በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አምስት ሚሊዮን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ አስጀምረዋል። በወቅቱም ፤ ኢንሼቲቩ ሰልጣኞችን ዘመኑን በዋጀው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል። የኢትዮጵያ የነገ ተስፋዎች የሆኑ ወጣቶችም ሥልጠናውን በጥሞና በመከታተል ሥራ ፈጣሪ፣ ኩባንያ ፈጣሪና በዓለም ገበያ ተወዳድረው የሚቀጠሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም ይህንን ትልቅ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ክህሎት በዲጂታል የታገዘ ማህበረሰብ ለማፍራት፣ አዳዲስ የሥራ እድሎችን ለመፍጠርና ለመሰማራት ወሳኝ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል። ነገር ግን ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በኢኮኖሚ ተመሳሳይ የእድገት ደረጃ ላይ ካሉ ሀገራት ጋር ጭምር ስትወዳደር ወደ ኋላ ቀርታለች። በአንጻሩ ሁሉም ነገር ሊባል በሚያስደፍር ደረጃ በየቀኑ ከቴክኖሎጂ ጋር እየተቆራኘ ይገኛል። ትምህርት፤ ግብርና፤ ኢንዱስትሪ፤ የአስተዳደር ሥራ፤ ፈጠራ ወዘተ ሁሉም ነገር የኢኮኖሚ ክህሎትና ብቃት የሚጠይቅ ሆኗል።
ብዙ መሥራት ብዙ መሆን የሚጠበቅበት አዲሱ ትውልድ ተገቢው የዲጂታል ክህሎት ከሌለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን ካለመቻሉ ባሻገር እንደ ሀገርም ተወዳዳሪነትን የሚጎዳ መሆኑ ግልጽ ነው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ያለባትን ክፍተት ለመሙላት የመሠረታዊ ኮሞፒውተር እውቀትና ሁለንተናዊ የዲጂታል ክህሎት መርሃ ግብር በመንግሥት ተዘጋጅቶ ለወጣቶች ተደራሽ እንዲሆን አየተሠራ ያለው።
አምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ” ፕሮግራም በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግሥታት መካከል በተደረገ ስምምነት የተነደፈ የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና መርሃ ግብር ነው። የመርሃ ግብሩ ዓላማ ወጣቱ ትውልድ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ የሚያስችለውን የዲጂታል ክህሎት እንዲኖረው ማስቻል ነው። ወጣቶቹ በመርሃ ግብሩ በመሳተፍ በግላቸው የሚያገኙት ጥቅም እንዳለ ሆኖ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት እና ተወዳዳሪነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ምንም ጥርጥር የለውም።
ፕሮግራሙ አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ለመድረስ ያለመ እንደመሆኑ የፕሮግራሙ ስኬት በሀገራችን የዲጂታላይዜሽን ሂደት ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚፈጥርም ግልጽ ነው። እዚህ ላይ ደስ የሚያሰኘው ነገር ይህ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መርሃ ግብር የሚተገበረው በመላው ሀገሪቱ መሆኑ ነው። ይህ አካሄድ ከተሞች ብቻ የመሠረተ ልማትና የቴክኖሎጂ ማእከል ሆነው እንዳይቀጥሉ በር የሚከፍትም ይሆናል። ይህንን ተከትሎ የሚኖረው የእውቀት ሽግግር በስፋትም በተደራሽነትም አድማሱን ማስፋቱ አይቀርም።
ዛሬ፣ ቴክኖሎጂ የሥራ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የለውጥ አራማጅ የሆነበት አዲስ የዘመን ምዕራፍ ላይ ተደርሷል። እንደማንኛውም ሀገር የሀገራችን የወደ ፊት እጣ ፈንታም የሚወሰነው በሀገር ተረካቢ ወጣቶች እጅ እንደሚሆንም ይታወቃል። የነገዋን ኢትዮጵያ የሚቀርፁት የፈጠራ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች እነዚህ ወጣቶች ናቸው። በመሆኑም የኢትዮ ኮደርስ ፕሮግራም ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በዲጂታል ሥነ ምህዳሩ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችላቸውን ክህሎትና እውቀት በማስታጠቅ አዳዲስ እድሎች እንዲፈጠርላቸው ያስቻላል። ይህም ሀገራችን በቴክኖሎጂው መስክ ወደፊት እንድትገሰግስ በር የሚከፍት ነው። ባጠቃለይም የኢትዮ ኮደርስ ፕሮግራም መንግሥት ወጣቶችን ለማብቃት፣ ፈጠራን ለማጎልበት እና የዲጂታል ዘመንን ግዙፍ አቅም ለመጠቀም እንደ ሀገር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
መርሃ ግብሩ ለሁሉም ተደራሽ የሆኑ የኦንላይን ኮርሶችንና ሌሎች ደጋፊ የሆኑ አገልግሎቶችን በማቅረብ በሶስት ዓመታት ውስጥ አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወጣቶቻችን በመሠረታዊ የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስና አንድሮይድ አፕሊኬሽን ልማት መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎትን በማስታጠቅ ሥራ እንዲፈጥሩ፣ ሀብት እንዲፈጥሩ፣ የሀገራችንን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርም ትርጉም ባለው መልኩ ወደፊት ለማሳለጥ ግብ ያደረገ ኢኒሼቲቭ እንደሆነ ተገልጾልናል።
ወጣቶች የኮዲንግ ክህሎት እንዲኖራቸው ሲደረግም የተቀመጡ መዳረሻዎች አሉ። እነሱም ሠልጣኞቹ ሰፊ ወደ ሆነው የዲጂታል ዓለም በልበ ሙሉነት እንዲቀላቀሉና ሌሎች የፈጠሩዋቸውን አፕሊኪሽኖች ለመጠቀም ብቃት እንዲኖራቸው ለማድረግ። በተጨማሪ ሀገርን የሚጠቅሙ፣ ሥራን የሚፈጥሩ እና የሰውን ሕይወት የሚያቀሉ በርካታ አፕሊኪሽኖችን በራሳቸው ማልማት እንዲችሉ ማብቃት ነው።
በአጠቃላይም ኢትዮኮደርስ ፕሮግራምን ለመተግበር የሚፈጠረው አደረጃጀትና አሠራር ከአንድ ፕሮግራም በዘለለ በጋራ ፈጠራን የሚያዳብር። ሥራ ፈጣሪነትን የሚደግፍና ወጣቶቻችን ለሀገራቸው ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አንቀሳቃሽ ኃይል እንዲሆኑ የሚያስችል የላቀ ሥነ-ምህዳር ለመገንባት ልዩ አጋጣሚ የሚፈጥር ይሆናል።
የዲጂታል ክህሎት ማለት የቴክኖሎጂ እቅውቀትን መቅሰም ብቻም አይደለም፣ ቴክኖሎጂን ማወቅና መጠቀምን ያቃልላል። አንድ ሰው የዲጂታል ክህሎት አለው የሚባለው ከቴክኖሎጂው ባሻገር በአስተሳሰብም ለዲጂታል ዘመን ብቁ ሆኖ ሲገኝ ነው። የዲጂታል ዘመን አስተሳሰቦች ትብብርና ትስስር የመፍጠር አቅም፤ ማስላትና ማሰላሰል፣ ፈልጎ ማግኘትና ማካፈል፣ ሁሌም ለመማርና ለመለወጥ መዘጋጀት የመሳሰሉ ህሊናዊ ሁኔታዎችን ያካትታሉ። በመሆኑም ወጣቶች ከቴክኖሎጂው እውቀት በተጨማሪ እነዚህ ህሊናዊና ባህርያዊ የሆኑ የዲጂታል ዘመን አስተሳሰቦችን ለመላበስ ራሳቸውን ዝግጁ ሊያደርጉ ይገባል።
በእርግጥ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ያለው የዲጂታል መሣሪያዎች ተደራሽነት ውስን መሆኑ የሥልጠናውን ተደራሽነት ሊፈታተነውም እንደሚችል ይገመታል። ከዚህም በተጨማሪ የወጣቶችን ተሳትፎ ዘላቂነት ማረጋገጥ ሌላው ፈተና ይሆናል። ምን አልባትም ሥልጠናውን ጀምረው የሚያቋርጡ በርካታ ወጣቶች ሊኖሩ ይችላሉ ተብሎ ስለሚታሰብ። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመመከትና የፕሮግራሙን ስኬት ለማረጋጋጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ ግልጽ ይመስለኛል።
የፕሮጀክቱ ተግበራ በዋናነት በፌዴራል ባለድርሻ አካላትና በክልሎች እንደሚሆን ተደጋግሞ ተገልጿል። በፌዴራልም ሆነ በክልል ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች፣ የግሉ ዘርፍ ፣ የልማት አጋሮች ፣ ሲቪል ማህበራት ፣ ወላጆችና ማህበረሰቡ በአጠቃላይ በጋራ ሊፈጽሙት የሚገባ ሀገራዊ ተልዕኮ ነው። በተጨማሪ በሀገሪቱ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸው ኮርሱን እንዲውስዱ ከማድረግ ባለፈ በየአካባቢያቸው ያሉ ወጣቶች የእድሉ ተቃሚ እንዲሆኑ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተጠቁሟል።
እንግዲህ ይህ የብዙዎችን ተሳትፎ የሚጠየቅ ሀገራዊ ተልእኮ በየትኛውም አካል መዳከም ምክንያት ሳይሳካ ቢቀር ጉዳቱ እንደ ሀገር የሁላችንም እንደሚሆን ይታወቃል። በመሠረቱ እነዚህን ሥልጠናዎች በግለሰብም ሆነ በመንግሥት ደረጃ ይመቻቹ ቢባል ይወጣ የነበረው ገንዘብ ከፍተኛ ነው። በዛ ለይ ብሩ እንኳን ቢገኝ ክፍያው በዶላር መሆኑ በራሱ ካለን የውጪ ምንዛሬ እጥረት አኳያ እንደ ቀልድ የሚታለፍ አይሆንም። የሥልጠናዎቹ ይዘቶች የሚቀርቡት ዓለም አቀፍ የዲጂታል ክህሎትን በኦንላይን በማስተማር ስመጥር ከሆነው ከ «ዩዳሲቲ ፕላትፎርም» ጋር በመተባበር ነው። ፕላትፎርሙ የተለያዩ የፕሮግራሚንግ የዌብ ልማትንና ሌሎች በፍላጎት ላይ የተመሠረቱ የኮዲንግ ሥልጠናዎችን ያካተተም ነው።
አምስት ሚሊዮን የሚለው ቁጥር ከኢትዮጵያ ወጣቶች ብዛት አንጻር ሲታይ ትንሽ ሊመስል ይችላል። በዚህ ረገድ ከሠለጠነው እና እውቀት ካለው ወጣት እንዲሁም ከምንጠብቀው ለውጥ አኳያ ሲመዘን እጅግ በጣም ብዙ ነው። ሥልጠናው በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊተገበር ከመታቀዱ ባለፈ ከመሠረታዊ የኮምፒውተር እውቀት ውጪ የሚጠይቀው መስፈርት አለመኖሩ በራሱ ተደራሽነቱን ፍትሀዊ የሚያደርገው ነው።
እንግዲህ ጥያቄውም አደራውም የሚነሳው እዚህ ጋር ይመስለኛል። ከላይ የዘረዘርናቸው በተለይም ከከተሞች ውጪ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ይህ የበሰለ ምግብ እንዳይበላሽ ትልቅ ሃላፊነትም አደራም አለባቸው። ጉዳዩ ከአንድ ወቅት ተነሳሽነትና ፉከራ የዘለለ ሊሆን ይገባል ። በጥቅሉ እንደ ሀገር የዛሬ ሶስት ዓመት በዲጅታል ክህሎት ሠልጠነው የተመረቁ ፤ የበቁ ወጣቶችን እንጠብቃለንና ለውጤታማነቱ ባለአደራዎችን አደራ ለማለት እወዳለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም