ቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች የሚሰበሰቡበት የምክክር ሂደት

 ዜና ትንታኔ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ የተፈጠሩ አለመግባባቶችንና የሃሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በቀጣይ ዓመት ያካሂዳል። በምዕራፍ የተከፋፈሉና ለምክክሩ የሚያስፈልጉ ሂደቶችን የማከናወን ሥራዎች ከተጀመሩ ደግሞ ከሁለት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡

በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥም በምክክር ሂደቱ ላይ ተሳታፊዎችን የመምረጥ ሥራ በተለያዩ አካባቢዎች ተከናውኗል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የምክክር ሂደቱ ወሳኝ ሚና ያለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ እየተካሄደ ይገኛል። በመዲናዋና በጋምቤላ የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ደግሞ በድሬዳዋና በተለያዩ አካባቢዎች ቀጥሏል።

ታዲያ ይህ የምክክር አጀንዳ በምን መልኩ ይዘጋጃል፤ ምንስ ያካትታል? ለምክክር ሂደቱስ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል? በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ኮሚሽነሮችና አማካሪዎች አነጋግረን ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም እንደሚገልጹት፤ የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ከሚጠይቃቸው ቁልፍ ተግባራት መካከል አጀንዳዎችን ማሰባሰብ ተግባሩ ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡

ኮሚሽኑ በሚተዳደርበት አዋጅ 1265/2014 አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት ከመላ ሀገሪቱ የምክክሩ ዜጎች፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት ሃሳባችንን ያሰሙልናል የሚሏቸውን ተሳታፊዎች ከለዩ በኋላ በክልሎችና በፌዴራል ደረጃ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ያስረዳሉ።

በመሆኑም የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያስፈልጋል የሚሏቸውን እጅግ መሠረታዊ ጉዳዮች በሕዝባዊ ውይይት የሚሰበስቡበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ይህም በኢኮኖሚ፣ማህበራዊ እንዲሁም ከጸጥታ አንጻር የሚነሱ ሃሳቦችና ጥያቄዎች ለማሰባሰብ እንደሚረዳ ያነሳሉ።

የሚሰበሰቡት አጀንዳዎችም ኢትዮጵያውያን በመካከላቸው ያሉ የሃሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችና መፍትሔዎች ዙሪያ በንግግርና ውይይት መፍታት የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያመላክት ግብአት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ኮሚሽኑ ከሚከተላቸው መርሆዎች ውስጥ አካታችነትና አሳታፊነት ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በዚህም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላትን በማካተት እየተሠራ መሆኑን ነው ያስረዱት። እነዚህ ተወካዮችም ከወረዳ ጀምሮ የሚገኙ ሴቶች፣ወጣቶች፣አካል ጉዳተኞች፣ተጽእኖ ፈጣሪዎች ፣መምህራን ፣የመንግሥት ሠራተኞች፣የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሳሰሉት ከተለያዩ ቦታዎች የተመረጡ ተወካዮች ሲሆኑ፤ ይህም እንደ ሀገር ለሚደረገው የምክክር ሂደት ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል ነው ይላሉ።

በየዘርፋቸው ብሎም በክልላቸው ያጋጠሟቸው መሠረታዊና መፍትሔ የሚፈልጉ እንዲሁም በሀገር ደረጃ የሚታዩ እጅግ መሠረታዊ ችግሮችን ነጻና ገለልተኛ በሆነ መንገድ የመለየት ሥራ የሚሠራበት ሂደት በመሆኑ አሳታፊነቱን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ይጠቁማሉ።

ኮሚሽነሩ እንደሚገልጹት፤ በአጀንዳ ማሰባሰብ ላይ ሁሉምን አሳታፊ ማድረጉም በየዘርፉ የሚያነሱትን ጥያቄዎችና አጀንዳዎች ለማካተት የጋራ ሀገራዊ መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል። የተሰበሰቡት አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ቀርበው ሰላምና ደህንነቷ የተጠበቀ ሀገር ለመገንባት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚለዩበት ወሳኝ የምክክር ምእራፍ ነው፡፡

በቀጣይም ኮሚሽኑ ከቀረቡት አጀንዳዎች ውስጥ እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮችን በመለየት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክር ቤት የሚቀርብ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በመጨረሻም ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ይጠራል፡፡በዚህም ቁጥራቸው ከ2ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በጉባኤው የምክክር ሂደት በማድረግ ለጉዳዩ የመፍትሔ ሃሳቦችን ያቀርባሉ ሲሉ ሂደቱን ያብራራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማካሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ በበኩላቸው፤ ለምክክሩ የሚሰበሰቡ አጀንዳዎች በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ችግሮችና መፍትሔ ላይ እንዲሁም ወደ ሰላም ለመግባት እንደሀገር ምን ይጠበቃል የሚሉ ወሳኝ ጉዳዮችና ጥያቄዎች የሚወጡበት ነው ይላሉ።

በሀገራዊ ምክክር ቀርበው ውይይት ሊደረግባቸው ይገባቸዋል የሚሉትን መሠረታዊ ችግሮችና ሃሳቦች በመለየት ያወጣሉ፡፡ ከዚህም በኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት መፈታት ያልቻሉ አጀንዳዎች ከተለዩ በኋላ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የሚለዩ ይሆናል ሲሉ ያመላክታሉ።

ፕሮፌሰር አድማሱ እንደሚገልጹት፤ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ ሴቶች፣ወጣቶች፣በተለያዩ የሥራ መስክ የተሠማሩ ባለሙያዎች ፣የሃይማኖት አባቶች፣ተጽእኖ ፈጣሪዎች፣አካል ጉዳተኞች ፣በተለያየ መልኩ የተገለሉ የማህበረሰብ አካላትን ጨምሮ እስከ ላይኛው እርከን ያካተተ ሲሆን፤ ሁሉም በዘርፋቸው አጀንዳዎቻቸውን በማሰባሰብ ሁለንተናዊ ነገሮችን ለመያዝ ያስችላል፡፡

እንደ አንድ ሀገር ዜጎች የተቀራረበ አስተሳሰብ ልንይዝባቸው በሚገቡ ሃሳቦችና ጉዳዮች መሸርሸር ተከትሎ ሳይፈቱ የተንከባለሉ ወይም አዲስ የተፈጠሩ ችግሮች አሉ፡፡ ይህም ሀገሪቱ በየአካባቢው ግጭቶች እና መፈናቀል ያስከተለ ሲሆን፤ ያለው አሳሳቢ ሁኔታ ወደ ምክክር እንድትገባ የሚያስገድድ ነው ይላሉ፡፡

በምክክሩ መካከል ያለውን ልዩነት የሚያስማማ ሃሳብ እንዲኖረን የማድረግ ዓላማ ያለው ነው፡፡ በዚህም ያለውን አለመግባባት ከማስቆም ባለፈም ወደበጎ መስመር በመቀየር በየዘርፉ የተሻለ አዲስ የዲሞክራሲያዊ ባህል መፍጠር ያስችላል ሲሉ ፕሮፌሰር አድማሱ ያመላክታሉ።

በመሆኑም ከየማህበረሰብ ክፍሎች የተመረጡ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ያለውን ፋይዳ በመረዳት ቁልፍ የሆኑ አጀንዳዎችን በማሰባሰብ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ይገልጻሉ። ኮሚሽነሩና አማካሪው እንደተናገሩት፤ የምክክር ሂደቱ ወሳኝ ምዕራፍ የሆነው የአጀንዳ ማሰባሰብ አሳታፊ፣ ግልጽና መፍትሔ የሚያመጣ ሂደቱን እንደተጠበቀ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You