የተሠበረው ጋሪ እና መዘዙ

ወርቅነህ የትውልድ ቦታው ደቡብ ክልል ልዩ ስሙ ሃዲያ አካባቢ ነው። ትምህርት የተማረው እስከ 5ኛ ክፍል ብቻ ነው። አዲስ አበባ ጎጃም በረንዳ አካባቢ የግል ሥራ የሚሠራ ሲሆን፤ በ20 ዓመቱ ለመማር ፍላጎት ባይኖረውም፤ ከጓደኞቹ በተለየ መልኩ ታታሪ ነው። ሠርቶ አይጠግብም። ኑሮን ለማሸነፍ ቀን ከሌት ይባዝናል። ሰዎችን የሚተባበር ቀና ወጣት ስለመሆኑም አብረውት የሚኖሩ እና አብረውት የሚሠሩ ጓደኞቹ ይመሰክሩለታል።

ቀደም ሲል ይሸከም ነበር። በኋላ ወደ የመንገድ ላይ ንግድ ገባ። አንዱ አልሸጥ ሲለው፤ ሌላ ንግድ ይቀይራል። አንድ ጊዜ በጋሪ ሙዝ ይዞ እየዞረ ይሸጣል። ሌላ ጊዜ ደግሞ አቮካዶ እያዞረ ይሸጣል። አልሆን ሲለው ሽንኩርት እና ቲማቲም ለመሸጥ ይሞክራል። በአንድ ጋሪ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ በሁለት ጋሪ እስከ መነገድ ይደርሳል። ይህንን ሲያደርግ አንዳንዶች ከመደገፍ ይልቅ እርሱን የሚያናድድ ተግባር ይፈፅሙበታል። ዕቃውን ተውሰው በአግባቡ አይመልሱለትም፤ ታግሶ ያልፋቸዋል። ትዕግስቱን አይተው ፈሪ ነው እያሉ ያሙታል። በተለይ ጋሪ እንዋስህ ሲሉት ጨክኖ አይከለክላቸውም። መልሶ ሠርተው እንዲመልሱለት ያውሳቸዋል። ጋሪውን ሲያበላሹበት እና ሲሰብሩበት ደግሞ በጣም ይበሳጫል። ነገር ግን ብስጭቱ ብዙ አይቆይም። መልሶ ይተወዋል፡፡

ወርቅነህ ከሰዎች ጋር የሚጣላ ሰው አይደለም። ከኤርሚያስ ጋር ደግሞ በልዩ ሁኔታ ይግባባሉ። ኤርሚያስ ለወርቅነህ ጓደኛው ነው። አንዳንዴ ተከራይተው አብረው ያድራሉ። ኤርሚያስ ‹‹ጋሪህን አውሰኝ ልነግድበት›› ብሎ ለወርቅነህ ጠየቀው። ወርቅነህ እንደተለመደው አልጨከነም፤ ‹‹ወስደህ ሥራህን ስትጨርስ መልስልኝ፡፡›› ብሎ ጋሪውን አዋሰው። ኤርሚያስ በጋሪው ሲሠራ ቆየ፤ ነሐሴ 12 ቀን ስምንት ሰዓት አካባቢ ኤርሚያስ ጋሪው የሚቀመጥበት ቦታ ላይ መለሰ።

የጋሪው መሰበር

ወርቅነህ በበኩሉ በጋሪው ሊሠራበት አስቧል። በዛውም ኤርሚያስ ጋሪውን በተገቢው መልኩ መመለሱን ለማረጋገጥ ጋሪው የሚቀመጥበት ቦታ ሄዶ ሲያየው ጋሪው ተሠብሯል። ወርቅነህ በጣም ተበሳጨ። ወደ ኤርሚያስ ሲሔድ ኤርሚያስ ከጓደኛው ዓለሙ እና ከቸርነት ጋር ነበር። ወርቅነህ ለኤርሚያስ ‹‹እንዴት ያዋስኩህን ጋሪ ትሰብራለህ?›› ብሎ ሲጠይቅው፤ ዓለሙ ጣልቃ ገባ። ለጓደኛው ለኤርሚያስ አግዞ፤ ‹‹ራስህ በሰበርከው እርሱ ላይ አታፍጥበት፡፡›› ብሎ ወርቅነህ ላይ መደንፋት ጀመረ፡፡

ወርቅነህ ‹‹አንተን አላነጋገርኩም ያነጋገርኩት ኤርሚያስን ነው፤ ስለዚህ ኤርሚያስ መልስ ይስጠኝ።›› አለው። ዓለሙ ግን ለያዥ ለገናዥ አስቸገረ፤ ‹‹ከእኔ ጋር እንነጋገር ና ይዋጣልን፡፡›› ማለት ጀመረ። ዓለሙ ደረቱን እየገፋ ግንባሩን እያሾለ ለመደባደብ ራሱን ሲያዘጋጅ፤ አብሯቸው የነበረው ቸርነት ለወርቅነህ፤ ‹‹አንተ መጀመሪያም ለምን ጋሪህን ትሰጣለህ?›› ብሎ መሐል ላይ ገብቶ ለመገላገል ሞከረ። በዛ ጊዜ ለጓደኛው ተቆርቋሪው ዓለሙ ለወርቅነህ ‹‹ዕቃህን አድርሰህ ና ወይም ልብ ካለህ ማታ እንገናኝ፡፡›› ሲለው ወርቅነህ ዝም ብሏቸው ከአካባቢው ራቀ።

ወርቅነህ ከነገር ለመሸሽ ከአካባቢው ራቅ ብሎ ቢሔድም፤ ወደ ማታ ሻይ የሚሸጥበት አካባቢ ጎዳና ላይ ሻይ እየጠጣ ብስኩት ሲበላ ስልኩ ጠራ። ስልኩን ሲመለከት የደወለው ዓለሙ ነው። ወርቅነህ ተናድዶ፤ ጥሪውን ለመመለስ ስልኩን አንስቶ ‹‹ምን ፈልገህ ነው?›› ብሎ አነጋገረው። ደዋዩ ‹‹የት ነህ?›› የሚል ጥያቄ አቀረበለት። ‹‹የትስ ብሆን ምን አገባህ? ለምን ፈለግከኝ?›› ብሎ ምላሽ ሳይጠብቅ ወርቅነህ ስልኩን ዘጋው፡፡

ዓለሙ መደወሉን አላቆመም። በድጋሚ ሲደውል፤ ወርቅነህ ‹‹በድጋሚ ስልኩ ጠራ፤ ›› እንደገና መልስ ለመስጠት ወርቅነህ ‹‹ሃሎ›› አለ። ዓለሙ ባሻገር ሆኖ ለወርቅነህ፤ ‹‹ወንድ ከሆንክ ናና ይዋጣልን፡፡›› አለው። ቀን የተጣላው ዓለሙ ማታም ሊተወው ፍቃደኛ አልሆነም። ወርቅነህ በዓለሙ ሁኔታ በጣም ተበሳጨ። ‹‹እሺ የቀኑ ቦታ ላይ ጠብቀኝ›› ብሎ ምላሽ ሰጠ። ነገር ግን ወርቅነህ ላለመጣላት በመፈለጉ መልሶ ተወው። ቀን የተጣሉበት ቦታ ላይ አልሔደም።

የምሽት ቀጠሮ

ወርቅነህ ለጠብ የቀጠረውን ዓለሙን ትቶ እራቱን ለመብላት ወደ ጎጃም በረንዳ መሔድ ጀመረ። ወርቅነህ ወደ ጎዳናው ሲመለከት ኤርሚያስ፣ ቸርነት እና ዓለሙ ከሩቅ ሦስት ሆነው አንድ ሕንፃ ሥር ቆመው ተመለከታቸው። እነኤርሚያስ ግን ወርቅነህን አላዩትም። ካዩት ሊያጠቁት እንደሚችሉ ገመተ። ምን ማድረግ እንዳለበት ሲያስብ፤ በጋሪ ቢላዋ የሚሸጥ ሰው አየ። ቢላዋ ገዝቶ ወደ ኪሱ ከተተ። ምንም እንዳልተፈጠረ እየተራመደ ሊያልፋቸው ሲል፤ ዓለሙ ወርቅነህን ሲያየው ተንደርድሮ ያዘው። እነቸርነት ለመገላገል መሐል ገቡ። ዓለሙ ከገላጋይ አልፎ ሁለት ጊዜ የወርቅነህ ፊት ላይ በቦክስ ሰንዝሮ መታው።

ወርቅነህ ቦክሱ ሲደጋገምበት በኪሱ የያዘውን ቢላዋ አውጥቶ የዓለሙን የግራ እግር ላይ ጭኑ አካባቢ አንድ ጊዜ ወጋው። የወጋበትን ስለት ቢላዋ በድጋሚ ሰንዝሮ ጎኑ አካባቢ ጎድኑን ወጋው። ዓለሙ ወርቅነህ ስለት መያዙን ሲያውቅ ጭንቅላቱን ግራ እና ቀኝ እያወዛወዘ አጎንብሶ ድንጋይ መፈለግ ጀመረ። ወርቅነህ በበኩሉ ድብድቡ እንዲያበቃ ፈልጓል። ነገር ግን ዓለሙ ካልገደለ የሚመለስ አይመስልም። ስለዚህ ወርቅነህ ፊቱን ሲያዞር የፖሊስ ጥበቃ ሴንተር ተመለከተ። ወደ ፖሊስ ማዕከሉ ጊቢ መሮጥ ሲጀምር፤ ዓለሙ ወርቅነህ ላይ ትልቅ ድንጋይ ከጀርባው ወርውሮ ጭንቅላቱን መታው። ወርቅነህ እየተንገዳገደ ቢላዋውን ግቢው በር ላይ ጥሎ ውስጥ ገብቶ ወደቀ።

ዓለሙም ከዛ በላይ መደባደብ አልቻለም። ሰውነቱ ዛለ፤ ጉልበቱ ተፍረከረከ። እርሱም ተዝለፍልፎ ግቢው ውስጥ በጀርባው ወደቀ። ወርቅነህ ከዚህ በላይ መቀጠል አይችልም ነበር። ቢላዋውን ግቢው በር ላይ ጥሎት ነበር። ዓለሙም ከወደቀበት ተነስቶ ለመደባደብ አልሞከረም። የዓለሙ ደም በከፍተኛ መጠን መፍሰስ ቀጠለ። ሁለቱም እንደወደቁ ሰዎች ተሰብስበው ወደ ማዕከሉ ገቡ። ወርቅነህን ሲያዩት ደህና ነው። ዓለሙ ግን የሚፈሰው ደም ብዙ ስለሆነ እንደተጎዳ ገምተው ወርቅነህን እዛው በፖሊስ ማዕከሉ ትተው ወደ ሆስፒታል ወሰዱት። ወርቅነህም እጁን ለፖሊስ ሰጠ። ዓለሙ ሆስፒታል እስከሚደርስ በሕይወት ነበር። ዓለሙን ሰዎች ተረባርበው ሊያድኑት ቢሞክሩም ሊሳካ አልቻለም። ደሙ በከፍተኛ መጠን ሲፈስ ስለነበር ሐኪሞቹ ብዙ ተጣጣሩ ነገር ግን በዛችው ቀን ሌሊት ሕይወቱ አለፈ።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ ጉዳዩን መመርመር ጀመረ። ከወርቅነህ የእምነት ክህደት ቃል ተቀበለ። ወርቅነህ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ላይ እንደሰፈረው፤ ወርቅነህ ‹‹ጥፋተኛ ነኝ›› ብሎ አምኗል። ድርጊቱን የፈፀመበትን ሁኔታ ሲያስረዳ ሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም የሟች ዓለሙ ዳዊት ጓደኛ የሆነው ኤርሚያስ አበራ በጋሪው ለመሥራት ወስዶ ነበር። ሥራውን ጨርሶ ጋሪውን ያስቀመጠበት ቦታ ሔዶ ሲያይ ጋሪው ተሰብሯል። ወርቅነህ ለምን ጋሪው ተሰበረ በሚል ብስጭት ኤርሚያስን ሔዶ ሲጠይቀው፤ አብሮት የነበረው ዓለሙ ለጓደኛው ለኤርሚያስ በማገዝ ራስህ የሰበርከውን እርሱን አትጨቅጭቀው ብሏል። አንድ ሁለት እያሉ ወደ ጠብ ገብተው ነበር።

በእምነት ክህደት ቃሉ ላይ እንደሠፈረው፤ ወርቅነህ ዓለሙ ይሞታል ብሎ አልገመተም ነበር። ከጠብ ለመራቅም ብዙ ሞክሯል፤ ነገር ግን በተቃራኒው ዓለሙ ወርቅነህ ተበሳጭቶ ወንጀል ውስጥ እንዲገባ ገፋፍቷል። ስልክ እየደወለ ‹‹ና ይዋጣልን›› ብሎታል። ወርቅነህ ሊሸሸው ቢሞክርም ሟች ዓለሙ ግን በተቃራኒው ወርቅነህን መንገድ ከልክሏል። በዚህ ምክንያት ወርቅነህ በስለት ራሱን ለመከላከል በወሰደው እርምጃ ሟች ዓለሙ ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል። በመጨረሻም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንዳለ የመምሪያው ኃላፊ የዓለሙ ሕይወት እንዳለፈ ሲነገረው እጅግ ደንግጧል። በድርጊቱ በጣም መፀፀቱን በመግለፅ ለምክትል ኢንስፔክተር በዕለቱ ድርጊቱን በመፈፀሙ መፀፀቱን እና በእርሱ ምክንያት የዓለሙ ሕይወት ማለፉን እንደሚያምን አረጋግጧል።

የፖሊስ ምርመራ ቡድኑ የእምነት ክህደት ቃል ከመውሰድ ባሻገር አስከሬን እንዲመረመር አደረገ። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል የአስከሬን ምርመራ ውጤቱን በደብዳቤ አሳወቀ። በደብዳቤው ላይ እንደተመላከተው በሟቹ ጭን ላይ 17 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው ቁስለት በስለት በመወጋት የተከሰተ ሲሆን፤ የ5ኛ የጎድን አጥንቱም ተጎድቷል። የሞቱ ምክንያት በግራ ጭኑ ላይ በተፈጠረ ቁስለት በነበረው ከፍተኛ ደም መፍሰስ ሕይወቱ ማለፉን ተመላክቷል።

በመጨረሻም የፖሊስ ምርመራ ቡድኑ ድርጊቱ የተፈፀመው በነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡30 መሆኑን ጠቅሶ፤ አራዳ ከፍለ ከተማ ወረዳ 02 ልዩ ቦታው ጎጎት ሆቴል ቡና ባንክ አጠገብ ቀን በነበረ ፀብ ምክንያት ቂም በመያዝ ስለት ይዞ በመጠበቅ ሟች ዓለሙ ዳዊት የተባለውን ሰው ወርቅነህ ጫኔ የግራ ጭኑን ከፊት በኩል አንድ ቦታ ላይ ወግቶ ከፍተኛ የደም መፍሰስ በማጋጠሙ የዓለሙ ሕይወት እንዲያልፍ አድርጓል በማለት ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት መረጃውን እና ማስረጃውን አደራጅቶ ዝርዝሩን አቀረበ።

የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ

የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በፖሊስ የምርመራ ቡድን የቀረበውን ክስ አደራጅቶ ወንጀሉ የተፈፀመው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ በመተላለፍ መሆኑን ጠቅሶ፤ የአስከሬን የምርመራ ውጤትን፣ የተከሳሽ ወርቅነህን የእምነት ክህደት ቃል እንዲሁም የሰው ምስክር አቀረበ። የግድያ ወንጀል መፈፀሙን ማስረጃዎች ተሰምተው እና ታይተው በበቂ የቀረቡ በመሆናቸው ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጠ።

                                                                                                       –  ውሳኔ

ተከሳሽ ወርቅነህ ጫኔ በተከሰሰበት ሰው የመግደል ወንጀል ክርክሩ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ሲካሔድ ቆይቷል። ፍርድ ቤቱ በሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ወንጀል ፈፃሚውን ያርማል ሌሎችንም ያስተምራል ብሎ ባመነበት የስድስት ዓመት ፅኑ እስራት ፈርዶበታል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You