ለሀገር ኢኮኖሚና መሰረተ ልማት ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳለው የሚታወቀው የኮንስትረክሽን ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችልና በዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶች አሸንፎ ለመውጣት እንዲችል የግድ ቴክኖሎጂ መጠቀም ይኖርበታል። ባደጉት ሀገራት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የሚደረገውም ይሄው ነው። እነዚህ ሀገሮች ይህን ያህል በዘርፉ ልቀው መውጣት የቻሉት የግንባታውን ዘርፍ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ነው፡፡
የዘርፉ ስራዎች በዲጅታል ቴክኖሎጂ መደገፍ ባለባቸው ዘመን ላይ እንገኛለን። በአሁኑ ወቅት የግንባታ ስራ በግንባታ መረጃ ሞዴል /ቢም/ እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ጭምር እየተመራ ይገኛል። ይህ መሆኑ የግንባታውን ዘርፍ ለማሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው በዘርፉ ባለሙያዎች ይታመናል። ቴክኖለጂውን በኢትጵያም ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረ ሲሆን፤ አንዳንድ የመንግሥት የግንባታ ተቋራጮች ይህን ቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
የግንባታ መረጃ ሞዴል ወይም የቢም ቴክኖሎጂ ግንባታን ለማዘመን፣ ከዲዛይንና ከግንባታ አኳያ ተሻጋሪ ስራ ለመስራት አቅም እንደሚፈጥር የኮንስትራክሽን ዘርፉ ባለሙያዎችም ይናገራሉ። የቢም ቴክኖሎጂን በኢትዮጵያ አስገዳጅ ለማድረግ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች ተጀምረዋል።
ይህም በአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ አውስትራሊያ፣ ሆንክኮንግ ጭምር ስራ ላይ የዋለና በሌሎች የተለያዩ ሀገሮችም በስፋት ስራ ላይ እየዋለ ይገኛል። መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ የቢም ቴክኖሎጂ በኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ግንባታ ወቅት ከቅድመ ግንባታ እስከ ድህረ ግንባታ በተግባቦት ላይ የተመሰረተ ውጤታማ የኮንስትራክሽን ስራ ለመስራት ያስችላል። አርክቴክቶች፣ ኢንጂነሮችና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ባለድርሻዎች በጋራ የሚጠቀሙበት፣ ልዩነት የማይፈጥርና ችግሮችን ለመቅረፍ ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡
ቴክኖሎጂው የዘመነ አሰራን የሚከተል፣ ስራውን ለማቀላጠፍ የሚያስችሉ ሶፍትዌሮችም አሉት። በባለሙያዎች፣ በገንቢዎች፣ በአማካሪዎችና በፕሮጀክቱ ባለቤት መካከል ይታይ የነበረውን በቅንጅት የመስራት ወይም የኮሙኒኬሽን ክፍተት ይቀርፋል።
ይህ በመሆኑም ግንባታው የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው ያግዛል። የህንጻ ዲዛይን ለመስራት፣ የግንባታ ሂደቶችን ለመተንተንና ሌሎች ተዛማጅ ስራዎችን ዘመናዊ በሆነ መልኩ ለማከናወንም ያስችላል። ይህ ንድፈ ሃሳባዊ የግንባታ ሞዴል የተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ዲጂታል በሆነ መልኩ ማቀድ፣ ዲዛይን ማድረግ፣ መገንባትና መጠቀም እንዲሁም መጠገን እና ማፍረስ ሲያስፈልግም ስራ ላይ ሊውል ይችላል፡፡
በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ሥርዓት ዴስክ ኃላፊ ኢንጂነር ፈለቀ አሰፋ እንዳብራሩት፤ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ሰፊ ስራ እየተሠራ ይገኛል። የቢም ቴክሎጂን ከ2017 ጀምሮ እንደሀገር ወደ ማስገደድ ለመግባት ከወዲሁ የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ ነው።
ቴክኖሎጂው የሀገሪቱን የኮንስትራክሽን ወጪ መቀነስ፣ የግንባታ ጊዜን ማሳጠር፣ ባለድርሻዎችን ማቀናጀትና የተናበበ ዲዛይን ማዘጋጀት ያስችላል። እስካሁን ባለው ልማዳዊ አካሄድ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የዚህ ዓይነት ዕድሎች አልነበሩም። የባለድርሻዎች ቅንጅትም አልነበረም።
የግንባታ መረጃ ሞዴል የተናበቡ ዲዛይኖችንና ባለድርሻዎችን አቀናጅቶ የታለመውን ፕሮጀክት ዕውን ማድረግ የሚቻልበትን አሰራር ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ ቴክኖሎጂው በተፈለገው ልክ ዲዛይን በማዘጋጀት መሬት ማውረድ ያስቻለ መሆኑንም አስታውቀዋል። መንግሥት ይህን ቴክሎኖጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ሰፊ ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንዱ ግንዛቤ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።
‹‹ተቋራጮች ቴክኖሎጂን እንዲጠቀሙ ወደ ማስገደድ ከመገባቱ በፊት ግንዛቤ መፍጠር፣ ማስተዋወቅ ይጠበቃል›› የሚሉት ኢንጅነር ፈለቀ፤ የቴክኖሎጂውን አዋጭነት፣ ተስማሚነትና ወጪ ቆጣቢነት ማስተዋወቅ እንደሚገባና ለዚህም መሰል መድረኮች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ የአቅም ግንባታ ሥራ ይሠራል። በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ላይ ያተኮረ ስልጠና በስፋት ይሰጣል። ባለሙያዎችን እያሰለጠነ፣ እያስፈተነ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ፕሮፌሽናል ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ይሰጣል።
ኢንስቲትዩቱ የምስክር ወረቀታቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ በአውቶዴስክ ደረጃ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ምስክር ወረቀት እንደሚሰጥም ተናግረዋል። የምስክር ወረቀቱም በተመሳሳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዳለው አስታውቀው፣ የኢንዱስትሪውን ችግሮች ለመፍታት እና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የሚያስችሉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችንም ይሠራል ሲሉ ያብራራሉ።
በቅርቡ በግንባታ ዘርፉ የተለያዩ አካላትን ያሳተፈ መድረክ መካሄዱን አስታውሰው፣ በቀጣይም ለሥራ ተቋራጮች፣ ለአማካሪዎች፣ ለኮንስትራክሽን ማኅበራት የግንዛቤ ማስጨበጫ ይሰጣል ሲሉ አስታውቀዋል። በመዲናዋ ለሚገኙ በመንግሥት ደረጃ ላሉ የከተማና መሠረተ ልማትን ለመሳሰሉ ተቋማት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ ነው።
የግንዛቤ ማስጨበጫው እንደተቋም ቴክኖሎጂውን መተግበር አለብኝ ብለው መወሰን እንዲችሉ የሚያስችል እንጂ ያዋጣል አያዋጣም የሚል አይደለም ሲሉም ጠቅሰው፤ ቴክኖሎጂውን ለመተግበር ዝግጁ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢንጂነር ፈለቀ እንዳስታወቁት፤ ቴክኖሎጂው በብዙ አቅጣጫ ጠቀሜታው የጎላ ነው። አንዱና ዋነኛው የመረጃ ክፍተትን ማስቀረት ነው። አርክቴክቶች በተለያየ አሰራር የሚሰሩ በመሆናቸው የእነሱን ዲዛይን ወደ አንድ ለማምጣት ሲሞከር የሚናበብ አይደለም። ስለዚህ በቢም ቴክኖሎጂ ዲዛይናቸውን በማቀናጀት በተናበበ መልኩ መገንባት የሚችል ዲዛይን ማዘጋጀት ይቻላል።
ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የምናዘጋጀው ዲዛይን ወደ መሬት ከወረደ በኋላ ተጨማሪና ተለዋጭ ሥራ አይጠይቅም። የተናበበ ዲዛይን ስለሆነ ስህተቶችን ያስቀራል። ሊገነባ የተዘጋጀው ዲዛይን ቀጥታ ወደ ትግበራ የሚገባ ነው፤ ይህ ማለት ሥራን በማቃለል የሚገጣጠሙ ነገሮች ተመርጠው ቀጥታ እየሰካኩ እንዲሄዱ የሚያስችል ነው። ይህም በግንባታ ወቅት የሚፈጠሩ መጓተቶችን በማስቀረት እንዲሁም ጊዜ በመቆጠብ ወጪን ይቀንሳል።
ጊዜው በረዘመ ቁጥር በእያንዳንዱ የኮንስትራክሽን ግብአት የሚፈጠረው ግሽበት የሚታወቅ በመሆኑ ከዚሀ አንጻር ቴክኖሎጂው አላስፈላጊ ወጪና ተጨማሪ በጀት እንዳይጠይቅ ያደርጋል። በመሆኑም ፕሮጀክቱን በታለመለት ጊዜና በጀት፣ ጥራቱን እንዲሁም የሰዎችንና የአካባቢውን ደህንነት አስጠብቆ ማጠናቀቅ የሚቻልበት እድል ሠፊ ነው። በተለይ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በዚህ ሲታገዙ ቀጣይነት ያለው የአካባቢ ጥበቃን መፍጠር ይቻላል።
የግንባታ መረጃ ሞዴል ዲዛይን በተለይ ባደጉት ሀገራት ግንባታ ባለበትና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ አስገዳጅ እንደሆነ የጠቀሱት ኢንጅነር ፈለቀ፤ የሕግ ማዕቀፍ እንደሆነ ነው የገለጹት።
እሳቸው እንዳሉት፤ የጨረታ የዲዛይን አካል እንደሆነና ጨረታ ሲወጣ የግንባታ መረጃ ሞዴል ዲዛይንን እንደ መስፈርት ይጠይቃል። ስለዚህ ባስገዳጅነት እየተተገበረ ያለ ቴክኖሎጂ ነው። በኢትዮጵያም ይህን ለማድረግ ፍኖተ ካርታው የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከ2011 እስከ 2017 ዓ.ም ፍኖተ-ካርታው ሰልጣኞችን በማፍራት፣ ግንዛቤን በመፍጠር፣ የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት፣ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋትና ሌሎች መደላድሎች ተፈጥረዋል።
በስድስት ዓመት እነዚህ በሙሉ ተጠናቅቀው ስታንዳርዱ ወጥቶ ጸድቋል። በአንድ ዓመት ውስጥ ብዙ ተሰርቷል። ዩኒቨርሲቲዎችን ጂ.አይ.ዜድ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በማቀናጀት ሀብት በመመደብ ብዙ ሰልጣኞችን ማፍራት የተቻለበት እድል ተፈጥሯል። ስለዚህ ይህንኑ ተከትሎ መሄድ በመቻሉ አስገዳጅ የማድረግ ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ አመላክተዋል።
ከሰልጣኞቹ የተገኘውን ግብረመልስ አስመልክተው ኢንጂነር ፈለቀ ሲያስረዱ፤ አዋጭነቱ ላይ ጥያቄ አለመኖሩን አመላክተዋል። ዲዛይንና ግንባታ ላይ እየተሳተፉ ያሉትን ባለሙያዎች በማምጣት እነዚህ ባለሙያዎች ከሚሠሩት አንፃር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። ወጥተው ቀጥታ ለመተግበር አቅርቦት እና መሠረተ ልማት ይፈልጋሉ። ከስልጠና በኋላ በምን እሠራለሁ የሚል ጥያቄ ያላቸው በመሆኑ ለስኬታማነቱ በፕሮጀክቱ ላይ የሚሠራ የባለሙያ ቡድን አቀናጅቶ መሄድ አስፈላጊ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ቴክኖሎጂውን ከማላመድ አንፃር እንደማሳያ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ያሉትን ፕሮጀክቶች ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቶ ወይም ቢም አስገዳጅ አድርጎ የግንባታ ሥራ ለመጀመር ተዘጋጅቷል። ዲዛይኖች ሙሉ በሙሉ በቢም እንዲሠሩ ከመንግሥት ተቋማት ጋር ስምምነት ገብቶ እየተሠራ ነው። በዚህ ዓመት ብቻ በተወሰኑ ፕሮጀክቶች 16 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ ተጠይቋል።
ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ኢንጂነሩ እንዳስታወቁት፤ በኢትዮጵያ ጊዜን ዋጋን ታሳቢ ያደረገ እና የተናበበ ዲዛይን የለም። ዲዛይን ይቀየር፣ እንዴት ይሠራ፣ አንዱ ከአንዱ እንዴት ይናበብ የሚል ነገር የለም። የሚያጸድቀውም አካል በቀላሉ በተለመደው አካሄድ ዲዛይኑን ያጸድቃል። ይህም ትግበራው ላይ ክፍተት ይፈጥራል።
በቢም ቢሰራ ግን ችግሩን መቅረፍ ይቻላል። በዚህ ላይ በተለይ በአዲስ አበባ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ ነው። አዲስ አበባ የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ነች። ትላልቅ ፕሮጀክቶች አሉ። ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች አዲስ አበባ ነው የሚሠሩት። አዲስ አበባ ወደ ጎን መስፋት አትችልም። ወደ ላይ ማደግ ነው የሚፈቀደው።
በመሆኑም በመዲናዋ ለሚገኙ ክፍለ ከተሞች ስልጠና ተሰጥቷል። በተመሳሳይ ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን፣ ለኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን እና ለሌሎችም ስልጠና እየተሰጠ ነው። ዓላማውም ቴክኖሎጂው አስገዳጅ ሲደረግ ዲዛይን በዚያው የሚገመገም መሆኑን ማስገንዘብ ነው።
የቢም ቴክኖሎጂ ባለሙያዋ ኢንጂነር ቤዛዊት ጌታቸው እንደሚሉት፤ መንግሥት የቢም ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ይፈልጋል። ኢንዱስትሪው ይሄን ቴክኖሎጂ እንዲያውቀው በምን መልኩ መተግበር አለበት የሚለውን ከአውቶዴስክ ጋር በመተባበር ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መፍጠርና ማሳወቅ ይገባል።
መንግሥት በያዘው ዕቅድ መሰረት በኢንዱስትሪው ላይ በሰፊው መስራት ይፈልጋል። ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎች በተያዘላቸው ጊዜ በጀትና ጥራት የማያልቁ ከሆነ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር በጀት በማባከን ለተፈለገው ዓላማ እንዳይውል ያደርጋል።
ስለሆነም የቢም ቴክኖሎጂ ቢስፋፋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ፤ ወጪንና ጊዜን ለመቆጠብ ያስቻላል። መንግሥት የግንባታ ኢንዱስትሪዎች ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙ ያነሳሳል። እንዲተገበርም ይፈልጋል። አዲስ ቴክኖሎጂን በአንድ ጊዜ መቀበል ተግዳሮት በመሆኑ መንግሥት እስካሁን ማስገደድ አልጀመረም። ይሁንና አንዳንድ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች በፍላጎታቸው ቴክኖሎጂውን መተግበር ጀምረዋል። የፕሮጀክቱን ጥቅም በመረዳት ቴክኖሎጂውን በራስ ተነሳሽነት እየተገበሩ ያሉ ኩባንያዎችም እንዳሉም ኢንጂነር ቤዛዊት ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ድርጅት፣ የፌዴራል ቤቶች ኤጀንሲ፣ ዓለም አቀፍ ካምፓኒዎች ጭምር በቢም እንደሚሰረቱ አመልክተው፣ መንግሥት ከዚህ በኋላ ማስገደድ ሲጀምር፤ ግንዛቤ መፍጠር ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
‹‹በሀገራችን በተለመደው አካሄድ በሚሰሩ የግንባታ ኢንዱስትሪዎች ዘንድ ያለመናበብ ችግር በስፋት ይታያል።›› ያሉት አማካሪዋ፤ ኮንትራክተሩ ሁሉም የሚሠራው ለየብቻ ነው። ግንጥልጥል ያለ ኢንዱስትሪ ነው ያለን›› ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በተለመደው አሰራር ሲሠራ ኤሌክትሪክ የሚዘረጋው፣ ውሃና ፍሳሽ የሚገጥመው ሁሉም መሰረተ ልማት ዘርጊ አካል ሳይነጋገር ነው የሚዘረጋው። ከዛ በኋላ እንደገና የቁፋሮና የማፍረስ ሥራ ይመጣል።
ቢም ቴክኖሎጂ በቅንጅት የሚሰራበት ነው። አንዱ ስለአንዱ ሥራና መረጃ ያውቃል። እያንዳንዱ ባለድርሻ አብሮ ተባብሮ ስለሚሠራ የተናበበ ዲዛይን ይኖራል። ስለዚህ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ፣ በጀትና ጥራት እንዲጠናቀቅ ያደርጋል ብለዋል።
ዋናው ነገር መረጃ አይባክንም። መረጃው ለኮንስትራክሽን ብቻ ሳይሆን ኮንስትራክሽን ለሚያሠራው አካል ለጠጋኞችና ለተግባሪዎች በቀላሉ ይደርሳቸዋል። ስለዚህ የሚገነባው ፕሮጀክት ላሰብንለት ዓላማ በቀላሉ እንዲውል የሚያደርግ በመሆኑ ቢም ለኮንስትራክሽን ዲዛይን ብቻ ሳይሆን ዲዛይኑን ለሚተገብሩት እና ለሚገነቡትም ይጠቅማል።
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ከዩኒቨርሲቲ አጥኚዎችና ከአውቶዴስክ ጋር በመሆን የሚያዘጋጃቸው የግንዛቤ መድረኮች በሀገራችን የግንባታ ዘርፉን ለማሳደግ እና ለማዘመን በሚደረገው እንቅስቃሴ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስኬዱ ናቸው ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የሀገር ውስጥ ስራ ተቋራጮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የውስጥ አሰራር ሥርዓታቸውን ማዘመን አለባቸው። ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የአሰራር ሥርዓትን መጠበቅ የሚያስችሉ ስልጠናዎች ለተለያዩ ስራ ተቋራጮች ተሰጥተዋል። የኮንስትራክሽን ዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የፕሮጀክት ማናጀሮችን ማብዛት ያስፈልጋል። ፕሮፌሽናል ማናጀሮች በስፋት ሲኖሩ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ የመምራት አቅም ይፈጠራል።
በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፉ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ለዚህም ችግሮችን አስቀድሞ ለመለየት የሚያስችሉ እንደ ቢም ቴክኖሎጂ በመሳሰሉት ላይ ስልጠናዎች በስፋት እየተሰጡ ናቸው። ይህም ለዘርፉ የትራንስፎርሜሽን አቅም እንደሚፈጥር በመረዳት ለተግባራዊነቱ መዘጋጀት ይገባል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው ኮንስትራክሽን ለሀገሪቱ ዕድገት ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን ገልጸው፤ መንግሥት ዘርፉን ለማዘመን እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። እያደገ የመጣውን የኮንስትራክሽን ፍላጎት ለመመለስ ከተፈለገ አሁን ካለው ይበልጥ የመንገድ ልማቶችን ለማከናወን እና ሌሎች ዘላቂ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ከተጋን የቢም ቴክኖሎጂ አማራጭ መሆኑን አመላክተዋል።
የቢም ቴክኖሎጂ የግንባታ ሂደት ዋነኛ ምሰሶ ከሆኑት መካከል አንዱ መሆኑን እሳቸውም ጠቅሰው፤ አርክቴክቸሮችን፣ ኢንጂነሮችን እና አማካሪዎችን በማቀናጀት ውጤታማ ስራ ለመስራት የሚያስችል ነው ብለዋል። በተወዳዳሪነት አሸንፎ ለመውጣት እና ከግንባታ ኢንዱስትሪው ጋር ተያይዞ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም እንደሚያስችልም ጠቅሰው፤ ከጊዜ፣ ከጥራት፣ ዘላቂ ስራ ከመስራት እና በሀብት አጠቃቀም ላይ ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት እንደሚያስችልም አስገንዝበዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም