ከፓርቲ በላይ የሕዝብ አንድነት፣ሰላምና ህልውናን ማስጠበቅ ይገባል

የታሪክ ተመራማሪና የፍልስፍና አዋቂው ፕሮፌሰር ዩቫል ኖህ ሐረሪ ዓለማችን ካፈራቻቸው ድንቅ ሥራዎችን ካበረከቱ ምሁራን መካከል በበርካቶች ዘንድ በግንባር ቀደምትነት ስማቸው ይጠቀሳል፡፡ እስራኤላዊው ፕሮፌሰር በተለይም Sapiens /ሳፒየንስ/ እና 21 Lessons for the 21st Century በሚል ባሳተሟቸው መጽሐፍ ይበልጡን ይታወቃሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ ሁለተኛ ላይ በተጠቀሰው ሥራቸው በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ ሊማርባቸው ይገባል ብለው ከዘረዘሯቸው 21 ነገሮች ውስጥ ጦርነት አብላጫውን ቦታ ይወስዳል፡፡

ፕሮፌሰሩ እኤአ በ2018 ባሳተሙት በዚህ መጽሐፍ የጦርነትን አስከፊነት በጥልቀት ከመተንተን ባሻገር የሰው ልጅ በታሪኩ ካሳለፋቸው ጦርነቶች ሊማር ግድ ስለመሆኑና በጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለ መለስ ብሎ መቃኘት እንደሚገባ አጽንኦት ይሰጡታል፡፡

እንደ እርሳቸው ሁሉ የጦርነትን አስከፊነት በሚመለከት በርካቶች ጽፈዋል፡፡ ስለ ሰላም ብዙዎች ዘምረዋል፡፡ አዚመዋል። አያሌዎች ሕይወታቸውን ሰውተዋል፡፡ ሰላምን ሁሉም በተግባር ይፈልገዋል፡፡ ይፈቅደዋል፡፡የተለየ ዋጋ ይሰጠዋል፡፡ በሁሉም ባህሎችና እምነቶች እንዲሁም ሕዝቦች ዘንድ ሰላም ከፍተኛ ዋጋ አለው፡፡

ሰላምን የማያስተምር እምነት የለም፡፡ በየቤተ እምነቱ በሚደረጉ ፀሎቶችም ሰላም ከቀዳሚ ርዕሶች የመጀመሪያው ነው፡፡ ሕዝብ እንደ የእምነቱ ፈጣሪን እለት እለት በሰላም ያሳደርከኝ በሰላም አውለኝ ከማለት አልፎ፤ ለሀገሩ፣ለሕዝቡ ሰላም መሆን ይመኛል፡፡ ይፀልያል፡፡

በተለይ በፖለቲካው ዓለም ፉክክርና የትግል ተሳትፎ ሁለናተናዊ ሰላም እውን ይሆን ዘንድ ከሀገርና ከሕዝብ በፊት ሥልጣንን ማስቀደም፣ ከራስ ክብርና ዝና በላይ ለሌላው አለመጨነቅና ዕብሪት አሸቀንጥሮ ማስወገድ የግድ ይላል፡፡ ልዩነትን ማቀራረብ ወይም ቅራኔን ማርገብ የሚቻለው በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ እንጂ፣‹‹የምፈልገውን አስፈጽማለሁ›› በሚል ጀብደኝነት አይደለም፡፡

ሰላምን በጉልበት የማምጣት ሙከራዎችም በአብዛኛው ትርፋቸው መከራ ነው፡፡ በጉልበትና በጠመንጃ የሚጠበቅ ሰላም ቀን ጠብቆ ፍርክርኩ መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡አንዳንድ ፀሐፍት እንዳውም በጉልበት የተገኘ ድል ከሽንፈት እኩል ያነፃፅሩታል፡፡ ምክንያታችን የሚሉት ደግሞ ጊዜያዊ መፍትሄ መሆኑን ነው፡፡

ኢትዮጵያ ታሪክ በቀደሙት ዓመታት አንድ ችግር ሲያጋጥምና ሰላም ሲደፈርስ ተነጋግሮ መፍትሔ ለማፍለቅ ከመትጋት ይልቅ ዱላ መምዘዝ የተለመደ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ግጭትን ወይም ጦርነትን ሙጥኝ በማለት ዓላማን ለማስፈጸም ጥድፊያው ሲበረታም ይታያል፡፡ ይህን ተከትሎም በየጊዜው የሰላም አየር ይደፈርሳል፡፡

የሩቁን ትተን የቅርቡን እንኳን ብናስታውስ ሀገሪቱ የሰሜኑ ጦርነት ባስከተለው ሁለንተናዊ ቀውስ ከባድ መንገራገጮችን ወይንም shocks ውስጥ ቆይታለች፡፡ በጦርነቱ ምክንያት በርካቶች ሞተዋል፡፡ ከአካላዊና ከሥነ ልቦናዊ ጉዳት በተጨማሪ ከሞቀ ጎጃቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ግምቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የሕዝብና የሀገር ሀብት ወድሟል፡፡

ይህ ቀውስ እልባት ያገኝ ዘንድ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ንግግር ሃሳብን በዋናነት ሲደግፉና እንዲጀመር ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ መቆየቱም የሚታወስ ሲሆን፤ ከብዙ ጥረት በኋላም በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የሰላም ንግግር እውን ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያን ጥቅምና ክብር ባስጠበቀ መልኩ ሰላምን እውን ለማድረግ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

ከውጭ ሀገራት አሸማጋዮች ይልቅ‹‹እኛው ለእኛው››በሚል መርህ መከወኑ ደግሞ በተለይ የአፍሪካ ሀገሮች ከምእራባውያን ይልቅ በራሳቸው አቅም ያለማንም ጣልቃ ገብነት ከቅኝ ግዛት እሳቤ ተላቀው የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ተጨባጭ ምሳሌ የመሆን ትርጉሙን ያልቀዋል፡፡

ይህም የሰላም መንገድ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነው:: በሰላም እንጂ በጦርነት ያተረፈ ሀገር አለመኖሩን በመረዳት ግጭትና ጦርነት ይብቃን መባሉ እጅግ የሚደገፍና የሚያስደስት ነው:: ከምንም በላይ ለሕዝባችን ትልቅ እፎይታ ነው፡፡የሰላም አየር መተንፈስ መጀመሩ በተለይ ኢትዮጵያ የታሪካዊ ጠላቶቿ መቀለጃና መፈንጫ እንዳትሆን ያደርጋል፡፡

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን አስረዝመው የሚያስገቡ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት እንዳይሳካ ግዙፍ ሚና ይጫወታል፡፡ ይህን ከግምት ከማስገባት በጦርነቱም ወቅት የታለፉ የጨለማ መንገዶችን ማስታወስ በቂ ነው፡፡

በሰለጠነ መንገድ በሰላም መንገድ ማራመድም ትሩፋቱ በርካታ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ የታሪካዊ ጠላቶቿ መቀለጃና መፈንጫ እንዳትሆን ያደርጋል፡ ፡ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን አስረዝመው እያስገቡ ያሉ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት እንዳይሳካ ግዙፍ ሚና ይጫወታል፡፡

የሰላም አየር መተንፈስ መጀመሩም ለኢትዮጵያ በተለይም ዘርፈ ብዙ ስቃይ ውስጥ ላሳለፈው የትግራይ ሕዝብ ዋጋው በምንም የማይገመት ነው፡፡ ከስምምነቱ በኋላም የክልሉ ሕዝብ በአንጻራሪ ሰላም ውስጥ እጁን ለልማት በመሰብሰብ እንቅስቃሴ ሲያደርግም ቆይታል፡፡ ይሁንና ይህ እንቅስቃሴው ምቾት ያልሰጣቸው አንዳንድ አካላት ዳግም ሰላሙን እንዲነጠቅ ከፍ ሲል ለጦርነት እጁን እንዲሰበስብ ሲገፋፉት ታዝበናል፡፡

እንደሚታወቀው፤ ሕወሓት በፕሪቶሪያው ስምምነት የፌዴራል ተቋማትን አሠራሮች፣ ሕጎችና አካሄዶች በጥብቅ ሊያከብር ግዴታ ጥሎበታል። ይህን ለማድረግ ተስማምቶም ፊርማውን አስቀምጧል፡፡ይሁንና የድርጅቱ አንዳንድ አመራሮች በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ ቀደም ሲል የተገባውን ግዴታ ሲሸራርፉ ታይተዋል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ በግልጽ ስምምነቱን ለማፍረስ የሚመስል እንቅስቃሴ እያስመለከቱ ናቸው፡፡

ከሕዝብ በላይ የድርጅቱን ህልውና ማስቀጠልን ታሳቢ ያደረጉ አንዳንድ የድርጅቱ አመራሮችና አሻ ጃግሬዎቻቸውም የሰላም አየር ለመበረዝ ከግራና ከቀኝ እጅ ጥምዘዛና ጉተታ የተያያዙት መስለዋል፡፡ የሰላም አምባሳደር ሚናን ከመወጣት ይልቅ ጥቅማቸውን እያሰቡ መራመድን ብቻ ምርጫ ሲያደርጉም እየተመለከትን እንገኛለን፡፡

በተለይ ከሰሞኑ የሚስተዋለው የፓርቲው አመራሮች የእርስ በእርስ ሽኩቻ እንዲሁም በሕወሓት እና ጊዜያዊ መንግሥቱ መካከል ያለ እሰጣ ገባ ከአንድ ፓርቲ የውስጥ ጉዳይነት አልፎ በክልሉ እና አጎራባች ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ንፁሐን ዜጎች ላይ ከባድ አደጋን ይዞ ሊመጣ የሚችል ነው፡፡

መሰል ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የማይንቀሳቀስ የትኛውም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመጨረሻ ግቡ ጥፋት ነው። የፌዴራል መንግሥት እንዳስታወቀውም፤የሕወሓት ድርጊት የትግራይ ሕዝብ ያገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንደመንጠቅ የሚቆጠር ነው፡፡

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እድገት ለማስመዝገብ መጀመሪያ ሊኖራት የሚገባው ሀብት ሰላም ነው። ሰላም በመገኘቱ የሚከስር ሕዝብም ሆነ የሕዝብ አጀንዳ የለም፡፡ ይሁንና ከሰላም ይልቅ ጦርነት ምርጫቸውና የደስታቸው ምንጭ የሆነ አንዳንዶች መኖራቸው የሚደበቅ አይደለም፡፡ የሰላምን መንገድ ስንራመድ ሰላም እውን እንዳይሆን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የተዳፈነውን እሳት እሳቱን ለማራገብ አድፍጠው እንደሚተጉም ለአፍታ መዘንጋት የለበትም፡፡

አንዳንድ የፓርቲው ሰዎችም እንደ ሀገር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ዘላቂ ይሆን ዘንድ ከመሰል እሰጣ ገባ በመራቅ ስለ ሰላም ኃያልነት መንገር ቋሚ መልዕክታቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ከፓርቲ በላይ የሕዝብ አንድነት ሰላምና ህልውናን ማስጠበቅ ግድ ይላቸዋል፡፡

በዚህ ሂደት በአንድ አፍ ስለሰላም እየዘመሩ በሌላ አፍ ጦርነትን የሚደግፉ የፖለቲካ ተዋንያንም ሆኑ አክቲቪስቶች፣ የሰላም መንገዱ እንዲዘጋና ጦርነቱ እንዲያገረሽ ከሚያደርጉ ፕሮፓጋንዳዎች እንዲታቀቡ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሕዝቡን ላልተፈለገ መስዋዕትነት ለመዳረግ የሚፍጨረጨሩ አካላትን አደብ ማስገዛትና በሕግና በሥርዓት ተጠያቂ ማድረግ የግድ ይላል፡፡

እድገት እንጂ ዝቅታዋን፣ ደስታዋን እንጂ ሃዘኗን፣ ክብሯን እንጂ ውርደቷን ፈፅሞ የማይመኙ የኢትዮጵያ ልጆችም ፣ሀገራቸው ከግጭት የፀዳች ሀገር እንድትሆን ያላቸውን ቁርጠኝነታቸውን በቀጣይም አጠናክረው በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡

መላው የትግራይ ሕዝብም ከፓርቲ በላይ አንድነት፣ሰላምና ህልውናውን ማስጠበቅ በተለይም በሴረኞች መረብ ላለመጠለፍ መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ በሰላም መንገድ እጅ ለእጅ ተያይዞ በመራመድ፣የኢትዮጵያን ዝቅታ ለሚመኙ ከፍታዋን ማሳየትና ወዟን የሚነጥቁ ውበቷንም የሚሰርቁ ቀማኞችን ሁለንተናዊ ፍላጎት ጠንቅቆ መረዳት ይኖርበታል፡፡

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You