”የውድደር ስርአት እየተቀየረ በመጣ ቁጥር ራሳችንን ከአለም ሁኔታ ጋር ማስኬድ አለብን ከአስር ሺ ያላነሰ ሯጭ ባለባት አገር ውስጥ አስር ሜዳሊያም ያንሳል” – አቶ መሠረት መንግስቱ የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ አትሌቲክስ አሠልጣኝ

ኢትዮጵያ የሜዳሊያ ረሃብና ጥሙ የማይበርድላቸው አገርን ከፊት ያስቀደሙ፤ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈው የአገርን እሴት ያስጠበቁ ብዙ አትሌቶች ነበሯት፡፡ ነገር ግን ይህ አልበገሬነትና አገራዊ ስሜት እየዋዠቀ በመምጣቱ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያስመዘግቧቸዉ ድሎች እና የሚያገኟቸዉ ሜዳሊያዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን የስፖርት ምሁራን ይናገራሉ፡፡

በአትሌቲክሱ እየተንሰራፋ የመጣው ተደጋጋሚ ውጤት የማጣት  ችግር ብቻ ሳይሆን እንደ ቀድሞ አትሌቶች ለረጅም ጊዜ ተፎካካሪነታቸውን በማስጠበቅ ስማቸውን መትከል የሚችሉ አትሌቶችን ማፍራት አልተቻለም፡፡  ታዋቂ የምንላቸው ነገር ግን ረጅም ጊዜ በውድድርና ድል ያልቆዩ አትሌቶች አሉ፡፡ አትሌት ኢማነ አመርጊያ፣ኢብራሄም ጄላን፣ ሁነኛው መስፍን፣ የኔው አላምረው እና የመሳሰሉት በተወሰኑ የውድድር መድረኮች ብቻ ታይተው ጠፍተዋል፡፡ በሚፈለገው ደረጃ መድረስ ስለምን አቃታቸው ብሎ ማሰቡ ትላንትን የታወስንበት አትሌቲክስ ነገንም እንድንከብርበት ያስችለናል፡፡

ረጅም ጊዜ በዓለም አቀፍ ውድድር መድረኮች  በአሸናፊነት  መቆየት የሚችሉ አትሌቶች ለምን ጠፉ? የአትሌቲክስ ስፖርቱ አሁን ወዴት እያመራ ነው? ውጤት መራቁስ ለምን? የሚሉና መሰል ጉዳዮችን ለመዳሰስ  የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል  የኢትዮኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ አትሌቲክስ አሠልጣኝ ከሆኑት አቶ መሠረት መንግስቱ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡

አደስ ዘመን የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ባህል ምን ይመስላል?

አቶ መሠረት፦  እንደሚታወቀው ረጅም ርቀት ሩጫ ላይ በተለይም ሲጀመር አካባቢ በማራቶን በኋላም በሂደት በአምስት ሺና 10ሺ ሜትር ላይ፤ እየገፋ ሄዶ በእነ ቀነኒሳ በቀለ ዘመን ደግሞ አገር አቋራጭ ላይ ያተኮረ ልምድ ነበር፡፡ እነዚህ በሙሉ የረጅም ርቀት ክፍልፋዮች ስለሆኑ በእነዚህ ዘርፎች በዓለም ውጤታማ የሆንበት አብዛኛው ህዝብም በዚህ የተነቃቃበት የእኛ ተብሎ እንደባህል መያዝ የታየበትም ነው፡፡

አብዛኛው የገጠር ልጅ በዚህ የሩጫ ሂደት ውስጥ ያለፈ ነው፡፡ የእለት ተእለት ህይወቱን ለመኖርና ኑሮውን ለመግፋ ሲል ትግል የበዛበትን ህይወት ሲመራ በጥንካሬውና በበርታቱ አዳብሮት ለረጅም ርቀት ውጤት መብቃት ችሏል፡፡ ስለዚህም አትሌቶች በዘመናዊ እሳቤ ተቃኝተው ያደጉ ሳይሆን በአብዛኛው አንዱ ከ አንዱ በሚያገኘው ለምድ ተወራራሽነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በእነ ኃይሌ ገብረሥላሴ ዘመን እነ አሰልጣኝ ወልደመስቀል ኮስትሬ የነበራቸው ሚና ትልቅ ነበር፡፡ አንዱ የአንዱን አደራ እየተቀበል የሚሄድበት መንፈስም ነበር፡፡ ሻምበል አበበ ቢቂላ ለሻምበል ማሞ ወልዴ እና ምሩጽ ይፍጠር አደራውን የሰጠበትና የእነርሱ መነሳሳት ደግሞ  በእነ ኃይሌ ልብና አእምሮ ውስጥ አርፎ እንደነ ደራረቱና ኃይሌ እንዲሁም ቀነኒሳ በቀለ እነ ጥሩነሽ ዲባባን የመሳሰሉ አትሌቶች  በእነርሱ እግር የተተካበት ሂደት ነው፡፡ ይህም እርስ በእርስ አንዱ ለአንዱ አርአያ ሆነው እንዲቀጥሉ አስችሏል፡፡

አዲስ ዘመን፦ በአትሌቲክሱ ረጅም ዓመታትን በአሸናፊነት መቆየት ማለት ምን ማለት ነው?

አቶ መሠረት፦ በሩጫው ዓለም በአሸናፊነት ረጅም አመት በውድድር መቆየት ማለት ለሶስት አሎምፒክ ሳይንገዳገዱ መሳተፍ ማለት ነው፡፡ ይህም አንድ ኦሎምፒክ የሚዘጋጀው በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ስለሆነ ቢያንስ ይህ ተባዝቶ እስከ 12ዓመት በውጤት መቆየት መቻል ነው፡፡ እነ ኃይሌ ገብረ ስላሴና ደራርቱ ቱሉ ሲታዩ በእንደዚህ አይነት ተግባር ለ20ዓመት ገደማ በውድድር ላይ ቆይተዋል፡፡ ይህ ቆይታ በውጤት የታጀበም ነበር፡፡ ይህ አይነት አካሄድ በአሸናፊነት ረጅም አመት በውድድር መቆየትን የሚያሳይ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ ለረጅም አመት በውጤት ታጅቦ በውድድር መቆየት ምን ጠቅም ያስገኛል?

አቶ መሠረት፦ አትሌቱ ከምንም በላይ ጤናማ ሆኖ፤ በልጅነቱ ጓጉቶና ህልሙ አድርጎ የጀመረውን ሩጫ ትልቅ ማማ ላይ እንዲደርስ ያስችለዋል፡፡ የሚፈልገውንም ስኬት ያገኛል፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረስም ዝናን ያተርፋል፡፡ ከዚህ በዘለለ የሚፈለገውን የገንዘብና ቁሳቁስ ሽልማት በማግኘት ራሱን በማሳደግ የኑሮ ለውጥ ያደርጋል፡፡ የውድድር መድረክ ባለበት ቦታ ሁሉ አገሩን በተደጋጋሚ በማስጠራት የአገር ክብርን ያስጠብቃል፡፡ ይህ በራስ የመተማመን የረጅም ጊዜ አሸናፊነት አገር በዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ያስገኛል፡፡ ለተተኪ ትውልድ ተምሳሌት የመሆን እድሉም ሰፊ ስለሚሆን ታዳጊ አትሌቶች እንዲነቃቁና ዝንባሌአቸው ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡ ሂደቱም የአትሌቲክስ እሴት እየሆነ ይቀጥላል፡፡ አገሪቱ ላይ ላሉ ዜጎችም የኩራት ምንጭ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ስትጠራ በሩጫው ዓለም በተደጋጋሚ ክብረወሰኖችን የሰበሩ አትሌቶች አብረው ግንባር ቀደም ሆነው ይነሳሉ፡፡ እነዚህ አትሌቶች በአንድ ውድድር ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ አሸናፊ በመሆናቸውና የአገራቸውን ባንዲራ በዓለም አደባባይ እንዲውለበለብ በማድረጋቸው ነው፡፡ በዚህ የስፖርት ዘርፍ ከየትኛውም ዓለም አገራት በተሸለ የክብር እንግድነትን አገኝተንበታል፡፡ ይህንን ያመጡት እንደነ ኃይሌ ገብረሥላሴ ያሉ በዝናቸው ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ አትሌቶች ናቸው፡፡ አትሌቶቻችን ተወዳዳሪ በሆኑባቸው መድረኮች ማሸነፍን እንጂ መሸናፍን የማያውቁና ለየትኛውም ተወዳዳሪ ድልን አሳልፈው የማይሰጡ በመሆናቸው ከሌላ ፕላኔት የመጡ እስኪመስላቸው ድረስ በመገናኛ ብዙኃን ሳይቀር ተወርቷል፡፡ ይህም አገሪቷ ስትተወቅበት የነበረውን የድህነትና የረሀብ ተምሳሌት ያስቀረ ነው፡፡

በተለይ ነጮች ለጥቁሮች ከነበራቸው የጥላቻ ስርአት ውስጥ ኢትዮጵያ በቅኝ አልተገዛችም በሚል ክፋቱ ልባቸው ውስጥ ሰርጾ ስለነበር፤ አለመሸነፍን በሩጫ ጭምር በመሳየት መጥፎ አመለካከቶች እንዲለወጡ ሆነዋል፡፡ የአገርን ገጽታ ከመለወጥና ከማስተዋወቅ አንጻር የአትሌቶቹ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ የሌሎች አገር አትሌቶች ወደ ውድድር የሚገቡት የጎደላቸውን መሰረታዊ ፍላጎት መሙላት ላይ ያተኮረ ሂደት ነው ያለቸው፡፡ ጀግና ተብለው የሚወሱትና በተደጋጋሚ የዓለም ቋንቋ ሆነው የቆዩት አትሌቶቻችን ግን አንዱ የአንዱን ክብረወሰን በመስበር አገርን የማስጠራት ተልእኮአቸውን ለመወጣት እንጂ ወደ ኪሳቸው የሚገባውን ብር አስቀድመው አይደለም፡፡ ይህ አርአያነትም ሁሌም የሚታወስ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፦ በዚህ ዘመን ረጅም ጊዜ በአሸናፊነት የመቆየቱ ባህል እንዲቀር ውጫዊ ተጽእኖው ምንድነው?

አቶ መሠረት፦ ከባዱ ጥያቄ ይህ ነው፡፡ ለአገሪቷ፣ ለባለሙያውና ለአመራሩ ፈታኙና ሳናውቀው ያለፈን ጉዳይ ነው፡፡ ትላንትና ያሳከነውን ስኬት እናውቀዋለን  ብሎ በድፍረት መናገር አይቻልም፡፡ ተከፍሎ የመጣው ትልቅ ዋጋ በተወሰነች ማስታወሻ እንኳን ስላልሰፈረችና ማስረጃ የሚሆን ነገር ስለሌለ የቀደሙ ልምዶቻችንን ማወቅ ተስኖናል፡፡ ፈረንሳይ አገር እ.ኤ.አ በ2003ዓ.ም የዓለም ‹‹ሻምፒዮን ሺፕ›› ሲካሄድ በ10ሺ ሜትር ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት አስገራሚ ድል ማስመዝገብ ችለን ነበር፡፡ ይህንን ውጤት ያመጣው ቡድን ተሞክሮው አልተጻፈም፡፡ ውጤቱ የመጣበት ባህል የኛው ሆኖ ሳለ በወቅቱ ያሉት አመራሮች ቀጣይ ለመጡት አመራሮች አላስተላለፉትም፡፡ ይልቁንም እኛ ያለፍንበትን የአሸናፊነት ልምድና ባህል ወደ ጎን በመተው የሌሎችን አገራት አሰራር ምን እንደሚመስል ለማየት ሙከራ አደረግን፡፡ ለዚህም ነው ያንን ውጤት መድገም ያቃተን፡፡ አሠልጣኝ፣ ባለሙያውና  አመራሩ እርስ በእርሱ በሚያደርጉት ሽኩቻ ምክንያት ሰነድና ታሪክ ሳይቀመጥ አለፈ፡፡ ይህ በመሆኑ የምንፈልገውን ነገር እጃችን ውስጥ ሳናስቀምጥ ቀረን፡፡

ከዚህ ሂደት በኋላ ዓለም መልኩን ቀየረ፡፡ በሩጫው በጣም የሚያጓጓው የሩጫው አጨራረስ ሆኖ ሳለ ሰዎች ለምን 25ዙር ሙሉ ተቀምጠው ይመለከታሉ? የሚል ጥያቄ ነጮቹ ያነሳሉ፡፡ ምክንያቱም ክብር የሚያሰጡ ትልልቅ ውድድሮችን የሚያዘጋጁ፣ ሽልማትን የሚሰጡ እነርሱ ናቸው፡፡ በመሠረቱ ይህ አካሄድ በፖለቲካዊም ይሁን ኢኮኖሚያዊ አንድምታው አቅማቸው ደካማ በሆኑ አገራት ላይ አሉታዊ  ተጽእኖ የማሳደር  ሚና አለው፡፡ ራሳችን ውድድር አዘጋጅተን እነርሱን የመጋበዝ አቅም የለንም፡፡ በመሆኑም ፈላጭ ቆራጭ የመሆን እድል አላቸው፡፡  እኛ ተወዳዳሪ ብቻ ስለሆንን  መሪነቱን በእነርሱ  ሞተርነት ነው የሚዘውሩት፡፡ በዚህ ሂደት ነው ረጅም ሰአት ሩጫን ማየት አሰልቺ ነው በሚል ሀሳብ ሩጫውን ቢዝነስ ተኮር በማድረግ ውድድሮችን በስፖንሰር መሸጥ ጀመሩ፡፡ ውድድሮችን ሲሸጡ ገዢዎቹ ወደ አትራፊነት ስርአት ውስጥ መግባት ስላለባቸው እንደሚያዋጣቸው አድርገው ነው የገዙት፡፡ ስፖንሰር ያላቸው ውድድሮች ደግሞ ቶሎ የሚያልቁና ጊዜ የማይፈጁ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሀሳባቸው የውድድር ባህሉ ተለውጦ 10ሺ እና አምስት ሺ ሜትርን በማቀጨጭ ወደ አጭር ርቀት ውድድር የማዘንበል አዝማሚያ ይዘው ብቅ ያሉት፡፡ በፊት ያልነበሩ አዳዲስ የሩጫ ርቀቶችም ተፈጥረርው የምናያቸው ለዚሁ ነው፡፡ የውድድር መልኩን በመቀየር እንታወቅበት በነበረው የመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫ ላይ እንድንዘናጋ ስላደረጉ ለረጅም ጊዜ በአሸናፊነት ውድድር ላይ የሚቆይ አትሌት ማፍራት አልቻልንም፡፡

በሌላ በኩል ለረጅም ርቀት የሩጫ ውድድሮች ተብለው የሚዘጋጁ ሽልማቶችን በአብዛኛው የሚወስዱት በኢኮኖሚ ደካማ የሆኑ  አገሮች በመሆናቸው ገንዘቡና ዝናው እጃቸው ላይ እንዲቀር ይፈልጋሉ፡፡ ለአብነትም የአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ታሪክ በፊት የነጮች ነበር፤ በሂደት ግን ጥቁር የበላይነትን ወሰደ፡፡ ነጮቹም ወደ ሞተርና የመኪና ውድድር አዘነበሉ፡፡ ምናልባት ጥቁሮቹ ወደ ሞተርና መኪና ውድድር ቢመጡ ደግሞ ነጮቹ የአውሮፕላን ውድድር ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡ ነጭ ከጥቁር ጋር ተወዳድሮ መሸነፍን ስማይፈልግ ወይ ይሸሻል አሊያም አዲስ ስትራቴጂ ይነድፋል፡፡ በተለይ በረጅም ርቀት ሩጫ ቀድሞ ምስራቅ ጀርመን፣ እነሃንጋሪና ቡልጋሪያ አካባቢ የነበሩት አሸናፊ ነበሩ ቀጥሎ ምስራቅ አፍሪካውያን ሲቀበሏቸው መሸነፍን ስለማይፈልጉ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኘውን ክብርና ሽልማት ለማስቀረት ወሳኝ ውድድሮችን በመሰረዝ የሩጫውን ባህል ማስቀየሩን ተያያዙት፡፡ ከውጭ የሚመጣብንን ጫና ያለማሰብና ያለ መተንበይ ችግር ክፍተቱን ፈጥሮታል ማለት ይቻላል፡፡

በአትሌቶች በኩልም ቢሆን፤ የዚህ ዘመን ወጣት አትሌቶች እንደ ፊተኞቹ ጤንነታቸውን ጠብቀው ለአገር ክብርና ዝና እሮጣለሁ የሚል ራእይና አስተሳሰብ የላቸውም፡፡ ይልቁንም በትንሹ የሚረካ፣ በአቋራጭ መንገድ የሚሄድ፣ ብዙ ድካም የማይፈልግ፣ ቢቻለው አጭበርብሮ በዶፒንግ ማሸነፍ የሚፈልግ አትሌት እያፈራን መሆኑ ክፍተቱን የፈጠረው ሌላ ምከንያት ሆኗል፡፡

አዲስ ዘመን ትላንት የነበረው አካሄድ ለመሰበሩ ውስጣዊ ሂደቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ምንድናቸው?

አቶ መሠረት፦ አመራሮቹ እየሄዱበት ያለው አሰራር ትክክል አይደለም፡፡ እውቅ አትሌቶችን አርአያ አድርገን አዲስ ትውልድ ለመቅረጽ አለተቻለም፡፡ መመሪያዎች ጥብቅ አይደሉም፡፡ የአትሌቶቹን መነሳሳትና ህልማቸውን ውስጣቸው መነቃቃት ባለበት ደረጃ የተቀረጹ ባለመሆኑ በትንሽ ጥቅም እንዲገደቡ ሆነዋል፡፡ ‹‹ባቄላ የዘራ ገበሬ እሸት ማብላት የሚችለው እሸቱ በሚደርስበት ትክክለኛ ጊዜው ላይ ነው፡፡ ቀድሞ ከቀጠፈው ቀንበጥ ነው የሚሆነው፤ የእሸቱን ዘመን ቢያሳልፈውም ይደርቅበትና እሸት መሆኑ ይቀራል፡፡ በአትሌቲክሱም እየሆነ ያለው የእሸትነቱ ደረጃ ላይ አለመድረስ ነው፡፡ አትሌቱ ሳይለፋና ሳይደክም ቶሎ ማናጀር በመያዝ አነስ ያለች ውድድር ይፈለግለታል፡፡ ከዚያም ባገኛት ትንሽ ጥቅም ከውድድሩ ይሰናበታል፡፡››

የአትሌት ማነጀሮች የሚባሉት በሚያሳዝን ሁኔታ ጥቁሮችን በተለይም የኢትዮጵያና የኬኒያን ሯጮች የማጥፋት ስራ ነው እየሰሩ ያሉት፡፡ የትራኩን ውድድር የማጥፋት ስራ ሲሰሩ ልጆቹን ወደ ማራቶንና የጎዳና ሩጫ ነው የሚወስዷቸው፡፡ የማራቶንና የጎዳና ሩጫው በፊት የምናውቀው በመኪና መንገድ ላይ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በአብዛኛው ዳገትና ቁልቁለት እንዲሁም ኮብል ስቶን የሚበዛበት የአየር ንብረቱ ተስማሚ ያልሆነበት ፈተኝ በመሆኑ የሰው ልጅ አካል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ የሚገኘውን ትንሽ ጥቅም በማሰብ ያለ ድግግሞሽ ከውድድር እንዲሰናበቱ ሆነዋል፡፡

ማናጀሮቹ ለአትሌቶቹ አስበው ሳይሆን የጥቁሮች የበላይነት እየደበዘዘ እንዲሄድ ነው አመቺ ያልሆኑና የጤና እክል ሊያጋጥም በሚችሉ ውድድሮች ላይ የሚያሳትፏቸው፡፡ አትሌቶቹ የሚያውቁት በሚመሯቸው አካላት ብር ሊያስገኝ በሚችል ውድድር ላይ መሳተፍ እንጂ ምን አይነት ጉዳቶች አሉት የሚለውን ግንዛቤ አልጨበጡም፡፡  በውጭው ተጽእኖና በአገር ውስጥ አስተዳደር ክፍተት ምክንያት ረጅም ዓመት በውድድር ላይ መቆየት የሚችል  አትሌት ጤንነቱን እያጣ ለትንሽ ገንዘብ ራሱን መስዋእት እያደረገ ይገኛል፡፡ ስለዚህም የአትሌቲክሱ አመራር ይህንን በማስተካከል ረገድ ክፍተት አለበት፡፡  አሁን እየተሸፈነ ያለው በሚገኙት አንድና ሁለት ሜዳሊያዎች ነው፡፡ ከአስር ሺ ያላነሰ ሯጭ ባለባት አገር ውስጥ አስር ሜዳሊያም ያንሳል፡፡  ችግር አለ ብሎ አለመግባባቱ ስላለ የአትሌቲክሱን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የከቱታል፡፡

አዲስ ዘመን፦ የችግሩ ግዝፈት በአትሌቲክሱ ስፖርት ላይ ምን አይነት ስጋቶችን ይፈጥራል?

አቶ መሠረት፦  ይህ ሂደት ባለበት የሚቀጥል ከሆነ ውጤት ማጣት ይመጣል፡፡ እኛ የለመድነው ውጤት በሜዳሊያ የሚለካ ነው፡፡ በነሀስና በብር ሜዳሊያ የማይረካ በወርቅ የሚረካና ፍጹም የበላይነትን የሚፈልግ ህዝብ ነው ያለን፡፡ እየሄድንበት ያለው ሂደት ግን በዚህ መንገድ አይደለም፡፡ አሰልጣኝና ዳኞችን የሚያበቁ ማሰልጠኛዎቻችን ስንቃኝ እንኳን አነስተኛ ነው፡፡ በዘርፉ የጥናት ማእከል የለንም፡፡ ስንቀባበል የመጣነውን የድል ችቦ በማስቀጠል በኩል ትልቅ ስጋት አለ፡፡ እያመማቻው የሚሮጡና ‹‹ይህ ውድድር የአገር ውድድር ባይሆን አቋርጬ እወጣ ነበር›› ብለው እንደሚናገሩት እንደነጥሩነሽ ዲባባ አይነት አትሌቶችን ማፍራት ይቸግራል፡፡ ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ሁሉም የእኔን አሸናፊነት ይጠብቃል ብሎ የሚያስብ ትውልድ ለመፍጠር ይከብዳል፡፡ አንቺ የጥቁሮች አገር የሆንሽ ኢትዮጵያ ትላንትና ድሃ ተብለሽ ተጽፈሻል፤ ዛሬ ደግሞ በጀግና እግሬ የጀግንነት ሥራ ሰርቼ ታሪክሽን እቀይራለሁ ብሎ የሚያስብ ሰው ማግኘት ይቸግራል፡፡ የማሸነፍ ስሜትንና አልሸነፍ ባይነትን አልበገሬነትን የሚያነግብ ትውልድ አይኖርም፡፡ ሁሌም በአቋራጭ መንገድ ትንሽ ነገር ለማግኘት የሚሮጥ ስፖርተኛ እየተፈጠረ ይሄዳል፡፡ መጨረሻ ላይ ስፖርቱ ውስጥ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄዎች ይመጣሉ፡፡ ሙያውንም ለቀን የምንወጣበት ስጋት ይመጣል ማለት ነው፡፡ እያንቀላፋን በሄድን ቁጥርም አትሌቲክስ የሚባል ስፖርት ከአገሪቷ ሊጠፋ ይችላል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ችግሮችን በመቋቋምና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ተከትሎ ለረጅም ጊዜ በውድድር ላይ በድል ለመቆየት ምን አይነት የመፍትሄ አቅጣጫ ሊወሰድ ይገባል?

አቶ መሠረት፦  በፌዴሬሽኑ በኩል ሥራ እየተሰራ አይደለም ባልልም የሚሰራበት መንገድ ግን ድብቅነት በዝቶበታል፡፡ የአትሌቲክሱ ስጋት ሊገባው ይገባል፡፡ ባለሙያዎችን አንድ ላይ የማወያየት፣ ችግር ፈቺ ጥናት የማስጠናትና ለባለሙያዎች የማቅረብ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ የችግሮችን መነሻ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የጥናቱን ውጤትም የሚመለከተው የመንግስትና የህዝብ  እንዲሁም ሙያው ላይ እስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ባለ ድርሻ አካል ቢያውቀውና ትችት ቢሰጥ ህመሙ ምን ላይ እንዳለ ማወቅ ይቻላል፡፡  ማንም ባለሙያ ለአገር አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል፡፡ ፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ክለቦችም በባለሙያዎች ሊመሩ ይገባል፡፡ ዘመናዊ የሆኑ ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማብዛት ያስፈልጋል፡፡ ለስፖርቱ ግብአት የሆኑ ቁሳቁሶች በትክክል ሊሟሉ ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እዳው ትልቅ ነው፡፡ በየክልሉና በየክለቡ ያሉትን አመራሮች ትክክለኛው ባለሙያ ትክክለኛው ቦታ ላይ ስለመቀመጡ መፈተሸ አለባቸው፡፡ አመጣጣችን ከፈረሱ ጋሪው እየሆነ ነው፡፡ ስለዚህ የተሰበረውን የአስተዳደር ክንፍ መልሶ መጠገን ይገባል፡፡ ይህ ካልተስተካከለና ገንዘብን እየበጀቱ መሄድ ቁልቁል መጓዝ ኢኮኖሚው ላይ ቤንዚል የማርከፍከፍ ያህል ነው፡፡

የውድደር ስርአት እየተቀየረ በመጣ ቁጥር ራሳችንን ከአለም ሁኔታ ጋር ማስኬድ አለብን፡፡ ሁሉም ነገር በድሮ በሬ አይተረሰም፡፡ ሌላው ወደ ትራክተር ሲገባ መወዳደር የሚቻለው በትራክተር በማረስ ነው፡፡ ቀድሞ በማሰብና ሌላ ስትራቴጂ በመውጣት የሩጫ ንግስናችንን ማስቀጠል ይገባል፡፡ ለረጅም ጊዜ በማቀድ ከዓለም ጋር ያለንን ክፍተት መድፈን ይገባል፡፡ ኬኒያዊያን ከእኛ ወደ ኋላ የቀረቡት ጊዜ ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ ጋር መጥተው ልምድ በመቅሰም የኛን የበላይነት እየወሰዱብን ነው፡፡ እኛ ወደ ኋላ እየተጎተትን ያለነው የራሳችንን ልምዶች ባለመጠቀማችን ነው፡፡ ትላንት ያለፍንበትን የስኬት መንገድ መመልከት አልቻልንም፡፡ የኋላውን ጥንካሬ ወስዶ ዘመናዊውን በመጨመር የተሻለ ለመስራት ያለው ተነሳሽነት አናሳ ነው፡፡ ዓለም እያዳከመው የሚገኘው የአምስት ሺህና 10ሺ ሜትር ውድድር ቢቀር እንኳን አጭር ርቀት ላይ ፊታችንን ማዞር አለብን፡፡ ይህንን ስርአት ማስቀጠል ቢቻል ስፖርቱ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የመቆየትና ህዝቡ ስፖርቱን በእኔነት ስሜት እንዲጠብቀው የማድረግ ስራ ይሰራል፡፡

አትሌቶቹም ቢሆኑ  ጭፍን የሆነውን ጉዞ ማስተካከል አለባቸው፡፡ መብታቸውን ብቻ ሳይሆን ግዴታቸውንም መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በአቋራጭ መንገድ ለመበልጸግ ብለው አካላቸው ላይ የሚደርሰውን የጤና ችግር ከመገንዘብ ባሻገር ሲሮጡ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከጀርባቸው እንዳለች ማወቅ አለባቸው፡፡ የአገርን ክብርና ስሜት በትክክል መረዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ውድ ጊዜዎትን ሰውተው ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ መሠረት፦ እኔም ከልብ አመሠግናለሁ፡፡

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 5  /  2010 ዓ.ም

Recommended For You