ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬታማነት

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በብዙ አለመረጋጋትና ውጣ ውረድ ውስጥ ቆይቷል። ኢኮኖሚውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ጭምሮ በየወቅቱ የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። ማሻሻያዎቹ ያስፈለጉበት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በብዙ የማክሮ ኢኮኖሚ አለመጣጣሞች ወይም መዛነፎች ውስጥ ስለነበረ ነው።

ከባድ የዕዳ ጫና፣ የተጋነነ የዋጋ ንረትና መሰል ችግሮች የሀገሪቱ ፈተናዎች ሆነው ቆይተዋል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ወደ ሥራ ገብቶ ተግባራዊ ተደርጓል።

በ2011 በጀት ዓመት ወደ ትግበራ የገባው የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ብዙ የኢኮኖሚ ዓላማዎችንና ግቦችን ያሳካ ነበር። ለአብነትም ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት በአማካኝ የሀገር ውስጥ ምርት እድገትን ሰባት ነጥብ አንድ በመቶ ማድረስ አስችሏል።

የመጀመሪያው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር ቀሪ ሥራዎች ያሉ በመሆኑና ከመጀመሪያው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር መልካም ተግባሮችን በማስቀጠል የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ሚዛንን ለማስተካከል ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መግባቷ ይፋ ተደርጓል።

በእስካሁን ሂደቷ ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን ኢኮኖሚ ገንብታለች። ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ሦስተኛው ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤትም ነች። መንግሥት የግብር ገቢ የመሰብሰብ አቅሙም ተሻሽሏል። እነዚህን ስኬቶች ከሚያስቀጥሉት መሠረታዊ ነገሮች መካከል የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን ማጠናቀቅ የሚያስችለው በአራት ምሰሶዎች የቆመው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉ ነው።

ከአራቱ ምሰሶዎች የመጀመሪያው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን እና ዘላቂነትን የሚደግፍ ዘመናዊ እና ጤናማ የማከሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ መመሥረት ሲሆን ሁለተኛው ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢ እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ነው። ሦስተኛው ደግሞ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ዐቅምን ማጠናከር ሲሆን፤ አራተኛውና የመጨረሻው ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን መቀነስና የንግድ ዕድሎችን በማስፋት የግል ሴክተሩ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ጉልህ ሚና ማሳደግ ነው።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው አጀንዳም ለጠንካራ፣ በግሉ ዘርፍ ለሚመራ፣ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት መጣል ነው። ስለሆነም ፕሮግራሙ በሚተገበርበት ወቅት ከፍተኛ እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ነጠላ አኅዝ የዋጋ ግሽበት ይኖራል ተብሎ ግብ ተጥሎበታል።

ይህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምና በመካከለኛው ዘመን የኢንቨስትመንትና የልማት እቅድ ላይ የተመሠረተ ነው። በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንክና በሌሎች ወሳኝ የልማት አጋሮች የሚደገፍ ነው።

መንግሥት የበጀት አስተዳደር ውጤታማነት እና የመንግሥት እዳ ተጋላጭነትን ያሻሽላሉ ያላቸውን መላዎች አስቀምጧል። ይህ ደግሞ የልማት ፋይናንስ አማራጮችን ያሰፋል፣ ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶችንም በሀገር ውስጥ አቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል ይፈጥራል፤ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ተብሎም ይጠበቃል።

ማሻሻያው በመጀመሪያው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል፣ የነበሩ ተግዳሮቶችን በማረም ተከታታይ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ይመዘገብበታል፤ የአስር ዓመቱን የልማት እቅድ ለማሳካት አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ይሆናል፤ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመፍጠርና የመንግሥትን እና የግሉን ዘርፍ ትብብርን ለማጠናከርም መደላድል ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን የተረጋጋ እንዲሆን ዘላቂ ልማትን፣ ምቹ ኢንቨስትመንትን፣ የንግዱን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ለመጨመር እንዲሁም የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ ያስችላል። የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ዘላቂነትን የሚደግፍ፣ ዘመናዊ እና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ መመሥረትም የሚያስችል እንደሆነ በስፋት እየተነገረ ነው ።

የፖሊሲ ማሻሻያው በገበያ ሥርዓት የሚመራ የውጭ ምንዛሪን የሚያካትት ነው። የውጭ ምንዛሪ እንደእኛ ላሉ ሀገራት ውድ ሀብት ነው። ገንዘብ የራሱ ዋጋ ቢኖረውም ስንወስንበት የኖርንበትን መንገድ ግን ማስተካከል የሚሻው ሆኖ ተገኝቷል። ለዚህም ነው በትይዩና በመደበኛ የውጭ ምንዛሪ መካከል የነበረ ልዩነት ሰፊ ሆኖ የዘለቀው።

ይህን ሥርዓት በማስያዝ በተመሳሳይና ወጥ በሆነ ገበያ እንዲገበያይ ማድረግ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሽለዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ በአጭርም ሆነ በረጅም ጊዜ ባለሀብቶች ወደ ውጭ የሚልኩት ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል የሚል እምነት አለ።

የውጭ ምንዛሪ ማስተካከል ማለት የውጭ ክፍያ ሚዛንን ቀጣይነትና አስተማማኝነት ባለው መንገድ ማስተካከል ማለት ነው። አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር፤ የምርት አቅርቦትን ለማሻሻል፤ የመንግሥት ገቢን ለማሳደግ ሆነ የታክስ አስተዳደሩን ለማዘመን የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ወሳኝ ጉዳይ ነው።

መንግሥት ሀገሪቱ ያለባትን ዕዳ ለመክፈልና እፎይታን ለማግኘትም የፖሊሲው መተግበር የራሱን ሚና ይጫወታል። በዚህ ዙሪያ ያሉ ስጋቶችም ይቀንሳሉ። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲበረታታና እንዲሻሻል ያደርጋል። ይህ በራሱ ለሀገራዊ እድገቱ ምቹ መደላድል ይፈጥራል። የሥራ ዕድል በመፍጠርም የዜጎች ገቢ የተሻለ እንዲሆን ያስችላል።

ትግበራው ዝም ብሎ የሚፈፀም ሳይሆን በበርካታ ደጋፊ ሥራዎች የሚታገዝ ነው። በሞኒተሪ ፖሊሲ፣ በፊሲካል ፖሊሲ፣ በምርትና ምርታማነት፣ በኤክስፖርት፣ በውጭ ምንዛሪ፣ በሁሉም በኢኮኖሚ ውስጥ ባሉና በፋይናንስ ልውውጥ እንቅስቃሴዎች በሙሉ መደገፍ ይገባዋል። ውጤቱም ያማረ እንዲሆን የሁሉንም ቁርጠኛ ተሳትፎ ይጠይቃል።

በእርግጥ ወደ ተሟላ ትግበራ መሸጋገሪያ ወቅት የሚኖር ጫና የሚጠበቅ ነው። ብዙ ሀገራትም ይህንን ሂደት አልፈውበታል። የሚመጣውን ተግዳሮት መቋቋም እንዲቻልም ሥራዎችን ይጠይቃል። ለዚህም መንግሥት በቂ ዝግጅት እንዳደረገ ገልጧል። ፕሮግራሙ የሚያስከትለውን ጫና ኅብረተሰቡ መቋቋም እንዲችል የማድረግ ሥራዎች በፕሮግራሙ ውስጥ ገብተዋል። የተሟላ ቅድመ ዝግጅትም ተደርጎበታል።

ሪፎርሙ ራሱ የሚያመጣቸው የዋጋ ጭማሪዎች ታሳቢ ተደርገዋል። በምንዛሪ ለውጥ ተመን ሳቢያ የሚመጡ የዋጋ ለውጦች ይኖራሉ። ማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ መድኃኒት ወዘተ… በብር የሚከፈለው መጠን ስለሚጨምር ዋጋቸው ይጨምራል። መንግሥትን ዋጋ ቢያስከፍለውም እነዚህን ለይቶ ዋጋ እንዳይጨምሩ ድጎማ ያደርጋል። የማዳበሪያ ዋጋም ሆነ የነዳጅ ዋጋ አሊያም ተመሳሳይ ምርቶች ዋጋ እንዳይጨምር መንግሥት እርምጃ ወስዷል።

ከእነዚህ ምርቶች ውጭ ሌላ ምርት ዋጋ ሊጨምርበት የሚችል ምንም ምክንያት የለም። ሆኖም ግን ሀገር የኢኮኖሚ ለውጥ ውስጥ ባለችበት በዚህ ጊዜ አግባብ ያልሆነ ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ ነጋዴዎች መኖራቸውን እየተመለከትን ነው። ሀገር በተለያዩ የኢኮኖሚ ለውጦች ውስጥ አልፋለች፤ እያለፈችም ነው። እንዲህ ያለውን ጊዜ በጋራ በመተባበር ማለፍ ሲገባ፤ የግል ጥቅምን አስቀድሞ ከራስ ወገን ትርፍ ለማግኘት መስገብገብ ለነገ የሚያስተዛዝብ ነው።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለአስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳይገጥማቸው ዕድል የሚፈጥር ቢሆንም ምርቶች በመጋዘኖቻቸው ውስጥ ደብቀው የለም ሲሉ እየተስተዋለ ነው። ለዚህ ዓይነቱ ተግባር አግባብ ያለው የሕግ አካል የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ ይገባል።

እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ ካልተገባ ጥቅም ከመፈለግ ውጪ ምንም ሌላ ምክንያት የለውም፤ ከዚህ አኳያ፤ መንግሥት የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እየወሰደ ያለው ርምጃ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በዚህ ሕገወጥነት የተሳተፉ የንግድ ተቋማትን ከማሸግ ባለፈ በተደራጀ መንገድ ከፍያለ እርምጃ ሊወስድም ይገባል።

የንግዱ ማኅበረሰብ በእንዲህ ዓይነት ጊዜያት ያልተገባ ትርፍ ከመፈለግ ይልቅ፤ ከኅብረተሰቡ ጎን በመሆን አጋርነቱን በተጨባጭ ማሳየት ይጠበቅበታል። ኅብረተሰቡም ሕገ ወጦችን ከመደበቅ ይልቅ ለሕግ አካላት አሳልፎ በመስጠት ለፖሊሲው ስኬታማ ተፈጻሚነት የድርሻውን ሊወጡ ይገባል ።

በርግጥ የፖሊሲ ማሻሻያው ትግበራ አሁን ላይ የተለያዩ ጫናዎች እንደሚበዙበት ይታመናል። ፖሊሲውን በተሟላ ሁኔታ በጠንካራ ዲሲፕሊን መፈጸም ከተቻለ ውጤታማ ይሆናል። ከዚህም የተነሳ የሀገሪቱም ቀጣይ ዕጣፈንታ ብሩህ ስለመሆኑ አጠያያቂ አይሆንም ።

ችግሮቻችን የጋራ እንደሆኑ ሁሉ ለመፍትሔያቸው በጋራ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ከሁሉም በፊት ስለ ሠላማችን በአንድነት ዘብ ልንቆም ይገባል። ዘላቂ ሠላም ማምጣት የሚያስችል የአስተሳሰብ ተሐድሶ መፍጠር ይጠበቅብናል። ይህን ማድረግ ከቻልን የጀመርነው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ውጤታማ መሆኑ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም ዋና ግብ በተረጋጋ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ፈጣን፣ ዘላቂ፣ ሁሉን አካታች እድገት ማረጋገጥ፤ የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታ በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲመጣና የክፍያ ሚዛን ጤናማ እንዲሆን ማስቻል ነው። ይህ ደግሞ ካለንበት ችግር ለዘለቄታው መውጫ መንገዳችን ነው ።

ለስኬታማነቱም የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ተሳትፎ እንዳለ ሆኖ በተለይም የንግዱ ማኅበረሰብ ካልተገባ ጥቅም ፍለጋ ወጥቶ ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። በሂደቱ አዋኪ አካላትም ይሁኑ አጋጣሚውን በመጠቀም ፈተና የሚሆኑ አንዳንድ ነጋዴዎችም አደብ ሊገዙ ይገባል !

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You