አሁን ባለንበት ዘመን ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ እንደምግብ፣ መጠለያና ልብስ ሁሉ መሠረታዊ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። ከቴክኖሎጂው ውጪ መሆን የማይታሰብበትና የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።
ያደጉ ሀገራት በዲጂታል ቴክኖሎጂው ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራትም የዚህን ቴክኖሎጂ ፋይዳ በሚገባ በመገንዘብ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነትን ለማስፋትና በቴክኖሎጂው ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ። ለእዚህም በዘርፉ የሰለጠነና ብቁ የሰው ኃይል እንዲኖራቸው የማድረጉን ስራ ቅድሚያ ሰጥተውታል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን አዘጋጅታ በመተግበር ላይ በምትገኘው ኢትዮጵያም ዲጂታል ምህዳሩን በማስፋፋት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ለማደረግ ዘርፉ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። ይህን ተከትሎ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባሮች መካከል ክፍያዎች፣ ግብይቶች እንዲሁም ጉዳዩ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲፈጸም እየተደረገ ያለበትን ሁኔታ ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፤ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማዘዋወር እየተቻለ ነው፤ እንግልትና ወጪን በመቀነስ ጊዜ መቆጠበ ተችሏል። አገልግሎቶችን ማቀላጠፍ፣ ማዘመን፣ ወዘተ የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን የማልማቱ ስራም ተስፋፍቷል።
በዲጂታል ቴክኖሎጂው በተለይ በመተግበሪያ ልማቱና በመሳሰሉት የበለጠ ልቆ ለመገኘት ዜጎችን በተለይ ወጣቶችን በኮዲንግ ላይ ማሰልጠን ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።
ኮዲንግ ሰዎች ከሚጠቀሙበት ስልክም ሆነ ኮምፒውተር ጋር ለመግባባት የሚያግዛቸው የኮምፒውተር ቋንቋ ስለመሆኑ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅትም የኮምፒውተር ቋንቋ ፋይዳው ብዙ እንደሆነ ሆኗል። በተለይ ወጣቶች በዚህ ቴክኖሎጂ ልቀው እንዲገኙ ለማድረግ ኮዲንግ ወሳኝ መሆኑ ነው።
በኢትዮጵያም ወጣቶችን በዚሁ ቴክኖሎጂ ለማሰልጠን የሚያስችል ምህዳር ተፈጥሯል። በቅርቡም ከዩናይትድ አረብ ኤሜሪት ጋር ወጣቶችን በኮዲንግ ለማሰልጠን የሚያስችል ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል። በዚህ ስልጠና አምስት ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን ‹የኢትዮጵያ ኮደርስ ኢንሼቲቭ› ስልጠና በቅርቡ በይፋ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን ኮደሮች ፈጠረች ማለት በሀገር ውስጥና በውጭ በቀላሉ ሥራ ሊያገኙ የሚችሉ ወይም ሥራ ሊፈጥሩ የሚችሉ አልያም ኩባንያ ሊፈጥሩ የሚችሉ ዜጎችን ፈጠረች ማለት ነው። ኮዲንግ ነገ ልክ እንደ ጎማ መቀየር ተራ ልምምድ ይሆናል። ያኔ ልጆቻችን ግራ እንዳይገባቸው ከወዲሁ መልካም ዘር ሊዘራባቸው ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል። ወጣቶች የተመሰከረላቸው/ ሰርቲፋይድ/፤ የሚፈጥሩ፣ የሚተጋገዙና ችግሮችን ለመፍታት የሚጥሩ፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የጀገኑ እንዲሆኑም አሳስበዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በበኩላቸው አምስት ሚሊዮን ወጣቶች በኦንላይን እንደሚሰለጥኑ ጠቅሰው፤ ስልጠናው ከሚፈጥረው መልካም እድል ባለፈ የመሰረተ ልማት ውስንነት እና የዲጂታል መሳሪያዎች ተደራሽነት ስለመኖሩ አመላክተዋል። ወጣቶች ለሀገራቸው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አንቀሳቃሽ ኃይል መሆናቸውን ተገንዘበው ለኢንሼቲቩ ለስኬታማነት መረባረብ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
አቶ ፊሊክስ ኢቴሳ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ባለሙያ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ኮዲንግ /ፕሮግራሚንግ/ስንል የሰው ልጅ ከማሽን ጋር የሚግባባበት ሥርዓት ነው። ይህም ኮምፒውተር እንዲሰራ የሚፈለገው ሥራ የሚታዘዝበት ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት /ሲስተም/ ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ መካከል የመጀመሪያው የሰው ልጆችን ሥራ ማቀላጠፍ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሰዎች ካሉበት ሆነው እርስ በእርስ እንዲገናኙ እንዲግባቡ ማድረግ ነው።
በኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን ወጣቶች በኮዲንግ እንዲሰለጥኑ ማድረግ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታው አለው ሲሉም አስታውቀዋል። ምክንያቱም ዓለም ወደ ግሎባላይዜሽን እየገባች ባለችበት በዚህ ዘመን እኛ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ርቀን መኖር አንችልም። ዲጂታል ቴክኖሎጂ ያስፈልገናል ሲሉም ጠቅሰው፤ በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ላይ ያለ ሰው ኮምፒውተር መጠቀም አለበት ብለዋል። በማሽን ወይም በኮምፒውተር በመታገዝ ብዙ ሥራዎች መስራት፣ ጊዜ፣ ገንዘብ እና ወጪን መቆጠብ የሚያስችል ቀላል የመግባቢያ ዘዴ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በኮዲንግ መስልጠን ለኢትዮጵያ በተለይም ለወጣቶች የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ ስለመሆኑ ያስረዱት አቶ ፊሊክስ፤ ለአብነት አንድ ታካሚን ለመመርመር አንድ ሰዓት የሚፈጅ ከሆነ፤ አንድ ቴክኖሎጂ ስንጠቀም ግን በአንድ ሰዓት ውስጥ አንድ ሺ ታካሚዎችን መርምሮ ወዲያውኑ ውጤቱን በማውጣት የሰውን ሕይወት ማዳን ይቻላል። በተለመደው መልኩ/በማንዋል/ ሲሰራ ደግሞ አንድ ሰው ለማከም አሥር ሰው የሚታይበትን ሰዓት ሊወሰድ ይችላል።በዚህም ሰዎች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በኦንላይን ውጤታቸውን ማየት ይችላሉ። ከዚያም በላይ የሆኑ ብዙ ሥራዎች ሊሰሩበትና ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ ስልጠና ለኢትዮጵያውያን መሰጠቱ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ስልጠናውን የሚሰጠው ድርጅትም ፕሮፌሽናል የሆነ ትልቅ ድርጅት ነው። ስልጠናውን መውሰድ ጥሩ እውቀት እንዲገኝ ያስችላል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያውያንም ጥሩ አጋጣሚ ነው። ሊሰጡ የታሰቡ ኮርሶችም ቢሆኑ በጣም ውድ የሆኑና በግል ለመማር ቢፈለግ በነጻ የማይገኙ ናቸው። ‹‹እነዚህን ኮርሶች መውሰዳችን ለኛ በጣም ትልቅ እድል ነው ብዬ እገምታለሁ›› ሲሉም አብራርተዋል።
ሌላው ደግሞ ቴክኖሎጂ መጠቀም ብዙ ችግሮች ለመፍታት ይጠቅመናል። ቴክኖሎጂ አስፈላጊ ብቻ አይደለም። ልክ ለሰው ልጅ እንደሚያስፈልጉ እንደ ምግብ፣ መጠለያና ልብስ ያሉ መሠረታዊ ነገሮች ቴክኖሎጂ አንዱ መሠረታዊ ነገር ነው። ምክንያቱ ከቴክኖሎጂ ርቆ መኖር ሆኖ ከቴክኖሎጂ ውጭ መሆን የማይቻልበት ጊዜ እየደረስን ነው ብለዋል ።
ስልጠናው አምስት ሚሊዮን ወጣቶች ሊወስዱት የሚገባ መልካም እድል ነው። አንድ ሀገር ላይ አንድ ሰው የመፍጠር ችሎታ ካለውና አዲስ ነገር መፍጠር ከጀመረ ኩባንያ ማቋቋም፣ በገቢና ወጪ ኢምፓርት ኤክስፖርት/ ንግድ ውስጥም መግባት ይችላል።
በኮዲንግ ሰልጥኖ መገኘት ወደውጭ ኤክስፖርት ከሚደረጉ ሀብቶች በበለጠ የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደ ውጭ መላክ ያስችላል። የሰለጠነ የሰው ኃይል ሲላክ አዲስ ቴክኖሎጂ፣ አዲስ እውቀትና ፈጠራም ለሀገሪቱ ይዞ ይመጣል። በተለይ በቴክኖሎጂ የታገዘ አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለት እና ከዚያ በላይ እውቀት ይዞ መገኘት ከዓለም እኩል እንዲሆኑ ይረዳል ሲሉም ጠቅሰው፤ የተጀመረው ኢንሼቲቭ ጥሩ ጅምር መሆኑንና እድሉን መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አቶ ፊሊክስ እንዳስታወቁት፤ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ብዙ ነገሮች ያስፈልጋሉ። አንድ ሰው ለመማር ኮምፒውተርና መሰል የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ያስፈልጉታል። እነዚህ መሳሪያዎች በቀላሉ የሚገኙባቸው ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሁነኛ የዲጂታል ፖሊሲ መኖር አለበት።
‹‹እንደዚህ አይነት እድሎች በመንግሥት በኩል ሲመጡ ወርቃማ እድል እንደሆኑ ይቆጠራሉ›› ያሉት አቶ ፊሊክስ፤ ህብረተሰቡ እድሎቹን በመጠቀም ቴክኖሎጂውን ለጥሩ ተግባር በማዋል በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት እና በሁሉም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ ያሉ ችግሮች መፍታት ይጠበቅብናል ሲሉ ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ፊሊክስ ማብራሪያ፤ በቀጣይም ኮዲንግ ብቻ ሳይሆን ከኮዲንግ በተጨማሪ ሳይንሱንም መማርና ማወቅ ያስፈልጋል። እነዚህን ነገሮች ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይገባል። ግንዛቤ መፍጠር ላይም መስራትን ይጠይቃል። ኀብረተሰቡ በየጊዜው የሚመጡ እድሎች ጥቅም ምንድነው የሚለውን ማወቅ አለበት፤ እድሉ ሊያመልጠው አይገባም። ምክንያቱም ለዚህ ኮርስ የወጣበት ፋይናንስም ቀላል የሚባል አይደለም። በተለይ ወጣቶች እድሉ ሊያልፋቸው አይገባም እድሉን ተጠቅመው ተምረው የራሳቸውን ስራ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ የለም ከተባለ እንኳን በሌሎች ሀገራት ሥራ የማግኘት እድል ይፈጥረላቸዋል። ኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ሕንድ በመሄድ መስራት ይችላሉ። በኢትዮጵያም ሥራ ፈጥረው መስራት ይቻላሉ›› ይላሉ።
በመንግሥት በኩል መሻሻል ያለባቸው ፖሊሲዎች በየጊዜው እንዲያሻሸሉ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመው፣ ገበያው ዲጂታል እንዲሆን በማድረግ የሥራ እድሎችን ማስፋት እንደሚጠበቅ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ በቀላሉ የማይገኙ ሀብቶች እንዲገኙ ያደርጋል። በተለይ በትምህርት በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ የማናገኛቸውን የትምህርት አይነቶች በኦንላይን ማግኘት ከማስቻልም ባለፈ የሥራ እድሎች በጣም እየሰፉ ነው። ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በመኖራቸውም ብዙ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል።
ቴክኖሎጂ ባህላዊና ማህበራዊ ተጽዕኖዎችም አሉት። ነገር ግን ቴክኖሎጂ ስናመጣና ተግባራዊ ስናደርግ ባህልና መሰል ነገሮችን ያገናዘበ መሆን አለበት። ምክንያቱም ቴክኖሎጂ ብቻ አምጥተን ተግባራዊ ማድረግ ሲያስፈልግ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር በማጣጣም ህብረተሰቡ ሊጠቀምበት በሚችል መልኩ ሊሰራበት ይገባል።
‹‹ምን ያህሉ ነው ስለቴክኖሎጂ ጥቅም የሚያውቀው፤ ምን ያህሉስ ኮምፒውተር አለው የሚሉትና የመሳሰሉትን ሳናጠና ሁሉን ነገሮች ኦንላይን ስናደርግ ከማንዋል አሰራር የበለጠ ዲጂታል ሲስተም ቀውስ ይፈጠራል›› ሲሉ ያስገነዘቡት አቶ ፊሊክስ፣ እነዚህና መሰል ሁኔታዎችን አሁን ከወጡ ፕሮግራሞች ጋር አስተሳስሮ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። ይህ ደግሞ ከመንግሥት ብቻ የሚጠበቅ ኃላፊነት እንዳልሆነም ተናግረው፤ ማህበረሰቡ ሊሳተፍበት እንደሚገባ አስታውቀዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ የኔትወርክ ማሳለጫ ፕሮጀክት መሪ አቶ ዳንኤል አድነው በበኩላቸው፤ አሁን እንደ ሀገር ሁሉንም ነገር ከውጭ እያወረድን ነው የምንጠቀመው ይላሉ። ዲጂታላይዜሽን በራሱ ኮዲንግን / ፕሮግራሚንግ/ ይጠይቃል ሲሉም ጠቅሰው፤ ኮዲንግ ለማድረግ ደግሞ የሰለጠነ የሰው ኃይል የምናስመጣው ከውጭ ነው ይላሉ። በኮዲንግ የተሰራውን ሥራ በራሱ ለማስተካከል የኮዲንግ እውቀት እንደሚያስፈልግ ተናግረው፤ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ኮድ የሚያደርግ የሰው ኃይል/ወጣቶች/ እንዲኖር ማድረግ የግድ መሆኑን አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ መረጃዎችን ኮድ በማድረግ አገልግሎቱ አንላይን እንዲሆን ሲፈለግ ቀድሞ ከነበረው የተለመደ አሠራር አውቶሚት የሚደረገው በኮዲንግ ነው። በዚህ ብዙ የሰለጠነ የሰው ኃይል ሲኖር ብዙ ሰዎች የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸውና ሥራውም በፍጥነትና በቅልጥፍና እንዲሰራ ያግዛል። ብዙ ኮድ የሚያደርጉ ወጣቶች ሲኖሩ ሁሉም ዘርፍ ላይ ያለውን መረጃ ከማንዋል አሠራር ዲጂታላይዝ በማድረግ አገልግሎቱን በኦንላይን በፍጥነት ማግኘት ያስችላል። የሥራ ፍጥነት እንዲኖር ማድረግ ብቻም ሳይሆን ኢኮኖሚ እንዲያድግም ያደርጋል።
በሁሉም ዘርፍ ኮዲንግን/ፕሮግራሚንግ/ ያላካተተ አውቶሜሽን የለም የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ ዲጂታይዝድ ማድረግ በሁሉም ዘርፍ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል። ለአብነት በግብርና ዘርፍ የእርጥበት መጠንን ለመለካት ቢፈለግ መሳሪያ ማስቀመጥ በተፈለገ ጊዜ መለካት ይቻላል። ያንን ለማወቅ ቦታው ድረስ መሄድ ሳያስፈልግ ኮድ ተደርጎ ከተሰራ ውጤቱን ባሉበት ቦታ ሆኖ ማግኘት ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ዳንኤል ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ኮደርስ ኢንሼቲቭ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተነደፈ ፕሮግራም ነው። በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኩል ይሄ ሥራ እንዲሰራ ምን ያስፈልጋል የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። ለምሳሌ አንድ ኮደር ለማሰልጠን የሚያስፈልጉ ነገሮች አሉ። ኮደሩ በሀገር ውስጥ ነው ወይስ ውጭ ሀገር ነው የሚሰለጥነው። በሀገር ውስጥ የሚሰለጥን ከሆነ የሚያሰለጥን የሰው ኃይል አለ ወይስ የለም የሚሉት በደንብ መታየት አለባቸው።
አምስት ሚሊዮን ኮደሮችን ለማስልጠን ከሚያስፈልጉት መካከል የፋይናንስ አቅምና መሳሪያዎች ይገኙበታል። መሳሪያዎች ስንል ኮምፒውተር፣ የተሰራው ኮዲንግ አርካይቨ የሚደረግበት የኦንላይንና የክላውድ አገልግሎቶች ሶፍት ዌርም እጅግ ያስፈልጋሉ።
እነዚህን በማሟላት ረገድ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኦፕሬቲንግ ሲስተም ሀገር ውስጥ እየስራ በመሆኑ ኦፕሬቲንግ ሲስተም የሚወጣው ወጪ ማስቀረት እንችላለን። ኮደሮቹ ኮድ የሚያደርጉባቸው የተለያዩ የፕሮግራሚንግ ቋንቋዎችን እና ክላውድ ሲስተምም ጨምሮ ብዙ የሚያስፈልጉ ነገሮች በሀገር ውስጥ ማቅረብ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን አቶ ዳንኤል አስታውቀዋል።
‹‹ይህን እድል ሳንጠቀምበት ቆይተናል። እንደ ህንድ፣ ኬንያ ያሉ ሀገራት ብዙ ተጠቅመውበታል፤ እኛም ብዙ ልንጠቀምበት የሚገባበት እድል ነው ›› ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ይህን እድል ወደ ተግባር ቀይርን ከተጠቀምንበት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ እድገት ያስገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም