ትውልድና ዕድገቷ ባህርዳር ከተማ ነው። አዲስ አበባ ስትመጣ የእሷንና የቤተሰቦቿን ኑሮ በተሻለ ለመቀየር አስባ ነበር። አገሬነሽ ለከተማ ህይወት አዲስ አይደለችም። የቦታ ለውጥ ካልሆነ በቀር ከተማ ለእሷ ግርታን አይፈጥርባትም። ሾፌሩ ባለቤቷ ለቤት ለትዳሩ መልካም ገቢ ለማግኘት ርቆ መሄድን ፈልጓል። ለዚህ ደግሞ ምርጫው ባህርዳር ሳይሆን አዲስ አበባ ነው።
ባልና ሚስት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ካሰቡት ስፍራ ከተሙ። እንደታሰበው ለጥቂት ጊዜያት ህይወት መልካም ሆነላቸው። ትንሹ ልጅ የግል ትምህርት ቤት ተመዝግቦ መማር ጀመረ። ኑሮ ቢከብድም ለእነሱ የሚያቅት አልሆነም። አባወራው ወጣ ብሎ እየሰራ ወይዘሮዋ ቤቷን በወጉ እየመራች ነው።
ውሎ አድሮ የጥንዶቹን ትዳር የሚፈትን አጋጣሚ ተፈጠረ። በድንገት ግዳጅ እንዲሄድ የተወሰነበት ሾፌሩ አባት ለወራት ቤተሰቡን ትቶ ሊለያቸው ሆነ። ይህ ጊዜ ብዙ ለሚያስቡት ባልና ሚስት አስቸጋሪ ነበር። ከፍ ባለ ክፍያ የሚማረው ህጻን በጀመረው አልቀጠለም። ለቤት ኪራይና ለሌሎች ወጪዎች በቂ ገንዘብ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ አባወራው በቅርብ የለም። ወይዘሮዋ ክፉኛ ተጨነቀች። ዛሬን እንደ ትናንቱ እየኖረች አይደለም። የህጻኑ ትምህርት ቤት ለወራት ሳይከፈል ቀጠለ። አገሬ ግራ ገባት። ከየት አምጥታ ግዴታዋን እንደምትወጣው አታውቅም።
ትንሹ ልጅ ጎበዝ የሚባል ተማሪ ነው። በዚሁ ከቀጠለ ለሀገር ተስፋ ለወገን አለኝታ ይሆናል። አሁን ግን በመንገዱ የሚቀጥል አይመስልም። የትምህርት ቤቱ ክፍያ በዕዳ መመዝገብ ይዟል። ብቸኝነትን ከችግሮች የተጋፈጠችው እናት ስለልጇ ትምህርት ብዙ ሞከረች። አንድ ሁለት ማለት የጀመረው ጊዜ እንደቀልድ ወራት አስቆጠረ። ሰኔ ደርሶ ትምህርት ቤት ሲዘጋ ጎበዙ ልጅ በጥሩ ውጤት ክፍሉን ተሻገረ።
አገሬ አሁን እንደትናንቱ እየከፈለች ልጇን ማስተማር አትችልም። ከአንደኛ ክፍል ወደቀጣዩ በጥሩ ውጤት ላለፈው ልጇ ሌላ ትምህርት ቤት መፈለግ አለባት። ለዚህ ደግሞ አቅሟ የሚችለውን ፈልጋ ማስተማር ግድ ይላታል። የልጇን ማስረጃ ከእጇ ለማድረግ እስካሁን በዕዳ የተማረበትን ክፍያ ማጠናቀቅ አለባት። እናት አፏን ሞልታ የትምህርት ማስረጃውን መጠየቁ ከበዳት። ዙሪያው ገደል ሆኖባት በትካዜ ከረመች።
ክረምቱ ሳብ ሲል የልጇ እኩዮች ትምህርት ቤት መመዝገብ ጀመሩ። አገሬ ይህን ማድረግ ባለመቻሏ የ‹‹በይ ተመልካች›› የሆነች ያህል ተሰማት። ዝም ማለት አልፈለገችም። መልሱን ብታውቀውም ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄዋን አቀረበች። የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ለወራት መክፈሏን አሳምረው ያውቃሉ። ቀጣዩን ዓመት ልጇ በትምህርት ቤቱ እንደማይማር ሲገባቸው ደግሞ ሃሳቧን ተቃወሙ።
ትንሹ ልጅ በትምህርት ልቆ የተሸለመበት የምስክር ወረቀት በእጁ ይገኛል። ይህ ብቻውን ግን አዲስ ትምህርት ቤት አያስገባውም። ተገቢው ማስረጃ ሊኖርና ማለፉ ሊረጋገጥ ግድ ነው። ጊዜው እየገፋ መፍትሄ እየራቀ ሲሄድ አገሬ መፍትሄ ላለችው ሃሳብ ፈጥና ሮጠች። ችግር ክፉ ነው፤ ያሸማቅቃል፣ የሰው ፊት ያሳያል። እናት ስለልጇ በየትምህርት ቤቱ፣ በየዘመድ ቤቱ፣ ደጅ ጠናች። ተማጸነች።
ጊዜው ሲደርስ ጸሎቷ ተሰማ። ብዙ ችግሮችን እያለፈች፣ በርካታ ፈተናዎች እየገጠሟት የቆየችው ሴት አንድ ቀን ከአንድ ትምህርት ቤት ደጃፍ ደርሳ በሩን አንኳኳች። የከፈቱላት እጆች አልገፏትም። ብሶቷን አደመጡ ፣ ችግሮቿን ተረዱ። በእሷ ጥያቄና በልጇ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ምን እንደሚባል አታውቅም። ቀጠሮ ተቀብላ ስትወጣ የቀጣዮቹን ቀናት ፈተናዎች እያሰበች ነበር።
ትምህርት ቤት ሊከፈት ጊዜው ተቃርቧል። ለልጆቻቸው ደብተር የሚገዙ ‹‹ዩኒፎርም›› የሚያሰፉ ወላጆች ስራ በዝቶባቸዋል። አገሬ አሁንም ስለልጇ ትምህርት ቁርጡን አላወቃችም። ትናንትናን ከዛሬ እያስታወሰች በሃሳብ ናወዘች።
ሁለት ልጆችን ከቤት አስቀምጦ ያለአንዳች መፍትሄ መኖር ይከብዳል። ልጁን እኩዮቹ ሲማሩ በር ዘግቶ ማዋል፣ ‹‹አትሄድም›› ብሎ ማገድ አይቻልም። ይህ አይነቱ ሀቅ ለአገሬ ሸክሙ የከበደ ውሉ የተቋጠረ ነው። ሁሌም በለቅሶ የምትውለው ወይዘሮ አሁንም በጭንቀት ተይዛለች።
ከቀናት በአንዱ በቀጠሮ ከተለየችው ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ በድንገት ተገኘች። በእንዲህ አይነቶች ቦታ መገኘት ለእሷ አዲስ አይደለም። እነዚህኞቹ ደግሞ ምን እንደሚሏት አታውቅም። ቀድሞ ባገኘቻቸው ጊዜ በመልካም እንደተቀበሏት ታውቃለች። ከቆይታ በኋላ ያሏትን አድምጣ፣ የምትላቸውን ሰምተው ተለያዩ። ውስጧ ልትገልጸው በማትችለው ድንገቴ ስሜት ተናወጠ።
ከጊዚያት በኋላ ወደ ግዳጅ የተላከው አባወራ በሰላም ወደቤቱ ተመልሶ ቤተሠቦቹን ተቀላቀለ። ወይዘሮዋ ስለሆነላት መልካም ነገር ፈጣሪዋን አመሰገነች። ባል ከቤቱ ሲገባ በኑሮው እንደገና ማንሰራራት እንዳለበት ገባው። በእሱ አለመኖር ከቤተሰቡ የጎደለውን ሁሉ አላጣውም። አሁን ተመልሶ የቤቱ ራስ ሊሆን ግድ ይለዋል።
በሰላም መመለሱ ለጎጆው፣ለባለቤቱና ለመላው ቤተሰብ ታላቅ ተስፋ ነው። ነገን በተሻለ ለመኖር ደግሞ ሥራ ወደተገኘበት ሁሉ ፣ መሄድ ይኖርበታል። ጥቂት ቆይቶ አባወራው መኪና ይዞ ወደ አንድ ስፍራ ተጓዘ። የሄደበት አካባቢ ሰርቶ ገንዘብ የሚያስገኝለት ነው።
እንዲህ በሆነ ጥቂት ጊዚያት በኋላ ለወይዘሮዋ ጆሮ ክፉ ዜና ደረሰ። ባለቤቷ መኪና ይዞ በተጓዘበት አካባቢ ባልታወቁ ሰዎች በጥይት መመታቱን ሰማች። ይህ እውነት ሞላ ጎደለ ለምትለው የቤት እመቤት ከመርዶ በላይ ቁጣ ሆነባት። አንዱ ችግር ሳይፋቅ ሌላኛው ተደረበ።
የዕድል ጉዳይ ሆኖ ባለቤቷ በህይወት ተርፏል። ተመልሶ አዲስ አበባ ሲመጣ ግን ሁለት እግሮቹ ተመተው ክፉኛ ተጎድቶ ነበር። ሁኔታው ‹‹በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ›› ይሉት አይነት ቢሆንም አገሬ አላማረረችም።
በህይወት ተርፎ ለቤቱ፣ በመብቃቱ ፈጣሪዋን ‹‹ተመስገን ›› አለች ።
ውሎ አድሮ ባለቤቷ ድኖ መራመድ ጀመረ። ዛሬ ላይ ደግሞ በቀድሞው ስራ መመለስ ይፈልጋል። የመንገዱ አለመረጋጋት፣ የሰላም ዕጦት ሁኔታ እንዲህ ሊያደርግ አላስደፈረውም። ወይዘሮዋ በችግርና ክፉ አጋጣሚዎች ተከባለች። ተስፋ ግን አልቆረጠችም። ልጇ ከቤት እንዳይውልና ትምህርቱን እንዲቀጥል ጥረቷ ሩጫዋ አልተገታም። ብሩህ ስሜት በውስጧ መመላለስ ጀምሯል።
ሆደባሻዋ ወይዘሮ
ወይዘሮ መሰረት ለታ ከአዲስ አበባ ወጣ ከምትል የገጠር ቀበሌ ተወልዳ አድጋለች። ገና በልጅነቷ ወላጆቿ ለባል ቢሰጧት ትምህርት ይሉትን ላታይ ተፈረደባት። ‹‹ጅዳ›› የምትባለው የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች መተዳደሪያቸው ግብርና ነው። የእሷም ህይወት በዚህ ተቃኝቷል። ባለቤቷ አራሽ ገበሬ ነው። በሬውን ጠምዶ መሬቱን ሲያርስ ሲገምስ ይውላል።
ያለ ይሁንታዋ በገባችበት ትዳር ባትደሰትም። ቤቷንና ባሏን አክባሪ ናት። ሁሌም ጎጆዋን ልትሞላ ትተጋለች። ይህ ድካሟ ግን ከአባወራዋ አልተዛመደም። ከስራ መልስ እየጠጣ ፣እየሰከረ ይረብሻት ያዘ። መሀላቸው ፅኑ ቅያሜ ገባ ችግራቸው እንደሌሎች በሽምግልና አልተፈታም።
ከቀናት በአንዱ መሰረት ባለቤቷ የእርሻ በሬዎቹንና ከብቶቹን እንደሸጣቸው ሰማች። ሁሉም የሆነው እሷ ሳታውቅ ነውና ውስጧ ጎሸ። አዘነች፣አለቀሰች። መለስ ብላ ሁለቴ አላሰበችም። ፈጥና ወሰነች ። ትዳርና ጎጆ ይሉት አስጠላት። ማንም ሳያውቅ ተደብቃ ወጣችና ጠፍታ አዲስ አበባ ገባች። የበደል ኑሮዋን ተወልዳ ባደገችበት ገጠር ምሳ፣ቆፍራ ቀበረችው ። የአዲስ አበባን ህይወት በሰው ቤት ተቀጥራ ስምንት ዓመታትን ሰራች።
የትናንቱን ክፉ ህይወት ካስረሳት ሰው ጋር ስትተዋወቅ ቀጣይ ኑሮዋ በትዳር ታሰረ። እሱ መልካም ሰው ነውና ሀሳቧን ያከብራል። በፍቅር የጸናው ጎጆ በመጀመሪያ ልጃቸው ተባርኮ በመከባበር ፀና። መሰረት ልጅዋን እያሳደገች የባሏን ሰላም ውሎ መግባት ተመኘች። ህይወቷ በፍቅር በደስታ ተሟሸ። አባወራዋን አክባሪ ትዳሯን ወዳድ ሆነች።
ከቀናት በአንዱ በድንገት የታመመው የመሰረት ባል በቀላሉ አልተሻለውም። ህመሙ ባይቆይበትም በስቃይ ሲንገላታ ከረመ። ሁለተኛ ልጇን ነፍሰጡር የሆነችው ወይዘሮ እሱን በማስታመም ተንገላታች። አልሆነላትም። በድንገት ሞት ደርሶ ቢነጥቀው ህይወቷ ተቃወሰ።
ነፍሰጡሯ ወይዘሮ ኑሮዋ እንደቋጥኝ ከበዳት። ከወለደች በኋላ ሁለት ህጻናት ያለረዳትና ወዳጅ ዘመድ ይዞ መኖር ለእሷ ቀላል አልሆነም። የቤት ኪራይ፣ የዕለት ወጪና የልጆች ቀለብ ተቸገረች። ልበ መልካሞች የቻሉትን እያገዟት ጥቂት ቀናትን አለፈች።
መሰረት ቤት ኪራዩን አልቻለችም ልጆቿን ይዛ ወጣ ለማለት ሞከረች። ቤት እየጠበቀች የምትኖርበት መጠጊያ አላጣችም። ልጆች ለማሳደግ እንግልቷ ቀጠለ። እንጀራ እየጋገረች፣ ጉልበቷን እየከፈለች ለልጆቿ ሮጠች። ዘመዶቿ ባይጠይቋትም የባዕድ ዘመድ አላጣችም። ያጣቸውን እየሰጡ፣ የጎደለውን እየሞሉ ክፉ ቀናትን አሻገሯት።
አሁን ህይወት ብላ የሰየመቻት ልጇ ትምህርት ቤት መግቢያዋ ነው። መሰረት ተጨነቀች። እኩዮቿ ከትምህርት ውለው መምጣታቸውን ስታይ አብዝታ አዘነች። እሷ ቢቸግራትም። ልጆቿ ዕውቀት እንዲነፈጉ አትሻም። ሆደባሻዋ እናት ቀን ከሌት አለቀሰች። አንድ ቀን ግን ዕንባዋን የሚያብስ፣ ችግሯን የሚካፈል አጋጣሚ አገኛት።
ወደአንድ ትምህርትቤት ቅጥር ስትደርስ የእሷን ብሶት የሚያደምጡ ፣ ጆሮዎች ትኩረት ሰጧት። ትኩስ ዕንባዋን የሚያብሱ እጆች አቅፈው ተቀበሏት። መሰረት የሆነውን አላመነችም። ያሳለፈችውን ህይወት፣ያለችበትን ኑሮ ሳትደብቅ ዘርዝራ ተናገረች።
በኦርቶተ አጸድ
አቶ ሀፍቶም ነጋ የኦርቶተ ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው። በ2014 ዓ.ም ስራውን የጀመረው ኦርቶተ ትሬዲንግ በበርካታ አባላት የተዋቀረ ስለመሆኑ ይናገራሉ። ትሬዲንጉ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች አንደኛው ደግሞ በትምህርት ዘርፉ የሚያካሄድ ሰፊ እንቅስቃሴ ነው።
ምስረታውን ለገጣፎ ‹‹ሆጬ›› ከተባለ ቦታ ያደረገው የኦርቶተ አካዳሚ ከአጸደ ሕፃናት ጀምሮ ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተናግዳል። ወደፊት ደግሞ አቅሙን እስከ ዩኒቨርሲቲ የማሳደግ ዕቅድ አለው። በቅርቡ ያስመረቃቸው የመጀመሪያዎቹ የአጸደ ሕፃናት ተማሪዎችም በታሪኩ ቀዳሚዎቹ ሆነው ተመዝግበዋል።
ትምህርትቤቱ ተማሪዎችን የሚቀበለው በክፍያ ነው። እንዲያም ሆኖ ችግር ያለባቸውንና ከፍለው መማር የማይችሉ እኩዮቻቸውን መዘንጋት አይሻም። የትምህርትቤቱ መከፈት ዋና ዓላማ ለትርፍና ክፍያ መሽቀዳደም አይደለም። በትምህርት የላቁ ተማሪዎችን ማፍራት ተቀዳሚ ዕቅዱ ነው።
አቶ ሀፍቶም እንደሚሉት ትምህርት ቤቱ በአካባቢው መከፈቱ የበርካታ ተማሪዎችንና ወላጆቻቸውን ጥያቄ ለመመለስ አስችሏል። በአሁኑ ጊዜ ልጆች ከአካባቢያቸው ርቀው እንዳይሄዱ ሆኗል። በተለያዩ ምክንያቶች የመማርን ዕድል ያላገኙ ተማሪዎችም የበረከቱ ተካፋይ መሆን ጀምረዋል። አገሬና መሰረትን የመሰሉ ወላጆች ደግሞ በጊቢው ደርሰው ዕንባቸው ታብሷል። ዛሬ ልጆቻቸው ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተዋል።
ትምህርት ቤቱ የተለየ ድጋፍ ለሚያሻቸው ተማሪዎችም በጀት አለው። ዮስያስን የመሰሉ በዊልቸር የሚጓዙ ልጆች ሲመጡም የትምህርት ዕድልን አልነፈገም። በሩን ከፍቶ ‹‹እነሆ ! ›› ከበረከቱ እያላቸው ነው። ኦርቶተ አካዳሚ በቅርቡ በነበረው ዝግጅት ደስታን ያቀበለው ለተመራቂ ተማሪዎቹ ብቻ አይደለም። ሕፃን ዮስያስን ለመሰሉ ብርቱ ተማሪዎቹ ጭምር እንጂ። ሕፃን እዮስያስ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ባጋጠመው የጤና ችግር የአካል ጉዳት አጋጥሞታል። ከወገቡ በታች ካለመንቀሳቀሱ ባሻገር የዳይፐር ተጠቃሚ ነው።
ወላጅ እናቱ ወይዘሮ ልኬለሽ ተፈሪ እሱን አሳድጋ ከዕውቀት ለማገናኘት በቀላሉ የማይገለጽ ዋጋን ከፍላለች። ትምህር ቤት ለማስገባት፣ ‹‹አስተምሩልኝ ››፣ ለማለት ልጇን አዝላ የበርካቶችን ደጃፍ ረግጣለች፤ የብዙዎችን ፊት አይታለች። በአካልና በአዕምሮ የተቀበለችው ስቃይም የዋዛ አልነበረም።
ልኬለሽ ወደአካባቢው ደርሳ የኦርቶተ አካዳሚን በጠየቀች ጊዜ ፊት የነሳት፣ በር የዘጋባት አልነበረም። ዮሲን ተቀብሎ ለማስተማር ይሁንታቸውን በፈገግታ የመለሱላት ብዙዎች ሆኑ። ዮስያስ በዊልቸር እየተገፋ ከጓደኞቹ ጋር ለትምህርት ተሰለፈ። ለእሱ ፍቅርና አክብሮት የሚሰጡት፣ አቅፈው የሚስሙት፣ ሲገባ ተቀብለው፣ ሲሄድ የሚሸኙት ተሸቀዳደሙ።
በቅርቡ ትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ያላቸውን ተማሪዎቹን ባስመረቀ ጊዜ ዮሲ ባልንጀሮቹና መምህራኖቹ መሀል ተገኘ። መመረቅን ያለፈው ቢሆንም ደስታውን ለመቀላቀል ግን የቀደመው አልነበረም።
ዮስያስ በዝግጅቱ መሀል ከመድረክ ላይ ወጥቶ ሀሳቡን በግጥም ገለጸ። ስለተሰጠው የመማር ዕድልም ትምህርትቤቱንና መምህራኖቹን አመሰገነ። ከዚህ በኋላ የነበረው አጋጣሚ ግን ለየት ያለ መልክ ነበረው። የአካዳሚው ቦርድ አባላት ተማሪ ዮስያሰን ባዩት ጊዜ ሰብሰብ ብለው መከሩ። ምክራቸው በቀና ልቦች የተዋቀረ፣ በክርክር ጭቅጭቅ ያልቆየ ነበር። ቃላቸው አንድ ሆኖ ውሳኔያቸውን አስታወቁ።
ሕፃን እዮስያስ ጎበዝና ጠንካራ ተማሪ ነው። ለመማር ያለው ፍላጎትና ፍቅር ደግሞ አክብሮት ሊሰጠው ይገባል። እናም የዕለቱ የሚከፍላቸውን ዋጋዎች‹‹የሚያልፋቸውን ፈተናዎች የሚያቀል፣መፍትሄ ያሻዋል።
ዮስያስ ከዚህ በኋላ ስለ ትምህርት ቤቱ ክፍያ አያስብም። የመማሪያ ቁሳቁሶችም በትምህርትቤቱ አቅም ይሸፈናል። በእጅጉ ለሚያስፈልገው የዳይፐር አቅርቦትም ከዚህ በኋላ ወጪውን የሚችልለት የገዛ ትምህርትቤቱ ሆኗል። ዕንባ ሳቅ የቀላቀለው ደስታ በብዙኃን ፊት ሲነበብ በግልጽ ተስተዋለ። ዮስያስና እናቱ የኦርቶተ አካዳሚን ከልባቸው አመሰገኑ።
አቶ ሀፍቱ እንደሚሉትም ትምህርትቤቱ ለጥቅም ብቻ የተመሰረተ ባለመሆኑ በየጊዜው ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚፈጥን ነው።በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ እሳቤ ተማሪዎች ሁለት መምህራን አሏቸው። የመጀመሪያዎቹ በስጋ የወለዷቸው ወላጆች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በሙያ የተቀጠሩት መምህራን ናቸው።
ትምህር ቤቱ ለወላጆች በቂ የሚባል ስልጠና ይሰጣል። በየጊዜው ከትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት መስራትም አዲስ አይደለም። በትምህርት ቤቱ ግቢ የፊት ለፊት ግድግዳ ላይ በጉልህ የተጻፈው አንድ ቃል ደግሞ በትክክል ገዢ ሆኖ ሲተገበር ይውላል።
‹‹ልጆቻችሁ ልጆቻችን ናቸው›› የሚለው ታላቅ መልዕክት።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም