የፓስፖርት ዋጋ ማሻሻያው ተገቢ አለመሆኑን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገለጹ

– የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከወጪው አንጻር ማሻሻያው ተመጣጣኝ ነው ብሏል

አዲስ አበባ:- የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የአሠራር ማስተካከያና ማሻሻያ ሳያደርግ በዋጋ ላይ ያደረገው ጭማሪ ተገቢና ፍትሐዊ ያልሆነ፣ የመንግሥትንም ክልከላ የጣሰ ነው ሲሉ ተገልጋዮች ቅሬታ አቀረቡ፡፡ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎቱ በበኩሉ ማሻሻያው ከወጪው አንጻር ፍትሐዊና ተመጣጣኝ ነው ብሏል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ቅሬታ አቅራቢዎች አሠራሩ አሁንም መሻሻል የሚጠበቅበት፣ ብዙ ችግሮችም ያሉበት ሆኖ ሳለ የዋጋ ጭማሪ መቅደሙ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ መታረም ያለባቸው በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይስተዋላሉ፣ ተቋሙ የአሠራር ማስተካከያ ሳያደርግ የዋጋ ማሻሻያ ብቻ ነው ያደረገው ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

ጭማሪው በጣም ይከብዳል፣ የማይታሰብና የማይገመት ነው ያሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ቅሬታ አቅራቢዎች፤ በመደበኛ ሲከፈል በነበረው ላይ በአንዴ ሦስት ሺህ ብር ተጨምሮበት እንዲከፈል መደረጉ ተገቢ አይደለም፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍልንም ያገናዘበ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ማንኛውም ጭማሪ እንዳይደረግ በከለከለበት ማግስት ተቋሙ ያደረገው ጭማሪ ተቀባይነት የሌለው፣ የመንግሥትን ውሳኔ እና ክልከላ በግልጽ የሚጥስ መሆኑንም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የሰነዶች ምዝገባና አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ታደሰ፤ አገልግሎቱ ለረጅም ጊዜ ትችት የበዛበት፣ ሕዝብ የሚያለቅስበት፣ ብዙ ቅሬታ ስሞታና እንግልት የሚቀርብበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሠራሩን ለማሻሻል ቴክኖሎጂውን በመቀየር፣ በሰው ኃይል፣ በማቴሪያልና በአጠቃላይ አደረጃጀት ማሻሻያ የማድረግ ተግባር አንድ ዓመት ወስዷል ነው የሚሉት፡፡

ፓስፖርቱ የውጭ ምንዛሪ የሚያስወጣ በመሆኑ በነበረው ክፍያ ብንቀጥል የምናወጣውና የምናስከፍለው ዋጋ ተመጣጣኝ አይሆንም፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ለዚህ አገልግሎት የመንግሥት ድጎማ ሊያስፈልገን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሁሉም ነገር መቶ በመቶ ሥርዓት ጠብቋል፣ ተስተካክሏል እያልን አይደለም፣ ነገር ግን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመንቀስ እያስተካከልን እንገኛለን፣ ተቋሙ ከሚያደርጋቸው ትግበራዎች የዋጋ ታሪፍ ማሻሻያ የሪፎርሙ አንድ አካል ነው፡፡ ይህ ባይሆን ደግሞ ችግሩ በነበረበት ሊቀጥል ይችላል ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ አምስት ዓመት የሚያገለግል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚቀርበው የተከበረ ሰነድ ተመጣጣኝ ክፍያ ነው የተተመነው፡፡

በመደበኛ ክፍያ አምስት ሺህ ብር እንዲከፈል የተወሰነው ከምናወጣው ወጪ አንጻር ፍትሐዊና ተመጣጣኝ ዋጋ ነው ብለን ነው የምናምነው ያሉት ኃላፊው፤ በየእያንዳንዱ ነገር ላይ መንግሥት ድጎማ ሊያደርግ አይችልም ብለዋል፡፡

ደንበኛው ለደላላና ለተለያዩ ወጪዎች ከሚዳረግ አሠራርን ማዘመን ተገቢ ነው ያሉት አቶ ሙሉጌታ፤ ደንበኞችን እቤት ድረስ ማገልገል ጀምረናል፣ ተግባሩንም ኅብረተሰቡ ሊያበረታታው ይገባል ብለዋል፡፡

ለበርካታ ጊዜ ሳይስተናገዱ የቆዩ ደንበኞችን እሁድን ጨምረን እያገለገልን፣ ውዝፎችንም እያጠራን እንገኛለን። በፊት እስከአምስት ቀናት ይፈጅ የነበረውን እስከ ምሽት ድረስም ቢሆን ቆይተን በማስተናገድ ጉዳያቸውን እንዲጨርሱ እያደረግን ነው፡፡

በመደበኛ አዲስ ፓስፖርት ከስድስት እስከ ሰባት ወራት፤ እድሳት ደግሞ ከ15 ቀናት እስከ አንድ ወር አካባቢ ይፈጃል፡፡ ይህንን ወደዜሮ ለማድረስ አቅደናልም ብለዋል፡፡ ትግበራው ሕገወጥ ደላሎችን ያስወጣል፣ የተገልጋዮችን ውጣ ውረድ ያስቀራል፣ በተቋሙ የሚስተዋሉ የአሠራር ችግሮችንም ይቀርፋል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም ምንም እንኳን አሁን ካለው የዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘ ችግሮች ቢኖሩም መቀየር አለበት። አሠራሩን አሻሽሎ፣ ሥርዓት ፈጥሮ ወደተግባር መግባቱ ግዴታ ነው፡፡ ደንቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፀደቀ ሦስት ወራት ሆኖታል፡፡ አሁን የተጀመረ አይደለም ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ ተመጣጣኝ እንዲሆን፣ ተደራሽ ለማድረግ፣ በርካታ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ለማስፋፊያ ሥራም የዋጋ ታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉ አስፈላጊ ነው ያሉት፡፡

አገልግሎቱ ባደረገው ማሻሻያ አዲስ ፓስፖርትም ሆነ የፓስፖርት እድሳት በመደበኛ ቀድሞ ሁለት ሺህ ብር ሲያስከፍል የነበረው በታሪፍ ዋጋ ማሻሻያው ወደ አምስት ሺህ ብር ማደጉ፤ አስቸኳይ በሁለት ቀናት 25 ሺህ ብር፤ በአምስት ቀናት ከሆነ ደግሞ 20 ሺህ ብር ከፍ ማለቱ እንዲሁም እድሳት እና እርማት ደግሞ መደበኛ 12 ሺህ 500 ብር፤ አስቸኳይ በሁለት ቀናት 32 ሺህ ብር እንደደረሰ ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You