ጉብዝና ያሸልማል!

የበርካታ ተማሪዎች የሂሳብ ትምህርት ውጤት ዝቅተኛ እንደሆነ ይነገራል። ሂሳብ ብቻ ሳይሆን ፊዚክስም ቢሆን ብዙ ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት ሚያገኙበት የትምህርት ዓይነት ነው። ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት ከትምህርት ሚኒስቴር የወጡ የፈተና ውጤት ትንተና መረጃዎች አመላክተዋል። በሁለቱ የትምህርት አይነቶች ዝቅተኛ ውጤት ለመመዝገቡ ታዲያ የተለያዩ ምክንያቶች ይቀርባሉ። የትምህርት አሰጣጥ ሥነዘዴው ቀላል አለመሆን፣ መምህራን ትምህርቱ የሚሰጡበት መንገድ ውስብስብ መሆን፣ በተማሪዎችም በኩል ትምህርቱን አክብዶ ማየትና ሌሎችም ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።

በርግጥ ጨወታ ተኮር የማስተማር ሥነ ዘዴ ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ሁሉንም የትምህርት አይነቶች በቀላሉ እንዲረዱ የሚያደርግ መሆኑ በተባበሩት መንግሥታት ትምህርት ክፍል ጭምር የሚመከር ነው። እንዲያም ሆኖ ግን የሂሳብ ትምህርት አሁንም ቢሆን ለብዙ ተማሪዎች የሚከብድና ከፍተኛ ውጤት የሚገኝበት የትምህርት አይነት አይደለም። ፊዚክስም እንደዛው። ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው እንግዲህ ተማሪዎች የሂሳብ ትምህርት ቀላል መሆኑን ተረድተው ውጤት እንዲያመጡ ለማበረታታት ማይ ሶሮባን ኢትዮጵያ የተሰኘው ተቋም ‹‹ጉብዝና ያሸልማል!›› በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተማሪዎችን በሂሳብ ትምህርት አወዳድሮ መሸለም የጀመረው።

አቶ ከበደ አጥናፉ የማይ ሶሮባን ኢትዮጵያ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ተቋሙ ሶስት ሥራዎችን በዋናነት ያከናውናል። አንዱ እድሜያቸው ከስድስት እስከ አስራ ሶስት ዓመት የሆናቸው ልጆችን የሂሳብ ትምህርት/አባከስ/ ሥልጠና ይሠጣል። ሁለተኛ ሀገር አቀፍ የሂሳብ ትምህርት ጥያቄና መልስ ውድድር ያካሂዳል። ሶስተኛ ደግሞ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ምን ያህል የሂሳብ ጥያቄዎችን መመለስ ይቻላል የሚል የሂሳብ ውድድሮችን ያደርጋል።

ከነዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛ የሂሳብ ትምህርት የጥያቄና መልስ ወድድር ሲሆን በ2016 ዓ.ም በሃምሳ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚገኙ ተማሪዎችን በማሰባሰብ ሲያወዳድር ቆይቷል። የሂሳብ ትምህርት ይከብዳል የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየር ‹‹ጉብዝና ያሸልማል›› በሚል መሪ ሃሳብም ነው ውድድሩን ሲያካሄድ የቆየው። የሂሳብ ትምህርት የጥያቄና መልስ ውድድሩ ሲከናወን የነበረው በአምስት ዙር ነበር።

የመጀመሪያው ዙር የሂሳብ ትምህርት የጥያቄና መልስ ውድድር በየከተሞቹ ነበር የተከናወነው። በቅድሚያ በየከተማው ለሚገኙ ትምህርት ፅህፈት ቤቶች ደብዳቤ ከተላከ በኋላ ትምህርት ፅህፈት ቤቶቹ በውድድሩ ላይ ተማሪዎቻቸው እንዲሳተፉ ሲፈቅዱ የአንደኛው ዙር የጥያቄና መልስ ውድድር በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጁ የሂሳብ ጥያቄዎች በየከተሞቹ እንዲላክ ይደረጋል።

በመቀጠል ተማሪዎች አንደኛውን ዙር የትምህርት ቤት ማጣሪያ ውድድር በየትምህርት ቤቶቻቸው ያካሂዳሉ። ይህንን የማጣሪያ ውድድር ያለፉ ተማሪዎች ሁለተኛ፣ ሶስተኛና አራተኛ ዙር ውድድር ካደረጉ በኋላ በከተማ ደረጃ ማእከል ተዘጋጅቶ ተማሪዎቹ ውድድራቸውን ያካሂዳሉ። ውድድሩም የሚካሄደው ከሶስተኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ደረጃ ባሉ ተማሪዎች መካከል ነው። ለማወዳደሪያ ጥቅም ላይ የሚውለው ቋንቋም መንግሥት ለማስተማሪያነት በሚጠቀማቸው ቋንቋዎችና መፅሃፍቶች መሠረት ነው። ተማሪዎቹም በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉና እነርሱ በሚገባቸው ቋንቋዎች ውድድራቸውን አካሂደዋል። ይህም ሀገሪቷ ላይ ባሉ ቋንቋዎች ሁሉ ተማሪዎች የሂሳብ ትምህርት ጥያቄና መልስ ውድድር ሲያካሂዱ የሂሳብ ትምህርት ቋንቋዊ ውበትንም ያሳያል።

አምስተኛው ዙር የተጠናቀቀውና የከተማ መዝጊያ የተሰኘው ውድድር ሲሆን በዚህ ውድድር ተማሪዎች ከየከተማው ከተማቸውን ወክለው ወደ ሀገር አቀፍ ውድድር የሚያልፉ ተማሪዎች የሚለዩበት ነው። ስድስተኛውና የመጨረሻው ውድድር ደግሞ ከሀምሌ 28 እስከ ነሃሴ አንድ 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በቅርቡ ተካሂዷል። ከየከተሞቹ የመጡት የከተማ አሸናፊ ተብለው የተለዩ 4ሺህ ተማሪዎች የመጨረሻውን ስድስተኛ ዙር የጥያቄና መልስ ውድድር አካሂደዋል። በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ ተማሪዎችም የአራት ሚሊዮን ብር የገንዘብና የአይነት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ባያሸንፉም ከተማቸውን ወክለው ለተሳተፉ ተማሪዎችም የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ስራ አስኪያጁ እንደሚያብራሩት የእንዲህ አይነቱ የጥያቄና መልስ ውድድር ዋና ዓላማ ሂሳብ ትምህርት ይከብዳል የሚለውን አመለካከት ለማስወገድና ጉብዝና እንደሚሸልም መልእክት ለማስተላለፍ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ ውድድር ዓላማ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሂሳብ ትምህርት ውድድር በኦሎምፒክ ላይም ጭምር ስላለ በዚህ የሂሳብ ትምህርት ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ እየተሳተፈች ባለመሆኑ በሂሳብ የተሻሉ ተማሪዎችን በመምረጥ በአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ነው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 /2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You