የሀገራችንን ስፖርት የገጠመው አንዱ ተግዳሮት የአሠራር ብልሽትና የሕዝባዊ አደረጃጀቱ የአመራር ችግር ነው። የስፖርት ማኅበራት ተጠቅልለው በተወሰኑ ግለሰቦች ቁጥጥር ስር ገብተዋል። እነዚህ ግለሰቦች ሲተነፍሱ አብረው የሚተነፍሱ እነሱ ሲያቆሙ ደግሞ እስትንፋሳቸው አብሮ የሚያቆም ሆኗል። እነዚህ ግለሰቦች ደግሞ ክፋታቸው ብዙ ጊዜ የሚተነፍሱ አይደሉም።
በዚህም ምክንያት እ.ኤ.አ በ2016 ከተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ ጀምሮ ሲያነክስ የመጣው የአትሌቲክስ ስፖርት ተንገራግጮ ሊቆም ግድ ብሎታል። በብልሹ አሠራርና በግለሰቦች የአመራር ችግር እግር ተወርች በመታሰሩ ከዚህ በላይ ሊንቀሳቀስ አልተቻለውም። በተወሰኑ አትሌቶችና አሠልጣኞች የግል ጥረት ሲወዛወዝ ቢቆይም የፓሪስ ኦሊምፒክን መሻገር ተስኖታል።
ሕግን የማይከተሉና የግለሰቦችን ጥቅም ብቻ ለማስከበር የሚነደፉ አሠራሮች ስፖርቱን አቀጭጨው እንዲዳከም አደረጉት። ከምንም በላይ ደግሞ ለጭቅጭቅና ለርስ በርስ አለመግባባት መንስኤ በመሆናቸው የስፖርቱን ገፅታ አበላሹት። ኦሊምፒክ የሠላም፣ የፍቅርና የአንድነት መድረክ መሆኑ ቀርቶ የንትርክና የመጠላላት ዋና መገለጫ እንዲሆን አስገደዱት።
የስፖርቱ የበላይ አመራር ነን የሚሉ ግለሰቦች የሥልጣን ጥማቸውን ለማርካት ሲሉ ብቻ ሕግ ቀየሩ ወይም አሻሻሉ። በሚያስደንቅ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤ ተብየውም በዝግ ተሰብስቦ ‹‹ጌቶች ሆይ ሕጋችሁን አፅድቄያለሁ›› የሚል አስገራሚ ምላሽ ሰጠ። ከዚህም በመነሳት ብዙ ዓለም አቀፍና የሀገራችንን ሕጎች ጥሶ የሥልጣን ጊዜያቸውን መርቆ ለሌላ የሥልጣን ዘመን አራዝሜያለሁ አለ። በምትኩም በአይነት፣ በገንዘብ እንዲሁም ኤፍል ታወር (Eiffel Tower) በሚደርስ የፓሪስ ሽርሽር ሽልማት ተበረከተለት። ምን አልባት በታሪክ የአንድ ተቋም (የኦሊምፒክ ኮሚቴ) ጠቅላላ ጉባኤ እና የፌዴሬሽን (የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን) የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የኦሊምፒክ ልዑክ ሆኖ ሲሄድ የመጀመሪያ ሳይሆን አይቀርም። ሪከርድ ሆኖ መመዝገብም ይኖርበታል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤን ለምን እንደዘነጉትና በልዑኩ ውስጥ ሳያካትቱት እንደቀሩ ግን እስካሁን አልገባኝም። ለነገሩ በተለያየ መንገድ አብዛኛው ተካቷል መሰለኝ።
ከዚህ ባለፈ ከጠቅላላ ጉባኤው በተረፈው ቦታ ላይ እንኳን በኦሊምፒክ የሚሳተፉ አካላት የሚለዩበት ግልፅ መስፈርት እና አሠራር አልተቀመጠም። ወደ ቦታው ሲሄዱ የሚሠሩት ሥራ ግምት ውስጥ ሳይገባ ለአመራሩ ቅርብና ባለውለታ የሆኑ ግለሰቦች ከዚህም አለፍ ሲል ዘመድ አዝማድ የሆኑት ብቻ ከያሉበት ተጠራርተው ጉዞ ወደ ፓሪስ አደረጉ። በሕዝብ ሀብት እንደዚህ ተቀለደ።
አሠራሩ ሁሉ ከጅምሩ አንስቶ እስከ መጨረሻው በብልሽት ታጀበ። ይህም በስፖርተኛው፣ በስፖርቱ ማኅበረሰብና በኢትዮጵያውያን ላይ ዳር እስከ ዳር ብስጭትን ቀሰቀሰ። የሁሉም ዓይን ወደ ፓሪስ እንዲሆን አደረገ።
የስፖርተኛው እንዲሁም ወደ ፓሪስ የሚሄደው ሚዲያና ጋዜጠኛ ምርጫም በተመሳሳይ መልኩ ሕግንና አሠራርን ያልተከተለና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የተከናወነ ባለመሆኑ ቅድመ ዝግጅቱንም ይሁን ውድድሩን እጅጉን አወከው። የዚህ ውጤትም ተወዳድሮ ከማሸነፍ ይልቅ መተራመስ ሆነ።
ከፓሪስ ቅድመ ዝግጅትና ውድድርም ባለፈ በተቋማቱ ያለው አሠራር እጅጉን ደካማ እንደሆነ ከብዙዎች ይደመጣል። አሳታፊ ያልሆነና የግለሰቦች አምባገነንነት ጎልቶ የሚንፀባረቅበት እንደሆነ በስፋት ይነሳል። ትልልቅ ጉዳዮች ሳይቀሩ በግል ይወሰናሉ፤ ይፈፀማሉ። ይህም ተጠያቂነት እንዳይኖርና ግለሰቦች እንደፈለጉ እንዲፈነጩ ዕድል ሰጥቷቸዋል። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤትም በከበርንበት የኦሊምፒክ መድረክ አንገት መድፋት ሆኗል።
ሕዝባዊ የስፖርት ተቋማት ሀብት የሚያስተዳድሩበት፣ ዓለም አቀፍ ውድድር የሚመሩበት፣ አትሌት የሚመለምሉበት፣ የሰው ኃይላቸውን የሚያስተዳድሩበት፣ ጠቅላላ ጉባኤ የሚመሩበት ውስጣዊና ውጫዊ የአሠራር ሥርዓት የሌላቸው እንዲሁም ያለውንም የመተግበር ሞራል ያጡ በመሆናቸው መጨረሻው የሀገር ውጤት ውድቀት ሆነ። በመልካም አስተዳደር ችግር ስፖርቱን ከላይ እስከታች ናጡት። በታላቁ የኦሊምፒክ አደባባይ የሀገር ውጤት በማሳጣት የስፖርቱንም ገፅታ ክፉኛ ጎዱት። ሕዝባችንንም አሳዘኑ።
ከዳዴ አልወጣ ያለውና ሁልጊዜ ጨቅላ የሚሆነው የስፖርት ሕዝባዊ አደረጃጀት (የስፖርት ማኅበር) ከሌሎች ክፍተቶቻችን ጋር ተዳምሮ ለዓለም አቀፍ ውጤታችን መዳከምና ለስፖርቱ መቀጨጭ ትልቁ መንስኤ ሆነ።
የሀገራችን ስፖርት ፖሊሲ ስፖርቱ ሕዝባዊ እንዲሆንና ቀስ በቀስ ራሱን መቻል እንደሚጠበቅበት ግልፅ አቅጣጫ ያስቀምጣል። ይህም ማለት ስፖርቱን በሀገራችን በማስፋፋት ኅብረተሰቡ በብዛት እንዲያዘወትረው ማስቻልንና እገረ መንገዱን ደግሞ በተለያየ መንገድ (በክለብ፣ በኮሚቴ፣ በማኅበር ወይም ከዚያ ከፍ ባለ ደረጃ) ተደራጅቶ እንዲመራው እንዲሁም ስፖርቱን ማስተዳደር የሚያስችለውን ሃብት እንዲያመነጭ ማድረግን የሚመለከት ፅንሰ ኃሳብ ነው። በውጤቱም ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ዜጎቿ እንደ ሌላው ዓለም ሁሉ ከኢንዱስትሪው ማግኘት የሚጠበቅባቸውን የጤና፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ማረጋገጥ እና በዓለም አቀፍ መድረክ ወጤት ማስመዝገብን ይመለከታል።
ይህን የፖሊሲ አቅጣጫ መሠረት በማድረግ ላለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት (26 ዓመታት) ዘርፈ-ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማስመዝገብ አልተቻለም። በተቃራኒው የፖሊሲው ፅንሰ ኃሳብ እየተዛባ መጥቶ በስመ ማኅበር የተወሰኑ ግለሰቦች ሀብት ወደመሆን የተሸጋገሩና ምንም የተቋምነት ይዘትና ቅርፅ የሌላቸውን የስፖርት ድርጅቶች መፍጠር ላይ ሊወሰን ግድ ብሎታል።
በዚህ ሂደትም የስፖርቱ ሕዝባዊነት እየቀጨጨ መጥቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፌዴሬሽን ወይም የኮሚቴ ስያሜን የያዙ ነገር ግን የአንድ ወይም ሁለት ግለሰቦች አዛዥ ናዛዥነት ጎልቶ የሚስተዋልባቸውን ደካማ ድርጅቶች እውን ማድረግ የመጨረሻ ውጤቱ ሆነ። እነዚህ የስፖርት ድርጅቶችም (ተቋም ያላልኩት ሳይንሳዊ መስፈርቱን ስለማያሟሉ ነው) በፍጥነት የውስን ግለሰቦች የግል ሀብት (Property) ወደ መሆን ተሸጋገሩ።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ አብዛኞቹ የታወቀ ተቋማዊ መዋቅር (Organizational Structure) ቀርፀው በግልፅ ማስታወቂያ የሰው ኃይል ቅጥርና ስምሪት ሲያከናውኑ አይታይም። ይህም ተቋማቱ በይፋ ኅብረተሰቡ የሚያውቀው ውስጣዊ አደረጃጀት የላቸውም አልያም ደግሞ በውስጥ ለውስጥ የዘመድ አዝማድ መሰባሰቢያ ሆነዋል የሚለው አንድምታ ላይ ያደርሳል።
ይህ ተቋማዊ አደረጃጀት ሠንሠለቱን ጠብቆ ከፌዴራል ወደ ክልል ከዚያም ወደ ክለብ እና ሌሎች መሰል መዋቅሮች እንዲወርድ ይጠበቃል። ነገር ግን በተሟላ መንገድ ሊሳካ አልቻለም። በሚያስገርም ሁኔታ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የክልል መንግሥታትን የስፖርት መዋቅር “የእኔ ቅርንጫፎች” የሚል ስያሜ ሲሰጣቸው ይስተዋላል። ይህ ፍፁም ስህተት ነው። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አፈጣጠር ከሀገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ስብስብ ብቻ እንደሚሆን ልብ ሊባል ይገባል።
በተመሳሳይ መልኩ ከተቋማዊ አደረጃጀት ባለፈ ከዓመት እስከ ዓመት አስፈላጊውን የስፖርት ልማታዊ እንቅስቃሴ መከወንም ይሁን ሥራ መሥራት የሚያስችል የሰው ኃይል የላቸውም። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን በምሳሌነት ወስደን ብንመለከት በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ቁጥራቸው 40 እንኳን የማይደርሱ ስፖርተኞችን በርከት ካሉ አጃቢዎች (የአመራሩ ቅርብ ሰዎች) ጋር ወደ ኦሊምፒክ መንደር ማድረስ ላይ ተወስኗል። ከዓመት እስከ ዓመት መሠራት የሚገባቸው የስፖርት ልማት እንቅስቃሴዎች እና የኦሊምፒክ ሶሊዳሪቲ ፕሮግራሞች በር ከተዘጋባቸው ሰነባብተዋል።
የስፖርት ድርጅቶቹ በየእርከኑ የመንግሥትን እጅ ከመመልከት ባለፈ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ተጨማሪ ሀብት የማመንጨት እና ራሳቸውን ችለው የመንቀሳቀስ ሞራላቸው ተሰልቧል። በዚህም ምክንያት ከዓመት ዓመት በራቸውን ዘግተው የሚከርሙ ሆነዋል።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ “ነፃ ነን” የሚለውን መፈክር ከፍ አድርገው ሲያዜሙት ይደመጣሉ። ብናጠፋ እንኳን መንግሥት ሊጠይቀን አይቻለውም የሚል አቋም እንዳላቸው በአደባባይ የመናገር ድፍረት ላይም ደርሰዋል። ከዚህም ባስ ባለ መንገድ እነሱ የሚሰፍሩለትና በቁጥጥራቸው ስር ያደረጉት አካል ካልሆነ በስተቀር ሕዝብም ቢሆን ሊጠይቀኝ አይቻለውም የሚል አመራርም እንደተፈጠረ የፓሪስ ኦሊምፒክ አሳይቶናል።
ጠቅለል አድርገን ስንመለከት በእነዚህ የስፖርት ድርጅቶች ውስጥ ተቋም የሚያስመስልና ሥራ መሥራት የሚያስችል ውስጣዊ አደረጃጀት፣ የሰው ኃይል፣ የፋይናንስም ይሁን ቁሳዊ ሀብት የለም። አንዳንዶቹ የነበረውንም አፍርሰው ያለ ሙያተኛ ስሙን ብቻ ይዘው ባዶ ቀርተዋል። ስለሆነም በዚህ ቁመናቸው ሕዝቡ የሚፈልገውን የስፖርት ልማትም ይሁን ሀገራዊ ውጤት ማረጋገጥ አይቻላቸውም። ለዚህም ነው መፍትሔው ስርነቀል ለውጥ የሚሆነው።
በድምሩ ስንመለከተው ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሊምፒክ ከወርቅ የራቀችው የስፖርት ተቋማት ብቃት የሌላቸው (Inefficient) እየሆኑ በመምጣታቸው፣ የስፖርቱ የአሠራር ሥርዓት (System) በየደረጃው በብልሹ አሠራር በመዋጡና Corrupted በመሆኑ፣ የስፖርተኛው ምልመላና ሥልጠና እጅግ በጣም ኋላ ቀር በመሆኑ፣ ስፖርቱ የእርስ በእርስ መበቃቀያና የብሽሽቅ ሜዳ እየሆነ በመምጣቱ፣ ስፖርቱ የተወሰኑ ግለሰቦች በማን አለብኝነት ብቻ የሚዘውሩት የግል ሀብት (Individual Property) ወደ መሆን በመሸጋገሩ፣ በአመራር (Leadership) ችግር….ወዘተ ነው።
ማህፀነ ለምለም የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ከጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ጀምሮ በታምራት ቶላ በፓሪስ ኦሊምፒክ እስከተገኘው የወርቅ ሜዳሊያ ድረስ በርከት ያሉ ጀግኖችን በሩጫው መስክ ለዓለም አስተዋውቃለች። ዓለም ኢትዮጵያውያን በሚሳተፉባቸው የረጅም ርቀት ውድድሮች መወዳደር እስከሚፈራ ድረስ የራሷን አረንጓዴ ጎርፍ ፈጥራ የውድድር መድረኩን በድል አጥለቅልቃው ኖራለች። ያ የአሸናፊነት ስሜትና ድል ለኢትዮጵያውያን ዋጋው እጅግ ብዙ ነው።
ነገር ግን ይህ የሀገር ፍቅርና አንድነት የሚታይበት አትሌቲክሳችን እ.ኤ.አ በ2016 በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ ተጎድቶ፤ በ2020 የቶክዮ ኦሊምፒክ ታሞ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ የሞት አፋፍ ላይ ደርሶ ታይቷል።
ከጅምሩ ብዙ እሰጣ ገባዎች በተከሰቱበት የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በ1 ወርቅና በ3 የብር ሜዳሊያዎች ከዓለም 47ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች። ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያውያን ዘንድ መከፋት ሆኗል።
ከላይ የተዘረዘረው እንደተጠበቀ ሆኖ የሥልጠና ሂደታችን ሳይንሳዊ መንገድን የተከተለ ባለመሆኑ፣ በአንድ ፊልድ የሚሮጡ አትሌቶች በተለያዩ አሠልጣኞች ስር መሠልጠናቸውና መገፋፋት በመኖሩ፣ ውድድሮች ከመካሄዳቸው በፊት ስለውድድሩ ቦታ ጥናት ተደርጎ ቦታውን በሚመስል ቦታ ሥልጠና መስጠት ባለመቻሉና የጋራ ሥራ የመሥራት እንዲሁም የጋራ ውጤት የማምጣት ተነሳሽነት በዘርፋ በመጥፋቱ ለውጤቱ መዳከም እንደተጨማሪ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።
አሠልጣኞችና የፌዴሬሽን አመራሮች እንዲሁም የኦሊምፒክ ኮሚቴው ቀድመው ውድድሩን ላናሸንፍ እንችላለን እና ተሳትፎ በቂ ነው እያሉ በሚናገሩበት ሂደት አልፎ ውጤት መጠበቅ ከባድ ነው።
በስፖርቱ ውስጥ በዘርፋ እውቀት ያላቸው ሰዎች ገብተው እንዲሠሩ መንግሥትም ቢሆን ጫናዎችን ማሳደር አለበት። ዕውቀትና ልምድ አንድ ላይ ካልተጣመሩ ውጤት እንደማይገኝ የዘንድሮ የፓሪሱ ኦሊምፒክ ጥሩ ማሳያ ነው።
በተለይ የቡድን መንፈስን የሚረብሹ ሂደቶችን በማስወገድ ግልፀኝነት የተሞላበት የስፖርት ተቋምና አሠራር ሊፈጠር ይገባል። አትሌቶች ወደ ውድድር ሲገቡ ሥነ-ልቦናቸው ሊጠበቅ ግድ ይለዋል። የርስ በርስ ፀብና መገፋፋት ባለበት ሁኔታ ከአትሌቶቹ ውጤትን መጠበቅ አይቻልምና ነው።
ኢትዮጵያ በተከታታይ ሦስት ኦሊምፒኮች በሪዮ፣ ቶክዮ እና ፓሪስ በየእያንዳንዳቸው ከአንድ ወርቅ በላይ ማሳካት አልቻለችም። በዘንድሮው የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በሁለት ርቀቶች በቀነኒሳ በቀለና በቲኪ ገላና ተይዘው የነበሩ ሪከርዶችን ለዩጋንዳና ለኔዘርላንድ አሳልፋም ሰጥታለች።
የዘንድሮ የኦሊምፒክ ውጤት የተቋምም፣ የአሠራርም ውድቀትን ያሳያል። ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያውያን ከሜዳሊያ ባለፈ የጽናት እና የአይበገሬነት ምልክት ነው። የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ታሪክ ለአፍሪካውያን የአሸናፊነት ሥነ-ልቦናን የከፈተ ነው። መድረኩ ሀገርን በማስተዋወቅ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው። አትሌቲክስን ከውጤት ባለፈ ከማንነታችን እና ከታሪካችን ጋር በአግባቡ አቆራኝቶ ማየት ተገቢ ነው።
የአሸናፊነትን መንፈስን በትውልዱ ለማስረጽ የውጤታማ አትሌቶቻችንን አብነት ማሳወቅ በእጅጉ ጠቃሚ ይሆናል። የሙያ ሥነ-ምግባር፣ ትጋት እና ሀገርን ማስቀደምን ከኢትዮጵያ ድንቅ አትሌቶች ሕይወት መማር ይቻላል። በፓሪስ ኦሊምፒክ ኅብረተሰቡ ቅሬታ የገባው ሕዝቡ የለመደውን ወርቅ ባለማግኘቱ ብቻ ሳይሆን በልዑኩ ውስጥ ያለው ልዩነት እና ያልተገባ አሠራር አደባባይ በመውጣቱ ጭምር ነው።
ምንም እንኳን በስፖርት ውስጥ ማሸነፍና መሸነፍ ያለ ቢሆንም አንበገርም፣ በቅኝ አልተገዛንም እያልን፤ በውድድሮቹ ለነጮች እጅ ስንሰጥ ሕዝቡን በተሸናፊነት ስሜት ቁጭት ውስጥ አስገብቶታል። የዘንድሮ ውጤት ስፖርቱ በተቋም እና በሥርዓት (ሲስተም) ደረጃ ያለበትን ውድቀት በግልፅ አሳይቷል። በስፖርት ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ብልሹ አሠራሮች ለሀገር ውጤት ሲባል ሊስተካከሉ ይገባል።
ስፖርት በአግባቡ ከተያዘ ለማኅበረሰባዊ አንድነት የማይተካ ሚና ሲኖረው፤ በአግባቡ ካልተያዘ ደግሞ የልዩነት ምንጭ እና ማስፊያ በመሆን ማኅበረሰቡ ላይ ተጨማሪ ችግር እንደሚጋርጥ ግልፅ ነው።
አትሌቲክሱ ላይ ያሉ ሁለንተናዊ ጉዳት የሚያመጡ ችግሮችን መናገርም የዜግነት ግዴታ መሆን አለበት። መንግሥትም በስፖርት ዘርፉ ላይ ያሉ የዕድገት ማነቆዎች ሊታረሙ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት ሁሉ።
መኮንን ይደርሳል
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም