የመጽሐፉአዘጋጅ፡- ሙሐዘጥበባትዲያቆንዳንኤልክብረት፤
- የኅትመትዘመን፡- 2016 ዓ.ም.
- የገጽብዛት፡- 575 ገጽ
- የወረቀትመጠን(ሳይዝ)፡- በሽሮመልክ A5 ወረቀት፣
- የመሸጫዋጋ፡- ብር 1000.00 (አንድሺህብር)፤
- ታተመ፡- ኢክሊፕስማተሚያቤት፤
“የትርክት ዕዳና በረከት” በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃው መጽሐፍ፤ በስድስት ክፍሎች የተደራጀ እና በ48 ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው:: አንድም መጽሐፍ ለመረዳት ርዕስ ትልቁ የመግቢያ በር ነው:: ከዚህ አኳያ ከታየ፤ የመጽሐፉን ርዕስ አጠቃላይ የመጽሑፉን ጭብጥ የተሸከመ ሲሆን፤ ከርእሱ ለመረዳት የሚቻለውም በኢትዮጵያ ሲነገር የኖረው ትርክት እንደ ሀገርም ሆነ ሕዝብ ዕዳም፣ በረከትም ያስከተለ መሆኑን ነው::
አንባቢም ከመጽሐፉ ርዕስ የተረዳውን ሃሳብ ይዞ የመጽሐፉን ገጾች ዘልቆ ሲያነብም፤ ትርክት ጠቀሜታው እና ዘላቂነቱ ታስቦበት በዓላማ ከተዘጋጀ ለሀገር መድህን ስለመሆኑ ያስገነዝቡታል:: በአንጻሩ፣ ከሀገር እና ከወገን ዘላቂ ጥቅም ይልቅ ለግል እና ለቡድኖች ጊዜያዊ ጥቅም ተብሎ ከተዘጋጀ፣ ትርክት ለሀገርም፣ ለሕዝብም ዕዳ ይዞ እንደሚመጣ ነው ከመጽሐፉ ገጾች የሚረዳው::
ይሄን የትርክት ዕዳነትም ሆነ በረከትነትን ከመግለጥ አኳያ፣ የመጽሐፉ ገጾች የሚያብራሩበት የራሳቸው አወቃቀር አላቸው:: ለዚህም ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት፣ በስድስት ክፍሎች የተደራጁ 48 ምዕራፎች በየፈርጃቸው የትርክትን ዕዳነትም፣ በረከትነትም ለማስረዳት ተሰናድተዋል::
በክፍል አንድ- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትርክት ማጠንጠኛዎችን፤ በክፍል ሁለት- ነገረ ሕወሓትን፤ በክፍል ሦስት- ነገረ “ጃውሳ”ን፤ በክፍል አራት- ነገረ ኦነግን፤ እንዲሁም በክፍል አምስት ቀደምት የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መልኮችን አስነብቧል:: የመጨረሻው ክፍል ደግሞ ሀገራችን የገጠሟት የተቃርኖ ትርክቶች መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ አመላክቷል::
መጽሐፉ፣ በዚህ መልኩ ተደራጅተው በቀረቡት ክፍሎቹ ባሉ ምዕራፎች ታግዞ፤ በ1960ዎቹ በነበሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲቀነቀን ኖሮ፣ መጨረሻም ሀገር እንድትመራበት ተዘጋጅቶ የቀረበው የተዛነፈ ትርክት ያስከተለውን ዕዳ፤ ስለ ገዥና ተገዥ የተሰጠ የተጣመመ ትርጓሜ ሀገራችን ለገጠማት ችግር ከፍተኛውን ሚና መጫወቱን ያብራራል::
በተለይ ከአለፉት ኀምሳ እና ስልሳ ዓመታት ጀምሮ ሲዘራ የኖረው የተሳሳተ የፖለቲካ ትርክት፤ ከፅንሰት እስከ ፍሬ ያሳየውን ዕድገት፣ የትርክቱ ፍሬዎች የፈጠሩትን ዕዳ፣ እንዲሁም ከተሳሳተው ትርክት ለመውጣት ሊከናወኑ ስለሚገባቸው ተግባራት ተንትኖ አቅርቧል::
“የሀገራዊ ትርክት ከትናንት እስከ ዛሬ” በማለት በሚጀምረው ምዕራፍ፤ ጸሐፊው መልካምም፣ እኩይም የሚላቸው ትርክቶች ምንጫቸው ከየት እንደሆነ ዳስሷል፤ እነዚህ እኩይ ትርክቶች አድገው ለፍሬ መብቃታቸውን አብራርቷል:: ትርክቶቹ ቅቡልነት እንዲያገኙ እድል የሰጡ ሽንቁሮች (መጠጊያ ምክንያቶች) መኖራቸውንም ገልጿል::
ለአብነት፣ ሀገር ለመምራት ቅቡልነት የማግኘት ፍርሃት የነበረበት ድርጅት፣ ለሥልጣን ሲበቃ የማይገናኙ ነገሮችን በማገናኘት አንድን የማኅበረሰብ ክፍል የመሥዋዕት ፍየል አድርጎ ማቅረቡን አመላክቷል:: የእንዲህ ዓይነቱን ፖለቲካዊ ዕሳቤ ደግሞ፣ ቅቡልነትን ያስገኝልኛል በሚል ምክንያት የመረጠበት የመጀመሪያው ነጥብ፣ የቀደመ ቁስልን መቀስቀስ መሆኑን፤ ይሄን መሰል አካሄድ ደግሞ በሌለ ጭራቅ ሌሎችን አስፈራርቶ የራሱ ተከታይ የማድረግ ሙከራ ስለመሆኑ ጸሐፊው ያስረዳል፤(ዳንኤል፣ 2016፣ 23)::
በዚህ መልኩ ጊዜያዊ ቅቡልነት ለማግኘት የሚፈጸም እንዲህ ያለ ትርክት እና ድርጊት ሀገራችንንም፣ ሕዝቦቿንም ዋጋ እያስከፈላቸው መሆኑን ጸሐፊው ደጋግሞ በገለጸበት በዚህ መጽሐፍ፤ ጠባብ፣ ትምክህት እና ነፍጠኛ የሚሉ ሦስት ስያሜዎችም በወቅቱ ጊዜያዊ ቅቡልነትን ለማግኘት ሲባል ለተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች መገለጫ ሆነው እንዲሳሉ ተደርገው የተሰጡ መሆናቸውንም አመላክቷል ::
ጸሐፊው፣ “እነዚህ ሦስት ስያሜ ቃላት ወደ ፖለቲካችን የገቡበት መሠረታዊ ምክንያት ሁለቱን የኢትዮጵያ ታላላቅ ብሔሮች አግልሎና አጋጭቶ ለመኖር ነው፤” (ዳንኤል፣ 2016፣ 28)፤ በማለት የስያሜዎቹን አመጣጥ ይተነትናል::
ስያሜዎች ፤ ይገዳደሩኛል ወይም ሥልጣን ይቀናቀኑኛል በማለት የሚፈራቸውን ብሔሮች እያጋጨ ለመኖር የተፈበረኩ መሆናቸውን ይገልጻል::
እነዚህ ደግሞ ሀገርንም ሆነ ሕዝብን ከፍ ላለ ችግር ያጋለጡ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ በቀጣይ እንዲህ ያለው ፍረጃ በሀገር ላይ ያስከተለውን መዘዝ በሚገባ በመረዳት ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘት ተብሎ በሀገር ላይ ዘላቂ ጥፋት ከሚያስከትል እኩይ ድርጊት መቆጠብ የሚገባ መሆኑን ያሳስባል:: ቀደም ብለው የተፈጠሩ እኩይ ትርክቶች ያስከተሉትን ዕዳ ወደ በረከት ለመቀየር መሥራት እንደሚያስፈልግም ጸሐፊው ጠቁሟል::
ጸሐፊው፣ የትርክት እዳን ወደ በረከት ለመቀየር ከሚያግዙ ጉዳዮች መካከል ሲጠቅስ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በየዘመናቱ ያሳየውን ዕድገትና የቀለማት መቀያየርን ያስተናገደ ስለመሆኑ ገልጿል:: የአሁኗ ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት ሰንደቅ ዓላማ ከመቼ ጀምሮ አገልግሎት ላይ እንደዋለም ጸሐፍትን አስረጂ በመጥቀስ ተንትኖ አቅርቧል:: በመቀጠልም የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ በምክክር ሊፈታ እንጂ ጦር ሊያማዝዝ እንደማይገባ መፍትሔ ይሆናል ብሎ ያመነበትን አጋርቷል::
የታሪክ አጻጻፍን በተመለከተም፣ ስለታሪክ አጻጻፍ የታሪክ ምሁሩን ክርስቶፈር ክላፋምን ጠቅሶ፤ “ታሪክ በዛሬው አመለካከት ላይ ተመሥርቶ ስለትናንት የሚነገር ትርክት ነው:: የዛሬ አመለካከት በተቀየረ ቁጥር የታሪክ ትርክትም ይቀየራል:: ምክንያቱም ምንም እንኳን ትናንትን ለመቀየር ባንችል ዛሬ የሚቀያየረው አመለካከታችን ስለ ትናንት የተለያዩ ጥያቄዎችን እንድናነሣ ያደርገናል፤” ይላል::
“ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጊዜ የታሪክ ሙግቶች ከትናንት ይልቅ በዛሬ የተመሠረቱ ናቸው:: ክርክሩ ትናንት ያ ድርጊት በመደረጉ የሚመጣ ሳይሆን፤ ዛሬ ያንን ድርጊት በምንመለከትበት መነጽር የተነሣ የሚመጣ ነው:: የሰው ልጅ አመለካከት እስከተለወጠ ድረስ በታሪክ ላይ የሚኖረን ክርክር መቼም ቢሆን ይኖራል፤” (ዳንኤል፣ 2016፣ 70-71)፣ በማለት የራሱን ሃሳብ አካፍሏል::
ትናንትን በዛሬ መነጽር ማየት ሀገራችንንም ሕዝቧንም ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን፤ ትናንት በተፈጸመው ዛሬን ለመበየን መነሣታችን፣ ለንትርክ የሚጋብዘን መሆኑን የታሪክ ምሁሩን ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴን ጠቅሶ፤ “በዓለም ላይ የኢትዮጵያውንን ያህል በታሪክ ጉዳይ የተያዙ ሕዝቦች በጣም ጥቂቶች ናቸው፤” (ገጽ 571)፣ በማለት ገልጾታል:: ይሄ አገላለጽ የሚያመለክተው፤ ታሪክን ለራሳችን በሚመች መልኩ ብያኔ እየሰጠን መጠቀማችን ዋጋ እያስከፈለን ስለመሆኑ ነው::
ችግሩን በዚህ ልክ መረዳት ከተቻለ፣ ለዚህ ችግር መፍትሔ ማስቀመጡ ይበጃልና፣ ታሪኩ ያልተጻፈ እንጂ ታሪክ የሌለው ማኅበረሰብ ባለመኖሩ የጎደለውን እየሞሉ ታሪካችን ሁሉንም አቃፊ ወይም አካታች እንዲሆን መሥራት፣ ጥፋቱም ሆነ ልማቱ የጋራችን መሆኑን ማመን፣ የተፈጸመውን ጥፋት በይቅርታ ማለፍ ከችግሩ ልቆ መሻገሪያ፣ ዕዳውንም ወደ በረከት መቀየሪያ አቅም መሆኑን ያስገነዝባል::
ከዚህ አኳያ፣ ታሪክ ዛሬ ላይ ሆኖ ስለትናንት የሚተርክ መሆኑ አጠያያቂ ባይሆንም፤ በዛሬ ድልድይነት የትናንትን መልካም ዕሴት ወደ ነገ በማሸጋገር ወይም ትናንትን ከነገ በማገናኘት ትውልድን የሚያኮራውንና ሀገራችንን የሚያስከብረውን ማስቀጠል የሚገባ መሆኑ መታወቅ አለበት:: እንዲህ ያለው ተግባር እውን የሚሆነው ደግሞ ከተጻፈው ታሪካችን የጎደለው እየተሞላ፤ ያልተስተካከለውም እየተቃና አካታች ሲሆን ነው:: ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ ታሪካችን በሙያው አንቱ በተባሉ የታሪክ ተመራማሪዎች በጥልቀት ሲጠና ነው::
“የትርክት ዕዳና በረከት” ጸሐፊ እንደገለጹት፤ ታሪካችን በምርምር እየዳበረ እንዲሄድ ከማድረግ ባሻገር፤ በየቦታው በቀደምት ኢትዮጵያውያን የተፈጸሙትን ታሪኮች እና ሥልጣኔዎች “የእኛ ናቸው” ብለን ልንቀበላቸው ይገባል:: በልዩ ልዩ ቦታዎች የተፈጸሙ ታሪኮችን “የእኛ ናቸው” ብሎ መቀበል ሲባልም፤ በዘመናት ሂደት በተጻፈው ታሪካችን መካከል ስሕተት ተካትቶ ቢሆን እንኳ ስሕተቱን እያስተካከሉ፣ የጎደለውን እየሞሉ መሄድ እንጂ፤ እኛ የጉዳዩ አካልም፣ ባለቤትም አይደለንም ማለት ተገቢ አይደለም:: ትርክትን የሚያቃናው እና ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን የሚያደርገውም እንዲህ ያለው ተግባር ነው::
ጸሐፊው በመጽሐፉ ደጋግሞ እንደገለጸው፤ የታሪክ መነጽር የሚቀየረው ሰዎች ታሪክን ሊጠቀሙበት የፈለጉበት መንገድ ወይም እይታ ሲቀየር ነው:: በዘመን ሂደት የተፈጸመን የሀገር ታሪክ፣ ከሀገር ይልቅ ግላዊ ጥቅምን በማስቀደም የእኛ አይደለም ብሎ መካድም ሆነ፤ የእነርሱ እና የእኛ ብሎ መከፋፈል የትርክታችን ዕዳ ሆኗል:: በመሆኑም ይህን ዕዳ ወደ በረከት ለመቀየር ከግል ጥቅም ይልቅ ሀገርን ማስቀደም፤ በሀገራችን የተፈጸመውን ጥፋትም ይሁን ልማት ሁሉ የእኛ ነው ብሎ መቀበል ይገባል:: ሀገራችን ከገጠማት ዕዳ የምትወጣበት መሰላልም ይሄው ነው::
ከዚህ በተቃራኒው ተጉዘን፣ በሀገራችን የተፈጸመውን ታሪክም ሆነ ሥልጣኔ የእኛ ብለን አለመቀበላችን እና እነርሱን እንጂ እኛን አይወክለንም ማለታችን ብዙ ታሪክ በተፈጸመበት ሀገር እየኖርን ታሪክ እንዳንማር እንቅፋት ፈጥሮብናል:: ለምሳሌ፣ በዩኒቨርሲቲዎቻችን የታሪክ ትምህርት እንዲሰጥ ሲደረግ፣ የእነ እገሌ እንጂ የእኛ ታሪክ አይደለም የሚሉ፤ ከሚያቀራርቡ ይልቅ የሚያለያዩ ነጥቦችን መምዘዙ ባሰ::ይሄን መሰሉ እንከን እየመዘዙ መነታረክን መፍጠር ደግሞ ትርፉ እዳ ስለመሆኑም አመላክቷል::
ታሪክ መማሪያ እንጂ መማረሪያ እና ሻምላ መማዘዣ እንዳይሆን በመስጋት ትምህርቱ እንዳይሰጥ ሆኗል:: እንዲህ ያለው ተግባር ደግሞ ትርክት ያስከተለው ዕዳ ስለሆነ፤ መነታረኩን ወደ መተቃቀፍ፣ ልዩነቱን ወደ አንድነት፣ ነጠላ የሆነውን ትርክት ወደ አካታች ትርክት ለመለወጥ የታሪክ ጥናትን በማጎልበት የጎደለውን መሙላት፣ የጠፋውን ፈልጎ ማግኘት፣ የተጣመመውን ማቃናት፣ ያልተካተተውን ማካተት ያስፈልጋል::
በዚህ ረገድ የዛሬ አመለካከት በተቀየረ ቁጥር የታሪክ ትርክት መቀየሩ የታመነ ቢሆንም፤ ታሪክን የማቃናት ሂደቱ በወጉ ካልተያዘ መልካም የነበረው ወደ መጥፎ፣ መጥፎ የነበረውም ወደ በለጠ መጥፎ የመቀየር ዕድል ስለሚኖረው በትኩረት ሊከወን የሚገባው ጉዳይ ነው:: ይሄን በማድረግም ነው መጥፎው አመለካከት ወደ መልካም እንዲቀየር ትርክትን መቀየር የሚገባውም፤ የሚያስፈልገውም::
ጸሐፊው አያይዞ ሲገልጽም፤ ትርክትን መቀየር ማለት ያልተፈጸመውን የተፈጸመ አድርጎ፣ የተፈጸመውን ደግሞ እንዳልተፈጸመ ቆጥሮ ማለፍ አይደለም:: ይልቁንም የጎደለውን እየሞሉ የእኔ ታሪክ አልተካተተም የሚል ስሜት እንዳይፈጥር ሁሉን አቀፍ ወይም አካታች በማድረግ ውስጥ የሚከናወን ነው::
ምናልባት፣ የተጣመመ ትርክት ያስከተለውን ዕዳ ወደ በረከት ለመለወጥ የሚያስችል ምን ጉዳይ አለ የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ቢኖር፤ ጸሐፊው፣ “የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ሕመም ሞልቷቸዋል:: የታሪክ አጻጻፋችን ግን የአካታችነትና የብያኔ ችግር አለበት:: የእኛ ዘመን የታሪክ ሊቃውንት ዋናው ሥራም የማቃናትና የማካተት ተግባር ነው::
ለዚህ የሚሆኑ መረጃዎችና ማስረጃዎች ደግሞ ሞልተዋል፤” (ገጽ 81)፣ ሲል አመላክቷል:: በመሆኑም የሚጻፈው ታሪክ፣ በየአጋጣሚው የኢትዮጵያ ተብለው የሚቀርቡ ዝግጅቶች፣ ትዕይንቶች እና ሌሎችም ነገሮች ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ማካተት ሲችሉ፤ ይህማ የእነ እገሌ እንጂ የእኔ ባለመሆኑ አይወክለኝም የሚሉ ወገኖች እየቀነሱ፤ የእኛ ነው የሚሉ ወገኖች እየበዙ ይሄዳሉ::
እንዲህ ያለውን ችግር ለማስወገድ መፍትሔ በማለት ጸሐፊው ከገለጸው መካከል፤ “ሁነኛ መፍትሔው የታሪክ ጥናትን በማበረታታት ሁሉንም ዓይነት ማኅበረሰብና ሁሉንም ዓይነት የማኅበረሰብ የታሪክ መልኮች እንዲዳስስ ማድረግ ነው:: የኢትዮጵያ ታሪክ የሚባል አለን:: ግን የተሟላ አይደለም:: መቼም ደግሞ አይሟላም:: እየተሟላ መሄድ ግን ይችላል:: ለዚህ ደግሞ የታሪክ ጥናት መስክን ማበረታታት ነው፤” (ገጽ 103)በማለት ያሰፈረው ሃሳብ ይገኝበታል::
ከዚህ በተጨማሪም፣ “ትርክቶች የትናንት ታሪኮችን እንደ እርሾ በመጠቀም ዛሬ ላይ ለምንፈልገው አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ ፍላጎቶቻችን የምንጠቀምባቸው፣ ፍላጎቶችን የምናሰባስብባቸው መሣሪያዎች ናቸው:: ትርክት ተቀባይነት የሚኖረው ስለማኅበረሰቡ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ግልጽ በሆነ የጊዜና የድርጊት ፍሰት ሲቀርብ፣ ድርጊቱ ደግሞ ትርጉም ባለው ሁኔታ መቀመጥ ሲችል ነው::
ትርክቶችን በአግባቡ መረዳት በዘመኑ ውስጥ የተስተናገዱትንና የነበሩትን በርካታ የተበታተኑ ክስተቶች በወቅትና በቦታ በማደራጀት እና በማቀናጀት በማኅበረሰቡ ዙሪያ ስለነበረው ሁኔታ ማወቅ፣ መረዳትና ማስተዋል እንዲሁም ማኅበራዊ ማንነቶቻቸውን (ዕሳቤያቸውን) በመገንዘብ ዛሬ ላይ የሚበጀንን የአኗኗር ሥርዓት ለመመሥረት ያስችላል፤” (ገጽ 108)፣ ስልም ትርክቶችን ከእዳነት ወደ በረከትነት የመቀየርን አካሄድ አስረድቷል::
ገንቢም ሆነ ጎጂ ትርክት ዓላማ ያለው መሆኑ፣ ታስቦበት ወይም በዘፈቀደ መዘጋጀቱ በጸሐፊው ተጠቅሷል:: የኢትዮጵያ የሆነውን ሁሉ የአንድ ወገን አስመስሎ ማቅረብም ሆነ፤ የሌሎች እኔን አይመለከተኝም የሚለው አስተሳሰብ በአንድ በኩል ያለመካተት ችግር ያስከተለው ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ ፖለቲካውን በዘር ተደራጅተው የሚመሩ አካላት የሚያደርጉት ቅስቀሳ ውጤት መሆኑን፡-
“ የቋንቋ መዋረሶች እንደ ጸጋ ሳይሆን እንደ መወረርና ማንነትን እንደ ማጣት ተደርገው ይወሰዳሉ:: በዚህ ምክንያት ጥያቄ እያነሡ መቆራቆሱ ዛሬም እንደ አዲስ ቀጥሏል:: ይህ ደግሞ የብሔር ፖለቲካው ያዋለደው ዕሳቤ መሆኑን የታሪክና የፖለቲካ ሊቃውንት ይናገራሉ:: ዛሬ ላይ በሀገራችን ቋንቋ ዳቦ ሆኖ ነፍስ ሲታደግ፤ በአንጻሩም ቋንቋ የጦር መሣሪያ እያስታጠቀና እያጋደለ ያለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ”
“ ቋንቋ በሁለት ጽንፍ ተቃርኖዎ እንዲገለጥ በማድረግ ሁነት ውስጥ መድረሳችን ደግሞ የፖለቲካችን የብስለት ችግር እንጂ የቋንቋዎች ችግር አይደለም:: ምክንያቱም ቋንቋ በተለያዩ ምክንያቶች ሊስፋፋም ላይስፋፋም ይችላል:: በደረስንበት ዘመን የተስፋፋውን መቀነስ ያልተስፋፋውን ደግሞ ጨርሶ መርሳት መፍትሔ አይደለም:: ቋንቋዎች ሁሉ በቻሉት መጠን እንዲያድጉና እንዲከበሩ ማድረግ፤ በራሳቸው በቋንቋዎች ውድድርና ትስስር መርሕ እንዲመሩ መተው፤ እና ብዝኃነትን የሚያከብር ፖሊሲ መከተል ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊሆን ይችላል” (ገጽ 86)፣ በማለት ችግሩን እስከ መፍትሄው ለማስቀመጥ ሞክሯል::
ከዚህ ገለጻ የምንረዳው፤የመጀመሪያው ነጥብ፣ የቋንቋ መዋረስን እንደ ጸጋ ሳይሆን እንደ መወረር ማየት ሀገራችንን እና ሕዝቦቿን ለችግር የዳረጋቸው መሆኑን ነው:: ሌላው ነጥብ፣ የቋንቋ ልዩነት እንደ በረከት መታየት ሲገባው፤ ቋንቋን ወፍራም እንጀራ ለመብላት መሣሪያ አድርገው የሚጠቀሙ አካላት ከኋላ ሆነው ብዙኃኑን እየገፉ ጦር እንዲያማዝዝ ማድረጋቸው ነው:: እንዲህ ያለው ዕሳቤ ደግሞ የብሔር ፖለቲካው ያዋለደው መሆኑን ጸሐፊው ገልጿል::
ሀገራችን እንዲህ ካለው የመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ እንድትገባ ገፍቶ ያደረሳት የፖለቲካው የብስለት ችግር እንጂ የቋንቋዎች ችግር አለመሆኑንም ጸሐፊው አስገንዝቧል:: ፖለቲካው ያስከተለው ችግር በዚህ ሳይወሰን ታሪክን አሽከር አድርጎ ያዘዘውን ሁሉ እንዲፈጽምለት ማስገደዱን “በእኛ ሀገር አሁን ታሪክ የፖለቲካ አሽከር ሆኗል:: መማሪያ ሳይሆን መማረሪያ ሆኗል” ሲል ከገለጸው በኋላ፤ “ይህ ትውልድ ነቅቶ ታሪክን ትጥቅ በማስፈታት ሲቪል ማድረግ አለበት” (ገጽ 117)፣ በማለትም መፍትሔ ያለውን ሃሳብ ለትውልዱ አቀብሏል::
ሌላው በጸሐፊው መፍትሔ ተብሎ የተጠቀሰው ነጥብ፣ “ግልጽነት የጎደለውን አደናጋሪ ትርክት ለመፍጠር ከመቻኮል ይልቅ በዘመናዊነት የዲዛይንና የነባራዊነት አረዳድ ክፍተት ካለ በንግግርና በሞያዊ ሂስ ማስተካከል እንጂ፤ ለመነታረክና ለግጭት ማዋል ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፤” (ገጽ 99)፣ የሚለው ነው:: ታዲያ እንዲህ ያለውን ምክር ተግባራዊ የሚያደርገው ቢገኝ ሀገራችን ከገባችበት ችግር የምትላቀቅ መሆኗ የታመነ ነው::
ታሪክን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የሆነውን ሁሉ፣ “የእኛና የእነርሱ በሚል ታሪክ ተሸብበን፣ አትድረስብኝ አልደርስብህም፣ አትይብኝ አላይብህም፣ ያንተ እንደ ታሪክ ይቆጠራል አይቆጠርም፣ በሚል ትርክት ታሪኮችን ከፍና ዝቅ ማድረግ ብዝኃነትን አለማክበርና ዋልታ ረገጥ ዕሳቤ የትናንት እስረኞች አድርጎናል፤” (ገጽ 144) ይላል ጸሐፊው::
“ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለማምጣት ኅብረ ብሔራዊነትን ከአንድነት ጋር አጣምሮ የያዘ፣ ትናንትን አግባብቶ ለነገ የሚያሻግር ስትራቴጂካዊ ትርክት ይፈልጋል:: … ዓላማው ለትናንት፣ ለዛሬና ለነገ ወሳኝ የሆነ ትርጉም መስጠት ነው፤” (ገጽ 145-146)፣ በማለትም ለችግሩ መፍትሔ ያለውን አስቀምጧል:: ትርክትን ኅብረ ብሔራዊ ማድረግ የሚቻለው ደግሞ አንዳችን ለሌላችን በመኖር ውስጥ መሆኑን ጸሐፊው ደጋግሞ በመጽሐፉ ውስጥ ገልጾታል::
ከትርክት በረከት ለመሳተፍ ወይም ትርክትን በኢትዮጵያውያን ሁሉ ቅቡል ለማድረግ ከሚያግዙ ተግባራት አንዱ በየአካባቢው ለሚገኙ ሥልጣኔዎች እና በየቦታው በኢትዮጵያውያን ለተፈጸሙ ታሪኮች ዕውቅና በመስጠት በአንድ አካባቢ የሚገኙ ሥልጣኔዎች የኢትዮጵያውያን ሁሉ መሆናቸውን መቀበል ዋነኛው መፍትሔ መሆኑንም አስገንዝቧል::
ጸሐፊው፣ የወል ትርክት ለመፍጠር በተቃርኖ ቁልፍ የተከረቸመውን መክፈት የሚቻልበትን መፍትሔ የጠቆመበት ሃሳብም፤ “ትንሣኤ ኢትዮጵያን ለማረጋገጥ ከቅንነት ባሻገር ከሕጸጽ የራቀ፣ የኢትዮጵያንን ኅብረ ብሔራዊ ሥልጣኔ የተገነዘበ እና የሕዝቦችን ተጨባጭ ፍላጎት ያማከለ የመበልጸግ ትርክትና አስተሳሰብ ያስፈልጋል፤” (ገጽ 516፣ 522)፣ የሚል ነው::
ሀገራችን ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ሥልጣን ላይ በወጡ መሪዎች ከምዕራባውያንም፣ ከምሥራቃውያንም የተቃረሙ ርእዮተ ዓለሞች ቤተ ሙከራ ስትደረግ ኖራለች:: እንዲህ ማድረጉ ከጥቅሙ ጉዳቱ በማመዘኑ፤ ብሎም የእኛ እና የእነርሱ እየተባባልን ለመቧደን ምክንያት በመፈጠሩ ወደ ራሳችን ማየት እና አካባቢያችንን ማማተር እንደሚገባን ጸሐፊው ይገልጻል::
ለዘመናት የየባህሉና የየቋንቋ ተናጋሪው ልሂቃን ሲጠቀምበት፣ ችግር ሲፈታበት፣ የተለያዩትን አንድ ሲያደርግበት፣ ለተተኪው ትውልድ ሲያስተላልፈው ወደ ኖረው የኢትዮጵያውያን ሁሉ ወደ ሆነው የልቡና ውቅር መመለስ እንደሚገባ መጽሐፉን ስናነብ የምንረዳው ሀቅ ነው::
አሁንም እንደ ገና ወደ ሌላ ሀገር ዕሳቤ ማማተር ሀገራችንን ለሌላ ዙር ቤተ ሙከራ መዳረግ መሆኑን፤ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የትርክት ዕዳ እና በረከት” በሚለው መጽሐፉ ደጋግሞ ያስገነዘበው እውነት ነው:: ሀገራችንን በየጊዜው እንደ አዲስ ጀማሪ ከማድረግ ይልቅስ ሀገር በቀል የሆነውን ዕሴታችንን ተጠቅመን፣ ዘመን ተሻጋሪ ተግባር ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝቧል።
“ሀገራችንን ከቤተ ሙከራነት ለማውጣት ዋናው መፍትሔ ያለፈውን በትክክል መዝኖ ችግሩን እያስተካከሉ መሔድ ነው፤” (ገጽ 554)፣ በማለት ነው:: እኔ ይሄን ያህል በወፍ በረር ካነበብኩት ካልኳችሁ፤ ቀሪውን እና እልፍ የምታተርፉበትን ሃሳብ ከመጽሐፉ እንድታገኙት ለንባብ በመጋበዝ ነው:: ቸር ይግጠመን፤ ሰላም!!!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም