በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ጥሪ ምላሽ በመስጠት ዳግም ታሪክ እንጻፍ!

ኢትዮጵያ አንድም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀልበስ፤ አንድም ከደን የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ትሩፋት ለመቋደስ እና የምግብ ዋስትና፣ የስራ ዕድል ፈጠራና መሰል ጉዳዮችን ለማሳካት በሚያስችላት መልኩ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን እየተገበረች ስድስተኛ ዓመት ላይ ደርሳለች፡፡ የዚህ ተግባሯ አንዱ መገለጫ ደግሞ በየአመቱ እያከናወነች የዘለቀችው በአንድ ጀንበር በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን የመትከል ተግባሯ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል መርሃ ግብር ደግሞ የመጀመሪያው የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ንቅናቄ ሲሆን፤ በዚህም በእለቱ 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት 354 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ከእቅድ በላይ የተከናወነ ተግባር ነበር፡፡ ይሄ መርሃ ግብር ለየት የሚያደርገው በሕንድ ተይዞ የነበረውን የአንድ ጀንበር ችግኝ የመትከል ክብረወሰን ኢትዮጵያ እንድትረከብ በማድረጉ ነው፡፡

በዚህ መልኩ የተጀመረው እና በአራት ምዕራፎች ተከፋፍሎ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደለት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፤ በአራት ዓመታት ጉዞው እና በመጀመሪያው ምዕራፍ ማጠናቀቂያ 2014 ዓ.ም ላይ 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ከእቅድ በላይ የተሳካበት፤ በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮችም ኢትዮጵያ የራሷን ክብረ ወሰን እያሻሻለች የሄደችበት፤ በሂደቱም በአማካይ በየዓመቱ 20 ሚሊዮን ዜጎች እየተሳተፉበት የተጓዘ ነበር፡፡

የመጀመሪያውን ምዕራፍም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መጠናቀቅን ተከትሎ፣ በ2015 ዓ.ም አንድ ብሎ የጀመረው የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም በማጠቃለያው 25 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እና አጠቃላይ በመርሃ ግብሮቹ የተተከሉ ችግኞችን 50 ቢሊዮን የማድረግ ግብ ያስቀመጠ ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ የመጀመሪያ ዓመት ሥራም ለዓመቱ የተቀመጠውንም ሆነ በአንድ ጀንበር ለመትከል የታሰበውን ከእቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል፡፡

ለምሳሌ፣ ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም በተካሄደ በአንድ ጀንበር የ500 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር፤ ኢትዮጵያ ዳግም የራሷን ክብረወሰን ያሻሻለችበትን የችግኝ መጠን መትከል ችላለች፡፡ በዚህ መርሃ ግብር የተያዘው ግብ 500 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር የመትከል ሲሆን፤ መላው ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ከፍ ያለ ርብርብ በእለቱ መርሀ ግብር 566 ሚሊዮን 971 ሺህ 600 ችግኝ መተከላቸውን ነው በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገለጹት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳስታወቁት፤ በእለቱ በ302 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የችግኝ ተከላ የተካሄደ ሲሆን፤ የተተከሉት ችግኞች ቁጥር በጂኦስፓሻል መረጃ መሠረት የተጠናቀረ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በጂኦስፓሻል ባልተካተቱ አካባቢዎች የተተከሉ ችግኞች በመኖራቸው የችግኞቹ ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም እያስቻላትም፤ መርሃ ግብሩ እንደ ሀገር ካለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ተጠቃሚ እንድትሆንም እያደረጋት ይገኛል፡፡

ዘንድሮም ለተከታታይ ስድስተኛ ዓመት ወይም የሁለተኛው ምዕራፍ ሁለተኛ ዓመት መርሃ ግብር ከፍ ባለ ውጤት ታግዞ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል በተደረገው ዝግጅት ከሰባት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተው በተከላ ሂደት ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ችግኞችም 60 በመቶ የሚሆኑት ለጥምር ግብርናና ፍራፍሬ፣ 35 በመቶ የሚሆኑት ለደን ልማት፣ እንዲሁም አምስት በመቶ የሚሆኑት ለውበት የሚሆኑ ናቸው፡፡

በዚህ ዓመትም እንደ ቀደሙት ሁሉ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ መርሃ ግብር የሚካሄድ ሲሆን፤ ይሄም በሁለት መልኩ የሚገለጽ ነው፡፡ አንዱ እስካሁን የተከናወኑ የአንድ ጀንበር መርሃ ግብሮች ምንም እንኳን የዓለም ክብረ ወሰንን የሰበሩ ቢሆንም፤ ለዚህ ዓለም አቀፍ እውቅናን ለመስጠት የሚመለከታቸው አካላት ምክንያት ሲደረድሩ ከርመዋል፡፡ እናም ተግባሩን የዓለም ሪከርድ አካል ለማድረግ በሚያስችል መልኩ በእነዚህ አካላት በተለዩ እና በጂኦስፓሻል (ጂ.አይ.ኤስ) መረጃ ክትትል በሚያደርጉበት አግባብ 150 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ነው፡፡

ሌላኛውና ዋነኛው ግን ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ክብረ ወሰን የሚሰብሩበት የ600 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር የመትከል መርሃ ግብር ነው፡፡ ይሄን መርሃ ግብር አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ “ነሐሴ 17፣ 2016 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አሻራችንን እናኑር፤” ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ በአንድ መንፈስ በመላው ኢትዮጵያ አሻራችንን እናኑር፡፡ አንድ ከሆንን ከዚህም በላይ እንችላለን፡፡ ይህ እንዲሆንም፤ አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ በመትከል ለሀገር ያለንን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለንን ስጦታ በተገቢው ስፍራ እንግለጥ በማለት ለኢትዮጵያውያን አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም ለዚህ ከፍ ላለው ራዕይ መሳካት ሲባል ለቀረበው ታሪካዊ ጥሪ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እና ዳግም ታሪክ ለመጻፍ መዘጋጀት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ነው!

አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You