አቶ ሁነኛው ጥላዬ በበበቃ ቡና እርሻ ልማት ድርጅት የእርሻ ክፍል ኃላፊ
አረንጓዴው ወርቅ እየተባለ የሚሞካሸውና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥም የአንበሳውን ድርሻ የያዘው የቡና ጉዳይ ሲነሳ የበበቃ ቡና እርሻ ልማት ድርጅት አብሮ ይነሳል። በተለይም ከአራት አስርት ዓመታት በፊት የነበረው ትውልድ ስለዚህ የልማት ድርጅት በደንብ ያስታውሳል። ‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና፣ ቡና…›› እየተባለ በሚዘመርበት ዘመን የልማት ድርጅቱም ስምና ዝና አብሮ ይነሳ ነበር።
በበቃ በኢትዮጵያ እድሜ ጠገብና ትልቁ የቡና ልማት ድርጅት ሲሆን፤ በሀገር ባለውለታነቱም ይጠቀሳል። የልማት ድርጅቱን ያቋቋመው የደርግ መንግሥት ድርጅቱን ሲያቋቋም እንደሀገር የቡና ምርታማነት እንዲጨምርና በሀገር ኢኮኖሚ ላይም አስተዋፅዖው ከፍ እንዲል ለማስቻል እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በበቃ መጀመሪያ ሲቋቋም መንግሥታዊ የልማት ድርጅት ሆኖ ነው የተቋቋመው። ከሚዛን ተፈሪ በ28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። በበቃ በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትም የላቀ ሚና ያላቸው የተለያዩ የቅመማቅመም ልማቶችን ለማከናወን በሚያስችል ምቹ አካባቢ ነው የሚገኘው።
በበቃ የመንግሥት እርሻ ልማት ሆኖ ለረጅም ጊዜ የሠራ ቢሆንም በመንግሥታዊ ይዞታነቱ አልቀጠለም። በአሁኑ ጊዜ ልማት ድርጅቱ በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥር ሆኖ ነው ልማቱን እያከናወነ የሚገኘው።
በአሁኑ ወቅትም በሜድሮክ ስር ሆኖ 95 በመቶ ድርሻ በመውሰድ በጥራትም በብዛትም ቡና እያለማ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል። በተጓዳኝም ቁንዶበርበሬና እርድ ቅመሞችን ያለማል። ኩባንያው ወደፊትም ከቡናው በተጨማሪ በከፍተኛ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ልማቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት አቅዷል። አጠቃላይ የልማት ድርጅቱን እንቅስቃሴ በተመለከተ በበቃ ቡና እርሻ ልማት ድርጅት የእርሻ ክፍል ኃላፊ ከአቶ ሁነኛው ጥላዬ ጋር ቆይታ አድርገናል። ውድ አንባቢያንም መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።
አዲስ ዘመን፤ እስኪ በቅድሚያ ስለበበቃ እርሻ ልማት ምሥረታ መለስ ብለው ያስታውሱን?
አቶ ሁነኛው፤– በበቃ እርሻ ልማት መንግሥታዊ ድርጅት ሆኖ የተመሠረተ ሲሆን፤ የተመሠረተውም በዋናነት ለቡና ለልማት እንዲውል ነው። ተቋሙ እንዲመሠረት ሀገሪቱ ያፈራቻቸው ትላልቅ ባለሙያዎች ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል። ብዙ ሰዎች ተሳትፎ አድርገው ሙያዊ አስተዋፅዋቸውን አበርክተዋል። አሁንም ዋና ልማቱ ቡና ነው። በተጓዳኝ ግን ቅመማቅመምና የበቆሎ እርሻ ሥራ ያከናውናል። የበቆሎ ምርት ለገበያ ሳይሆን በአብዛኛው ለሠራተኛ ነው የሚውለው።
በበቃ እርሻ ልማት በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ነው የተቋቋመው። በኩታገጠም በሰፊ የቡና ማሣ ላይ የቡና ልማት የሚካሄድበት አካባቢ ነው። ይህም በሀገራችን ብቻ ሳይሆን፤ በምሥራቅ አፍሪካም ተጠቃሽ ነው። በ10ሺ ሄክታር ክልል ውስጥ ነው የሚገኘው። ከዚህ ውስጥ ለአካባቢው የአየር ንብረት መጠበቂያ ተብለው የማይነኩ ከጫካና ረግረጋማ ቦታዎች በስተቀር ወደ ስድስት ሺህ ሄክታር የሚሆነው መሬት በተለያየ የሰብል ልማት የተሸፈነ ነው።
በበቃ ቡና እርሻ ከ2003 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ጀምሮ ከመንግሥት ይዞታነት ወጥቶ ወደ ግል ተዛውሯል። አሁን ላይ እርሻ ልማቱን የሚያስተዳድረው ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ነው። ኩባንያው ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ልማቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ልማቱ ከኩባንያው ተጠቃሚነት አልፎ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አወንታዊ አስተዋፅዖ እንዲያበረክት በአደረጃጀትና በምርታማነት በየጊዜው ለውጥ በማድረግ ላይ ይገኛል። እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችም ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ለውጥ እያስገኙ ነው።
አካባቢው ለቡና ተስማሚ የሚባል ነው። ሆኖም ግን የአየር ፀባዩ እንደሚባለው ከፍተኛ የሆነ የቡና መጠን የሚያስገኝ ነው ብሎ አፍ ሞልቶ ለመናገር አያስደፍርም። በበቃ እርሻ ልማት ለዘመናት ሲያመርት የነበረው በሄክታር ከሁለት ኩንታል የበለጠ አልነበረም። ሜድሮክ ኩባንያ በዚህ በኩል የወሰደው እርምጃ እራሱም የጥናት ሥራው አካል ሆኖ ለአካባቢው የአየር ፀባይ ተስማሚ የሆነ አዲስ የቡና ዝርያዎች የሚለሙበትን መንገድ አመቻችቷል።
ከ86 በመቶ በላይ የቡና ዝርያዎች ተቀይረዋል። በአሁኑ ጊዜም በጅማ እርሻ ምርምር ማዕከል በጥናት የወጡ የተለያየ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች እየተለቀቁ ነው። ሀገራዊ ስም እየተሰጣቸው ከምርምር እንዲወጡ እየተደረገ ሲሆን፣ ስያሜ የመስጠቱ ሂደት ገና አልተጠናቀቀም። የምርምር ሥራው እና ሂደቱ የተካሄደው ልማቱ በሚገኝበት የኩባንያው ድርጅት ውስጥ ነው። በዚህ መልኩ ለአካባቢው የአየር ፀባይ የሚስማሙ የቡና ዝርያዎችን ማግኘት ተችሏል። ኩባንያው ወደፊት በስጦታና በተለያየ መንገድ የአካባቢው አርሶ አደርም እንዲጠቀም የማድረግ እቅድ አለው።
ኩባንያው የቡና ዝርያዎች መቀየር ላይ የወሰደው እርምጃ ትክክል ነው የነበረው። ለድርጅቱ ሥራ መለወጥና እድገት እንዲሁም እንደሀገር ጉልህ አስተዋፅዖ እንዲኖረው አስችሎታል። በአሁኑ ጊዜ የሚሰበሰበው ቡና በሄክታር ከሰባት እስከ አስር ኩንታል አንዳንዴም ከዚያ በላይ ይሆናል። ይህን ውጤት ማስመዝገብ የተቻለው ዝርያ በመለወጥ ብቻ እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል። የተለያዩ ግብዓቶችንም በመጠቀም ጭምር ነው። የማዳበሪያ አቅርቦትና የአፈሩ ተስማሚነት ሁሉ በደንብ ይታያል። በተለይም አፈር ምርመራ ላይ በልዩ ጥንቃቄ ይሠራል። በየሁለት ዓመቱ የአፈር ምርመራ ይደረጋል። የጎደለው ንጥረነገር ካለም ሳይንሱን ተከትሎ ይሟላል።
በአጠቃላይ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ከጥናት ሥራ እስከ ችግኝ ማፍላት ድረስ ባለው ሂደት በልዩ ትኩረት ነው የተሠራው። በሥራው ላይም ቁርጠኛ አመራሮች ባይኖሩና ያላሰለሰ ጥረት ባያደርጉ ኖሮ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ነበር። ለውጡን ለማምጣትም ከፍተኛ የገንዘብ ወጪም ተደርጓል።
በአጠቃላይ ኩባንያው በእውቀት ላይ የተመሠረተ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ወጭ በማድረግ ነው ለውጥ ያመጣው። በአንድ ዓመት ብቻ ከአንድ ሺ ሄክታር መሬት ላይ አሮጌ ቡና ተነቅሎ በአዲስ ተተክቷል። ቡና ምርት የሚሰጠው በሦስት ዓመት ነው። ይሁን እንጂ ወደፊት የሚገኘውን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ ነው እርምጃው የወሰደው። ይሄን ጊዜ ለመጠበቅ ሲወሰንም ቁርጠኝነትን ነው የሚሳየው።
ለውጡ አዲስ እይታ ነው ማለት ይቻላል። እንደሀገርም ከፍተኛ ቡና እንዲመረት የበኩላችንን ጥረት አድርገናል፤ ለውጥም አምጥተናል። አሁን ላይ አፍ ሞልተን ስለለውጡም መናገር የቻልነው መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ በመሠራቱ ነው። ቁርጠኛ እርምጃ ተወስዶ ሥራ ባይሠራ ኖሮ የቡና ልማቱ በሌላ የሚተካበት ሁኔታ ይፈጠርም ነበር። ምክንያቱም ለውጥ ከመደረጉ በፊት በነበረው የቡና ልማት ይገኝ የነበረው የምርት መጠን ለመቀጠል የሚያስችል ስላልነበር ነው።
አሁን ላይ ኩባንያው የሚያለማው ቡና በአቅራቢያው ካሉ ቡና አልሚዎች ጋር ሲወዳደር ውጤታማነቱ ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም። ለቡና ተስማሚ የሚባሉ ሎውላንድ አካባቢዎች እንደ ሊሙ አካባቢ ያሉ ቡና አልሚዎችን ጭምር መቅደም ችሏል። ቀደም ሲል ግን በበቃ እርሻ ድርጅት ለሠራተኞቹ ደመወዝ ለመክፈል እንኳን ተቸግሮ ነበር። ሊሙ አካባቢ ቡና ከሚያለሙ ድርጅቶች ብድር እስከመውሰድ ደርሶ ነበር። ለሠራተኞቹ አነስተኛ ደሞዝ የሚከፍለውም በበቃ ቡና እርሻ ልማት ነበር። አሁን ላይ ግን የተገላቢጦሽ ነው የሆነው። በበቃ የለውጥ ጎዳና ላይ ነው። በእውቀት ላይ የተመሠረተ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አድርጎ ለውጥ አምጥቷል።
አዲስ ዘመን፤ ኩባንያው ምርታማነትን ለማሳደግ በገንዘብም በእውቀትም የታገዘ ሥራ መሥራቱን ገልጸውልናል። በሰው ኃይልም ሆነ በካፒታል ያለውን አደረጃጀት እንዲሁም ለአካባቢው የተፈጠረውን የሥራ ዕድል በተመለከተ ቢገልጹልን?
አቶ ሁነኛው፤ ኩባንያው ምርታማነቱን ለማሳደግ የተሻለ የቡና ዝርያ ለማግኘት የደከመውን ያህል አምራች የሆነ የሰው ኃይል ለማፍራትም ጥረት አድርጓል። በእርሻው፣ በሰው ኃይል አስተዳደሩም፣ በፋይናንሱም በሁሉም ዘርፎች በእውቀት የተደራጀ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። እዚህ ላይ መግለጽ የምፈልገው ኩባንያው እርሻ ልማቱን ሲረከብ የነበረውን የሰው ኃይልም አንድ ላይ ነው ያስቀጠልነው። እኔም ስለነበርኩ ምስክር መሆን እችላለሁ።
የሰው ኃይሉን በእውቀት የማብቃት ሥራ ክፍተቶችን በመለየት ክፍተቱን የመሙላት ሥራ ነው የተሠራው። ጤናማ የሥራ መንፈስ ለመፍጠር አመለካከት ላይም ተሠርቷል። ለድርጅቱ ቀጣይነት የሰው ኃይሉ ላይ መሥራት አስፈላጊም በመሆኑ ኩባንያው ትኩረት ሰጥቷል። ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ሠራተኛ የአካባቢው ነዋሪ ነው።
የሰው ኃይሉን በተመለከተም አሁን ላይ ቋሚ ሠራተኞች ከሁለት ሺ በላይ ናቸው። ወቅታዊ ሥራዎች ሲኖሩ ደግሞ ከስድስት ሺ እስከ ሰባት ሺ ጊዜያዊ ሠራተኞች ይቀጠራሉ። ጊዜያዊ ሠራተኞች ቁርጥ ሥራ በሚባል የአሠራር ዘዴ ስለሚሠሩ ሌላ ቦታም ተጨማሪ ሥራ መሥራት ዕድሉ አላቸው። በቡና ለቀማ ወቅት ግን የሰው ኃይሉ እስከ 11ሺ ይደርሳል። ኩባንያው በተቃራኒው የሰው ኃይል እጥረት ነው የሚያጋጥመው። ከፍተኛ የሰው ኃይል በሚያስፈልገበት ወቅት ሠራተኛ ለማግኘት ያስቸግራል።
አዲስ ዘመን፤ ቡና መቼ እንደሚለቀም፣ በዓመት ምን ያህል ምርት እንደሚገኝና ተከላውንም አያይዘው ቢገልጹልን?
አቶ ሁነኛው፤ ቡና አብቦ ለፍሬ ለመብቃት እስከ ዘጠኝ ወር ጊዜ ይወስድበታል። በዚህ ሁኔታ ቡና በዓመት አንድ ዙር ለቀማ ይከናወናል ማለት ነው። አንድ የቡና ዛፍ በተለያየ ጊዜ ስለሚያብብ የለቀማ ጊዜው ከሦስት እስከ አራት ወራት ጊዜ ይወስዳል። በአማካይ ከ45ሺ እስከ 60ሺ ኩንታል ይገኛል። በያዝነው በጀት ዓመት ግን 166ሺ ኩንታል ቡና ተለቅሟል። ይሄ ከፍተኛው ነው። ከሚሰበሰበው ቡና 95 በመቶ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው። በእሸቱ ተለቅሞ እና ታጥቦ ነው የሚዘጋጀው።
በእርሻ ልማቱ ከቡና ልማቱ ጎን ለጎን የቁንዶ በርበሬ እና የእርድ ቅመም ይለማል። ቁንዶበርበሬ ከሦስት እስከ አምስት ሄክታር መሬት ላይ፣ እርድም ተመሳሳይ በሆነ ሄክታር መሬት ላይ ነው የሚለማው። ዓመታዊ ሰብል ውስጥ ነው የሚመደቡት። ቁንዶበርበሬ ቅመም ለለቀማ
ሲደርስ ለቅሞ ለመጨረስ እስከ ሁለት ወር ጊዜ፣ እርድ ደግሞ እስከ አንድ ወር ጊዜ ይወስዳል። 180 ሄክታር መሬት ላይ የሚለማውን በቆሎም እንዲሁ ምርቱ ሲደርስ ይሰበሰባል። ልማቱ በዚህ መልኩ እየተከናወነ በመሆኑ በበቃ ላይ ዓመቱን ሙሉ ሥራ አይቋረጥም።
አዲስ ዘመን፤ በኩባንያውና በሠራተኞች መካከል የተለያዩ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በምን መልኩ እንደሚፈታ፣ የቀን ሠራተኞች የሚያነሱት የክፍያ ማነስ ጥያቄ፣ የሠራተኛ ማኅበር ማቋቋም ጋር ተያይዞ ያለውንም ቢገልጹልን?
አቶ ሁነኛው፤- ሠራተኞች መብትና ግዴታቸውን ለመወጣት እንዲያስችላቸው ማኅበር አቋቁመዋል። ማኅበሩ ከተቋቋመ ረጅም ጊዜው ነው። መሠረታዊ በሆነ ነገር ላይ መግባባት መኖር አለበት። ሠራተኛው የሚኖረው ድርጅቱ ዘላቂነት ሲኖረው ነው። ድርጅቱም ቀጣይነት የሚኖረው ሠራተኛው ሠላማዊ ሆኖ ሥራውን መሥራት ሲችል ነው። በዚህ ላይ አስተዳደሩም ሆነ የሠራተኛው ተወካይ የጋራ ግንዛቤ አላቸው። ይህንን መሠረት ያደረገ የኅብረት ስምምነት ያወጣሉ። ዳኛ ሆኖ የሚያገለግለውም የጋራ ስምምነቱ ነው። ይህ ሲባል ግን የመብት መጣስ የለም፣ ፍጹም ነው የሚል ድምዳሜ ላይ አንደርስም። ሠራተኞች የተለያዩ ጥያቄዎችና ቅሬታ ይኖራቸዋል።
መብቴ ተጥሷል የሚል ሠራተኛ ካለ ቅሬታ ማቅረብ ይችላል። በተቀመጠው የቅሬታ አፈታት መሠረት ይታይለታል። ችግሩ በደረጃ እስከ ሠራተኛ ማኅበሩ ድረስ ደርሶ የሚፈታበት አግባብ ስላለ ሠራተኛው መፍትሔ ያገኛል። በሠራተኛውና በአሠሪው መካከል መፋጨቶች የሚኖረው የኅብረት ስምምነትን ለማምጣት ነው። ሌላው በድርጅቱ በኩል ለሠራተኛው ከሚያሟላቸው አንዱ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ነው። ሠራተኛው እየተጠቀመባቸው ያሉ መኖሪያ ቤቶች ከተገነቡ ረጅም ጊዜ ሆኗቸዋል። መታደስ ይኖርባቸዋል። ጊዜ የወሰደ ቢሆንም ደረጃ በደረጃ እድሳቱን ለማከናወን በእቅድ ተይዟል።
የቀን ሠራተኛን በተመለከተ ቅሬታ ውስጥ የሚከት ነገር የለም። የቀን ሠራተኛ ሥራ ከመጀመሩ በፊት የሚሠራውንም የሚያገኘውንም ገቢ ቀድሞ ያውቃል። ኩባንያውም ቀድሞ በማስታወቂያ ስለሚያሳውቅ ተስማምቶ ነው ሥራውን የሚጀምረው። ቁርጥ ሥራ ነው የሚሠራው። መካድ የማይቻለው የቀን ሠራተኞች የክፍያ ማነስ ጥያቄ ያነሳሉ። ይህም ሆኖ በስምምነት ነው የሚሠራው። ግን ድርጅቱ መሸከም በሚችለው መጠን ጥያቄውን ለመመለስ ጥረት እያደረገ ነው። ችግሩን ለመጋራት በየጊዜው ማሻሻያ ያደርጋል። ምናልባት ፍላጎት ላይሟላ ይችላል።
አዲስ ዘመን፤ ኩባንያዎች የአካባቢ ማኅበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ አንፃር ኩባንያው የሠራው ሥራ ካለ ቢያብራሩልን?
አቶ ሁነኛው፤ አንዳንድ ክፍተቶች ነበሩ። አንዱ ክፍተት ኩባንያው የሚያከናውናቸውን የልማት ሥራዎች ፋይዳ በውል ያለመረዳት ነው። ኩባንያው የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ሊያግዝ እንደሚችልና ሌሎችንም አስፈላጊ ነገሮች ተመካክሮና ተወያይቶ ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት ዕድሎች መኖራቸውን ባለመገንዘብ ድንበር የማበጀት ሁኔታ ነበር።
ኩባንያው ድርጅት ሆኖ እንዲቀጥል የአካባቢው ማኅበረሰብን መያዝ እንዳለበት እምነት ስላለው የነበረውን ክፍተት ከመቅረፍ ጀምሮ ነው የተንቀሳቀሰው። በዚህም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጀምሮ በየእርከኑ ካሉ አመራሮች ጋር ጭምር ጤናማ የሆነ ግንኙነትና መቀራረብ መፍጠር ተችሏል። በሂደትም የኩባንያው አስፈላጊነት ጥሩ ግንዛቤ እያገኘ መጥቷል። ነገሮች በዚህ መልኩ ከተስተካከሉ በኋላ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል።
በልማት በኩል የመንገድ ሥራ ይገኝበታል። የእርሻ ልማቱ በሰባት አቅጣጫ ይዋሰናል። አዋሳኝ በሆኑ ሰባት ቀበሌዎች መንደር ከመንደር፣ እንዲሁም ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ የመንገድ መሠረተ ልማት ለመሥራት ጥረት ተደርጓል። ትምህርት ቤትን ጨምሮ የተለያዩ ግንባታዎች ሲከናወኑም ጥያቄዎች ስለሚቀርቡ በተቻለ መጠን ትብብር ይደረጋል።
ሙያዊ እገዛ ላይ ትብብር ያደርጋል። በበቃ እርሻ ልማት አምስት ዐቢይ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በዐቢዮቹ ሥር ደግሞ ንዑስ ክፍሎች አሉት። በነዚህ አደረጃጀቶች ውስጥ የሚሠሩ ከፍተኛ ባለሙያዎች አሉን። በነዚህ ባለሙያዎች አማካኝነት ነው ለአካባቢው አርሶአደሮች ድጋፍ እያደረግን የምንገኘው። የቡና ችግኝም ሲፈልጉ ከወረዳዎች ጋር በመሆን ነው ስርጭቱ እንዲከናወን የምናደርገው። በቅርቡ የሚለቀቁ ምርታማ የሆኑ የቡና ችግኞችን ለወረዳ ለመስጠትም ታቅዷል። ለአካባቢው ማኅበረሰብ እየተደረገ ያለውን ድጋፍ እኛ ከምንናገር እራሳቸው ቢገልጹ የሚሻል ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፤ ቡና አረንጓዴው ወርቅ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ይታወቃልና ከዚህ አንጻር በበቃ እርሻ ልማት በሀገር ምጣኔያዊ እድገት ላይ ያበረከተው አስተዋፅዖ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ሁነኛው፤ በበቃ እርሻ ልማት ድርጅት ትልቅ ትምህርት ቤት ሆኖ አገልግሎት የሰጠ የሀገር ባለውለታ ነው። አስተዋፅዖው የሚገለፀው ምርቱን ገበያ ላይ አውሎ የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በሀገር ኢኮኖሚው ላይ ባለው ፋይዳ ብቻ አይደለም። በቡናው ዘርፍ ትላልቅ የሚባሉ ባለሙያዎችንም አፍርቷል። በግላቸው በቡና ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት እያበረከቱ ካሉ ባለሀብቶች የወጡት ከበበቃ እርሻ ልማት ነው። ትላልቅ ኩባንያዎችን በኃላፊነት የሚመሩ ባለሙያዎችንም አፍርቷል።
የውጭ ምንዛሪን ለሀገር ከማስገኘት አኳያም ሚናው የላቀ ነው። ከሚያመርተው ቡና 95 በመቶው ለውጭ ገበያ እያቀረበ መሆኑ በቀላል የሚወሰድ አይደለም። ከፍተኛ እመርታ ነው። ለቡና ልማት ተስማሚ የሆነ የአየር ፀባይ የለም በሚባልበት አካባቢ ላይ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለውጥ በማምጣት ምርታማነት እንዲጨምር ማድረግም በራሱ የተቋሙን ጥንካሬ ነው የሚያሳየው። የሀገር ባለውለታነቱንም ነው የሚያረጋግጠው። በጥራትና በብዛት ማምረት እንዲቻልም እንደሀገርም የመጀመሪያ የሆነ ዘመናዊ የምርት ማዘጋጃ ተቋም ገንብቶ አገልግሎት ላይ አውሏል።
አዲስ ዘመን፤ እርሻ ልማቱ ውስጥ አሁን ላይ በመከናወን ላይ ከሚገኙ የልማት ሥራዎች በተጨማሪ ሌሎች ልማቶችን የማከናወን እቅድ አለ?
አቶ ሁነኛው፤ -አዎ እቅድ አለው። ዋናው ልማት ቡና ይሁን እንጂ ሌሎች ሰብሎች አሉ። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተለይም ዝቅተኛ በሚባለው አካባቢ ላይ ቅመማ ቅመም በስፋት ሊመረቱባቸው ይችላሉ። በዚሁ በኩልም እየሄድንበት ነው። ቁንዶ በርበሬ የቅመም ንጉሥ ተብሎ ነው የሚጠራው። በመሆኑም በገበያ ላይ በዋጋ ውድ ነው። የእርድ ቅመምም እንዲሁ በገበያ ላይ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው።
ለመኪና ጎማ ጥሬ እቃ የሚውል ተክል ለማልማትም ጥረት እየተደረገ ነው። ተክሉ በዋናነት ለጎማ ጥሬ እቃነት የሚያገለግል ቢሆንም ለሌሎች ግብዓቶችም ይውላል። አሁን ላይ በአነስተኛ መሬት ላይ እየለማ ነው። ካካዎ የተባለውን ተክልም ለማልማት ታስቧል። ወደፊት ልማቱን ማስፋት ይቻላል። በእቅድ ውስጥም ተካቷል። በአጠቃላይ ሁለገብ የልማት ሥራ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፤ በቆይታችን ያላነሳናቸውና ሊነሱ ይገባቸዋል የሚሉት ካለና በተለይ ደግሞ በድርጅቱ በኩልም ሆነ በሌላ አካል መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ካሉ ቢያነሱልንና በዚሁ ብናጠቃልል?
አቶ ሁነኛው፤ ድርጅቱ ሰፊ እንደመሆኑ በእኔ እምነት ለአካባቢው እንደዓይን ብሌን የሚታይ ነው ። ይሄን ለማለት ያስቻለኝ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ አመራር ያለው ሁሉ ለልማት ድርጅቱ እያደረጉ ያለው ድጋፍ ከፍተኛ በመሆኑ ነው። ማኅበረሰቡ በየደረጃው ያለው አመራር ለልማት ድርጅቱ ጥበቃ ባያደርጉ ይህ ግዙፍ ድርጅት ምርታማነቱ ዘላቂ አይሆንም ነበር። ለወደፊትም ሰፊ እቅድ አያቅድም ነበር። የፀጥታ መደፍረስም ሆነ የተለያየ ችግር ሲኖር ፈጥኖ በመድረስ እያደረጉ ያለው ትብብር እንዲቀጥልና እገዛቸው እንዳይለየን ብዬ ነው የምጠይቀው።
ድጋፍና ክትትል በመኖሩ አልፎ አልፎም ቢሆን አካባቢው ላይ በነበረው የፀጥታ መደፍረስ የልማት ድርጅቱ ላይ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ አላጋጠመውም። የፀጥታ መደፍረስ በአንዳንድ አካባቢ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች እንቅስቃሴያቸው መገታቱን፣ ሀብትና ንብረታቸውም መውደሙንና ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን እንሰማለን። በበቃ ቡና እርሻ ልማት ድርጅት ግን እንዲህ ያለው ፈተና አልገጠመውም። ይሄ በመልካም ጎኑ የሚገለጽ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፤ ለነበረን ቆይታ እጅግ በጣም እናመሰግናለን።
አቶ ሁነኛው፤ እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም