ቆፍጠን ጅግን ካላልክ የዚህችን ዓለም ትግልና ቀንበር መቋቋምና መመከት አትችልም፤ በዛሬዋ ዓለም እውነታን አስመስለው እንደሚተውኑ አርቲስቶች በምናብ እየተወኑ መጓዝና ድል አደርጋለሁ ብሎ ማሰብ ቂልነት ብቻ ሳይሆን ጅልነትም ጭምር ነው ብዬ አስባለሁ።
ቆፍጣናነትና ጀግንነት በስሜት ሳይሆን በስሌት ሲመሩ ውጤታቸው ያምራል ይሰምራልም። ጀግና ማለት ደግሞ ጨለማን የሚጋፈጥ፤ ሕይወትን የሚያስውብ፣ ያልተፃፉ መልዕክቶችን የሚያነብ፣ ሳትናገር የሚረዳህ፣ ውለታን ሳይሻ ነገን አስቦ መልካም የሚውል ነው። የእነዚህ ሰዎች መፈጠርና መኖር ሀገርንና ሕይወትን ውብ ያደርጋል።
ሺ ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን ብንቃኝ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት የዓለማችን የሁለንተናዊ ዕድገት ደረጃ ቁንጮ ተብሎ ከሚታወቁት አምስት ሀገራት ውስጥ አንዷ ነበረች። ይሁንና የእኛዋ አቢሲኒያ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በሚገባ መያዝና መፍታት ስላልቻለች በዚሁ ምክንያት የተገነባው ትልቅነቷና ዕድገት ቀስ በቀስ አሽቆልቁሎ ከልዕለ ኃያልነት ወደ ተረጂነት እየወረደች መጥታለች።
ገናናዋ ኢትዮጵያና ኩሩ ሕዝቦቿ ከረጂነት ወደ ተረጂነት ተሸጋግረው በማይመጥናት ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ እየተገነባ የመጣውን የ900 ዓመታት የማያቋርጥ ገናናነት ከ6ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በእርስ በእርስ ጦርነት ፈተና ውስጥ በመግባቱ ሥርዓተ መንግሥቱና “ትልቅም ነበር ትልቅም እንሆናለን” የሚለው ትልቅ ራዕይ ምኞት ብቻ ሆኖ ቆይቷል።
ልዩነቶችን አቻችለንና ሀገራዊ አንድነታችንን አጠናክረን መቀጠል ሲገባን ከዚህ በተቃራኒው እየተባባሰ የመጣው የርስ በርስ ጦርነትና ግጭት የሀገሪቷን ፈተና 1262 ዓ.ም. ጀምሮ የጎንደር ዘመነ መንግሥት በ1632 ዓ.ም እስከሚመሠረት ድረስ ኢትዮጵያ ወደለየለት ዝቅጠት የምትሄድበት ዘመን አመላካች ሆኗል።
ለዚህ በአብነት የሚጠቀሰው በአክሱምና ላስታ ለዘመናት የአንድ መንግሥት አዛዥነትን ገንብቶ የማስተዳደር ልምድ የዘለቀ ቢሆንም፤ ወቅቱ አንድ ማዕከላዊ መንግሥት የሚቀመጥበት ማዕከል የሌለበት፣ የሥርዓተ መንግሥት አመራር መስጫና ልዩ ቦታ ያልተገነባበት፣ በስም ብቻ በአካባቢያዊ መጠሪያ “የደጋ ክርስቲያን መንግሥት“ በሚል ንግሥና በቤተሰባዊ ውረድ ተዋረድ የሚተላለፍበት ነበር።
ሀገር የምትመራበት መርሕ እያጣች ስትመጣ፣ የንግድ መስመሮቿ በሰሜን በኩል በቱርክ፣ በምሥራቅ በኩል በአዳል መንግሥት ተቀማ፤ በዚህም በወቅቱ እራሱን እንደ ማዕከላዊ መንግሥት የሚመለከተው “የደጋ ክርስቲያን መንግሥት” ወደ ጦርነት ገብቷል ።
አንዳንድ በአሉታዊ ትርክት የተካኑና አክራሪ የታሪክ ጸሐፊዎች ጦርነቱ በሃይማኖቶች መካከል የተደረገ ጦርነት ለማስመሰል ቢሞክሩም ሐቁ ግን የምሥራቁን ወደብ ተቆጣጥሮ የንግድ መስመሩን የማስተዳደር ፍልሚያ፤ የኢኮኖሚ የበላይነትን የመቆጣጠር ጉዳይ እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ ፡፡
ይህንን ተከትሎ በሀገሪቱ ይስተዋል የነበረውን ሥልጣንን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን በማስቆም፤ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የመመሥረት ጥረት በዓፄ ቴዎድሮስና ዮሐንስ ቢጀመርም፤ የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል። ይህ ጥረት በዓፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ፍሬ አፍርቶ ሀገርን በአንድነት ማቆም ተችሏል። ይህም ሆኖ ግን ሥርዓቱ የቆመበት ፖለቲካ ኢኮኖሚ አጠቃላይ የሆነውን የሕዝቡን ፍላጎት የሚመልስ አልሆነም።
የአፄ ኃይለ ሥላሴ የአገዛዝ ሥርዓትም በዘመናዊነት ስም በጭቆና የተቃኘ ንጉሣዊ/ሉዓላዊ ሥርዓት መሆኑ፤ ሀገሪቱ ለገዛ ዜጎቿ የእስር ቤት ያህል የሆነችበት፤ ዜጐችም የገዛ ሀገራቸው ባለቤት ከመሆን ይልቅ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚቆጠሩበትን ሁኔታ ፈጥሯል። እነዚህንና መሰል እውነታዎች ለዘመናት በልዕለ ኃያልነት ትታወቅ የነበረችውን ሀገር በግጭት አዙሪት ዋጋ እንድትከፍል አድርጓታል። በሕዝቦች የመብት ጥያቄ ስም የተደረጉ “የነፃነት’’ ንቅናቄዎችም ችግሩን እያባባሱት መለያዋ ስደት፣ ችግር፣ ረሃብ ሆኗል።
በትንንሽ የመንደር አለቆች ያገነገነው፣ በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ላይ የቆመው የአፄዎቹ ሥርዓት በውስን የመሬት ባለቤትነት፣ መላውን ሕዝብ ጭሰኛ አድርጎ የሄደበት መንገድ፤ ሕዝቡ የሚፈልገውን ነፃነት፣ እኩልነት እና ፍትሕ ለማግኘት አላስቻለውም። የሕዝቦችን ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አላስቻለም። ይህም ኃይልን ያካተተ ያልተደራጀ ትግል እዚህም እዚያም እንዲፈጠር አድርጓል።
በራያና ቆቦ፣ በጐጃም፣ በባሌና በጌዴኦ ሥርዓቱን ለመጣል የተደረጉ ጥረቶች የዚሁ ማሳያ ናቸው። ሙከራ ትግሉ በወቅቱ ከነበረበት የአደረጃጀትና የአመራር ክፍተት እንዲሁም፤ ሥርዓቱ ከነበረው ዘመናዊ ወታደራዊ አደረጃጀትና ጦር መሣሪያ የበላይነት አኳያ ውጤታማ መሆን ሳይችል ቀርቷል።
ሥርዓቱ በየቦታው በተነሱ የመብት ጥያቄዎች አጣብቂኞች ውስጥ ገብቶ በነበረበት በዚህ ወቅት በተፈጠረ የረሃብ፣ የኑሮ ውድነት፣ ሙስናና አጠቃላይ የሕዝብ ቅሬታ የ1966ቱ አብዮት እንዲፈነዳ ግድ ሆነ። ተቀጣጥሎ የነበረው የሕዝቦች ትግልም የተደራጀ ኃይል ባለመኖሩ በወታደራዊ መንግሥት ተጠልፎ የለውጡ መሻት ጉዞ ወደ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ተቀይሯል። ጭቆናን የሚታገሉ ኃይሎች ትግላቸውን ወደ ትጥቅ ትግል በመቀየራቸውም የዜጎች ደም መፍሰስ ተባብሶ ቀጥሏል።
በሀገሪቱ በተፈጠረውን የፖለቲካ አለመረጋጋት እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ የወሰደው ወታደራዊ መንግሥት ወደሥልጣን መጥቷል እሱም ቢሆን በሥልጣን ላይ በነበረባቸው 17 ዓመታት፤ ሀገር ከውስጥም፤ ከውጪም ያጋጠማትን ፈተናዎች መሻገር ባለመቻሉ፤ ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን ካስከፈለ እና ከብዙ የደም መፋሰስ በኋላ በጠበንጃ ትግል በተለመደው የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ከሥልጣን ተወግዷል።
በ1983 ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ/ም ወደ ሥልጣን የመጣው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ለ27 ዓመታት በልዩነት ትርክት /በዘር፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት/ ሀገሪቱን ገዝቶ፤ በ2010 መስዋዕትነት በጠየቀ የሕዝብ ትግል ከሥልጣን ተሰናብቷል። በሥልጣን ዘመኑ የፈጠራቸው የልዩነት ትርክቶችም አሁን ላይ ፈተና በመሆን ሀገሪቱ ከተለመደው የግጭት አዙሪት እንዳትወጣ አድርጎናል ።
ይሄን ሀገራዊ የታሪክ ትርክት በወፍ በረር ለማንሳት እና የጽሑፌ መንደርደሪያ ያደረግኩበት አንድም የመጣንባቸው ያለመደማመጥ /የግጭት/ መንገዶች የቱን ያህል ዘመን እየተሻገሩ ዛሬ ድረስ እንደ ጥላ እየተከተሉን፤ ብዙ ያልተገባ ዋጋ እያስከፈሉን፣ “ከትናንት ገናና ታሪካችን አውርደው ዛሬ ላይ እንዳቆሙን፤ ከሁሉም በላይ ከትናንት አለመማራችን ችግሩ ዛሬም ፈተና እንደሆነብን ለማሳየት ነው።
እነዚህን ረጅም የፈተና ጊዜያትን /የግጭት ዘመናትን ሳስብ ለምን “ከሱሪ ሱሪህን“ እልህ ወጥተን በሠለጠነ መንገድ ቁጭ ብለን በችግሮች ዙሪያ ተወያይተን፤ ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ አቃተን፤ ለምን የየዘመኑ ትውልድ ከትናንት ጥቁር ታሪካችን መማር አቃተው፤ በርግጥ ከቀደመው የገናናነት ታሪካችን አኳያ ችግሮቻችን ከኛ በላይ ናቸው የሚሉት ጥያቄዎች በውስጤ ይመላለሳሉ።
ዛሬ ምፅዋት የምንለምናቸውና አንዳንዶቹም የዓለም ፖሊስ የሆኑ ሀገራትን ስናይ አሁን ለደረሱበት ደረጃ ውስጣዊ ጉዳዮቻቸውን በራቸውን ዘግተው በራሳቸው ማንንም ጣልቃ ሳያስገቡ እርስ በርሳቸው ተነጋግረው መፍታት በመቻላቸውና መድረሻቸውን ሳይጀምሩ በሀሳብ የጨረሱ ያወቁ በመሆናቸው ነው።
ዛሬ ሁላችንም የምንመኛትና የምንናፍቃት አሜሪካ በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ሕዝቦቿ በቆሻሻ፣ በነፍሳት እና በአስቸጋሪ ጠረኖች ውስጥ ይኖሩ እንደነበር የተለያዩ ጽሑፎች ያስረዳሉ። የእርሻ ቦታዎቻቸውም ጭምር በእንስሳት እዳሪ (ቆሻሻ) የተጥለቀለቀና በየቦታው ፍግ የተበተነ የገበሬዎቹ ቦት ጫማ እና ሱሪ ንፅሕና የጎደለው ነበር።
ምንም እንኳን አሁን በዘመናዊና በሳይንሳዊ መንገድ እየከወኑ ለዓለም የተረፉ ቢሆንም፤ የሥራ ልብሳቸው ብዙውን ጊዜ ቆሻሻ እና ደረቀ ላብ የበዛበት ከመሆኑ የተነሳ የጠነከረ፤ የወንዶቹ ሸሚዝ ደግሞ በትምባሆ ጭማቂ “በቢጫ ኅብር ወይም ሪቫሌቶች” የተበከለ ነበር፤ ነገር ግን ነገን አስበውና የሚደርሱበትን ከጅምሩ ጨብጠው በጥፍራቸው ቆመው ለማደግና ለመለወጥ ታግለዋል።
ዛሬም እኛ በታሪክ አጋጣሚ የዛሬው ትውልድ ላይ የምንገኝ ፈጣሪ የሚሰጠንን አዳዲስ ቀንና መልካም ዕድሎችን በመጠቀም ከግጭት አዙሪት የምንወጣበትን መንገድ ማፈላለግ፤ ለዚህ የሚሆን ድፍረት እና ዝግጁነት ያስፈልገናል። ለትውልድና ለአገር የሚበጅ ነገር መከወን ለነገ ድርጊቶቻችን የሕይወት ዘመን ሽልማቶቻችን መሆኑን በመረዳት “ደግ አባት ዕርስት ያቆማል ክፉ አባት ዕዳ ያቆያል” እንደሚባለው በቅን መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል።
የሕይወት ዘመን ዓላማ እና ግባችን ከራስ ጥቅም በላይ ትውልድን እና ሀገርን ተሳቢ ያደረገ፤ ከቋንቋ እና ከማስመሰል ባለፈ ሆኖ መገኘት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። በርግጥ መኖር ማለት አለመሞት ከሆነ እስትንፋስ ያለው ሁሉ እየኖረ ነው። እውነታው ግን ከዚህ ያለፈ ነው፤ መኖር ማለት ራስን መሆን፣ ለዓላማ መቆም ሕሊናን አለመዘንጋት ፍርድ አለማጓደል ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌላው ራስን መስዋዕት ማድረግ ብሎም አርዓያ የሚሆን ነገር ጥሎ ማለፍ ነው።
ዋጋውን በሰው ዕይታ ውስጥ ሳይሆን በሕሊናው ውስጥ መፈለግ ያቃተው እና ዓሣውን ከውሃ ውስጥ አውጥቶ ከመስመጥ አዳንኩት ከሚል ጉንጭ አልፋ ሙግት ከሚገጥም ጋር ጊዜ ማባከን አስፈላጊም አይደለም። ለራሳችን ታማኝ ሆነን ማምለጫ አጀቦችን ሳንደረድር ምክንያታዊ የሆነ ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማግኘት የምናደርው ጥረት አስደሳች ስሜትን እንድንጎናጸፍ የሚያደርገን ከመሆኑም በላይ፤ ኢትዮጵያ በምትባል ትውልድ የሚቀጥልባት ሀገር ውስጥ ተወዳሽ አልያም እንደ ሥራችን ተወቃሽ የሚያደርገን ነው።
መንፈሳዊ ዕድገት የሚገኘው ከራስ የበላይ ማንነት ጋር የሚኖር መስተጋብር ሲጎለብትና ይኸው የራስ የበላይ ማንነት እያንዳንዷን የሕይወታችንን ሂደት እንዲመራ ስንፈቅድ ነው። በማንበብ፣ በመማር፣ በመመራመር፣ ታላቅ ፍጥረት መሆናችንን በመገንዘብና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ምክንያታዊ ስንሆን ዛሬ ከነበርንበት መስፈንጠር እንችላለን።
በእርግጥ ወደ ብልፅግና የምናደርገው ጉዞ መራራ ነው፤ ነገር ግን ጨክነው ከወሰዱት ወይም ከጠጡት እንደኮሶ መድኃኒት ያሽራል፣ ይፈውሳልም። ሺህ ዓመት ጎመን እየበሉ ከመኖር የተወሰነ ሰዓት ጨከን ብሎ ጎመንን በልተው ሺህ ዓመታትን በብልፅግና እና በተድላ መኖር ተመራጭም የግድም ሊሆን ይገባል፡፡
ድሮ ድሮ ልጅ እያለሁ አክስቴ “ድሃ ለአንድ ቀን ጨክኖ ጎመን እንዳይበላ ዕድሜ ልኩን እየተሰቃየ ይኖራል” ትለኝ ነበር። አሁን ላይ ቆም ብዬ ሳስበው ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ያለው መልዕክት ትልቅ ነው። ስለሆነም አሁን ላይ ይበቃል፣ እስከ መቼስ ኋላ ቀር፣ ተመፅዋች እና ድሆች እየተባልን እንኖራለን በማለት የምንቆጭ ብቻ ሳይሆን የችግሩ መቋጫችንም መሆን ይኖርብናል።
የሸረሪት ድር አድርቶባት ለነዋሪዎቿ የማትመች እንደነበረችው ከተማችን አዲስ አበባ ጨክነን ግልጥልጥ በማድረግ እንደስሟ ውብ እንደተደረገው ሁሉ መራራም ቢሆን እንቆቆውን አልመን በመጨለጥ ከትናንት በሽታችን እንፈወስ። ከትናንት የግጭት ታሪኮቻችን ተምረን ለዘላቂ ሰላማችን እና ከዚህ ለሚመነጨው ብልፅግናችን ዘብ እንቁም ።
እንደ ሀገር አንድነታችንን እና ወንድማማችነታችንን ማጽናት ለኛ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፤ የነገ ተስፋችን እና ብሩህ እጣ ፈንታችን ከዚህ የሚመነጭ ነው ።ለዚህ ደግሞ በችግሮቻችን ፤በአለመግባባቶቻችን ዙሪያ ከአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት እና ትርክቱ ከፈጠረው እና ሊፈጥረው ከሚችል ጥፋት ወጥተን ወደ አዲስ የመደማመጥ መንገድ መምጣት አለብን ።
በተለወጠ ማንነት ፤በሰከነ መንፈስ ከልዩነት ይልቅ በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በማተኮር ፤ የጋራ ትርክቶቻችን ላይ ቆመን ፤ የተለወጠች ሀገር ለመፍጠር መትጋት ይኖርብናል ።ይህም የምንመኛወን ሀገራዊ ብልጽግና ተጨባጭ ለማድረግ አልፋ እና ኦሜጋ ነው። ይህንን በአግባቡ በቅንነት መረዳት እና ተግባራዊ ማድረግም ከሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ የሚጠበቅ ነው። አይቀሬውን የለውጥ /የመለወጥ ተግዳሮት በጽናት መሻገር የምንችለው በዚህ እና በዚህ ብቻ ነው ፡፡
ሰላም!!!
ይታወስ ታሪኩ ከካዛንቺስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም