አሁን ላይ በዓለም ላይ 132 ሀገሮች በጦርነት እና በግጭት ውስጥ መሆናቸውን ፤ በ2023 ብቻ 17 ነጥብ 5 ትርሊዮን ዶላር ለጦርነት መዋሉን መረጃዎች ያመላክታሉ። በራሺያ እና በዩክሬን፣ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል በየቀኑ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለጦርነት እየዋለ ነው።
በራሺያ እና በዩክሬን፣ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የሚደረገውን ጦርነት ጨምሮ በሌሎችም ሀገሮች ባለው ጦርነት ሳቢያ 13 በመቶ የዓለም አጠቃላይ ምርት ለጦርነት እየዋለ እና ሰላም በመጥፋቱ ምክንያት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እና ስደት ዓለምን እያስጨነቀ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
የዓለም አካል የሆነችው ኢትዮጵያም በሰላም እጦት የተነሳ የምትፈልገውን ልማትና መረጋጋት ማምጣት አልቻለችም። ለሁለት ዓመታት ያህል በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዳጣች በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። ከዚያ በኋላ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሱ ግጭቶች ሰላም ደፍርሷል፤ በርካቶች ተፈናቅለዋል፤ተሰደዋል፤ህይወታቸውን አጥተዋል።
እነዚህ የሰላም መደፍረሶች ደግሞ ሀገሪቱን ዋጋ አስከፍለዋታል፡፤ ሀገሪቱ የጀመረቻቸው አጓጊ ፕሮጀክቶች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተዳርሰው እርካታ እንዳይፈጥሩ እንቅፋት ሆኗል። በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ብትሆንም ሰላሟ የተሟላ ባለመሆኑ የቱሪስቶችና የውጭ ባለሀብቶች መናኸሪያ እንዳትሆን የራሱን ጥላ አጥሎባታል። በዚህ ሁሉ ግጭትና አለመረጋጋት ውስጥም ሆና ሀገሪቱ በአፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከል በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መረጃ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከል አምስተኛ ደረጃን ይዛለች። ይህንንም ደረጃ ልትቆናጠጥ የቻለችው 205 ነጥብ1 ቢሊዮን ዶላር የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ገቢ(GDP) በማስመዝገብ ሲሆን፤ ይህም ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ግስጋሴ ውስጥ እንድትገኝ አመላካች ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ ፣ከግብፅ፣ከአልጄሪያ እና ከናይጄሪያ ቀጥሎ በአምስተኛ ደረጃ ተጠቃሽ ነች። ኢኮኖሚዋም በቀጣይ የተሻለ እድገት ሊያስመዘግብ እንደሚችል ብዙ ተስፋ የተጣለበት ጭምር ነው። መንግሥትም የተመዘገበውን ውጤት የተሟላ እና ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየወሰደ ነው።
ከእነዚህ ውስጥ በአይነቱ የተለየ እና እምርታዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበትን አዲስ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥርዓት ተግባራዊ አድርጓል። የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል ሲሆን፤ ዋና ግቡ ቀጣይነት ያለው፣ መሠረተ ሰፊና ሁሉን አሳታፊ የኢኮኖሚ ዕድገት መኖሩን ማረጋገጥ ነው።
የማይክሮ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ፤የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወስንበት የገበያ ሥርዓት የሚያሸጋግር ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሚና፣ ገበያውን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ እንዲሆን የሚያደርግ፤ የውጭ ምንዛሪን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታን ያስቀረ ነው።
ላኪዎችና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው ማስቀረት እንደሚችሉ የሚደነግግ ፤ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በእጅጉ የሚያሻሽል ፣ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለራሳቸው ያስቀሩት የነበረው 40 በመቶ ወደ 50 በመቶ ከፍ የሚያደርግ ነው። ይህም ላኪዎች የበለጠ ተበረታትተው እንዲሰሩ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እንዲያመጡ በር የሚከፍት ነው።
ከውጭ የሚላክ ሐዋላን፣ ደመወዝን፤ የኪራይ ገቢን እና ሌሎች ገቢዎችን በውጭ ምንዛሪ ለመክፈል የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ ሂሳቦችን መክፈት የሚያስችል፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ሂሳቦች ተጠቅመው የውጭ አገልግሎት ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ የሚፈቅድ ነው። ይህም በሀገሪቱ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እንቅስቃሴ እንዲኖር ከማስቻል ባለፈ እጥረቱንም እንደሚያቃልል ይታመናል።
የውጭ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ሰነድ መዋእለ ንዋይ ገበያ (Ethiopian Securities Exchange) እንዲሳተፉ የሚፈቅድ፤ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚሠሩ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን ሙሉ በሙሉ ለራሳቸው መያዝን ጨምሮ ልዩ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም መብት የሚሰጣቸው ነው።
በተመሳሳይም ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት የሚጓዙ ወይም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞችን ሊይዙ በሚገባ የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ተጥለው የነበሩ የተለያዩ ጥብቅ ደንቦች እንዲላሉ አድርጓል።እነዚህ እርምጃዎች የዶላር እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡና ገንዘባቸውን በተለያዩ ልማት ስራዎች እንዲያፈሱ ዕድል የሚሰጥ፤ ቀጣዩን የኢትዮጵያን የዕድገት ደረጃና ከቀረው የዓለም ሀገራት ጋር ያላትን እያደገ የመጣውን ትስስር ለማጠናከር የሚረዳ ነው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባችበት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥርዓት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያድግና የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲኖር ያስችላል።ለዚህ ግን ከሁሉም በላይ የሰላም ጉዳይ ወሳኝ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም ። የውጭ ባለሀብቶችም ሆኑ ቱሪስቶች ወደ ሀገር ውስጥ መጥተው ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላም ለነገ የሚባል የቤት ሥራ አይደለም።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ተነጻጻሪ ሆነ ሰላም ካላቸው ሀገራት አንዷ ብትሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሰላሟን የሚያደፈርሱ ክስተቶች እየተስተዋሉ ናቸው። በሀገሪቱ ፍላጎታቸውን በነፍጥ ማሳካት የሚፈልጉ ቡድኖች እየተበራከቱ መጥተዋል። ከውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚቀናቸውና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ የሚረብሹ፣ አብሮነቱን የሚያውኩ ፣የኢትዮጵያን መረጋጋትና ሉአላዊነት የሚገዳደሩ ቡድኖች እዚህም እዚያም አቆጥቁጠዋል።
እነዚህ ወገኖች በሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥም ልማት ተደናቅፏል፤ የሰዎች ወጥቶ መግባት ተስተጓጉሏል፤አለፍ ሲልም የሀገር ህልውናም አደጋ ላይ ወድቋል። ሀገር በሰላም ውላ እንድታድርና እድገትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ እነዚህን የሰላም ጸሮች በጋራ መመከት ያስፈልጋል።
መንግሥት በሀገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ የተጋረጡ በርካታ ችግሮችን በማስወገድ ብልፅግናን ለማምጣጥ በሁለንተናዊ መልኩ እየተንቀሳቀሰ ነው ።ለዘመናት የተከማቹ ኢኮኖሚ ስንክሳሮችን ለማስወገድም ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ገብታለች። ይህ አዲስ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተሟላ መልኩ ውጤት እንዲያመጣ ሰላም ያለውን የጎላ ድርሻ ሁሉም ዜጋ ሊያስተውለው ይገባል።
የሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት አለ። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከተካሄዱ ጦርነቶችና ግጭቶች ገና አላገገምንም ፤ሥራ አጥነት አሁንም አሳሳቢ ነው፤አሁንም ከድህነት ያልወጣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ አለ፤በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ድርቅ ደጋግሞ እያጠቃን ነው።
እነዚህን ችግሮች ለመሻገርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሰላም ወሳኝ ነው። ሰላም ለማምጣት ደግሞ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመሳሪያ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ቁጭ ብሎ የመነጋገር እና የመወያየት ባህል ማዳበር ይገባል። እንደ ሀገር እድገትና ብልጽግንና ማረጋገጥ የሚቻለውና የታለሙ ሀገራዊ ዕቅዶችንም በተሟላ መልኩ መተግበር የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው። ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። እንኳን እድገትና ብልጽግና ለማረጋጥ በቀላሉ የእለት እንጀራን ለማሟላት ሰላም ያስፈልጋል።
ዜጎች ለሰላም ትኩረት መስጠት አለባቸው። በተራዘመ የሰላም እጦት ሳቢያ ሀገሪቱ ከእድገት እና ልማት ወደ ኋላ ቀርታለች።ትናንት በእድገት ተመጣጣኝ የነበሩ ሀገራት ዛሬ በእድገትና በስልጣኔ ገስግሰዋል፤የሕዝባቸውን ህይወት አሻሽለዋል፤በዓለም ላይም ተደማጭ ሆነዋል።
ኢትዮጵያውያን ከንግግር እና ውይይት ይልቅ የሃሳብ ልዩነቶቻቸውን በጠመንጃ እና በኃይል ለመፍታት በመሞከራቸው እድገታቸው ቁልቁል ከመሆኑም በሻገር በዓለም ላይ ተደማጭነታቸው እያሽቆለቆለ መጥቷል። በዓለም ላይ በተረጂነት ከሚታወቁ ሀገራት ግንባር ቀደሙን ቦታ ለመያዝ በቅተዋል።
ይህ ሀገርን እና ሕዝብን የጎዳ አካሄድ አንድ ቦታ መቆም አለበት። ኢትዮጵያውያን ጦርነትና ግጭት በቃን ሊሉ ይገባል። ችግሮችን በአፈሙዝና ነፍጥ በማንሳት ለመፍታት መሞከር ዋጋ እንዳስከፈለን ሊረዱ ይገባል። በየስርቻው ነፍጥ እያነሱ እኔ አውቅልሃለሁ የሚሉ ቡድኖች ሊያወግዛቸው ይገባል።
ዛሬ ዘመኑ ተለውጧል። ዓለም በሳይንስና በቴክኖሎጂ በሚራቀቅበት ወቅት እኛ ዛሬም ከመንደር ሳንወጣ ነፍጥ አንግበን ጫካ ለጫካ መዞር ሊያሳፍረን ይገባል። በመረጥነው ግጭትና ጦርነት የዓለም ጭራ መሆናችን ሊያንገበግበን ይገባል። ክብር የሌለንና እርዳታ ጠባቂዎች መሆናችን ሊያሳፍረንና ሊያሸማቅቀን ይገባል።
ኢትዮጵያ ዛሬ ከዓለም ተርታ ለመሰለፍ በመንደርደር ላይ ትገኛለች። ዓለም ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ለመድረስ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት (በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ትኩረት ሰጥታለች። ቴክኖሎጂ ወሳኙ መንገድ መሆኑን በመረዳት ወጣቶቿን በስልጠና እና በፈጠራ በስፋት በመሳተፍ ላይ ትገኛለች።
አልፎ ተርፎም ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት እንዲጎለብት የውጭ ባለሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉ በሯን ክፍት አድርጋለች።በችርቻሮና በጅምላ ንግድ ሳይቀር የውጭ ባለሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉ አውጃለች። የውጭ ባንኮች እንዲገቡና እንዲሰሩም ጥሪ አድርጋለች።ዶላር በገበያ ዋጋ እንዲገዛና እንዲሸጥ በመወሰንም ገበያ መር ኢኮኖሚን አውጃ ሙሉ ለሙሉ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች።
እነዚህ ውሳኔዎቿ ደግሞ የውጭ ባለሀብቶች በስፋት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ሰፊ እድል ይሰጣሉ። በዚህም የሥራ እድል እንዲከፈትና ሥራ እጥነት እንዲቀንስ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። የሀገሪቱን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሀብቶች ለመጎብኘት የሚመኙ ብዙዎች ናቸው ።
ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ሰላም ሲኖር ነው። በተለይም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ ሙሉ ትግበራ የገባችበት የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው በርካታ ቱሪስቶችን እና የውጭ ባለሀብቶችን በእጅጉ የሚስብ ነው።ይህ እንዲሆን ደግሞ ሀገሪቱ በሰላም ውላ ልታድር ይገባል።ለዚህ ደግሞ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ትልቅ ነው።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም