶችና ሃሳቦችን ሲያንጻበርቁ ታይተዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ከማጽናቱም ባሻገር በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ የነበሩትን የትግራይ፤ የአማራና የአፋር ሕዝቦችን እፎይታ ያጎናጸፈ ነው።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት ቀጥሎ የተካሄደው የናይሮቢ ስምምነት መተማመንን የፈጠረና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም መንገድ የሚያጸና ነው። በተለይም በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችንና ሰብዓዊ ድጋፎችን በሚፈለገው መልኩ ለማድረስ መሠረት የጣለ ነው።
በዚሁ መሠረትም በትግራይ፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተቋርጠው የነበሩ የቴሌኮሙኒኬሽን፤ የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎቶች መልሰው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ለማድረግ አስችሏል።
ለሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መሠረት የሆነውና የዜጎች ሰቆቃ እንዲበቃ ያደረገው የፕሪቶሪያው ስምምነት ቅድመ ሁኔታ የለውም፤ በስምምነቱ መሠረት የሚጠበቀውን መፈጸም ከሁሉም ወገን የሚጠበቅ ነው።
ሰሞኑን እንደታየው በሕወሓት ውስጥ ያሉ አንዳንድ አካላት በተደጋጋሚ ስምምነቱን የሚጥሱ ተግባራትን በግልጽም በስውርም ሲያደርጉ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር የሰፈነውን የሰላም አየር የሚበርዝና ዳግም ወደ ጥፋት የሚወስድ በመሆኑ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል። ከጥፋት መንገድ ማንም አትራፊ እንደማይሆን ከትናንት ስህተታቸው ሊማሩም ይገባል።
አሊሴሮ
አዲስ ዘመን ኞ ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም