የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመጀመሪያው ትኩረት የጎረቤት ሀገራት በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከየትኛውም ዓለም አቀፋዊም ሆነ አህጉራዊ ጉዳዮች በበለጠ ለጎረቤት ሀገራት የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ትሰጣለች፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግም ግጭት እና ሁከት ውስጥ የሚገኙትን ሶማሊያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በመሪዎች መካከል ተደጋጋሚ ውይይት እንዲደረግ ኃላፊነትን በመውሰድና አልፎ ተርፎም የሰላም አስከባሪ በመላክ ሀገራቱ አንጻራዊ ሰላም እንዲኖራቸው አበክራ በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡
ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሆና ለዓመታት ቆይታለች። ኢትዮጵያ ባደረገችው ጥረት እኤአ ከ2008 ጀምሮ ሶማሊያ መንግሥት መስርታ አንጻራዊ ሰላም አግኝታ ቆይታለች፡፡ ለሶማሊያ መረጋጋትና የሶማሊያን ሕዝብ ለመታደግ ሲባልም ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን አጥታለች፡፡ በተመሳሳይም ሱዳን ግጭት ውስጥ በገባችበት ወቅት ከሕዝቡ ጎን በመቆም ሱዳን ወደ ተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንድትመጣ ኢትዮጵያ የበኩሏን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ከአንድ ወር በፊትም በግጭት አዙሪት ውስጥ የምትገኘውን ይህችን ሀገር ወደ ሰላሟ እንድትመለስ ማንም መሪ ባላደረገው መልኩ ፖርት ሱዳን ድረስ በመሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አል ቡርሃን ጋር ተወያይተው ተመልሰዋል፡፡ ውይይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም “የወንድም ሱዳን ሕዝብ ችግር የኛም ችግር፣ሰላማቸውም ሰላማችን በመሆኑ ለሱዳን ሕዝብ እፎይታ እና የብልፅግና ጉዞ ዛሬም እንደ ትናንቱ ከልብ እንሠራለን።” ሲሉ ገልጸዋል።
አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳንም እንደ ሀገር እንድትቆም ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚና ከመጫወቷም ባሻገር በሀገሪቱ የነበረው የእርስ በእርስ ግጭት እንዲያባራና አንጻራዊ ሰላም እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚና ተጫውታለች፡፡ በጎረቤት ሀገራት የሚታየው ግጭትና ጦርነት እንዲያበቃ ከመሥራት ጎን ለጎንም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በልማት እንዲተሳሰሩ በማድረግ ረገድም የኢትዮጵያ ሚና የጎላ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ በበርካታ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በቀጣናው የሚታየውን ድርቅ በዘላቂነት ለመቋቋም አበክራ በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ የቀጣናውን ሀገራት ልማት በማቀራረብ ረገድ እየተጫወተች ያለው ሚና በአካባቢ ጥበቃ ብቻ የተገታ አይደለም፡፡በተለይም ከዓባይ ግድብና ከጊቤ ሦስት ግድቦች የሚነጭ ኃይልን ለጎረቤት ሀገራት በተመጣጣኝ ዋጋ በማዳረስ ቀጣናው በኃይል እንዲተሳሰር በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም የኢትዮጵያውያን የዘመናት ጥያቄ የሆነው የዓባይ ወንዝን በትብብር የማልማት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ አበክራ ስትሠራ ቆይታለች፡፡ ሰሞኑንም ደቡብ ሱዳን የናይል የትብብር ማዕቀፍን ማጽደቋም የዚሁ ጥረት አንዱ ማሳያ ነው፡፡የተፋሰሱ ሀገር የወሰደችውን ርምጃ፣ የጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “ታሪካዊ” ሲሉ አድንቀዋል፡፡
በሌላ መጠሪያው “የኢንቴቤ ስምምነት” እየተባለ የሚታወቀው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት፣ በደቡብ ሱዳን መጽደቁ፣ ስምምነቱ በተፋሰሱ ሀገራት ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበትን በቂ ድጋፍ የሚያስገኝ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳን ስድስተኛ ሀገር ሆና የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን መፈረሟ፣ ስምምነቱ “ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝና ወደ ተግባር እንዲሸጋገር የሚያስችል ነው፡፡
አሥራ አንዱም የተፋሰሱ ሀገራት የሚጋሩትን የናይል ወንዝ፣ “ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ለግብጽ እና ለሱዳን ብቻ ያከፋፍላሉ፤” በሚል የሚተቹትን የቅኝ ግዛት ስምምነቶች የሚሽርም እርምጃ ነው፡፡ ይህንን ኢ ፍትሐዊ አካሄድ ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትታገለው የቆየችው ነው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በደቡብ ሱዳን መጽደቁ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ነው፤” ሲሉ በማህበራዊ የትስስር ገጾቻቸው ያወደሱት፡፡
የናይል ወንዝን በጋራ ለማልማት ወደ ሚያስችል ስምምነት ለማምጣት 11 ዓመታት ወስዷል፡፡ ለ11 ዓመታት ከዘለቀ ውይይት በኋላ፣ በ2002 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ 2010) ግንቦት ወር ላይ በኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ዑጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ኬንያ ሲፈረም፣ ብሩንዲ በቀጣዩ ዓመት ስድስተኛ ሀገር ሆና ፈርማለች፡፡ በቅርቡ ደግሞ ደቡብ ሱዳን ስድስተኛዋ የስምምነቱ አጽዳቂ ሀገር ሆናለች፡፡
በዓለም ላይ ወደ 276 የሚጠጉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አሉ። ይህንን 145 የሚሆኑ ሀገራት ይጋራሉ። አንዳንድ ሀገራት ወንዞቹን የሚመለከት ሕግ አላቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ የጋራ የውሃ አጠቃቀም ሕግ የላቸውም። ነገር ግን ሕጉ ያላቸው ሀገራት ውሃን ዘላቂና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ።
የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የዓባይን ውሃ በጋራ፣ በእኩልነትና ምክንያታዊ በሆነ ሁኔታ ውሃውን መጠቀምና አብሮ መንከባከብ የሚያካትትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚተዳደሩባቸውን መርሆችን ጭምር ያካተተ ማዕቀፍ ነው። ይህም በአሥራ አንድ ሀገራት መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው።
ጉዳዩን የኢትዮጵያ መንግሥት የቅርብ ክትትል ያደረገበት በመሆኑ የተሳካ እየሆነ መጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሥራ ባልደረቦቻቸው የተለያዩ ሀገራት መሪዎችን በሚያገኙበት አጋጣሚ የውሃ ሀብትን በጋራ ማልማትና መጠቀም የሚቻልባቸውን መንገዶች ያነሳሉ። ይህም የኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማሲ ሥራ ማሳያ ነው።
በየዓመቱ የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ መድረክ ላይ የውሃ ሚኒስትሮች ይሰበሰባሉ። በዚህም ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የውሃ ሀብቶችን በትብብር ማልማትና ማስተዳደር የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ እና ለጋራ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያ ሁሌም ቅድሚያ እንደምትሰጥ ተናግራለች። ይህም ደቡብ ሱዳንን የመሳሰሉ ሀገራት የትብብር ማዕቀፉን እንዲፈርሙና የናይል ትብብር ኮሚሽን ከስድስት ወራት በኋላ እንዲቋቋምና ተቋም ሆኖ እንዲወጣ በር የሚከፍት ነው፡፡
እንደ ናይል ትብብር ማዕቀፉ ሁሉ የባህር በር ባለቤት ለመሆንም ዲፕሎማሲ ጥረቶች ቀጥለዋል፡፡ በቱርክ አደራዳሪነትም ለሁለት ጊዜያት ያህል በአንካራ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያደረጉት ድርድርና በቀጣይም የሚያደርጉት ውይይት የዚሁ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማሳያ ነው፡፡
የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው፡ ፡ይህን መነሻ በማድረግ የባህር በርና ወደብ አማራጮችን ለማግኘት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላማዊ በሆነ መልኩ ጥያቄውን በማቅረብ ላይ ትገኛለች፡፡ ሆኖም ይህንን ጥያቄ ቀድማ የተቀበለችው ሶማሌላንድ ብቻ ነች፡፡ ዋናዋ ሶማሊያም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ የመሆን ዕድል ቢኖራትም ጥያቄውን ስትገፋ ቆይታለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፓርላማ ተገኝተው እንዳሉት፤ ‹‹የሶማሊያ መንግሥት በአንድ ሰዓት በረራ እና በአንድ ሰዓት ውይይት ይህን ነገር መልክ ማስያዝ ይችላል። በጣም ቀላል ነገር ነው። ምክንያቱም ከሶማሌ መንግሥት ጋር ምንም ጸብ የለንም፡፡
እኛ ለመነጋገር ዝግጁ ነን። ሶማሊያ እንድትጎዳ፣ እንድትፈራርስም ፣ እንድትበተንም የሚፈልግ መንግሥት አይደለም፡፡ ቢሆን ኖሮ ልጆቹን ልኮ እንዲሞቱ አያደርግም ነበር ።የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ የባህር በር ጥያቄ ነው። ይሄ ሕጋዊ ጥያቄ ነው ። ይሄን በሰላማዊ እና በንግግር መልኩ እንደማንኛውም ኮሚዲቲ / ሸቀጥ ለመቀበል ኢትዮጵያ ዝግጁ ነች።›› ሲሉ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ሀገር ጋር ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን በመጠቀም ብቻ የባህር በር ጥያቄዋ መልስ እንዲያገኝ እንደምትሰራ ተናግረዋል፡፡
ይህ ሀገሪቱ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት፤ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና እያገኘ የመጣ ፣ ለተግባራዊነቱ የሀገራት አዎንታዊ ድጋፍ እየተቸረው ይገኛል ።በመጪዎቹ ጊዜያትም ጥረቶቹ ፍሬ አፍርተው ፣ ሀገሪቱ የአዲስ የባህር በር ትርክት ባለቤት መሆን እንደምትችል ተስፋችን ጠንካራ ነው ።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም