ከተመሰረተች ከ130 ዓመት በላይ የሆናት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መናኸሪያ፤ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአፍሪካ መዲና እና የተለያዩ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ ናት። ከ90 በላይ ኤምባሲዎችን በማቀፍም በዓለም ላይ ካሉት ጥቂት የዲፕሎማቲክ ማዕከል ከሆኑት ከተሞች ውስጥ ግንባር ቀደምም ናት፡፡
ሆኖም ይህቺ የዲፕሎማሲ መናኸሪያ ስሟና ግብሯ ለዘመናት ተራርቆ ቆይቷል፡፡ ከተማዋ ከምስረታዋ ጀምሮ በዘመናዊ ማስተር ፕላን የተቆረቆረች ባለመሆኗ እና ለዘመናትም አስታዋሽ አጥታ በመቆየቷ በእርጅና ብዛት ለመፍረስ ተቃርባ ነበር፡፡የመሰረተ ልማት ዝርጋታዋም ሆነ አረንጓዴ ሽፋኗ አንድ ከተማ ሊያሟላ ከሚገባው ዝቅተኛ መስፈርት በእጅጉ የራቀ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አዲስ አበባን እንደ ገጠር ማስተዳደር በሚል የተሳሳተ መርህ መሠረትም ከተማዋ የኋሊት ስትጓዝም ቆይታለች፡፡
ሆኖም የመንግሥትን ለውጥ ተከትሎ ከተማዋ ባገኘችው ትኩረት አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብ አበባ የመሆን እድል አግኝታለች፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብሎም አፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ የሆኑ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑባት ነው፡፡ከተማዋ በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት የሚያበቋት የተለያዩ መሠረተ ልማቶችና የመዝናኛ ስፍራዎች በስፋት እየተከናወኑባት ይገኛሉ፡፡
የአዲስ አበባን ገጽታ የሚቀይሩ እና የቱሪስት ፍሰት የሚያሳድጉ ሥራዎችንም በመሥራት ከኢትዮጵያ አልፋ የአፍሪካ መዲና የሆነችው ከተማ በጎብኚዎች ተመራጭ ሀገር እንድትሆን የተሠራውም ሥራ የብዙዎችን ቀልብ የገዛ ነው፡፡ በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት የአንድነት፣ የወንድማማችነትና የእንጦጦ ፓርኮች ከአዲስ አበባ አልፈው የሀገር ኩራት ለመሆን በቅተዋል። በአዲስ አበባ የተሠሩት አመርቂ ሥራዎችም ኮይሻን፣ ጎርጎራንና ወንጪን ለመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መነሻ ለመሆን በቅተዋል፡፡
በቅርቡ ደግሞ የአዲስ አበባን ገጽታ ከመሰረቱ የሚለውጥ ግዙፍ የኮሪደር ልማት በአምስት አቅጣጫዎች መተግበር ጀምሮ ወደ መገባደዱ ተቃርቧል፡፡ የኮሪደር ልማቱ የተጎሳቆለውን አዲስ አበባ ገጽታ ለመቀየር ከማስቻሉም በላይ አዲስ አበባ ከአቻ የዓለም ከተሞች ጋር መሳ ለመሳ እንድትቆምና የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን በር የሚከፍት ነው፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም በባለሀብቱና በመንግሥት ቅንጅት የከተማዋን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት የሚያጎለብቱ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በዋነኛነት በቻይና እና በተባበሩት አረብ ኤምሬት መንግሥታትና ባለሀብቶች ትብብር የሚሠሩ ጉልህ የልማት ሥራዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ከእነዚህ ጉልህ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ደግሞ ሰሞኑን የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የአዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ነው፡፡ በ35 ሄክታር መሬት ላይ ከቻይናው “ሲሲሲሲ” ጋር በመተባበር የሚገነባው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በከተማ ውስጥ አዲስ ከተማን የመገንባት ያህል የሆነው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከመሠረቱ የአዲስ አበባን ገጽታ የመቀየር አቅም እንዳለው ታምኖበታል፡፡ የኢኮኖሚ ዞኑ በውስጡ ትላልቅ ሞሎችን፣ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን፣ ቢሮዎችን፣ የትምህርት እና የጤና ተቋማትን እንዲሁም ሰፋፊ መዝናኛዎችንና የውሃ አካላትን እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትን ያካተተ ነው፡፡
አዲሱ የኢኮኖሚ ዞን ለመዲናዋ አዲስ ገፅታ የሚያላብስ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን የሚያጎላ፣ ተጨማሪ የውበት ምንጭ የሚሆን፣ ለነዋሪዎች ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጥር እና ንግድን የሚያሳልጥ ትልቅ ዓለም አቀፍ የግብይት ማዕከል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በአጠቃላይ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና አዲስ ለማድረግና አልፎ ተርፎም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ያረጋገጠች ከተማ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ መለወጥም የአፍሪካ መዲናነቷን ለማጽናት ከማስቻሉም ባሻገር ከተማዋን የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ መነቃቃት የማይተካ ሚና እንድትጫወት ያደርጋታል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም