በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ የሕግ የበላይነት ቅድሚያ ከተሰጣቸው ግንባር ቀደም ጉዳዮች መካከል እንደሆነ ይታወቃል። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ ከመስጠት አልፎ በህገ መንግስቱ አንቀፅ ዘጠኝ ላይ እንዲደነገግ አድርጓል ። በዚህ አንቀፅ ስር የሕግ የበላይነት በሀገራችን የሚኖረው ሁኔታ በሚገባ ተብራርቷል።
ኢትዮጵያ ያፀደቀችው ሕገ መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲል ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝ የተከለከለ መሆኑን ያስረዳል ። የትኛውም አካል ሕገ መንግስቱ ላይ ከተደነገገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ውጪ ነፍጥ አንግቦ ሥርዓቱን በኃይል ለመጣል የሚያደርጋቸውን ማናቸውም አይነት ተግባራት ይከለክላል።
በማናቸውም ቦታ የሕግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ሕጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች አይከበሩም። በሕገ መንግሥቱ ላይ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁ ለይስሙላ የተደነገጉ አይደሉም።
ሕግና ሥርዓት ከማንኛውም ሰው፣ ተቋም፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፣ ቡድንና ስብስብ በላይ ነው። እነዚህ ሁሉ ከሕግ እና ሥርዓት በታች ናቸው። ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የማይንቀሳቀስ የትኛውም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመጨረሻ ግቡ ጥፋት ነው። የሕወሓት ያለፉት ዓመታት የግትርነት ባህሪም የዚሁ ምሳሌ ነው።
በቅርቡ እንኳን የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ተወካይ ነኝ የሚለው ሕወሓት ከለውጡ ማግስት ፤ በዲሞክራሲያዊ ምርጭ ወደ ስልጣን ከመጣው መንግሥት ጋር የነበረውን ልዩነት በኃይል ለመፍታት የሄደበት ያልተገባ መንገድ ሀገርን ፤ በተለይም የትግራይን ሕዝብ ያስከፈለው ዋጋ ምንያህል የከፋ እንደሆነ ለማስታወስ አይከብድም።
የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ተጠሪ አድርጎ እራሱን የሚቆጥረው ሕወሓት ፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በትግራይ ሕዝብ ስም በሀገር ሆነ በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጠራቸው ምስቅልቅሎች ያስከፈለው ዋጋ ሊዘነጋ የሚችል አይደለም። በወቅቱ መንግሥት ችግሩን ለዘለቄታው በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በወሰደው እርምጃ ችግሩ በድርድር በሰላም ስምምነት ባይፈታ ኖሮ ሊያስከትል ይችል የነበረውን ተጨማሪ ጥፋት መገመት ቀላል ነው።
ሕግ እና ሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓትን በማክበር ላይ የተመሰረተው የሰላም ስምምነቱ ከሁሉም በላይ ለትግራይ ሕዝብ ሰላም ማስፈን አስችሏል። ሕዝቡ ግጭት ከሚፈጥረው ሞት ፣ የአካል ጉዳት ፣ ስደት እና የስነልቦና ቀውስ ወጥቶ ፊቱን ወደ ሰላም ማዞሩ ይታወቃል።
ይሁንና “ቀበሮ መልኩሳ አመሏን አትረሳ ”እንደሚባለው ከሰሞኑ ቡድኑ በተፈጠረው ሰላም እፎይታን ያገኘው የትግራይ ሕዝብን ዳግም አንገት ለማስደፋት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል። ሕወሓት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው አዋጅ ተራምዶ ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ትዕዛዝ ንቆ ከሕግ ውጪ ጠቅላላ ጉባኤውን አድርጓል።
የሰሜኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ሦስት ወራት ገደማ በኋላ የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት በምርጫ ቦርድ መሰረዙ ይታወቃል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነባሩን የፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር አዋጅን በማሻሻል በኃይል እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፉ ለነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ሕጋዊ ዕውቅና የሚሰጠው አዋጅ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጸድቋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው ይህ አዋጅ፤ ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጽ ተግባር ተሳትፎ የነበረ የፖለቲካ ቡድን በልዩ ሁኔታ በፓርቲነት የሚመዘገብበትን ሂደት በዝርዝር ያስቀምጣል። ፓርቲው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ እንዲችል በደብዳቤ ጥያቄ አቅርቧል።
ምርጫ ቦርድ ሕወሓት ያቀረበውን ማመልከቻ እና ሰነዶች መሠረት በማድረግም ፓርቲው በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ ወስኗል። በዚህም ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ከማካሄዱ ከ21 ቀናት በፊት የጉባዔውን ቀን ለቦርዱ ማሳወቅ አለበት። ቦርዱ በቀሪዎቹ ጊዜያት የፖለቲካ ፓርቲው “ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑ” ክትትል የማድረግ እና ግብረ መልስ የመስጠት ኃላፊነት አለበት።
ምርጫ ቦርድ ይህንን ቢልም ሕወሓት ከሕግ ውጪ ጠቅላላ ጉባኤውን ማድረጉ ሕገወጥ ያደርገዋል። ቡድኑ ሕግና ሥርዓትን ባላከበረ መልኩ የሚያደርገው ፖለቲካ እንቅስቃሴ ከራሱ ከፓርቲው ጭምር ነቀፌታ ደርሶበታል። የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጭምር ጉባዔው የትግራይን ሕዝብ ደኅንነት አደጋ ላይ ከመጣል የዘለለ እርባና እንደሌለው ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት የመመለስን ጉዳይ በሚመለከትም “የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ሕወሓት እንደ አዲስ እንዲመዘገብ የሚያደርግ፣ የትግራይ ሕዝብ የከፈለውን መስዋዕትነት የሚያጎድፍ፣ በቀጣይም ቅርቃር ውስጥ የሚከት መሆኑን በመገንዘብ፣ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ በማዕከላዊ ኮሚቴው አባላት ከመግባባት ተደርሶ ነበር” ሲሉ የቡድኑ አካሄድ ከሕግ አግባብ ውጪ የሚደረገው ጉዞ ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን የግል ፍላጎትን ግብ እንዳደረገ አጋልጧል።
ትናንት ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመፅ ተግባሩን በማቆም ሕገ-መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ የተስማማው ሕወሓት ከሕግ ውጪ ሊሆን የሚችልበት አሠራር እንደሌለ ጠፍቶት አይደለም። የቡድኑ ድርጊት ትናንት በፈጠረው ስህተት የቆሰለው የትግራይ ሕዝብ ቁስል ሳይሽር አዲስ ቀውስ ለመፍጠር ሽርጉድ እንደማድረግ ይቆጠራል።
ቡድኑ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ አልበቃ ብሎት ሕዝቡን ለዳግም መከራ ለመዳረግ እያሟሟቀ መሆኑን በሕገ ወጡ ጉባኤ ላይ በድፍረት እየተናገረ ይገኛል። ሕገ ወጡን ጉባዔ የመሩት ደብረጽዮን (ዶ/ር) ጉባዔውን ማካሄድ ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት የትግራይን ሕዝብ ከተጋረጠበት አደጋ ለማዳን እንደሆነ ተናግረዋል። “እኛ ከሌለን ሀገር መምራት አይቻልም፤ የትግራይ ሕዝብ ያለኛ አይኖርም” የሚል ቆሞ ቀር አስተሳሰብ በሕገ ወጡ ጉባኤ ላይ ተንጸባርቋል። ይህ እሳቤ የትግራይ ሕዝብን መናቅ፤ ከእውነት መራቅም ነው።
የትግራይ ሕዝብ ከፓርቲው ያተረፈው ምንድነው? ተብሎ ቢጠየቅ ፤ ጦርነት ፣ሞትና ድህነትን ነው ። ሕዝቡ ለራሱ፣ ለቤተሰቡ እና ለሀገሩ ተስፋ የነበረን ትውልድ ለሞት እና ለአካል መጉደል፣ በትሪሊዮን የሚቆጠር የሀገር ሀብት ለውድመት አትርፏል። ከዚህ ሁሉ ጥፋት በኋላ “እኔ አድንሃለው” የሚልፈሊጥ የሚያሳፍር ነው።እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ መሆን ያለበት የትግራይን ሕዝብ ከማን ነው የሚያድነው? የትግራይ ሕዝብ አሁን ላይ የሚፈልገው ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት የሚታደገውን ነው። ለዚህ ደግሞ ሕወሓት የታደለ አይደለም፤ ደግሞ ያለፉትን ሁለት አስርት የስልጣን ጉዞውን ማጤን በቂ ነው ።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው እንዳሉት፤ ከሕዝብ ፍላጎት እየተቃረኑ በትግራይ ሕዝብ ስም የሚፈጸም ሕገ ወጥ ተግባር የግል ፍላጎትን ለማሟላት የሕዝብን መከራና ሰቆቃ ለማራዘም የሚደረግ እኩይ አካሄድ ነው፤ ሊቆም ይገባል። በጥቂት ቡድኖች የስልጣን ፍላጎት ።ዳግም የትግራይ ሕዝብም ሆነ ሀገር ዋጋ መክፈል የለባቸውም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆነ የትግራይ ሕዝብ የዘመናት መሻቱ ሰላም እና ልማት እንደሆነ ይታወቃል። ሕዝቡ በተለያዩ ጊዜያት የከፈላቸው መስዋእትነቶች ይህንን እውነታ ተጨባጭ ለማድረግ እንደሆነ መረዳት ይገባል። ስለሆነም የትኛውም ለሕዝብ ፍላጎት እታገላለሁ የሚል ኃይል ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በሕግ አግባብ መሆን አለበት።
ከዚህ አኳያ ማንኛውም የሕዝብ ፍላጎት ፍላጎቴ ነው የሚል አካል ሕግ እና ሕጋዊ ሥርዓትን ማክበር ፣ ልዩነቶችን በውይይት እና በድርድር መፍታት ፣ ከሁሉም በላይ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸውን ተቋማት ውሳኔ ማክበር ፣ ለውሳኔያቸው ተፈጻሚነት ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል። ከዚህ ውጪ በሕዝብ ስም የሚደረግ የትኛውም እንቅስቃሴ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ተቃርኖ መቆም ነው። በራስ ላይ አደጋ መጋበዝም ነው።
መንግሥትም ይህ አይነቱን የሕዝብ ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ከሕዝብ ፍላጎት ጋር የተቃረነ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴና አካሄድን አደብ ማስያዝ አለበት። ፓርቲው ሕግና ሥርዓት ባላከበረ መልኩ የሚያደርገውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማስተካከል ይኖርበታል። የትግራይ ሕዝብም፤ የሕግ ሥርዓት ከማንኛውም ሰው፣ ተቋም፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፣ ቡድን፣ ስብስብ በላይ መሆኑን ማሳየት ይኖርበታል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም