16 ወራት ያስቆጠረውን የሱዳን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ንግግር በጄኔቫ ተጀምሯል

የሱዳን ተፋላሚ ጀነራሎችን ለማቀራረብ ያለመ ምክክር በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ተጀምሯል።

በአሜሪካና ሳኡዲ መሪነት እየተካሄደ ባለው መድረክ ግን ዋነኛ ተፋላሚዎቹ አልተገናኙም።

የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ (አርኤስኤፍ) ተወካዩን ወደ ጄኔቫ ቢልክም በጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ግን በድርድሩ አልሳተፍም ብሏል።

በዚህም ምክንያት ሁለቱን ተፋላሚ ሃይሎች ፊት ለፊት ለማገናኘት የተያዘው እቅድ ሳይሳካ መቅረቱን በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሬሎ ተናግረዋል።

የሱዳን ጦር ተወካዩን አለመላኩ 16 ወራት ያስቆጠረውንና ሚሊዮኖችን ያፈናቀለውን ጦርነት በድርድር ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት ተስፋ ሰጪ እንዳይሆን አድርጎታል።

ከትናንት በስተያ በጄኔቫ በተጀመረው የሰላም መድረክ ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ በይነመንግሥታት (ኢጋድ)፣ የአረብ ኤምሬትስ እና ግብፅ ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

ተቋማቱና ሀገራቱ በሱዳን ግጭት ቆሞ የሠብዓዊ ድጋፎች የሚደርሱበትን ሁኔታ የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ እንደሚያዘጋጁ ሬውተርስ ዘግቧል።

ሱዳንን ለሶስት አስርት ዓመታት የመሩትን ኦማር ሀሰን አልበሽር በሃይል ከሥልጣናቸው ለማንሳት የተባበሩት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጦር ተማዘዋል።

ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያፈናቀለውን ጦርነት ለማስቆም የተደረጉ ጥረቶች እምብዛም ለውጥ ሳያመጡ ጦርነቱ አሁንም ድረስ ቀጥሏል። የሱዳን ጦር የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ከተቆጣጠራቸው ከተሞች ሳይወጣ እና በንፁሃን ላይ የሚፈፅመውን ጥቃት እስካላቆመ ድረስ ለድርድር አልቀመጥም የሚል መግለጫ አውጥቷል።

ሄሜቲ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) በበኩሉ በሱዳን ጦር የሚቀርቡበትን የዘረፋና ንፁሃንን የማጥቃት ክሶች ውድቅ በማድረግ ለሰላም ንግግር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የሱዳን ጦር ትናንት በጄኔቫ በተጀመረው የሰላም ንግግር ላይ ያልተሳተፈው በአሜሪካ እና ሳኡዲ አደራዳሪነት ከዚህ ቀደም የተደረሰው ስምምነት ተፈፃሚ ባለመሆኑ ነው ብሏል።

ስምምነቱ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ተዋጊዎቻቸውን ንፁሃን ከሚገኙባቸው አካባቢዎች እንዲያስወጡ ያዛል።

ይሁን እንጂ የሱዳን ጦርም ሆነ ፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ስምምነቱን አለማክበራቸውን አደራዳሪዎቹ ይናገራሉ። የሱዳን ጀነራሎች የእርስ በርስ ጦርነት ከግማሽ በላይ ሕዝቧ (25 ሚሊዮን) የምግብ ድጋፍ የሚሻባትን ሀገር ሰቆቃ ማባባሱን ተያይዞታል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You