ከፍተኛ ትኩረት የሚሻው የወርቅ ኮንትሮባንድ

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ላይ ሕገ ወጥ ወይም በተለምዶ የኮንትሮባንድ ንግድ በርካታ አሉታዊ ተጽእኖዎችን ሊያስከትል ይችላል። ከነዚህም ውስጥ ቀዳሚው የኢኮኖሚ ውድመት ነው ፤ሕገ-ወጥ ንግድ ሕጋዊ የንግድ ድርጅቶችን በማዳከም የመንግሥትን ገቢ ይጎዳል። ታክስ እና ቀረጥ ይቀንሳል። እንዲሁም የገበያ ዋጋን ያዛባል። እንዲሁም ማህበራዊ ቀውሶችን ያስከትላል። ሥራ አጥነትን በማባባስ በዜጎች መካከል ከፍተኛ የሀብት ልዩነት ይፈጥራል። በተጨማሪም፣ የተደራጁ ወንጀሎች እና ሙስና እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ በማድረግ መረጋጋት እንዳይኖር ያደርጋል።

የኮንትሮባንድ ንግድ በዜጎች ጤናና ደህንነት ላይ አደጋ ይደቅናል። በኮንትሮባንድ የሚገቡ መድሃኒቶች ወይም ደህንነታቸው ያልተረጋገጠ የፍጆታ ምርቶች በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ የጤና ጠንቅ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ኮንትሮባንድ የመንግሥት ተቋማትን በማዳከም ሕገ-ወጥ ንግድን ሙስናን እና ጉቦን በማስፋፋት የሕግ የበላይነትን ስለሚያዳክም የተደራጁ ወንጀለኞች እንዳሻቸው እንዲፈነጩ በማድረግ ሥርዓት አልበኝነትና አጠቃላይ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል።

እንዲሁም አካባቢያዊ ጉዳት ያስከትላል። በዱር እንስሳት ወይም በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደረግ ሕገ-ወጥ ንግድ የአካባቢ መራቆትን፣ ብዝሃ ሕይወትን መጥፋት እና ዘላቂ ያልሆነ የሀብት ብዝበዛን ያስከትላል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ጠንከር ያለ የሕግ ማስከበር፣ የተሻለ የድንበር ቁጥጥር እና ዓለም አቀፍ ትብብርን የሚያካትቱ አጠቃላይ ስልቶችን ይፈልጋል።

በሀገራችን እየተባባሰ የመጣው የጦር መሣሪያ፣ ወርቅን ጨምሮ የከበሩ ማዕድናት፣ የቁም እንስሳት፣ የመድሃኒት፣ የውጭ ምንዛሬ፣ የግንባታ ቁሳቁስ፣ የኤሌክትሮኒክስ፣ የልባሽ ጨርቅና የሌሎች ሸቀጣሸቀጥ የኮንትሮባንድ ንግድ በኢኮኖሚያችን ብቻ ሳይሆን በሀገራችን ህልውና ላይ አደጋ እየደቀነ ነው። በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ኢንዱስትሪና ፋብሪካ አልባ እንዳያደርገን ያሰጋል።

በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በትግራይ ክልል ያለው የወርቅ የኮንትሮባንድ ንግድ የውጭ ዜጎችን ሳይቀር ያሳተፈ፣ በተደራጁ ወንጀለኞች የሚመራ ከመሆኑ ባሻገር ለወርቅ ማውጫ የሚጠቀመው ኬሚካል አካባቢ እየበከለ ይገኛል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ለብሔራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ እየቀነሰ በኮንትሮባንድ ስለሚወጣ የሀገር ኢኮኖሚ እየደማ ይገኛል። ብሔራዊ ባንክ ወርቅን በዕለቱ የምንዛሬ ዋጋ እንደሚገዛ ቢያሳውቅም ሕገ ወጥ ንግዱ ፈተና መሆኑን ቀጥሏል።

ኮማንድ ፖስትና ብሔራዊ ደህንነት ጣልቃ ቢገቡም የወርቅ ኮንትሮባንድ ሊቆም አለመቻሉን በዚያ ሰሞን የመገናኛ ብዙሃን አጀንዳ ነበር። በዚህ የተነሳ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የማዕድን ኮሚቴ አዲስ መርሐ ግብር ለማዘጋጀት ተገዷል። በመከላከያ ኮማንድ ፖስትና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጭምር ክትትል ቢደረግም፣ በክልሎች እየጨመረ የመጣው የወርቅና የማዕድናት ኮንትሮባንድ ሊቆም አልቻለም::

በማዕድናት ሕገወጥ ግብይት፣ ኮንትሮባንድና የፀጥታ ችግር ምክንያት በዘጠኝ ወራት ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው ወርቅ ሦስት ቶን ብቻ እንደሆነ፣ ይህም ከዕቅዱ 50 በመቶ ብቻ መሆኑ ታውቋል:: የወርቅ ገቢም ከታቀደው 363 ሚሊዮን ዶላር 67 በመቶ ብቻ መሳካቱን ለማወቅ ተችሏል:: በመጋቢት ወር ብሔራዊ ባንክ የገባው ወርቅ 350 ኪሎ ግራም ሲሆን፣ ይህም በ2014 ዓ.ም. መጋቢት ወር ከተገኘው 800 ኪሎ ግራም በእጅጉ ያነሰ ነው ተብሏል::

በሀገሪቱ ያሉ ወርቅ አምራቾች የባህላዊና የኩባንያ ተብለው ሲከፈሉ፣ በተለይ በባህላዊ አምራቾች የሚወጣው ወርቅ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባት ያቆመ መሆኑን፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከታቀደው 2‚306 ኪሎ ግራም ውስጥ 609 ኪሎ ብቻ (26 በመቶ) መቅረቡን መረዳት ተችሏል:: በተለይ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ካቀዱት አንፃር የቀረበው እጅግ አናሳ መሆኑን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የማዕድን ሚኒስቴር ሪፖርት ያሳያል::

ይሁን እንጂ ፈጽሞ ወርቅ ካላቀረቡት የትግራይ፣ የአፋር፣ የደቡብ ኢትዮጵያና የሶማሌ ክልል አንፃር የበፊቶቹ እንደሚሻል ሪፖርቱ ያሳያል:: በኩባንያዎች ከቀረበው 2‚400 ኪሎ ግራም ወርቅ ውስጥ ሚድሮክ ጎልድ በከፍተኛ መጠን ያቀረበ ሲሆን፣ ወደ ሥራ ገብተዋል የተባሉ ሌሎች ዘጠኝ የወርቅ ኩባንያዎች ሲደመሩ ያቀረቡት ከ100 ኪሎ ግራም በታች ነው:: ከእነዚህም ውስጥ ስቴላ፣ ዙምባራ፣ ኦሮሚያ ማይኒንግ ኤልኔት፣ ኢዛናና ኢትኖ ማይኒንግ የሚባሉት ይገኙበታል:: በተለይ ኢዛና 375 ኪሎ ግራም አቀርባለሁ ቢልም ምንም ዓይነት ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዳላስገባ በሪፖርቱ ተመላክቷል::

ከወርቅ በተጨማሪም የታንታለም አፈጻጸም 40 በመቶ ብቻ የተሳካ ሲሆን፣ ኦፓል 49 በመቶ ነው:: በአንፃሩ የሊትዬም፣ የጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ማዕድናት የወጪ ንግድ የተሻለ አፈጻጸም ታይቶበታል:: አብዛኛው የባህላዊ አምራቾች ወርቅ በሕገወጥ ግብይትና በኮንትሮባንድ ከሀገር የሚወጣ መሆኑን፣ በአንፃሩ ኩባንያዎች ደግሞ በፀጥታ ምክንያት ወደ ሥራ ሊገቡ እንዳልቻሉ ሪፖርቱ ያትታል::

በተለይ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያና በደቡብ አካባቢዎች በወርቅ ማውጫ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እንዲጠበቁና የክልል መንግሥታት ከኮማንድ ፖስትና ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ መደረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል::በእነዚህ ክልሎች ፕሬዚዳንቶች፣ የቢሮ ኃላፊዎችና የማዕድን ማውጫ አካባቢዎች አስተዳዳሪዎች ከኮማንድ ፖስት ኃላፊዎችና ከፌዴራል ተወካዮች ጋር ርብርብ እያደረጉ መሆናቸው ተገልጿል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀደም ባለ የባህር ዳር የብልፅግና ፓርቲ ስብሰባ ላይ የወርቅና የማዕድናት ኮንትሮባንድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው፣ በተለይ አሶሳና ሽሬ ከፍተኛ የሕገወጥ ወርቅ ዝውውር መተላለፊያ መሆናቸውን አስረድተው ነበር:: በተለይ ሕገወጥ ወርቅ በሱዳን፣ በኬንያና በሶማሊያ ድንበሮች ከሀገር በመውጣት በዋናነት ዱባይና ህንድ እንደሚደርሱ፣ እንዲሁም እስከ ኡጋንዳ ድረስ ከዚያም ወደ ዱባይ የሚያመራ ሰንሰለት እንዳለ ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ::

በሕጋዊውና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የምንዛሪ ክፍተት ዋነኛው የችግሩ ምንጭ እንደሆነም በሪፖርቱ ተጠቅሷል:: ከጥቂት ወራት በፊት ብሔራዊ የማዕድን ልማት አስተባባሪ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ አመራሮችና የክልል ፕሬዚዳንቶች የኮሚቴው አባል ናቸው:: በአሁኑ ጊዜ ኮሚቴው በማዕድን አምራች አካባቢዎችና በማዕድን ኩባንያዎች ፕሮጀክቶች በመገኘት ምልከታና አሰሳ ካደረገ በኋላ፣ የማዕድናት ኮንትሮባንድን ለማስቀረት አዲስ የድርጊት መርሐ ግብር እያረቀቀ መሆኑን በሪፖርቱ ተጠቁሟል::

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በአንድ አጋጣሚ እንዳሉት፣ የወርቅ ምርት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱ የኤክስፖርት ምርቶች መካከል አንዱ ነው። ‹‹ከጥቂት ዓመታት በፊት ከወርቅ ኤክስፖርት ብቻ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፤›› ብለው እንደገለጹትም፣ በ2014 ዓ.ም. ከወርቅ ኤክስፖርት ብቻ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 672 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን በማዕድን ሚኒስቴርና በብሔራዊ ባንክ ይፋ ከተደረጉ የሰነድ መረጃዎች ለመገንዘብ ተችሏል። በ2014 ዓ.ም. ብቻ ሳይሆን ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ከወርቅ ኤክስፖርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል።

በእነዚህ ከፍተኛ ገቢ በተገኘባቸው ዓመታት በባህላዊ የወርቅ አምራቾች ተመርቶ ለገበያ የቀረበው የወርቅ መጠን በአማካይ 9,000 ኪሎ ግራም የነበረ ሲሆን፣ አልፎ አልፎም እስከ 12 ሺህ ኪሎ ግራም ተመርቶ ለብሔራዊ ባንክ ቀርቦ እንደሚያውቅ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከ2010 እስከ 2011 ዓ.ም. ጨርሶ ምርት አለተመረትም በሚያስብል ደረጃ አንድ ሺህ ኪሎ ግራም ብቻ ነበር የተመረተው። በ2015 ዓ.ም. ግን በእጅጉ በማሽቆልቆል 3,900 ኪሎ ግራም ወርቅ ብቻ ነው ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው።

የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) ከ2000 ዓ.ም. አንስቶ ለ15 ዓመታት በባህላዊ አምራቾች የተመረተውን የወርቅ ምርት መጠን መረጃ በመዳሰስ፣ ለዓመታት የቀረበውን የወርቅ ምርት መጠን ሁኔታ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል። በዚህም መሠረት ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ለብሔራዊ ባንክ የሚያቀርቡት የወርቅ መጠን ቋሚ ሳይሆን በየዓመቱ የሚዋዥቅ ነው። የ15 ዓመታት የወርቅ ምርት አቅርቦት ሁኔታን በመዳሰስ ባቀረቡት ሪፖርትም፣ ባህላዊ አምራቾች ለብሔራዊ ባንክ የሚያቀርቡት የወርቅ መጠን በሕጋዊና በጥቁር ገበያው መካከል ባለው የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነት እንደሚወሰን አስረድተዋል።

ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ባለፉት 15 ዓመታት በባህላዊ ወርቅ አምራቾች ተመርቶ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው ትልቁ የወርቅ መጠን 12 ሺህ ኪሎ ግራም ሲሆን፣ ትልቁ ዓመታዊ አማካይ ደግሞ 9,000 ኪሎ ግራም ነው። ከዚህ የወርቅ መጠንም በአማካይ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል። ለብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ወርቅ በቀረበባቸው በእነዚህ ዓመታት በሕጋዊና በጥቁር ገበያው መካከል የነበረው የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነት ጠባብ እንደነበረ፣ በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ በዓለም የወርቅ ዋጋ ላይ እስከ 35 በመቶ ማበረታቻ ጭማሪ በማድረጉ ከፍተኛ ወርቅ እንደቀረበለት አስረድተዋል።

በአንፃሩ፣ የጥቁር ገበያው የምንዛሪ ተመን ከሕጋዊ ገበያው በከፍተኛ ልዩነት በጨመረባቸው ዓመታት፣ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን እጅግ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። የማዕድን ሚኒስትሩ ሲያጠቃልሉም፣ ‹‹የባህላዊ የወርቅ ምርትን ችግር ውስጥ የከተተው በሕጋዊና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ተመን መስፋት ነው፤›› ብለዋል።

በወርቅ ኮንትሮባንድ ረገድ ያሉትን ችግሮች በየመልካቸው ተረድቶ ከክልሎች ጋር ለመሥራት ያደረጉት ጥረት ቀላል አለመሆኑን የተናገሩት የጉምሩክ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቀበታ፣ አንደኛው መፍትሔ ለወርቅ አምራቾች ፈቃድ በሚሰጡ ክልሎችና በአምራቾቹ መካከል ያለውን ግንኙነት የጠራ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ‹‹ፈቃድ የተሰጠው አምራች በየዓመቱ ምን ያህል ወርቅ የማምረት ዕቅድ እንዳለው ታውቆ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፤›› ሲሉ ኮሚሽነሩ ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ በበኩላቸው፣ የሚመረተው ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲመጣ ለማድረግ የተለያዩ የአጭር ጊዜ የመፍትሔ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል። አንደኛው ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከዓለም የወርቅ ገበያ ዋጋ በተጨማሪ ከ60 እስከ 70 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲመጣ ማድረግ ነው። በመሠረታዊነት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የማዕድን ዘርፍ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ብሔራዊ የማዕድን ካውንስል የተቋቋመ መሆኑን፣ ይህም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማቀናጀት የተሻለ ሥራ ለማከናወን መታቀዱን ገልጸዋል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ (ኢንጂነር)፣ የተቋቋመው ብሔራዊ የማዕድን ምክር ቤት በዘርፉ ላሉት መሠረታዊ ችግሮች መፍትሔ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። በዚህ ምክር ቤት የመጀመሪያ ውይይት ላይም በማዕድን ዘርፍ ያለውን ኮንትሮባንድና የፀጥታ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የማዕድን ፖሊስ ሠራዊት እንዲደራጅ መወሰኑን አክለዋል። በዘላቂነት ደግሞ የወርቅ ሀብቱ ኃላፊነት በሚሸከሙ ከፍተኛ ወርቅ አምራች ኩባንያዎች እንዲመረት ማድረግ፣ የሀገሪቱን ጥቅም መጠበቅ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ሻሎም ! አሜን።

 

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

 

አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You