ውጤቱ ምንም ይሁን ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል!

በርካታ ድራማዊ ክስተቶችን ሲያስተናግድ የቆየው 33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ ትናንት ተጠናቋል። ከመክፈቻ መርሐ ግብሩ አንስቶ ተቃውሞ ያስተናገደው የፓሪስ ድግስ በሳምንታት ቆይታው አስገራሚ፣ ያልተጠበቁ፣ አስደሳች እንዲሁም አሳዛኝ ክስተቶችን አሳልፏል። በኦሊምፒኩ ተካፋይ ከነበሩ ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም አነጋጋሪ የሆነ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋን ከተለመደ ውጤት ርቃ በአንድ ወርቅና ሦስት የብር ሜዳሊያ አጠናቃለች።

ከኦሊምፒኩ አስቀድሞ ከነበረው የዝግጅት ወቅት አንስቶ አለመግባባትንና እሰጣ ገባን ሲያስተናግድ የቆየው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፓሪስም ከምንጊዜውም በላይ የቁልቁለት መንገድ ተጉዟል። ዘመን በማይሽራቸው ድንቅ አትሌቶቿ በኦሊምፒክ የከበረችው ኢትዮጵያ ፓሪስ ላይ በውጤት አንሳ ታይታለች። በዚህም አትሌቲክስን የክብሩ መገለጫ ያደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተከፍቷል።

በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ድል መታወቂያቸው የሆኑ ብርቱ አትሌቶቻችን በአመራሩ ንትርክ የደረሰባቸው የሥነልቦና ጫና በራስ መተማመን ሲርቃቸውና ከለመዱት ውጤት ሲነጣጠሉ ተመልክተናል። ዓለም ቆሞ ያጨበጨበላቸው አንጋፋ አትሌቶቻችንም ክብራቸውን በማይመጥን ደረጃ ቦታ አጥተው የሕግ ያለህ ማለታቸውን ታዝበናል።

የስፖርት ቤተሰቡ ከመነሻው ሲተገበሩ የቆዩ ሕገወጥ ተግባራትን ለአትሌቶች ሞራል ሲባል ተመልክቶ ማለፍን ቢመርጥም ጥፋት ጥፋትን እየወለደ በታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል። በብርቱ አትሌቶቻችን ጥረት፣ ላብ እና ደም የተገነባው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ክብር፣ በጥቅም በተሰባሰቡ ሰዎች መናዱ የብዙዎችን ልብ ሰብሯል።

በዝግጅት ወቅት በኦሊምፒክ ዕጩዎች ምርጫ ላይ ብርቅዬ አትሌቶችን በማሳዘን የጀመረው ጥፋት ዕውቅና በሌለውና በድብቅ በተካሄደው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ምርጫ ነበር የቀጠለው። ይህ ሁኔታ መፍትሔ እንዲያገኝ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ከመስጠት ይልቅ እያድበሰበሱ በማለፍ እንዲሁም ስፖርቱን ለሚመራው መንግሥታዊ አካል ባለመታዘዝ ሁኔታዎች እንዲወሳሰቡና ጥፋቱ እንዲገዝፍ አድርጓል። ኦሊምፒኩ ከተጀመረ በኋላም እንደ ሠንሠለት እየተቀጣጠለ የሄደው ዝርክርክ አሠራር ሀገርን ለውጤት ቀውስ ዳርጓል።

የማይናወጥ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን በመገንባት ስለ ግል ጥቅም ሳይሆን ስለ ሃገር ክብር የሚቆሙ ምርጥ አትሌቶችን ያፈራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከፈረሰ በኋላ ስፖርቱ በማይገባው መንገድ እየተጓዘ ይገኛል። በተነጣጠለ ሁኔታ በግል አሠልጣኝ ተዘጋጅቶ ሃገርን መወከል ለውጤት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ቢናገሩም ጆሮ የሰጣቸው ግን የለም።

በራሳቸው መንገድ ሲዘጋጁ የቆዩ አትሌቶችን ሰብስቦ በአንድነት እንዲወዳደሩ መደረጉ ውጤቱን በግልጽ እያሳየ ይገኛል። ስለ ሰንደቅ ዓላማ ክብር ሲሉ ከራሳቸው ይልቅ የሃገራቸው ልጅ የሚያስቀድሙ፣ የሚደጋገፉ፣ የሚተባበሩና በአንድነት ስሜት ለተፎካካሪዎቻቸው ራስ ምታት የሚሆኑ አትሌቶች እንደ ደመና እየራቁ፤ የኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ተሳትፎም ውበትና ለዛውን እያጣ መጥቷል።

ከታመመ ዓመታትን በተሻገረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ መድኃኒት ከማቀበል ይልቅ ቁስሉ ላይ እንጨት መስደድን ሥራዬ ብለው የተያያዙ ሰዎች አሁንም የስፖርቱ ነቀርሳ ሆነው ወደ ሞት እያንደረደሩት እንደሚገኙ ፓሪስ ላይ ቁልጭ ብሎ ታይቷል። ከአራት ዓመት በፊት በተመሳሳይ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ የተፈጠሩ ስህተቶችና ጥፋቶች ተገቢውን መፍትሔ ሳያገኙ ነገሮች ባሉበት መቀጠላቸውም በጠራራ ፀሐይ ሃገር ስትዋረድ በግልጽ እንድንመለከት አድርጎናል።

ነገሮች ‹‹ስትሄድ እንቅፋት የመታህ ድንጋይ ስትመለስ ካገኘህ …›› እንደሚለው አባባል እየሆኑ፤ ኢትዮጵያን ባሳነሰው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ዋና ተዋንያን በፓሪስም እንዲቀጥሉ ዕድል መስጠቱ በራሱ ግራ አጋቢ ነው። በመንግሥት በኩል ይህ ሁሉ ምስቅልቅል እንዲሆን መተውና እየሆነ ባለው ነገር ጣልቃ ያለመግባት ሕዝቡን ጥያቄ ውስጥ እየከተተውም ነው።

ከዚህ ቀደም የተደረጉ ሕገወጥ ተግባራት መቋጫ ሳያገኙ በእንጥልጥል መቅረታቸው የልብ ልብ የሰጣቸው የስፖርቱ አመራሮች አሁንም ነውራቸውን በግልጽ ከማሳየት ወደኋላ አላሉም። ስፖርቱን የሚመራውን የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ንቆ ከመንግሥትና ከሕዝብ በጀት እንዲለቀቅ ማድረግና ድጋፍ ማግኘት አሠራሩን ጥያቄ ውስጥ አይከትም? መንግሥትስ ይህን ሁሉ ጥፋት ሠርቶ የመጣውን የስፖርት አመራር እያባበለ ሊቀጥል አይገባም።

ከተሳታፊ አትሌቶችና ከሚመለከታቸው ሰዎች በእጥፍ የሚበልጡ ልዑካን ፓሪስ ተጉዘዋል። አመራሩ ቤተሰብና ዘመድ አዝማዱን አስከትሏል። ይህንን እጅግ አስከፊ ያደረገው ደግሞ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የሄዱ አካላት በሚጠበቅባቸው ስፍራ አለመኖርና አትሌቶች የሚፈልጉትን አገልግሎት በማጣት መጉላላታቸው ነው። አሠልጣኞችንና ውድድራቸውን የጨረሱ አትሌቶችን ማዋከብና በፍጥነት ወደ ሀገር እንዲመለሱ በማድረግ ቦታ የማሸጋሸጉንም ተግባር ከሰሞኑ የታዘብነው ጉዳይ ነው።

የክልል ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎችና የስፖርት ማኅበራት የሥራ አስፈጻሚዎች በሙሉ ጉዞ ማድረጋቸው የልምድ ልውውጥን ሽፋን ቢያደርግም እንኳን ተቀባይነት ያለው አይደለም። ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ ባለፈ በቦክስ፣ በብስክሌት እና እግር ኳስ ኦሊምፒክ ላይ በተሳተፈችባቸው ዘመናት ሳይቀር እጅግ የተመጠነ ቁጥር ያላቸው የኦሊምፒክ ኮሚቴ ተወካይ፣ የቡድን መሪዎች፣ በየስፖርቱ የቴክኒክ ባለሙያዎች፣ አሠልጣኞች እና የሕክምና ባለሙያዎች ነበሩ ከተወዳዳሪዎች ጋር የሚጓዙት።

ከኦሊምፒኩ አስቀድሞ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ ላይ ከመገናኛ ብዙኃን ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ከልዑካን ጋር የተያያዘ ነበር። በዚህም ወቅት የኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት የሰጡት ምላሽ ‹‹ሙሉ የኢትዮጵያ ሕዝብስ ቢጓዝ ምን አለበት›› የሚል ነበር። ይህ አሳፋሪ ምላሽ በድህነት ውስጥ ለምትዳክርና ከፍተኛ በሆነ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ ያለችን ሃገር ሁኔታ ያለማገናዘብ ነው። የጉዞ ሁኔታ ከአቅም ጋር የሚያያዝ ብቻም ሳይሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸውና በቀጥታ የሥራ ኃላፊነት ያላቸውን የሚያካትት ነው። ባይሆንማ በኢኮኖሚ አቅማቸው የፈረጠሙ ሃገራት ሕዝባቸውን ፓሪስ ላይ እንዲከትም ባደረጉ ነበር።

እንዳለፈው ጊዜ ሳይሆን በግልጽ የጉዞ ሪፖርት፣ ከውጤት ጋር በተያያዘ አስቀድሞ ከታቀደው የሜዳሊያ ቁጥር አንጻር ምን ያህሉ ተሳክቷል የሚለውን እስከ ምክንያቱ (ለኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ብቻውን ግብ አለመሆኑን ልብ ይሏል)፣ የገቢ እና ወጪ ኦዲት እንዲሁም ከጉዞ አስቀድሞ የነበሩ አለመግባባቶችንና በኦሊምፒኩ ወቅት ሲነሱ የነበሩ ጉዳዮች ላይ በሚገባ የተብራራ ምላሽ ሕዝቡ ይፈልጋል። ለሕግ የበላይነት የቆመው መንግሥትም ኃላፊነት የሰጠው የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር በምን ሁኔታ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንዳልቻለና በበላይነት የሚመራው የስፖርት ማኅበራት አልታዘዝ እንዳሉት መጠየቅ ይገባዋል።

ስፖርት ሃገሪቷ ከፍተኛ ወጪ የምታደርግበትና ምናልባትም በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድልን የፈጠረ አንድ ዘርፍ ነው። መንግሥትም ይህንን በመረዳት በመላ ሃገሪቷ ታላላቅ የስፖርት ፕሮጀክቶች ላይ ሃብቱን እያፈሰሰ ይገኛል። የስፖርት ቱሪዝምን በማሳደግ ከዘርፉ ከፍተኛ ገቢ ለማመንጨት በማሰብም በሃገራዊ የቱሪዝም መስሕቦች ውስጥ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ከማካተት ጎን ለጎን የውድድር ዕድሎችንም እየፈጠረ ይገኛል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ይህንኑ ዘርፍ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ስመጥር የስፖርት ሰዎችን በመጋበዝ ጭምር ስፖርቱን በአዲስ መንገድ ለማነቃቃት እየተገበሩ ያሉትን ሥራም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው።

ይህ ዓለምን በማንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ግዙፍ ዘርፍ ለሃገራት የገቢ እንዲሁም የገጽታ ግንባታቸው ምንጭ ሆኗል። ኢትዮጵያን በበጎ ያስጠራት አትሌቲክስም ባለውለታዋ ነው። ይህንን መልካም ዕድል መጠቀም ሲገባ በየአራት ዓመቱ በመሰል አሳፋሪ ተግባራት የሃገርን ገጽታ ማጠልሸት፣ ሕዝቡን ማስከፋት እንዲሁም ከመንግሥት ካዝና የሚወጣን ገንዘብ በኃላፊነት አለመጠቀም ሊያስጠይቅ ይገባል። በመሆኑም መንግሥት የሁኔታውን አሳሳቢነት በመረዳትና ሂደቱን በመመርመር ሳይውል ሳይድር በጥፋተኞች ላይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 /2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You