ስለማዕድን ስናነሳ ማዕድንን ለማወቅና ለመለየት የምንጠቀምባቸውን ላቦራቶሪዎች አለማንሳት አይቻልም። ማዕድኑ ያለበት ቦታ ከታወቀ በኋላ በምን ያህል መጠን ይገኛል የሚለውን ለማወቅ ናሙናውን ወስዶ በላቦራቶሪ መመርመር የግድ ይላል። የዚህም የላቦራቶሪ ውጤት በዘርፉ ለሚሠማሩ አምራቾችና ላኪዎች በእጅጉ ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ማዕድንን ካለ ላቦራቶሪ ማልማት አስቸጋሪ እንደሆነ ያሳያል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በማዕድን ሀብት ልማት የሚታወቁ ሀገራት ደረጃቸውን የጠበቁ የማዕድን ላቦራቶሪዎች አላቸው። አሜሪካ፣ ካናዳና ጃፓንን የመሳሰሉ ሀገራት ረጅም እድሜን ያስቆጠሩና ትልልቅ የሚባሉ እውቅ የማዕድን ላቦራቶሪዎች ባለቤቶች ናቸው። ከአፍሪካም ደቡብ አፍሪካ ተጠቃሽ ናት።
በርካታ የማዕድን ሀብት ያላት ኢትዮጵያም ብዙ ላቦራቶሪዎች ባይኖሯትም ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ የማዕድን ላቦራቶሪዎች እንዳሏት ይገለጻል። ከእነዚህ አንዱ የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን ላቦራቶሪ ነው።
አቶ ወረደ ሳሕሉ የኮርፖሬሽኑ የላቦራቶሪ ክፍል ኃላፊ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ በማዕድን ዘርፉ ከሚከናወኑ በርካታ ሥራዎች መካከል አንዱ የማዕድን ላቦራቶሪ ሥራ ነው። በማዕድን ላቦራቶሪ ውስጥ ሁለት ዓይነት የምርመራ ዘዴዎች አሉ። የመጀመሪያው የኬሚካል ምርመራ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሚኖሮሎጂ የተሰኘ የምርመራ ዘዴ ነው። የኬሚካል ምርመራ አሁንም ሙሉ በሙሉ እየተሠራበት ይገኛል። ሚኖሮሎጂ ምርመራ ማዕድናት በተፈጥሯቸው በምን መልኩ እንደሚገኙ የሚገልጽ ነው። ይህ የምርመራ አይነት በመዋቅር ደረጃ ያለ ቢሆንም፣ እስካሁን በዘርፍ ደረጃ አልተቋቋመም።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የኬሚካል ምርመራ ሲባል በቀጥታ ግንኙነት የሚኖረው ለኢንዱስትሪ ግብዓት ከሚውሉ ማዕድናት እና ከሜታሊክ ማዕድናት (ወርቅ፣ ብረት፣ ብር፣ መዳብን፣ ኒኬል) ከመሳሰሉት ጋር ነው።
ለኢንዱስትሪ ግብዓት ከሚውሉ ማዕድናት መካከል ለሲሚንቶ እና ለሴራሚክ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት ይጠቀሳሉ። የእነዚህን ማዕድናት የኬሚካል መጠን ለማወቅ የላቦራቶሪ ምርመራ ይካሄዳል። በምርመራው እያንዳንዱ ማዕድን በአፈር ውስጥ የሚገኝበት መጠን ይታወቃል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ምድርን ሁሉ እንደ ወካይ ማየት አይቻልም። ወካይ ናሙና መምረጥ የግድ ይሆናል። ለአብነትም ወርቅ በተፈጥሮ አፈር ውስጥ ተቀላቅሎ ስለሚገኝ በዓይን አይቶ መለየት ሊያስቸግር ይችላል። በመሆኑም ወካይ ናሙናውን ፈጭቶ ለምርመራ ማዘጋጀት ይቻላል። ይህ ናሙናም የተለያዩ የምርመራ ዘዴዎችን በመጠቀም ምርመራ ይደረግበታል።
አምስት አይነት የምርመራ ዘዴዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያው የምርመራ ዘዴ ቤዝ ሜታል በመባል ይታወቃል። ቤዝ ሜታል መሠረታዊ የሆኑ የብረት አይነቶች (ኮፐር፣ ዚንክ፣ ኒኬል፣ ኮባልት፣ ሊድ እና መሰል) ማዕድናት ለመመርመር የሚጠቀም ዘዴ ነው። የቤዝ ሜታል ምርመራ በአብዛኛው ጥቅም ላይ የሚውለው ከወርቅ ምርመራ ጋር በተያያዘ ነው። ይህን አይነቱን ምርመራ ጂኦሎጂስቶች ወይም ጥናት አድራጊዎች ይፈልጉታል። የኮፐርን ወይም የኒኬልን መጠን ደረጃ መለየት ለወርቅ ምርመራ ስለሚያገለግል ይህንን ዘዴ በመጠቀም ምርመራ ይካሄዳል።
የወርቅ ምርመራ በሁለት አይነት መልኩ ይካሄዳል። አንደኛው በአፈር ውስጥ ያለውን የወርቅ መጠን አሟሙቶ ማየት የሚያስችል ዘዴ መጠቀም ሲሆን፤ ሁለተኛው ወርቅን በማቅለጥ አንጥሮ በማውጣት ነው። ሁለቱም ዘዴዎች ልዩነት አላቸው። ወርቅን አሟሙቶ ለማውጣት ሥራ ላይ የሚውለው ዘዴ የወርቅ የማሟሟት ኃይሉ ውስን ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የተወሰነ ወርቅ ያስቀራል፤ ከ90 በመቶ በላይ ያለውን ወርቅ ለማወቅም አያስችልም። ሁለተኛው ግን በጣም ጥሩ የሚባል ወርቅን የበለጠ ትክክለኛ በሆነ መንገድ የማግኛ ዘዴ ነው። በዓለም ላይ ቀደም ብሎ የተጀመረና እስካሁንም እየተሠራበት ያለ የተሻለ ዘዴ ነው ሲሉ ያብራራሉ።
እነዚህን ሁለት ዘዴዎች ተጠቅመን ወርቅን ከመረመርን በኋላ በአቶሚክ አብዞርፔሽን /Atomic–Absorptio/ አማካይነት በመሣሪያ እንዲነበብ ያደርጋል። ይህ የምርመራ ዘዴ አሁን በዓለም ጥቅም ላይ እየዋለ ያለ ዘመናዊ የመመርመሪያ ዘዴ ነው።
በዓይን የማይታየውን ወርቅ /ተነጥሮም ቢሆን እንኳ/ በዚህ መሣሪያ በመጠቀም በረቀቀ ሁኔታ እስከ ነጥብ 01 ፒፒኤም ድረስ ማንበብ እንደሚቻል አቶ ወረደ ገልጸዋል። ወርቅ በተፈጥሮ በአፈር ውስጥ የሚኖረው መጠን አነስተኛ መሆኑን ተናግረው፣ ወርቅን ውድ እንዲሆን የሚያደርገው አንዱ ምክንያትም ይሄው መሆኑን ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ወርቅ አፈር ላይ ያለው መጠን በጣም በከፍተኛ ደረጃ ከተባለ 100ፒፒኤም ነው። ይህም 100 ግራም በቶን እንደ ማለት ነው። እስካሁን በሀገራችንን እየተመረተ ያለው ትልቅ ምርት የሚባለው ሰባት ግራም በቶን ነው። ይህም አንድ ቶን አፈር ወስዶ ከዚያ ውስጥ ሰባት ግራም ማግኘት እንደ ማለት ነው።
ሌሎች የብረት አይነቶችን ለመመርመር ‹‹ኦር›› የሚባል የመመርመሪያ ዘዴ ጥቅም ላይ እንደሚውልም ተናግረዋል። ብረት፣ ክሮሜየም፣ ኒኬል፣ የመሳሰሉትን ማዕድናት በማሟሟትና ወደ ፈሳሽነት በመለወጥ እና በአቶሚክ አብዞርፔሽን አማካኝነት እንዲነበብ በማድረግ የመለየቱ ሥራ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። በዚህ ዘዴ በሀገሪቱ ያለው ክሮሜየም መለየቱን ጠቁመዋል።
ሌላው በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ተፈላጊ እየሆነ የመጣው ሊትየም ማዕድን መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ማዕድንም የሚመረመረው በእዚሁ መንገድ መሆኑን አመልክተዋል። የሊትየም ማዕድን ከአፈር ውስጥ በማንጠር እንደሚወጣ ጠቁመው፣ አፈር ውስጥ የሚኖረው መጠንም በ‹‹ኦር›› ይመረመራል ይላሉ።
አቶ ወረደ እንዳብራሩት፤ ሊትየም ኢትዮጵያ ውስጥ በፈሳሽና በጠጣር መልኩ ይገኛል። አፋር አካባቢ በፈሳሽ መልኩ በተወሰነ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን፣ የዚህ ምርመራ ውጤትም ለድርጅቶች እና ኤክስፖርት ለሚያደርጉ አካላት ይሰጣል።
ለኢንዱስትሪ ማዕድንነት የሚውሉ ግብዓቶች የሚለዩባቸው ዘዴዎች እንዳሉም ኃላፊው ተናግረዋል። ለምሳሌ ለሲሚንቶ ግብዓትነት የሚውለው ካልሼም ካርቤኒት በውስጡ ካልሼም፣ ማግኒዝየም፣ ሶዲየም፣ ፖታሼም እና ካርባንዳይኦክሳይድን ሊይዝ ይችላል። ለእዚህም በተፈጥሮ በሚገኘው ካልሼም ካርቤኒት ላይ ምርመራ ይደረጋል። ሌላው ለሲሚንቶ ፋብሪካ ግብዓት የሚውለው ጂብሰም ነው። ለዚህ የሚያስፈልገው ካልሼም ሰልፊት በምን ያህል መጠን እንዳለ ከታወቀ በኋላ ፋብሪካው እነዚህን ውሕዶች በመውሰድ አቀነባብሮ ሲሚንቶ ያመርታል ።
ሌሎች ካኦሊን፣ ቤንቶናይት፣ ዳይቶማይት፣ በተፈጥሮ የሚገኙ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በውስጣቸው የሚገኘውን የንጥረ ነገር መጠን ለማወቅ በላቦራቶሪ ፍተሻ እንደሚደረግባቸው ይገልጻሉ። ኮርፖሬሽኑም አብዛኛዎቹ የሲሚንቶና የሴራሚክ ፋብሪካዎች ደንበኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የኢንዱስትሪ ማዕድናቱን በመመርመርና በምን ያህል መጠን እንዳሉ በመለየት እንደሚያሳወቅ ይገልጻሉ።
ከሚኖሮሎጂ ዘርፍ ውስጥ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ የድንጋይ ከሰል ምርመራ ይካሄዳል ሲሉ ጠቅሰው፣ የድንጋይ ከሰል ምርመራን ለማካሄድ የተለያዩ ዘዴዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ተናግረዋል። በቅርቡም የሙቀት መጠኑን ለመለካት የሚያስችል መሣሪያ ለማስመጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ሌሎች የፊዚካል ደረጃ የምርመራ አይነቶች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ወረደ፤ እነዚህ አገልግሎቶች በላቦራቶሪው እንደሚሰጡ ያመላክታሉ።
የላቦራቶሪ ሥራው ምንም አይነት ብክለት አካባቢ ላይ እንዳይደርስ ማድረግ በሚያስችል መልኩ እንደሚከናወንም ገልጸዋል። ለዚህም የተለያዩ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይናገራሉ። ጥቅም ላይ በሚውሉ ኬሚካሎች ላይ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ጠቅሰው፣ ‹‹አንድ ላቦራቶሪ አስፈላጊ ተብሎ እስከተቋቋመ ድረስ ምንም አይነት ብክለት እንዳያስከትል በሚደረገው ከፍተኛ ጥንቃቄ ምክንያት ባሉት መሣሪያዎች አማካኝነት አጣርቶ እንደሚያስወግድ፣ መጠራቀም ያለበትንም እንዲጠራቀም እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
አቶ ወረደ፤ የማዕድናቱ ናሙና ውጤት ማዕድን ማምረት የሚፈልገው አካል የሚፈልገው ማዕድን የትኛው ቦታ ላይ በምን ያህል መጠን አለ የሚለውን ለማወቅ እንደሚጠቅመው ይገልጻሉ። ውጤቱን ወስዶ መሬት ላይ ያለውን ነገር ለማወቅ ይጠቀሙበታል ብለዋል።
በማዕድን ዘርፍ ላይ መሰማራት የሚፈልጉ አካላት ቦታውን ከያዙ በኋላ ናሙና ይዘው ወደ ላቦራቶሪ ያመጣሉ የሚሉት አቶ ወረደ፤ ኮርፖሬሽኑም አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ ውጤቱን እንደሚሰጣቸው ይገልጻሉ። ይህም በዳታ ላይ የተመሠረተው ምን ያህል የክምችት መጠን እንዳለ ተረድተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ያስችላቸዋል ይላሉ።
እነዚህ የላቦራቶሪ መረጃዎች ለጂኦሎጂስቶችና ለምሑራን አቅጣጫ ጠቋሚ መሆናቸውንም ይገልጻሉ። ለምሳሌ ወርቅ ያለበት አካባቢ ኳርዝ የተሰኘ ነጭ ድንጋይ ስላለ በነጭ ድንጋዩ ውስጥ ያሉት ንጥረ ነገሮች እንዲለዩና ሌላ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያካሄዱ እንደሚያግዛቸው አመላክተዋል።
ቀደም ሲል ምርመራ ይደረግባቸው የነበሩ፣ አሁን የማይመረመሩ ማዕድናት እንዳሉም አቶ ወረደ አስታውቀዋል፤ ጨረር አመንጪ የሆኑ እንደ ዩራኒየምና ታንታለም የመሳሰሉ ማዕድናት የሚመረመርበት መሣሪያ መበላሸቱን ጠቅሰው፣ እነዚህን ማዕድናት የመርመር አገልግሎት እንደማይሰጥ አስታወቀዋል።
እንደ አቶ ወረደ ማብራሪያ፤ በላቦራቶሪው ውስጥ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች አሉ። በቅርቡ ደግሞ በጨረር አማካኝነት ምርመራ ማካሄድ የሚያስችሉ ሁለት ዘመናዊ መሣሪያዎች ወደሀገር ውስጥ ይገባሉ።
በዓለም ላይ 103 እስከ 120 አይነት ንጥረነገሮች በላቦራቶሪዎች ይታያሉ። የኮርፖሬሽኑ ላቦራቶሪ አሁን ባለበት ደረጃ ከ37 በላይ አይነቶች ንጥረነገሮችን የመመርመር አቅም አለው። ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለተለያዩ ምርመራ ማዕከሎች የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮችን የመመርመር ሥራ እየተሠራ ነው።
በሚቀጥለው ዓመት ተጨማሪ ንጥረ ነገሮችን ለመመርመር የሚያስችሉ መሣሪያዎች ወደ ሀገር ይገባሉ፤ ይህ ሲሆን ደግሞ 67 ንጥረ ነገሮችን የመመርመር አቅም ላይ ይደረሳል። ቀሪዎችን በተመሳሳይ ሁኔታ የተለያዩ ዘዴዎች በመጠቀም ለመመርመር ታቅዷል።
የኮርፖሬሽኑ ላብራቶሪ አሁን በዓለም ላይ ያሉ ላቦራቶሪዎች የሚጠቀሟቸውን ቁሳቁስ በመጠቀም ማዕድናት መመርመር የሚያስችል ነው የሚሉት አቶ ወረደ፤ ለዚህም በማዕድን ዘርፉ ፍቃድ እንዳለውም ገልጸዋል። አሁን ያለው አቅም ከሀገር ውስጥ አልፎ ለሌሎች ሀገሮችም ምርመራ ለማድረግ በቂ መሆኑን አስታውቀዋል።
አቶ ወረደ ላቦራቶሪው በማዕድን ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ላቦራቶሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚያስችለው የምስክር ወረቀት እንደሌለው ተናግረው፣ ይህን የምስክር ወረቀትም በሚቀጥለው ዓመት ለመውሰድ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
አሁን ለማዕድን ይጠቅማሉ የተባሉ ምርመራዎች ሁሉ እዚሁ ይሠራሉ የሚሉት አቶ ወረደ፤ እንደ ላቦራቶሪ ውስን የሚያደርገን በአፈር ላይ ያለው የንጥረ ነገር መጠን ነው ይላሉ። ‹‹ለምሳሌ በአፈር ላይ ያለው የወርቅ መጠን ዜሮ ነጥብ 002 ሆኖ ቢመጣ የእኛ መሣሪያ መመርመር አይችልም ሲሉ ጠቅሰው፣ ከ0.01 ፒፒኤም/በአንድ ቶን ውስጥ ነጥብ 01 ግራም ቢኖር የመጨረሻው ይታወቃል። ከዚያ በታች ያለውን አሁን ባለው አቅም ማወቅ አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል።
ይህንን ምርመራ ለማድረግ ሌላ መንገድ መጠቀም እንደሚቻል ጠቅሰው፣ ይህ ደግሞ ትርፋማ አይደለም›› ሲሉ ያብራራሉ። የዚህ አይነት ምርመራዎች ብዙም እንደማይጠቅሙ ተናግረው፣ ምርመራውን የግድ የሚፈልጉ አካላት ካሉ ደግሞ ወደወጪ ሊላኩ ይችላሉ›› ብለዋል። ታንታለም የተሰኘውን ማዕድን ለማስመርመር ወደ ውጪ የሚላክበት ሁኔታ መኖሩንም ይገልጻሉ።
ለማዕድን ላቦራቶሪ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች አብዛኛውን ጊዜ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደሚመጡ ተናግረው፣ በዚህ የተነሳ የግብዓት እጥረቶች ያጋጥማል ይላሉ። አንዳንድ ጊዜ አንድ ኬሚካል በማጣት ብቻ መሥራት ያለባቸው ሥራዎች ሳይሠሩ የሚቀሩበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቅሳሉ።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የላቦራቶሪ ናሙናዎች ወደ ተቋም ከመጡ በኋላ በላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤቱን የማስረከቡ ሁኔታ እንደማዕድኑ አይነት ቢለያይም በአብዛኛው በስምንት ቀናት ውስጥ ውጤቱ ይደርሳል። አንዳንዴ ችግሮች ሲያጋጥሙ እስከ አስራ ሁለት ቀናት ሊቆይ ይችላል።
አሁን በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሠማሩ ሰዎች የላቦራቶሪውን ውጤት ከወሰዱ በኋላ በራሳቸው ሌላ ጥናት አድርገው ውጤቱን አስተያይተው የሚያረጋግጡበት ሁኔታ እንዳለም አመለክተዋል። የውጪውን ምርመራ ተመልክተው የኮርፖሬሽኑን የምርመራ ውጤት ትክክለኛነት የሚመሰክሩበት ሁኔታ እንዳለም አቶ ወረደ አስታውቀዋል። የውጭ ባለሀብቶች በሀገር ውስጥ ባለው ላቦራቶሪ ማዕድናትን ለመመርመር የሚቸግር አርገው እንደሚያስቡ ገልጸው፣ ውጤቶቹን በራሳቸው ውጭ ልከው በማስመርመር አስተያይተው ተመሳሳይ ውጤት ሲመለከቱ በድርጅቱ አቅም መገረማቸውን የሚገልጹበት ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል።
‹‹ኢንቨስትመንትን ከሚያበረታቱ ነገሮች አንዱ ላቦራቶሪ ነው›› የሚሉት አቶ ወረደ፤ ላቦራቶሪ የሌለው ሀገር ማዕድን ለማልማት እንደሚቸገርም ነው ያስታወቁት። ምክንያቱንም ሲያብራሩ አንድ ማዕድን ለመፈለግ የሚሰበሰበው ናሙና በጣም ብዙ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው፣ ያንን ወደ ውጭ በመላክ ማስመርመር ደግሞ አይቻልም ብለዋል። የመጨረሻውን ናሙና እንኳን ለማስመርመር የሚጠይቀው ወጪ ብዙ መሆኑን አስገንዘበዋል።
እሳቸው እንደገለጹት፤ የኮርፖሬሽኑ ቀጣይ ሥራ በተቻለ መጠን ሀገር ውስጥ የመመርመር አቅምን በማጠናከር ወደ ውጭ የሚላኩ ናሙናዎች በሀገር ውስጥ እንዲመረመሩ ማስቻል ነው። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ጥናት አድራጊዎች ናሙና ወደ ውጪ ልከው ያስመረምራሉ። ያልተሟሉ መሣሪያዎችን እንዲሟሉ በማድረግ ይህን በማስቀረት ለኢንስቲትዩቶችና ለምርምር ተቋማት አገልግሎት መስጠት ሀሳቡ አለው። የመመርመር አቅምን በመጨመር አገልግሎቱ እንዲሰፋ ለማድረግ ይሠራል ሲሉ በማለት ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም