ሞትን በገንዘብ መግዛት

በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ የሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍና ለአካል ጉዳት በመዳረግ ወደር የለውም። ኢትዮጵያ ጥቂት ተሽከርካሪ ካላቸውና ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ እና ሞት መጠን ከሚመዘገብባቸው ሀገራት ግንባር ቀደሟ ናት።

በኢትዮጵያ በየቀኑ በአማካይ 14 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ እና 31 ያህሉ ደግሞ ለከባድ የአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ ከመንገድ ትራፊክ ደህንነት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ መረጃ ደግሞ በየሁለት ሰዓቱ አንድ ሰው እንደሚሞት ጥናቶች ያሳያሉ። 85 በመቶ የሚሆነው የትራፊክ አደጋ የሚከሰትባቸው አካባቢዎች ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ክልል እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ናቸው። በእነዚህ አካባቢዎች የሚደርሱ አደጋዎች ሲሰሙ ሰውነትን ይሰቀጥጣሉ፤ ጆሮን ጭው ያደርጋሉ።

በእነዚህም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት በሚደርሱ ዘግናኝ አደጋዎች እንደ ሰው ልባችን ሲሰበር ኖሯል። ሆኖም ችግሩ ዛሬም አልተቀረፈም። ከጥቂት ጊዜያት በፊት የደረሱትን የትራፊክ አደጋዎች መለስ ብለን ስንመለከትም ሰው ሆኖ መፈጠርን ጭምር እንድንጠላ የሚያደርጉ ናቸው። የጉዳታቸው ጥግም ከግለሰብም አልፎ ሀገር ላይ ጥቁር ዐሻራ ጥሎ የሚያልፍ ነው። ከእነዚህ ዘግናኝ አደጋዎች ውስጥ ጥቂቶቹን እናስታውስ።

ቦታው ሸጎሌ አካባቢ ነው። ከጳውሎስ ሆስፒታል ወደ ሸጎሌ በሚወስደው መንገድ ዓለም ፀሐይ ድልድይ አካባቢ አንድ የከተማ አውቶብስ ለለቅሶ የተጣለ ድንኳን ጥሶ በመግባት ባደረሰው ጉዳት የሶስት ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል።

አደጋው የደረሰው ቅዳሜ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ሲሆን፤ የ 3 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ20 በላይ ሰዎች ላይም ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በድንኳን ውስጥ ለባለቤቷ ለቅሶ የተቀመጠች ኀዘንተኛም በዚሁ አደጋ ወላጅ እናቷንም አጥታለች። ሕይወታቸውን ያጡትና ጉዳት የደረሰባቸውም ኀዘንተኛዋን ለማጽናናት በድንኳን ውስጥ የተቀመጡ መሆናቸው ተነግሯል።

ሌሎች አደጋዎችን እንመልከት ። እሁድ ሐምሌ 9/2015 ዓ.ም. ንጋት ላይ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ ወረቢ ተብላ በምትጠራ ሥፍራ አንዲት እናት አራት ልጆቿን ጨምሮ 14 ሰዎች ሞተዋል። በአደጋው ወቅት የ14 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ፖሊስ ሲያስታውቅ ሦስት ሰዎች ደግሞ ቆስለው ነበር።

ለዚህ የትራፊክ አደጋ ምክንያቱ ቁልቁለት ቦታ ላይ ከባድ የጭነት መኪና በሕዝብ ማመላለሽ ሚኒባስ ላይ ስለወጣበት መሆኑን ፖሊስ ያስረዳ ሲሆን አደጋውን ያደረሰው የጭነት ተሽከርካሪ ከአዲስ አበባ ወደ ባሕርዳር 500 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ተሳቢ መኪና ነው። ፖሊስም “ቁልቁለት ላይ ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ ሲጓዝ ነበር” ብሏል።

ከባድ ተሽከርካሪው ቁልቁለት መንገድ ላይ ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ በኋላ፣ ሁለት መኪኖችን ገጭቶ በመጨረሻ የሕዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ መኪና ላይ ሙሉ በሙሉ ስለወጣበት በውስጡ የነበሩ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል።

በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት 14 ሰዎች መካከል መምህርት አስመሬ ጎሶማ እና አራት ልጆቿ ይገኙበታል። መምህርቷ የ 18፣ 15፣ 8 እና የ 1 ዓመት ልጆቻቸውን ይዘው ከአዲስ አበባ ወደ ጎሃ ጽዮን ቤተሰብ ጥየቃ እየተጓዙ የነበረ ሲሆን፣ በአደጋው የእናት እና የሁሉም ልጆቻቸው ሕይወት አልፏል።

ሌላውን አደጋ ደግሞ እንመልከት። በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ባጋጠመ የትራፊክ አደጋ ልጃቸውን አስመርቀው ሲመለሱ የነበሩ አባት ከተመራቂ ልጃቸው ጋር ሕይወታቸው ያለበት አደጋ ሁልጊዜም የሚረሳ አይደለም። አቶ ደረጄ ጌታቸው የተባሉት አባት ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀችውን ረድኤት ጌታቸው የተባለችውን ልጃቸው ይዘው ወደ መኖሪያ ከተማቸው ሲመለሱ ነበር የትራፊክ አደጋው አጋጥሞ ሕይወታቸው ያለፈው።

የ51 ዓመቱ የደብረ ሊባኖስ ወረዳ ሠራተኛ የሆኑት አቶ ደረጀ ሁለተኛ ልጃቸውን አስከትለው በሴት ልጃቸው የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመታደም ወደ ሃዋሳ ያቀኑት ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም. ነበር። ከምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ በኋላ ቅዳሜ ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም አባት እና ሁለት ልጆቻቸው ሰሜን ሸዋ ውስጥ ወደ ሚገኛው መኖሪያ ከተማቸው ሻራሮ እየተመለሱ ሳለ ነው ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ሱሉልታ ውስጥ ነበር የትራፊክ አደጋው የደረሰው።

በአደጋው የአቶ ደረጄ እና የልጃቸው ረድኤት ደረጄ ሕይወት ወዲያው ሲያልፍ የ 16 ዓመቱ ታናሽ ልጃቸው ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶበታል።

የአቶ ደረጄ የቅርብ ጓደኛ እና ጎረቤት የሆኑት አቶ አሸናፊ አብዲሳ ለቢቢሲ ሲናገሩ የረድኤት ምርቃትን በማስመልከት ድግስ ተደግሶ ወዳጅ ዘመድ ከቤት ሆኖ መምጣታቸው ሲጠበቅ ነው አደጋው መድረሱ የተሰማው። “ለምረቃው ከብት ታርዶ፣ ጠላ ተጠምቆ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። እኔም እንደ ጓደኛ እና ጎረቤት ተሳትፎ ሳደርግ ነበር። የረድኤት እናትም ተመርቃ የምትመጣዋን ልጃቸውን ለመቀበል እየጠበቁ ነበር። ጎረቤት በሙሉ ቤት ሲደርሱ ለመቀበል እየተጠባበቅን ነው ይህን መርዶ የሰማነው።”

የትራፊክ አደጋው የደረሰው ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው ሊደርሱ 50 ኪሎ ሜትር ሲቀራቸው፣ ሱሉልታ ወረዳ ቆሬ ሮባ ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ ነው። ረድኤት ደረጄ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ትምህርቷን ተከታትላ ለምረቃ የበቃች ሲሆን፣ ወላጆቿ ከምርቃቷ በኋላ ሥራ ይዛ ትጦረናለች ብለው ተስፋ ሰንቀው እንደነበረ ቢቢሲ ያናገራቸው የሟች ጎረቤት እና ጓደኛ ገልጸዋል።

“ይህ አደጋ እጅግ ሰቅጣጭ ነው። ለቤተሰብ አይደለም፤ ለጎረቤት አይደለም አደጋውን ለሰማው ሁሉ በጣም ከባድ ነው። ልጃቸውን በደስታ አስመርቀው ወደ ቤት ሲመለሱ፣ ልጅ እና አባት እንደወጡ ቀርተዋል” በማለት አቶ አሸናፊ የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ለቢቢሲ አማርኛ ክፍል ገልጸዋል።

የሱሉልታ ወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት እንዳለው ለአባት እና ልጅ ህልፈት ምክንያት የሆነው የመኪና አደጋ የደረሰው ሲጓዙበት የነበረው ተሽከርካሪ ከሌላ መኪና ጋር ተጋጭቶ መሆኑን አመልክቷል። በዚህም ሳቢያ አባት እና ልጅን ጨምሮ አምስት ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።

እነዚህ ሁሉ አደጋዎች ዘግኛኝ ከመሆናቸውም በላይ የሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል፤ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፤ ንብረት አውድመዋል፤ ቤተሰብ በትነዋል፤ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ኪሳራ አስከትለዋል፤ እንደሀገርም ዋጋ አስከፍለዋል።

ከ1.5 ሚሊዮን ብዙም ያልዘለለ ቅተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር ላላት ሀገር ኢትዮጵያ የአደጋው መጠን ከፍተኛ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚው የራሱ ሆነ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም በዋነኝነት ግን ችግሩ የተያያዘው ከአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ ጋር የተያያዘ መሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። በሀገሪቱ ከሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች 68.3 በመቶ ያህሉ ምቹ በሆኑ መንገዶች ላይ የሚከሰቱ መሆናቸው እና ከሚደርሱት አደጋዎች መካከል 85.9 በመቶ በአሽከርካሪው ስህተት፣ 3.3 በመቶ በተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ጉድለት፣ 2.8 በመቶው ደግሞ በእግረኞች ችግር የሚያጋጥሙ ናቸው።

በመንገድ ችግር የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች 0.7 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የመንገድ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ጥናት ያመለክታል።

ስለዚህም አደጋውን በዘላቂነት ለመከላከል አሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም የአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ ለዚህ ሁሉ አደጋ መንስኤ እንደሆነ በጉዳዩ ዙርያ የሚሠሩ የትራፊክ ባለሙያዎችና የትራንስፖርት ዘርፍ ኤክስፐርቶች ይናገራሉ።

በተለይም አሁን አሁን መንጃ ፈቃድ የሚሰጥበት መንገድ በአብዛኛው ከገንዘብ ጋር የተያያዘ መሆኑ ለአደጋው መበራከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የሚናገሩ ብዙ ናቸው። በአግባቡ አስፈላጊውን ስልጠና ወስዶና ተምሮ መንጃ ፈቃድ የሚያወጣው ሰው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱና በምትኩ እቤታቸው ቁጭ ብለው መንጃ ፈቃድ የሚመጣላቸው ሰዎች መብዛታቸው የአደጋውን ቁጥር ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን እንዳደረገው ይናገራሉ።

ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት በተሰበሰበ መረጃ አንድ ሰው መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ወራትን መሠልጠንና መማር አይጠበቅበትም። 28ሺ ብር ካለው እቤቱ ድረስ መንጃ ፈቃድ እንደሚመጣለት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ሃሳባቸውን አጋርተውኛል።

ተመዝግበው ሥልጠናና ትምህርቱን ወሰዱ የሚባሉትም ቢሆኑ በስተመጨረሻ 4 ሺህ ብር ጉቦ መክፈል የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህንኑ በመተማመን በበቂ ሁኔታ ሥልጠናውን ከመውሰድ ይልቅ የሚከፍሉት 4ሺህ ብር በመተማመን ወደ ፈተና የሚሄዱና የመንጃ ፈቃድ ባለቤት የሚሆኑ በርካቶች ናቸው።

ያለ በቂ ልምድና ሥልጠና መንጃ ፈቃድ ማውጣት ማለት ሞትን በራስ እና በሌሎች ንጹሃን ላይ መጋበዝ መሆኑን የሚረዱ ጥቂቶች ናቸው። መንጃ ፈቃድ በገንዘብ ማውጣት ማለት ሞትን እቤት ድረስ መጋበዝ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

ማሽከርከር ትልቅ ሙያ ከመሆኑም ባሻገር ከፍተኛ ኃላፊነትንም የሚጠይቅ ነው። ከራስም አልፎ የሌሎችን ሕይወት የሚቀጥፍና በርካቶችንም ለማይሽር ጠባሳ እና ጉዳት የሚዳርግ ነው። ሆኖም ብዙዎች አሽከርካሪነትን የሚመለከቱት መሪ መጨበጥንና በጎዳና ላይ ፈልሰስ ብሎ መሄድን ብቻ ነው። ጉዳዩ ግን ከዚህ በጣም የራቀ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ሙያ ቢሆን የዚህን ያህል አደጋ የሚያስከትል የለም። በሙስናና እና በብልሹ አሠራር ምክንያት በእንዝላልነትና በግዴለሽነት በሚታደሉ መንጃ ፍቃዶች የብዙዎችን ሕይወት አጨልመዋል፤ በርካቶችን እስከወዲያኛው እንዲያሸልቡ አድርጓቸዋል፤ ለማይሽር የአካል ጉዳት ዳርጓቸዋል።

ቤተሰብን በትኗል፤ እናትን ያለልጅ አስቀርቷል፤ ልጅን ወላጅ አልባ አድርጓል፤ የሚዋደዱ ባልና ሚስቶች እንደ ቀልድ ወጥተው በዛው ቀርተዋል፤ በአንድ ጀንበር አንድ ሙሉ ቤተሰብ ከመኖር ወደአለመኖር ተሸጋግሯል።

ይህ ሁሉ እየታየ ግን ዛሬም መንጃ ፈቃድ እንደቆሎ ይቸበቸባል። አንደዳቦ በየቤቱ ይታደላል። ይህ ጉዳይ የሚመለከተውም የትራንስፖርት ባለሥልጣን አደጋው አፍንጫው ሥር ሆኖ ሺዎችን እየፈጀ ዝምታን መርጧል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 /2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You