እነሆ ዛሬ 180ኛ ዓመት ተቆጠረ:: ከ180 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ተወለዱ:: አጼ ምኒልክ ከኢትዮጵያ ነገሥታት ሁሉ ስማቸው ጎልቶ ይጠቀሳል:: አንዱና ዋናው የዓድዋ ድል ነው:: ይህ ዓለም አቀፍ ዝና አስገኝቶላቸዋል:: የጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነፃነት ተምሳሌት የሆነው ዓድዋ በአጼ ምኒልክ የሚመራ ነበርና የጥቁር ሕዝብ የጀግና ተምሳሌት አድርጓቸዋል::
የዛሬው ሳምንቱ በታሪክ ድንቅ የታሪክ ግጥምጥሞሽ ያለበት ነው:: ይሄውም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጎልተው የሚታወቁት አጼ ምኒልክ እና ባለቤታቸው በአንድ ቀን የተወለዱ መሆናቸው ነው:: በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸውን ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና ባለቤታቸውን እቴጌ ጣይቱን ያስታውሰናል:: ባልና ሚስት በሃይማኖታዊ አገላለጽ ‹‹አንድ አካል አንድ አምሳል›› ይባላሉ፤ አንድ ናችሁ ለማለት ነው:: የዳግማዊ አጼ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ባልና ሚስትነት ይህን አገላለጽ ያሟላል:: አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነው አንዲት ሀገር ገንብተዋል:: አንዲት ኢትዮጵያን አጽንተዋል:: ዓድዋን የሚያክል ዓለም አቀፍ ግዙፍ ድል አስመዝግበዋል:: ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ተምሳሌት እንድትሆን አድርገዋል:: የእነኝህ ንጉሥና ንግሥት ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ደግሞ የተወለዱበት ቀን ተመሳሳይ መሆኑ ነው:: የዓመተ ምህረት ልዩነት ቢኖረውም ሁለቱም ነሐሴ 12 ቀን ነው የተወለዱት:: ይህ ብቻ አይደለም ግጥምጥሞሹ፤ የዓድዋው ጀግና ፊታውራሪ ገበየሁም የተወለዱት ነሐሴ 12 ቀን ነው:: የእቴጌ ጣይቱን እና የዳግማዊ አጼ ምኒልክን ታሪክ ዘርዘር አድርገን እናያለን::
ጣይቱ ብጡል ከ184 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ልክ በዛሬዋ ቀን ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም ጎንደር ውስጥ ፋርጣ በታሪካዊቷ ደብረ ታቦር ከተማ ተወለዱ:: አባታቸው ደጃች ብጡል ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ የደብረ መዊዕ እመቤቷ ወይዘሮ የውብዳር ናቸው:: ‹‹እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ›› በሚል ስም ይታወቃሉ:: የዘር ሐረጋቸውም ከጎንደር፣ ከስሜን፣ ከጎጃምና ከየጁ ወረ ሴህ ይመዘዛል:: በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወርቃማ ስም ካላቸው ሴት የነገሥታት ሚስቶች አንዷ ናቸው::
እንደነ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ያሉ የታሪክ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ እቴጌ ጣይቱ የትውልድ ሐረጋቸው ከብዙ የሰሜን ኢትዮጵያ መሳፍንት ጋር መተሳሠሩ ለንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፤ ግዛታቸውን ለማደላደል አግዟቸዋል:: የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ከእቴጌ ጣይቱ ጋር መጋባት ጠቀሜታው በክብር ብቻ ሳይሆን በፖለቲካም ጭምር ነበር::
በቤተ ክህነት ብዙ መንፈሳዊ ትምህርት፣ ሕግና ሥርዓት የተማሩት እቴጌ ጣይቱ፤ ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጋር ሚያዚያ 25 ቀን 1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኒዓለም በቁርባን ጋብቻቸውን ፈጸሙ:: ከዚያ በኋላ የንጉሠ ነገሥቱ ሚስት ብቻ ሳይሆኑ በብዙ ምክሮች ስማቸው የሚጠራ የዳግማዊ ምኒልክ ስኬታማ የአስተዳደር ዘመን ምክንያት ለመሆን በቁ:: ታላቁ የዓድዋ ድል ስኬት የእቴጌ ጣይቱ ብልህነት የተሞላበት ለመሆኑ ዓድዋ በመጣ ቁጥር ሲተረክ የምንሰማው ነው::
ጥንዶቹ አጼ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ንጉሠ ነገሥት እና እቴጌ ተብለው ሲሰየሙ ከተለያዩ የየአካባቢው ገዢዎች ጋር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጥምረት በመፍጠር አልያም ወታደራዊ አቅም በመጠቀም የበለጠ ግዛታቸውን አስፋፍተዋል።
እቴጌ ጣይቱን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስማቸው በተደጋጋሚ እንዲነሳ የሚያደርጋቸው በዓድዋ ጦርነት ጊዜ የነበራቸው ድፍረት እና ብልህነት ነው:: ከጣሊያን ጋር ከተደረጉ ስምምነቶች መካከል ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዢ ሊያስደርጋት የነበረው የውጫሌውን ስምምነት ውል አንቀፅ 17 ውድቅ በማድረግ ይታወቃሉ። መቀሌን ተቆጣጥረው የነበሩትን የጣሊያን ወታደሮች ለማሸነፍ እንዲቻል ጣይቱ ባቀረቡት ሃሳብ ይታወቃሉ። በዚህም መሠረት ጣሊያኖች የሚጠቀሙበትን የውሃ ምንጭ በኃይል በመቆጣጠር ከመቀሌ እንዲወጡ ለማስደረግ ተችሏል። ጣይቱ ብጡል ጣሊያኖች በተሸነፉበት እና በድል በተጠናቀቀው የዓድዋ ጦርነት በነበራቸው ሚናም ይታወቃሉ። እቴጌ ጣይቱ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ የሞከረውን የጣሊያን ጦር ለመዋጋት በስራቸው 5000 እግረኛ እና 600 ፈረሰኞችን አሰልፈው ነበር።
እቴጌ ጣይቱ ለዚህኛው ዘመን ሴቶች ተምሳሌት ሆነው ይጠቀሳሉ:: ለብዙ ነገሮችም ስያሜ መሆን ችለዋል:: ጣይቱ ማለት ስም ብቻ ሳይሆን ጀግንነት፣ ብልህነት ማለት መስሏል:: ይህ የሆነው በእቴጌ ጣይቱ ነው::
እቴጌ ጣይቱን ታሪክ በሰፊው ያስታውሳቸዋል:: በስማቸው ብዙ ነገሮች ተሰይመዋል:: ብዙ ዘፈኖች ተዘፍነዋል:: ‹‹የኛ›› የሙዚቃ ቡድን በ2006 ዓ.ም ካወጡት የጋራ ዘፈን ውስጥ እነዚህን ስንኞች እናገኛለን::
ኩሩ ንግሥት የሴት አርበኛ
አትንኩኝ ባይ ፍርድ አወቅ ዳኛ
ለነፃነት ፋና የሆነች
ብልህ ጀግና እመቤት ማነች?
ፀሐይ ሆና ሀገር የሞቃት
ፊት አውራሪ ዓለም ያወቃት!
በቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ጥቁር ሰው›› ዘፈን ውስጥ ደግሞ ይቺን ስንኝ እናገኛለን::
የቀፎው ንብ ሲቆጣ ስሜቱ
ከፊት ሆና መራችው ንግሥቲቱ
እቴጌ ጣይቱ ከባለቤታቸው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ሕልፈት አራት ዓመታት በኋላ ባደረባቸው ህመም የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ.ም በ78 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፤ ሥርዓተ ቀብራቸውም ራሳቸው ባሰሩት በእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል::
በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ ውስጥ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ትልቅ ቦታ ያላቸው ንጉሥ መሆናቸው ተደጋግሞ ሲነገር የቆየ ነው:: የታሪክ ባለሙያዎች እንደሚሉት አሁን ያለው የኢትዮጵያ ቅርጽ በአጼ ምኒልክ የሀገር ግንባታ ሂደት የተገነባ ነው:: የብልህነትና የታጋሽነት ምሳሌ ይደረጋሉ:: በ1874 ዓ.ም በተደረገው የእምባቦ ጦርነት የጎጃሙ ንጉሥ ተማረኩ፤ ተማርከውም ንጉሥ ምኒልክ ጋ ደረሱ:: የእምባቦ ጦርነት በሸዋው ንጉሥ ምኒልክ እና በጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት የተደረገ ጦርነት ነው:: ንጉሥ ምኒልክ በትህትና እና በጨዋ ደንብ ሲነግሯቸው ንጉሥ ተክለሃይማኖት ተገረሙ:: ንጉሥ ምኒልክም ንጉሥ ተክለሃይማኖትን ‹‹አንተ ብትሆን ምን ታደርገኝ ነበር?›› ሲሉ ጠየቋቸው:: ንጉሥ ተክለሃይማኖትም ስሜታቸውን አልደበቁም:: ‹‹ጠላት ሆነን እየተዋጋን ነው፤ አልዋሽህም እኔ ብሆን እገልህ ነበር›› በማለት ንጉሥ ምኒልክን ‹‹አንተማ እናት ነህ!›› አሏቸው:: ‹‹እምዬ ምኒልክ›› የሚለው የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ቅጽል ስም የመጣው በዚህ ምክንያት ነው ይባላል::
እኝህ የኢትዮጵያ ታላቅ ንጉሥ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የተወለዱት ከዛሬ 180 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ከአባታቸው ንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ እና ከእናታቸው እጅጋየሁ ለማ ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም በሸዋ አንኮበር አንጎለላ ነው:: አካባቢውም አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ይባላል:: ቦታው ዛሬ ድረስ ዓድዋ በመጣ ቁጥር ጉብኝት ይደረግበታል::
ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ሸዋን ለማስገበር ከጎንደር ወደ ሸዋ በሄዱበት ወቅት ንጉሥ ኃይለመለኮት ታመው ሲሞቱ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ልጅ ምኒልክን ወደ መቅደላ ይዘዋቸው ተመለሱ:: ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኋላ፣ በ1857 ዓ.ም ልጅ ምኒልክ ከመቅደላ አምልጠው ሸዋ ገቡ፤ የአባታቸውን የንጉሥ ኃይለመለኮት ሳሕለሥላሴን አልጋ ወረሱ:: ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆኑ:: ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በንግሥና ዘመናቸው የሠሯቸው ዓለም አቀፋዊና የሀገር ውስጥ ሥራዎች በየታሪክ አጋጣሚው የሚነገሩ ናቸው::
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ባደረባቸው ህመም ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም በ69 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፤ ሥርዓተ ቀብራቸውም ራሳቸው ባሰሩት በባዕታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል::
በዚሁ ቀን የተወለዱት ፊት አውራሪ ገበየሁ ሌላኛው የዚህ ሳምንት የታሪክ አካል ናቸው:: የንጉሠ ነገሥቱ የመሐል ጦር አዛዥ የነበሩት ፊታውራሪ ገበየሁ ከጣልያኖች ጋር በተደረጉ በሁሉም ጦርነቶች ጀግንነታቸውን ያስመሰከሩ ሀገር ወዳድ ሰው ነበሩ:: ዋነኛው የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት ዓድዋ ላይ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ አምባላጌ ላይ በተደረገው ውጊያ የአምባላጌውን ምሽግ በመስበር በጣሊያን ላይ የመጀመሪያውን የድል ደወል ያሰሙትና ዋናው የድሉ ባለቤት እርሳቸው ነበሩ:: በዚህም ምክንያት በወቅቱ የፈረንሳይ ጋዜጦች ‹‹የአምባላጌው የኢትዮጵያ ጀግና›› በማለት እንዳወደሷቸው አንጋፋው የታሪክ ፀሐፊ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ጽፈዋል::
ፊታውራሪ ገበየሁ ገና ወደ ዓድዋ ሲዘምቱ ‹‹ስሸሽ ከኋላዬ ከተመታሁ አሞራ ይብላኝ፤ ከፊት ለፊት ስፋለም ከወደቅሁ ግን ሬሳዬን አፅሜን ትውልድ ቦታዬ ውሰዱልኝ›› በማለት ተናዘውም ነበር ይባላል:: ይህ ንግግራቸውም ዓድዋ በመጣ ቁጥር ይነገራል:: ከጠላት ጋር በፅናት ሲፋለሙ ስለ ሀገራቸው ነፃነት ዓድዋ ላይ ወደቁ:: በኑዛዜያቸው መሠረትም ከሞቱ ከሰባት ዓመት በኋላ አፅማቸው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተወስዶ እዚያው አረፈ::
የዓድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው!
ተብሎም የተገጠመላቸው ለዚህ ጀግና ነው::
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ በየዓመቱ ነሐሴ 12 ቀን ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ (ፒያሳ) በሚገኘው ጣይቱ ሆቴል የመታሰቢያ ፕሮግራም ሲዘጋጅላቸው እንደነበር ይታወሳል:: እነሆ በአንድ ቀን የተወለዱትና አንዲት ኢትዮጵያን አጽንተው ያቆዩት ባልና ሚስቱ በታሪክ ሲታወሱ ይኖራሉ::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን እሁድ ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም