ፍትህ ለሁሉም የተሰኘው ተቋም መስራች ናቸው። በበጎ ፍቃደኝነት በተቋቋመው የአገር ሽማግሌዎች ምክር ቤትም ሰብሳቢና በተለያዩ አገራዊ የሽመግልና ሂደቶች ላይ የነቃ ተሳትፎን ያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ምርጫ 97ትን ተከትሎ በአገሪቱ ላይ በተፈጠረው አለመግባባት ለእስር ተዳርገው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከአስር እንዲፈቱ የመሪነት ሚናን ተጫውተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በበጎ ፈቃደኛ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ውስጥ ባላቸው የምክትል ሰብሳቢ ኃላፊነት በተለያዩ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ለእስር የተዳረጉ ዜጎችን አያያዝ፣ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ እንዲሁም የሚፈጠሩ ችግሮችን በቅርበት ይከታተላሉ። ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ የዛሬ የአዲስ ዘመን ዕለተ ዕረቡ እንግዳ በመሆን በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን አካፍለውናል።
አዲስ ዘመን፡- ፍትህ ለሁሉም (justice for all) በተሰኘ ተቋም ምን ዓይነት ሥራዎች እያከናወናችሁ ነው? በምሳሌ የሚጠቀሱ ካሉ?
ፓስተር ዳንኤል፡- ኢትዮጵያ ከደርግ ስርዓት ወደ ኢህአዴግ አስተዳደር ከገባች በኋላ እኛ ሥራችንን ወደ ማረሚያ ቤቶች በማድረግና የታራሚ አያያዝ፣ ንጽሕና፣ ምግብ ፣ አልባሳትን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት አያያዛቸው ምን እንደሚመስል እናያለን። አገሪቱ ውስጥ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ማረሚያ ቤቶች እንዲኖሩ ለማድረግና ግንባታዎችን በመገንባት የማሳያ ሥራ አከናውነናል።
በሌላ በኩልም የአገሪቱን የፍትህ ስርዓት የሚመሩ አካላትን አስተሳሰብ ለመለወጥ የአሌልቱ የማሰልጠኛ ተቋምን የስልጠና መመሪያ (ካሪኩለም) ገንቢ በሆነ መንገድ በማሻሻል አቅርበናል፤ ከዛሬ 9 ዓመት ጀምሮም በዚሁ በተሻሻለው የስልጠና መመሪያ እየተሠራ እንደሚገኝ አውቃለሁ። በዚህም ደግሞ ዓለም አቀፍ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ጀነራል ስብሰባ ላይ ሸልማት አግኝተንበታል።
በተጨማሪም ፖሊስ ተጠርጣሪዎች ላይ ያለውን አያያዝና በጣቢያዎች በኩል የማቆያ ቦታዎች ላይ የሚስተዋለው ክፍተት ከፍተኛ በመሆኑ ፖሊሶችን ስለ ሰብዓዊ መብት አያያዝ የማሰልጠንና ለዚህ ክፍተት ምክንያት የሆነውን በአገሪቱ ያሉ ተቋማት የሚመሩበት ግልጽ የሆነ ማንዋል አለመኖሩ በመሆኑ ይህንን ለመሻገር ከፖሊስ ጋር በመተባበር የእንግሊዝን አገር ተሞክሮ በማምጣትና የአገራችንን ህጎች በማካተት ፖሊስ ጣቢያ የሚገቡ ሰዎች ሊተዳደሩበት የሚገባ መጽሐፍ አዘጋጅተናል። በምርመራ ማንዋል ዙሪያ ከኮሚሽነሩ ጋር በመተባበር የምርመራ ማንዋል ተሠርቶ ተጠናቅቋል።
ይህ ደግሞ የፊሊፒንስ፣ የኮርያ፣ የእንግሊዝና በተለይም ኤፍ ቢ አይ አሜሪካን ከእኛ ጋር በመሆን የዕውቀትና የፋይናንስ እገዛ አድርጎልን ነው የተሠራው።
ሌላው በኮሚውኒቲ ፖሊሲንግ ዙሪያ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፤ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ተባብሮ ችግር ከመከሰቱ በፊት እራሱን እንዲጠብቅ ለማስቻል መመሪያ ሠርተንም አስረክበናል። ከፍርድ ቤት ጋር በተያያዘም ሰበር ሰሚ ችሎት የሚተዳደርበትን ማንዋል በመሥራት ላይ ስንሆን አሁን አንድ ወርክሾፕ ብቻ ነው የቀረን።
ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጋርም እንዲሁ የወንጀል ህጉ ብዙ ዓመት የቆየ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ይህንን ለማሻሻል ላለፉት 12 ዓመታት ሠራዎች እየተሠሩ ናቸው። በተጨማሪም ከ50 ዓመት በላይ ያገለገለውን የኢትዮጵያን የንግድ ህግ ለማሻሻል ሥራዎች ተጀምረዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በኋላ እንደታዩት ማረሚያ ቤቶች ደረጃቸውን
ያልጠበቁ፤ አንዳንዶቹም ሰዎች ሊቆዩባቸው የማይገቡ ነበሩ ፤ የእናንተን ሥራ ተቀብሎ በማስቀጠሉ በኩል የሚመለከተውን አካል ዝግጁነት እንዴት ያዩታል?
ፓስተር ዳንኤል፡- እኛ መንግሥታዊ እንዳልሆነ ተቋም ሃሳብ እናመነጫለን፣ ከዓለም አቀፍ ህብረተሰብ በሰበሰብነው ገንዘብ ሠርተን እናሳያለን፤ ተረክቦ የሚያስቀጥለው ደግሞ መንግሥት ነው፤ እንዲያውም አሁን መንግሥት እኛ የሠራነውን ሥራ ምሳሌ በማድረግ በየክልሉ በራሱ በጀት እየሠራ ነው። በተለይም የመተዳደሪያ ስታንዳርዶች ላይ።
አዲስ ዘመን፡- ማንዋሎቹን እየተጠቀመባቸው ሊሆን ይችላል፤ ግን ደግሞ እናንተ ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት ያስፈልጋል ብላችሁ ሠርታችሁ ስታስረክቡ ይህንን በሌላው ቦታ ላይ መድገም ለምን አስቸገረ?
ፓስተር ዳንኤል፡- አዎ ሥራዎች ሁሉም ቦታ ላይ መድረስ መቻል አለባቸው። ይህ እንዲሆን እኛም እንገፋለን፤ ግን በመንግሥት በኩል ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት አለ፤ ሌላው ግን አንዳንድ አመራሮች ለጉዳዩ ትኩረት አይሰጡትም፤ ሰው ከታሰረ በኋላ ዞር ብሎም የሚያይ አመራር የለም። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ችግሮቹን ለመፍታት ከፍተኛ የሆነ ተነሳሽነት ያላቸውም አሉ።
እነዚህ ተነሳሽነት ያላቸው መሪዎች የሚነበብ ቦታ በሚይዙበት ወቅት መሻሻሎች ይኖራሉ፤ በተቃራኒው ሲሆን ደግሞ ሥራው ይሞታል። ትልቁ ችግር ግን ባለሙያዎች በተለይም በማረሚያ ቤቶች አካባቢ ለመሥራት ፍቃደኝነት ማጣት ነው። ማስታወቂያ ወጥቶ እንኳን የሚቀጠር ሠራተኛ የሚጠፋበት ጊዜ ብዙ ነው።
በመሆኑም ማረሚያ ቤቶቻችን መሻሻል ላለማሳየታቸው የሰው ኃይል እጥረት፣ የፋይናንስ ችግር፣የአመለካከት ዝንፈት፣ የክህሎት ማጣት፣ ትኩረት ያለመስጠት ይጠቀሳሉ። አሁንም ግን የመሪዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የመወጣት ተግባር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል።
አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን ከፍትህ አካላት ጋር በሠራችሁት ሥራ የመጣውንስ ለውጥ እንዴት ይገልጹታል?
ፓስተር ዳንኤል፡- ብዙ ለውጦች ታይተዋል፤ ለምሳሌ እኛ የሠራነውን ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት በማየት አዳማ ላይ ተሠርቷል። እንዲያውም ማረሚያ ቤቱን ከመገንባት በተጨማሪ ታራሚዎች ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትስስር ፈጥረው እስከ ዲፕሎማ ድረስ እንዲማሩ እየተደረገ ሲሆን፤ እነዚህ ባለሙያዎች ለከተማው መንግሥታዊ ተቋማት የቢሮ ዕቃዎችን ሠርቶ በማቅረብ ሴቶች ታራሚዎች የሽሮና በርበሬ ማዘጋጀት ፕሮጀክት እንዲጀምሩ በማድረግ ለከተማው ሆቴሎች በማቅረብ ላይ ናቸው። ይህንን ማባዛት ነው የሚያስፈልገው።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ዓመታት ማረሚያ ቤቶች የማየት እስረኞችን የመጠየቅ ዕድል ነበርዎትና በማረሚያ ቤቶች ሲፈጸሙ የነበሩ አሰቃቂ ድርጊቶች ደግሞ ከለውጡ በኋላ ወጥተዋል፤ እነዚህን ችግሮች ያውቋቸዋል?
ፓስተር ዳንኤል፡- በአገሪቱ 130 ማረሚያ ቤቶች አሉ፤ ስንቱ ላይ ነው ይህ ችግር የደረሰው? ሁሉም ላይ አይደለም ጥናቶቻችንም ይህንን አያሳዩም። ሆኖም እንደዚህ ዓይነት ችግር ያለባቸውን ቦታዎች እናይ ነበር። በተለይም ችግሮቹ የነበሩት ምርመራ ላይ ማስረጃ ለማግኘት አውጣ እመን አትመን በሚል የጉልበት ኃይል መጠቀም እንደነበር ከእስረኞች ሰምተናል። ያን ጊዜም ብዙ አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች እናይም ስለነበር «ኸረ አደጋ እየደረሰ ነው ፤ ስለ እግዚአብሔር ተው» በማለት እንናገርና ለመንግሥትም እንጠቁም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ግን ችግሮቹን ለየትኞቹ አመራሮች አሳውቃችኋል?
ፓስተር ዳንኤል፡- ለከፍተኛ አመራሮቹ ነበር የምንናገረው። ሆኖም አሁን ከለውጡ በኋላ የታዩትን ችግሮች በወቅቱ ለመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ እናውል ብንል የበለጠ ግንኙነታችን ይበላሽና የባሰ በበቀልና በእልህ የተሞላ ጉዳት ይመጣ ነበር። ስለዚህ የሰዎችን ህይወት ለማዳን እኛ ቀጥታ ማስረጃ በመያዝ ቢሯቸው በመግባት አናግረናቸዋል።
በወቅቱም ችግሮቹን ተቀብሎ ለማረም የሚጥሩ አመራሮች የነበሩ ቢሆንም በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ደግሞ ሲነገራቸው እንኳን ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆኑ አመራሮችም ነበሩ። ስለ ሰብዓዊ መብት ለመስማት ፍላጎት የሌላቸው ጭንቅላታቸውን ሙሉ በሙሉ ያደነዘዙና ስለ ፖለቲካቸው ብቻ የሚጨነቁም ብዙ አመራሮች ነበሩ።
በሌላ በኩልም አብዛኞቹ መርማሪዎች ፖለቲካሊ የተቃኙ እንጂ ሙያዊ ዕውቀት ያላቸው ስላልነበሩ በሙያና በአመለካከት መካከል መቀላቀል ፈጥሮባቸው አስተሳሰባቸውን ለማስረጽ ብቻ የፈለጉትን ያደርጉም ነበር። በወቅቱም የህግ የበላይነት የሚባለው ነገር ቀርቶ ፖለቲካ አመለካከቱ በልጦ ነበር የሚታየው።
አንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ላይ ባለሙያዎች ይቀመጣሉ፤ እነዚህን ሰዎች ግን አንድ ወር በሰላም አያሠሯቸውም፤ ወዲያው ይቀየሩና በምትካቸው አቅም የሌላቸው ሰዎች ይተካሉ። ስለዚህ ያየናቸውም ሆነ የሰማናቸው ችግሮች ለምን ተፈጠሩ ብለን ስንጠይቅ መልሱ ሙያና ፖለቲካዊ አመለካከት በመቀላቀላቸው የሚል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በማረሚያ ቤቶች ላይ ባለፈው አንድ ዓመት ምን ለውጥ መጥቷል ? ካለፈው ተግባርስ ተምረናል?
ፓስተር ዳንኤል፡- ባለፈው አንድ ዓመት የአስተሳሰብ ለውጥ መጥቷል። ችግሮቹ ግን አሁንም ሙሉ በሙሉ ተፈተዋል ብሎ ለመናገር ማስረጃዎች ያጥሩኛል። አልፎ አልፎ የሚታዩ ምልክቶች ስላሉ። በተለይም በስታንዳርድ ደረጃ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ገና ብዙ ይቀራል።
ለውጡ ገና አንድ ዓመቱ ነው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህ ይህ ነገር ተሠርቷል ብሎ ለመናገር ትንሽ ጊዜ ይፈልጋል። ሆኖም ለውጦች አሉ ግን ችግሮችም አሉ። ነገሮች ድብልቅልቅ ያሉበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ እየጠሩ የሚሄዱ አመለካከቶች ግልጽ የሆኑ ፖሊሲዎችና አሠራሮች እያደጉ ሲሄዱ መናገር ይቻላል። ግን በአመለካከት ደረጃ በጣም የተሻሻሉ ነገሮች አሉ።
ካለፈው ችግራችን ተምረን ተመሳሳይ ክስተትን እንዳንፈጥር መጠንቀቅ ይገባል። ያለፈው ይበቃል ልንልም ይገባል። በፖለቲካ አመለካከት በብሔር በቡድናዊነት መደራጀታችንን ወደ ጎን በመተው የህግ የበላይነት ሊገዛን ይገባል፤ የህግ የበላይነትን ሲስተም አድርገን ቤታችንንና አገራችንን መምራት እስካልቻልን ድረስ ሁሌም ታጥቦ ጭቃ ነው የምንሆነው።
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ገብተው አስረኞችን ዓይተው ሲወጡና መረጃዎችን ይዘው ለመንግሥት አቅርበው ምላሽ ሲያጡ ምን ይሰማዎት ነበር ?
ፓስተር ዳንኤል፡- እንደ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም በገባንባቸው ቦታዎች ላይ ውጤታማ ነን ብዬ አስባለሁ፤ ለምሳሌ የይቅርታ ቦርድ አዋጅ ኢትዮጵያ ውስጥ እውን እንዲሆን የሃሳቡ አመንጪዎች እኛ ነን። መንግሥትም አዋጁን አጽድቆ ባለፉት 14 ዓመታት ከ3 መቶ ሺ በላይ እስረኞች ተለቅቀዋል።
ይህንን እንደ ድል እቆጥረዋለሁ፤ ግን ጥያቄውን ለመመለስ እስረኞች በጥፋታቸው አልያም ተጠርጣሪ ሆነው ይገባሉ፤ በጥፋቱ የገባው በቆይታው ታርሞና የህግ የበላይነትን አውቆ መውጣት ይኖርበታል።
ነገር ግን ምንም ሳያጠፋ በተለያየ አመለካከት እስር ቤት የሚቆዩ ሰዎች ነፃ እንዲሆኑ ብዙ ጥረት አድርገናል። ብዙም ተሟግተናል። ባይሳካልንም። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከመጡ በኋላ በሙሉ ይቅርታ በማድረግ አስረኞች በተለይም በአመለካከት የገቡት ወጥተዋል። በወቅቱ እኛ ያቃተንን ነገር እርሳቸው ሞልተውታል።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በአገር ሽማግሌ ምክትል ሰብሳቢነት እያገለገሉ ነው፤ አሁን ደግሞ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ተቋቁሟልና ምን አስተያየት አለዎት?
ፓስተር ዳንኤል፡- እርቀ ሰላም ኮሚሽኑ በመቋቋሙ በጣም ደስተኛ ነኝ። የሚያሠራ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ብዙ ይሠራሉ ብዬም አስባለሁ። እኛም መደገፍ ይኖርብናል። ግን ይህ ኮሚሽን ሲቋቋም እንደ ሃሳብ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለምን አባል ይሆናሉ የሚል አስተያየቶች ሰጥተናል። ገለልተኛ መሆን ስለሚያስፈልገው። በኮሚሽኑ አባል የሚሆን ሰው ቢያንስ አንድ ሰውም ቢሆን እንኳን ያስታረቀና ሙሉ ፍላጎት ያለው ቢሆን የሚል ሃሳብ አቅርበናል። ከዚህ ውጪ ባለው ሁኔታ ግን ኮሚሽኑ መቋቋሙ ብዙ ነገሮችን ይፈታል።
እኛ እኮ በበጎ ፍቃደኝነት እስረኞች ይቅርታ ይደረግላቸው እያልን ስንጠይቅ የሰው ፊት እያየን፤ የምንመራበት የህግ ከለላ ሳይኖር፤ በህገ መንግሥትም በአዋጅም የሚደግፈን ነገር አልነበረም፤ ይህ በአዋጅ የተቋቋመ ኮሚሽን ግን ብዙ ሊሠራ የሚችል እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- አገሪቱ እዚህም እዚያም በሚነሱ ያለመግባባቶች በችግር ውስጥ ናትና ከእናንተ የአገር ሽማግሌ ምክር ቤትም ሆነ ከተቋቋመው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ምን ይጠበቃል?
ፓስተር ዳንኤል፡- በኢትዮጵያ ውስጥ በአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ለአንድ ሁለት ወር ከሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ጋር ቁጭ ብለን በመመካከር በአራቱም ክልሎች በመሄድ ከህዝቡ ጋር ተወያይተናል፤ የሽምግልና ባህላቸው እንዴት ነው የሚያድገው የሚለውንም ለማየት ሞክረናል። በነገራችን ላይ መንግሥትም ሆነ ህዝቡ ሊያውቀው የሚገባው ነገር በአገራችን ችግሮች ተከስተው ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱት 20 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው፤ ሌሎቹ 80 በመቶ የሚሆኑት የሚፈቱት ባህላዊ በሆነ እርቅ ነው።
እናም ለእንደዚህ ዓይነት ማህበራዊ ችግር መፍቻ መሳሪያዎች መንግሥት ትኩረት አልሰጠም፤ አላገዘም። ባለፉት 40 ዓመታት ባህልን ስናጠፋ ነው የቆየነው ግን የሚጠፋ ስላልሆነ አሁንም ቀጥሏል።
በመሆኑም በዚህ ደረጃ ችግሮችን በራሱ የመፍታት ልምድ ያለው ማህበረሰብ ይዘን በጣም የሚወደሰውና የሚወራው ግን መንግሥት የሠራው ብቻ ነው። ስለዚህ የተማርን ሰዎች፣የህግና የፖለቲካ ሊቆች በትንሽ ገንዘብና የሰው ኃይል ባልተማሩ ሽማግሌዎች የሚሠሩ ሥራዎችን ማጣጣል ሳይሆን ማሳደግ ነው ያለብን።
አዲስ ዘመን፡- ይህን መሰሉ ችግርን የመፍቻ ቁልፍ ባህል እያለን ከችግሮች መውጣት ያቃተን ምናልባት ወጣቱ ላይ የሠራነው ሥራ ስለሌለ ይሆን?
ፓስተር ዳንኤል፡- ለዚህ ሥራ ሽምግልናን እውቅና መስጠትና ወደ ቦታው መመለስ ያስፈልጋል፤ ወጣቱ ባለፉት 27 ዓመታት በህገ መንግሥት፣ በፌዴራሊዝም፣በትምህርት ቤት፣ በፖለቲካ የተቃኘውን ቅኝት ማስተካከል አለብን። በሌላ በኩልም በሚያስማሙን ነገሮች ላይ ተስማምተን ሁላችንንም እኩል ባደረገ መልኩ ልንሄድ የምንችልበትን ስርዓቶች መፍጠር አለብን።
እኔ በጣም ነው የማዝነው በየክልሉ ወጣቶች ለትምህርት ሄደው እየሞቱ ነው፤ ችግሩ ደግሞ የሁላችንንም ቤት የሚያንኳኳ ሆኗል፤ በመሆኑም ወደሌላ የከፋ ደረጃ ከመሄዳችን በፊት መመለስ የምንችልበትን መንገድ መዘርጋት ያስፈልጋል።
ተማሪ ለትምህርት ሄዶ ወላጅ አስከሬን የሚቀበልበትን ሂደት በቃ ብለን ልንመልስ ይገባል፤ አገር፣ ብሔር ይኖራል፤ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ሰው ይኖራል እናም ሰዎች በቋንቋቸው መናገራቸውና መዳኘታቸው ደስ ይላል አከብረን መያዝ እንጂ ለመጨራረሻ የምንጠቀምበት ምክንያት ሊሆን አይገባም፤ በመሆኑም ይህ ጎጂ አስተሳሰብ ነው ብለን ማስወገድ የሚጠቅመንን መያዝ ይገባናል።
ይህ ሲባል ደግሞ በተለይም በፌዴራሊዝም ላይ ያለውን አስተሳሰብ ማመጣጠን ያስፈልጋል፤ ለአንዱ ትንሽ ለሌላው ትልቅ ቦታ መስጠት አይገባም። አንድ መረዳት ያለብን ነገር ቢኖር በብሔሬ ተጎድቻለሁ የሚልን አካል በትክክል የተጎዳውን ነገር መጠየቅና ማዳመጥ አለብን፤ ዝም ብለው ነው ማለት ተገቢ አይደለም፤ ይቅርታ መጠያየቅም ካለብን ያንን ማድረግ ይኖርብናል።
በሌላ በኩል ደግሞ የድሮ ፋይሎች መዘጋት አለባቸው በአያቶቻችን በማታውቂው በማላውቀው እኔ ልኮነን አይገባም። እሺ ነገሩም እኔን የሚያስጠይቀኝና ዋጋ የሚያስከፍለኝ ከሆነ ቆም ብሎ በማሰብ «የእኔ አያት ጎድተህ ነበር እኔ በወቅቱ አልነበርኩም ግን ይቅርታ » ብንባባል ብልህነትም ጀግንነትም ነው።
ይህንን ሳናደርግ ግን ያረጁ ያፈጁ ፋይሎቻችንን መቼ ልንዘጋቸው ነው? ቁርሾው እኮ እየቀጠለ ነው የሄደው፤ ይህ ሁኔታ አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል? እንደ አገር ሽማግሌ ደግሞ ለፍትህ አካላት፣ ለህብረተሰቡ እንዲሁም ለመንግሥት የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድን ነው?
ፓስተር ዳንኤል፡- ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደሚጨነቁት እኔም እየተጨነኩ ነው፤ ጸሎትም አደርጋለሁ። በተለይ አሁን ከተከሰተው ኀዘን ጋር ተያይዞ ብዙ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉ። ኤታማዦር ሹምን የሚያህል ሰው የሞተባት አገር፣ የአንድ ክልል በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ህዝቦችን የሚመራ ርዕሰ መስተዳደር የሞተበት ሁኔታ እጅግ ከባድ ነው። በንግግርም የሚያልቅ አይደለም። ችግራችን ከፍቷል፣ ጥልቅም ሆኗል። ለዚህ መፈትሔው ደግሞ ቆም ብሎ በደንብ አሰላስሎ ጥናት ሠርቶ የምናውቃቸውንም ነገሮች ጠረጴዛ ላይ አምጥቶ መወያየት ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ፈሪሀ እግዚአብሔርና ሰፊ ልብ ያለው አብሮ በመኖር ለአፍሪካም ለዓለምም ተምሳሌት የሆነ ነው፤ ሆኖም ከችግሩ የሚያወጣ ፖለቲካዊ መፍትሔ በአስቸኳይ ሊሰጠው ይገባል ፤ ነገር ግን መፍትሔው እስከሚገኝ ድረስ ህዝቡ አገሩንና ሰላሙን መጠበቅ አለበት።
የፖለቲካ አመራሩም አሠራሩን ማስተካከል፣ ችግሮቹን ከንግግር ባለፈ በሲስተም መመለስ መቻል አለበት፤ ይህ ግን ምናልባትም በአንድ ሌሊት ስለማይመጣ ህዝቡ በፍቅርና በትዕግስት መኖር መቻል አለበት።
የፍትህ አካላትም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ በፍጹም ለድርድር የሚያቀርቡት ጉዳይ መሆን የለበት። ፖለቲከኞችና መንግሥት ችግሩ የእናንተን በር እያንኳኳ መሆኑን ተረድታችሁና ከግዴለሽነት ወጥታችሁ ፈጣን የሆነ ለውጥ ማደረግ ይገባችኋል። ምናልባት ይህ ለውጥ አሠራሮችን በመፈተሽ በመቀየር ሲስተሞችን በመቀየርና በቦታው ላይ ያሉ መሪዎችን በማየት ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ በማስቀመጥ ሊገለጽ ይችላል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ምሁራን የሚያለያየንን ሃሳብ ትተን የሚያቀራርበንን ማምጣት የማህበራዊ ድረ ገጽ ተዋናይና አክቲቪስቶችም ነገ በእግዚአብሔርም በታሪክም ተጠያቂ መሆን ስለማይቀር የሚያጠፋፋንን ሃሳቦች ከማቀበል ተቆጥበን በሚያቀራርቡን አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ ብናተኩር። ተማሪዎችም በስሜት ሳይሆን በእውነትና ምክንያታዊ በሆነ ጉዳይ ላይ መነጋጋር መቻልን መልመድ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ጨርሻለሁ አመሰግናለሁ።
ፓስተር ዳንኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሰኔ ሰኔ 26/2011
እፀገነት አክሊሉ