አቶ ደስታ ዲንቃ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ
የደርግ መንግሥት ውድቀትን ተከትሎ በመጣው ለውጥ በኢትዮጵያ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት በቅተዋል። አብዛኞቹ ፓርቲዎች ግን ያላቸውን አቅምና በሕዝብ ዘንድ የነበራቸውን ቅቡልነት ይዘው ለመዝለቅ አልታደሉም። በራሳቸው ድክመትም ሆነ በውጭዊ ጫና ከፖለቲካው መድረክ የተሰናበቱትም በርካቶች ናቸው። ስም በመቀየር፤ ለሁለት በመከፈል እና ጥምረት መፍጠር አባላትና ደጋፊዎቻቸውን ግራ ሲያጋቡ የነበሩም በርካቶች ናቸው።
ይህም ሆኖ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚዲያም ሆነ የተለያዩ መድረኮችን ሲያገኙ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠባብ ነው በሚል ቅሬታ ከማቅረብ በዘለለ ያለውን አጋጣሚ ሲጠቀሙ አይታይም። ለምርጫ ሰሞን ከሚደረግ ጥድፊያ በዘለለም በንቃት ዓመት ከዓመት ሲሰሩም አይስተዋልም። አብዛኛዎቹ ድምጻቸውን የሚያሰሙት መንግሥትን በረባ ባረባው ለመቃወምና ስህተቶችን ፈልጎ በማውጣት ችግር መኖሩን ለመግለጽ ብቻ ነው። ዛሬም ድረስ ሀገሪቷ ካላት ብዝሀነት እና ካሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አኳያ አዳዲስ ሃሳቦችን፤ ከችግር መውጫ መንገዶችንና ሀገራዊ አጀንዳዎችን ይዘው የሕዝብን ቀልብ ገዝተው የሚንቀሳቀሱ አሉ ለማለት አያስደፍርም።
በቅርቡ የተከሰተው ለውጥም ቢሆን ብዙዎቹን ፖለቲከኞች ከእስር በማውጣት በተለያዩ ሀገራት የነበራቸውን እንቅስቃሴ ወደ ሀገር ቤት እንዲያመጡ ቢያደርግም በነበረው ሙቀት መቀጠል አልተቻለም የሚሉና ተያያዥ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ይሰማል።
እኛም ለዛሬው እትማችን ከላይ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች በማንሳት ያላቸውን አስተያየት እንዲያካፍሉን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ፀሐፊ አቶ ደስታ ዲንቃን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፤- የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሲመሰረት መዳረሻ አላማው ምን ነበር?
አቶ ደስታ፤– የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በ2011 ዓ.ም ሲመሰረት አላማው ያደረገው አዲስ መንግሥት መምጣቱን ተክትሎ በወቅቱ የነበረውን ተቃውሞ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመቀየርና መረጋጋት ለመፍጠር ነበር። ከዚያ በኋላም ግን የነበረውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፤ ገዢውን ፓርቲና መንግሥትን ጨምሮ የፖለቲካ ፍላጎትና አመለካከት አለን የሚሉ አካላት ለሕግ ተገዢ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።
በተጨማሪም ፓርቲዎች ሀገራዊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ተመሳሳይና ተቀራራቢ አቋም በመያዝ በኢኮኖሚ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች አብረው ለመሥራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ባጠቃላይም በመንግሥት በዜጎችና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረው ግንኙነት ሕገ መንግሥታዊ እንዲሆን ግቡን ያደረገ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም የፈረሙትን የቃል ኪዳን ሰነድ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። በተግባርም የጋራ ምክር ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ መድረክ እንዲወያዩና አላማን በኃይል ለማሳካት የሚደረግ እንቅስቃሴ እንዲቀንስ ለማድረግ የበቃም ነው። በጋራ ምክር ቤቱ ስር ያሉት ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰላምን መንገድ የመረጡ ናቸው። በመሆኑም ምክር ቤቱ ከተቋቋመ በኋላ እነዚህን ፓርቲዎች ተከትሎ የተፈጠሩ የሰላም መደፍረስ ችግሮች አለመከሰታቸውም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
አዲስ ዘመን ፤- የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ወቅታዊነት ይስተዋልበታል፤ መቃወም ላይ የሚያተኩሩ ናቸው ፤ የሕዝብ ቀልብ ይስብልናል የሚሉት አጋጣሚ ካልተፈጠረ ሲንቀሳቀሱ አይስተዋልም የሚሉ ትችቶች ይሰሙባቸዋል፤ ለእነዚህ ሃሳቦች ያለዎት ምላሽ ምንድን ነው?
አቶ ደስታ፤– በዚህ ሃሳብ አልስማማም፡፡ እንደ ጋራ ምክር ቤት እኛ ሁልጊዜም ሥራ ላይ ነን። በአቅም ውስንነት የኮሙዩኒኬሽን ሥራው ደካማ በመሆኑ ለሕዝብ አይደርስም እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ዓመቱን ሙሉ ሥራ ላይ ናቸው። አሁን እየተካሄደ ያለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ሊደረግ የቻለውም በእኛው አነሳሽነት ነው። በጋራ ምክር ቤቱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጥምረት ብቻ ሳይሆን የገዥው ፓርቲ አባላትም አሉ። ለምሳሌ የእኔ ምክትል በገዢው ፓርቲ ውስጥ የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍን የሚመሩ ናቸው።
ከዚህ ቀደምም በሚያዝያ ወር ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ውጤታማና ጥሩ የሚባል የተሳካ ውይይት አድርገናል። ይህንንም ተከትሎ የክልል ፓርቲዎች ከትግራይ ክልል ውጭ ከክልል መንግሥታት ጋር ውይይት ማካሄድ ችለዋል። በተጨማሪ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች በፖለቲካ ፓርቲዎቹና በከተማ አስተዳደሮቹ መካካል ተመሳሳይ ውይይት ተከናውኗል። የጋራ ምክር ቤቱ ያልተሳተፈበት በሲዳማ የተካሄደው ውይይት አሳታፊ ያልነበረ ሲሆን በእኛ እይታ አጥጋቢ ውጤት የተገኘበትም አልነበረም። በተጨማሪ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ አደም ፋራህ ጋር ውይይት ተካሂዷል። ከዚህ ሁሉ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝቡን ጥያቄዎች በመያዝ ሐምሌ አሥራ አምስት ቀን ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በመገናኘት ውይይት ያካሄድነው። ውይይቱም ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል። ስለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡበት ሁኔታ የለም፡፡
አዲስ ዘመን፤ – ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር እያካሄደች ነው፡፡ ሆኖም በውይይቱ ያልተሳተፉ የጋራ ምክር ቤቱ አባል የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ?
አቶ ደስታ፤- የጋራ ምክር ቤቱ አባላት የሆኑ በውይይቱ ያልተሳተፉት ፓርቲዎች አሉ። ምክንያታቸው ደግሞ አባሎቻችን ታስረውብናል፤ ቢሮዎች ተዘግተውብናል የፖለቲካ ምህዳሩ አልተስተካከለም፤ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መብታችን ተጠብቆልን መንቀሳቀስ አልቻልንም፤ በመንግሥት በኩል በውይይት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ርምጃ እየተወሰደ አይደለም የሚል ምክንያት ያላቸውና ያኮረፉ ናቸው። በዚህም ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ጋር ከምናደርጋቸው ውይይቶችም ራሳቸውን አግልለዋል።
ከዚህ ውስጥ አንዳንድ እኛም የምንቀበላቸው ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ሰባት የኦነግ አመራሮች ክስ ሳይመሰረትባቸው ለሁለት ዓመታት የታሰሩ አሉ። በዚህም ፓርቲው አንዳንድ ውሳኔዎች ለማስተላለፍ ከግማሽ በላይ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አመራሮች መገኘት ስላለባቸው መወሰን ሳይችሉ የቀሩበት ሁኔታ አሉ። ይህም ሆኖ እስካሁን ከቆየንበት የፖለቲካ ባሕል መውጣት እንዳለብን እናምናለን። አሁንም ድረስ ያለን የፖለቲካ አካሄድ የሚያሳየን የአመለካከት መለያየትን እና የፍላጎትን ልዩነትን በአግባቡ ማስተናገድ ሳንችል ቆይተናል። ይህ አካሄድም እንደ ሀገር በኢኮኖሚው በፖለቲካውና በማህበራዊ መስክ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። በመሆኑም ዛሬም ነገም አማራጭ ሊሆን የሚገባው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ብንሆን በሰላማዊ መንገድ እየተገናኙ መምከር ብቻ ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን፤- ከለውጡ በኋላ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ለማለት ያስደፍራል?
አቶ ደስታ፤- ችግር የለም ሁሉም ነገር ምቹ ነው የሚል ምልከታ የለንም። የጋራ ምክር ቤቱ ሲቋቋም ቃል ኪዳን የተግባባነው በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለመንቀሳቀስ ነው። ሁሉም ነገር የተስተካከለ ሊሆን እንደማይችል ግንዛቤው አለን። መሥራት ያለብን በዛ ችግርና ጫና ውስጥም ሆነን ቢሆን በሰላማዊ መንገድ አላማችንን ለማሳካት ነው። ይህም ሆኖ እንደ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን እንደ ግለሰብም በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ለመሳተፍም ስጋት አለ። በዚህም ዜጎች ራሳቸውን ከፖለቲካ ሲያገሉ ይታያል። ከእነዚህም መካከል ለውጥ የለም እና ለውጡ አዝጋሚ ነው የሚል ምልከታ ያላቸውም አሉ።
ሌላው በተፎካካሪ ፓርቲዎችና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ከሚያደርጉት መካከል አንዱ የሰላም መደፍረስ ነው። ይህን በተመለከተ ስህተቱ የመንግሥትም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ሊሆን ይችላል:: እኛን ግን በማንኛውም ሁኔታ ያለ የሰላም መደፍረስ ያሳስበናል። ግጭቶች በማህበረሰቡ ሰላም፤ በሥራ ፈጠራ በኢንቨስትመንት ጫና እየፈጠሩ ይገኛል። ብዙ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ተግባራቸው እንዲስተጓጎሉ ሆነዋል፡፡ የጤና ኬላዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህ እንደ ጋራ ምክር ቤቱም አባላት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያሳሰብ ነው።
ይህ ችግር በሰላም እንዲፈታ የሰላም ሚንስትሩን አቶ ብናለፍ አንዱዓለምን አነጋግረናል። ከእሳቸውም ሆነ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በነበረን ውይይት ችግር ስለመኖሩ ከስምምነት ደርሰናል። እነዚህ ችግሮች አለመፈታታቸው ቅሬታ ፈጥሮብናል።
ለምሳሌ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የተንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ፓርቲዎች ፈቃድ ማግኘት አልቻሉም። ምክንያቱ ደግሞ የሰላሙ ሁኔታ አስጊ በመሆኑ እንደሆነ መንግሥት አስቀምጧል። ይህ ፍርሃት እንዲወገድና በዜጎች መካከል መተማመን እንዲፈጠርና አንዱ የሌላው ስጋት እንዳይሆን መሥራት የሚጠበቅ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ ውይይት ተመራጭ መንገድ ነው። እየተወያየን እየተግባባን ፍላጎቶቻችንንም ስጋቶቻችንንም እየገለጽን በህብረት የፖለቲካ ባሕላችን መቀየር ይጠበቅብናል። በአሁኑ ወቅት በተደጋጋሚ ውይይቶች እንዲካሄዱ እየሰራን ያለውም ለዚሁ ነው።
አዲስ ዘመን ፤- የጋራ ምክር ቤቱም ሆነ የምክር ቤቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገርና የሕዝብ ሰላም እንዲጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጡ ከሆነ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች የተፈጠሩ የፀጥታ መደፍረሶች ተወግደው ሰላም እንዲሰፍን ምን የሰሩት ሥራ አለ?
አቶ ደስታ ፤- እኛ አጣብቂኝ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ መንግሥትን ደግፈህ ከተናገርክ ጫካ የገቡት በጠላትነት ይፈርጁናል። እነሱንም ደግፈን ከተናገርን መንግሥት በተመሳሳይ በጠላትነት ያስቀምጠናል። በዚህ ሁኔታ የሽምግልና ሚና መጫወትም ይከብዳል። እንደ እኛ ለሰላም ሲባል መሳሪያ ሳያነሱ መታገል ይሻላል የሚል አቋም አለን።
እኛ በተቃዋሚ ጎራ ሆነን የማንቀሳቀሰው ትግላችንን ስናካሂድ እንሰቃያለን፤ እንታሰራለን ፣ እንሞታለን ብለን እንጂ እንገድላለን፣ እናስራለን፣ እናሰቃየለን እያልን አይደለም። ሁሉም እንደኛ ይህንን መንገድ ቢከተሉ ይሻላል የሚል እምነትም አለን። የኃይል ርምጃ እና ጦርነት ወገንን ለስቃይና ለሞት ይዳርጋል፤ ንብረት ያወድማል ሰላም ያደፈርሳል በመሆኑም የሰላም መንገድ ቀዳሚ አማራጭ ነው። የሰላም መንገድን ይዞ በቀስታ ወደ ዲሞክራሲ መጓዝ ይቻላል። የጋራ ምክር ቤቱም ሆነ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍላጎትና እንቅስቀሴም ሰላም ነው። መንግሥትን የዲሞክራሲ ምህዳሩን እንዲያሰፋ የምንጠይቀውም ለዚህ ነው። የጋራ ምክር ቤቱና የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጥረት፤ በመንግሥትም በኩል እየታየ ያለው ፍላጎት እነዚህ ችግሮች በሚፈቱበት ጉዳይ ላይ ለመሥራት ነው። ለዚህም በቀጣይ የፖለቲካ ባሕሉን ለመቀየርና ለማዘመን የምንሰራቸው ሥራዎች ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን፤- በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ተስፋ ከተጣለባቸው ጉዳዮች መካከል ሀገራዊ ምክክሩ አንዱ ነው። ከምክክር ኮሚሽኑ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
አቶ ደስታ፤- የሀገራዊ ምክክር አላማዎች መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ መግባባትን ለመፍጠር፣ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከልና ከመንግሥት ጋር ያለን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመንን ለማጎልበት፣ የመነጋገር ባሕልን ለማጎልበት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት በጋራ ለመገንባት፣ ልዩነቶችን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለመፍታት፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ሽግግር ለማስቻል፣ ልማትን ለማፋጠን ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ነው።
እነዚህ አላማዎች ደግሞ ምክር ቤቱና አባላት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደግፉት ነው። በመሆኑም ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ጋር በቅርበት እየሰራን እንገኛለን። እስካሁንም የፖለቲካ ፓርቲዎች አጠቃላይ ተሰባስበን ከኮሚሽነሮቹ ጋር እየተገናኘን በተደጋጋሚ መክረናል። በተጨማሪ ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶችም ጋር በመተባበር እየሰራን እንገኛለን። በቢሾፍቱ ሶስት ጊዜ አዲስ አበባ ሁለት ጊዜ የጋራ መድረክ በማዘጋጀት ኮሚሽነሮቹ ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ምን እየሰሩ እንዳለ ገለጻ አድርገዋል። ምን ያህል ከፖለቲካ ነፃ ሆነው እየሰሩ መሆኑን እንዲያሳውቁ ሁኔታዎችን አመቻችተናል። ከአዲስ አበባ ውጭ ወጥተው ሲንቀሳቀሱ በእኛ በኩል ሊደረግላቸው የሚፈልጉት ነገር ካለም ድጋፍ እያደረግንላቸው እንገኛለን።
አዲስ ዘመን ፤- የፖለቲካው መድረክ የተለያዩ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩበት ለማድረግ በገዢው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ካለው ውይይት ባለፈ በተፎካካሪዎች መካከልም የሃሳብ ልውውጥ እንዲደረግ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ የሰራችኋቸው ወይንም ልትሰሩ ያስባችሁት ካለ ቢያካፍሉን?
አቶ ደስታ ፤- እስካሁን ባለው ሂደት የጋራ ምክር ቤቱ በመንግሥትና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል እንደ ድልድይ በመሆን በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን በቅቷል። ነገር ግን ከዚህም በዘለለ ዋነኛ አላማው የሃሳብ የበላይነትን የተከተለ የፖለቲካ ምህዳር እንደ ሀገር መፍጠር በመሆኑ በዚህ ረገድ ሁሉን ሥራዎች አቅማችን በፈቀደ የምንሰራ ይሆናል። እስካሁን ድረስም ውይይቶች ተካሂደዋል ስንል የጋራ ምክር ቤቱ አባላት አንድ ሃሳብ አንድ አቋም ይዘው ከመንግሥት ጋር የሚሞግቱበት ሳይሆን እርስ በእርስ የሚቃረኑ ሃሳቦች የሚስተናገዱባቸው ናቸው።
በአንዳንድ ወገኖች እይታ ተቃዋሚዎችን ሁሉ አንድ አድርጎ የማየት ነገር ይስተዋላል። ግን በውስጣችን የተለያዩ ልዩነቶች አሉ። ምን አልባት በአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት በሃሳብ ደረጃ ከመንግሥት ጋር ካለው የሰፋ ሊሆን ይችላል። ይህ አስተያየት ራሱ ካልተስተካከለ የፖለቲካ አመለካከት የሚመነጭና ብዙዎቻችን ውስጥ ያለና ሊስተካከል የሚገባው ነው።
እኛ ባለን መረጃ አንደ ሃሳብ የሚነሳው የጋራ ምክር ቤቱ መንግሥትን ማለትም ገዢውን ፓርቲ የሚገዳደር ሳይሆን ራሱ የመንግሥት አንድ ወገን ተደርጎ እንደሚወሰድ ነው። እኔ ራሴ በ2002 ዓ.ም ፖለቲካውን ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ የመንግሥት ሰዎችን አልቀርብም ነበር። መንግሥትን መቅረብ እንደ ስህተት፤ እንደ ክህደት ፖለቲካውን እንደ ማበላሸት የምንቆጥር የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙዎች ነን። በአንዳንድ ወገኖች በኩል እንደ ወንጀለኝነትም ሲታይ ይስተዋላል። እኔ ይህ አካሄድ አዋጭ አለመሆኑን ከተረዳሁ ውዬ አድሪያለሁ። መነጋገር ሲኖርብን በሰላማዊ መንገድ እስከሆነ ድረስ መነጋጋር መወያያት አለብን። ይህ አካሄድ ሊለመድ ይገባል።
የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚያበላሹና በሕዝብ ዘንድ አመኔታን የሚያሳጡ ተግባራት የሚያከናውኑ በገዢው ፓርቲና በመንግሥት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተፎካካሪ ፓርቲዎችም ውስጥ አሉ። በተለይም ከለውጡ በኋላ ጠንካራ የተባሉ ለውጥ ያመጣሉ የተባሉ ፖለቲከኞች የፖለቲካ አላማቸውንና ደጋፊዎቻቸውን እርግፍ አድርው ትተው አሁንም ሕዝብን በማታለል ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞች አሉ።
አዲስ ዘመን፤- በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሀገር በሚጠቅም መልኩ የተቃኘ እንዲሆን ከገዢው ፓርቲ/ ከመንግሥትም ሆነ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ይጠበቃል።
አቶ ደስታ፤ – በዚህ ረገድ እንደ ጋራ ምክር ቤት የያዝነው ሃሳብ እስካሁንም በቀጣይም የምንሰራበት ለሰላማዊ እንቅስቃሴ ቅድሚያ መስጠት ነው። የእኛም ቀዳሚ ትኩረት ይሄ ነው። በቅርቡ ለጠቅላይ ሚንስትሩ በሀገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ያለውን ግጭት መንግሥት በሰላም በሆደ ሰፊነት እንዲፈታ ጠይቀን ነበር። እሳቸው በሰጡን ምላሽ ሰላም እንዲሰፍን ሙሉ ፍላጎት እንዳለ ለዚህም መሥራት ያለባቸውን ሥራ እየሰሩ እንደሆነ ነግረውናል። ነገር ግን መሳሪያ አንስተው የሚተኩሱ ሰዎችን ዝም ማለት የማይቻል መሆኑን ተናግረዋል። እኛ ግን እንደ ዛሬው ሁሉ ነገም የትኛውም ትግል በሰላማዊ መንገድ እንዲሆን ከመሥራት አንቆጠብም።
ለሰላም የሚሰራ ሥራ በአንድ ወገን እንቅስቃሴና ፍላጎት ብቻ ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ሁላችንም ለሰላም አንዱ ለሌላው የህልውና ስጋት ሳይሆን መንቀሳቀስ መቻል አለብን። ለዚህም እንደ ጋራ ምክር ቤትም፤ እንደ ፖለቲካ ፓርቲም፤ እንደ ግለሰብም ለጦርነትና ለግጭት ከሚዳርጉ አመለካከቶችና ተግባራት መቆጠብ እንዳለብን አምነን እየሰራን ነው።
ይህም ሆኖ የአንድ ሀገር ፖለቲካ እንዲስተካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን የሌሎች አካላትንም ተሳትፎ ይጠይቃል። የፖለቲካው መስክ ብዙ ተዋናዮች አሉት። ከእነዚህ መካከል ሚዲያው ትልቅ ድርሻ አለው። ሚዲያው የሚታመን ሥራ ይሰራል ብለን አናምንም። ይህንን ስንል መንግሥትን ይቃወም እኛን ይደግፍ ማለታችን አይደለም። ነገር ግን በማህበረሰቡ ዘንድ ያሉ ችግሮችን እየተከታተለ የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለበት ይሰማናል። ይህ አካሄድ በቀጥታ የሀገሪቱን ፖለቲካ መስመር የሚያሲይዝ ነው። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ የሚንቀሳቀሰው እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ማህበረሰብ እወክለዋለሁ ያለውን ሕዝብ ችግር ለመቅረፍ ነው። ሚዲያው ችግሩን ለሕዝብና ለመንግሥት ተደራሽ አድርጎ መፍትሔ የሚያሳይ ከሆነ በፖለቲካው መስክ ትልቅ ሚና ይጫወታል ማለት ነው፡፡ በዚህም ትልቅ ሀገራዊ ሥራ ሰራ ማለት ነው። እንደ ጋራ ምክር ቤት ይህ እንዲሆን እንፈልጋለን።
በተመሳሳይ ከሌሎች መንግሥታዊ ከሆኑ ተቋማትና ከፍትህ ሥርዓቱም ይበቃል። እነዚህ ተቋማት ሕግን መሠረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የሕዝብን መብት አስከበሩ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ሰጡ ማለት ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲከኞችም የመጨረሻ ግብ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት፤ የሕዝብን ችግር መቅረፍና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። በመሆኑም እንደ ሀገር ሲታይ በየትኛውም መንገድ ቢሆን የሚፈለገው የሕዝብ ጥያቄ መፍትሔ ማግኘቱ ነው።
አዲስ ዘመን፤- በቀጣይ ከጋራ ምክር ቤቱ ምን እንጠብቅ ?
አቶ ደስታ፤- የጋራ ምክር ቤቱ የራሱ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት የለውም። ራሱ በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ አመለካከት የተስተካከለ እንዲሆን መሥራት ነው። የተስተካከለ ማለት ደግሞ በዋነኝነት የፖለቲካ አመለካከቶችን በሰላማዊ መንገድ በመቻቻልና በመነጋጋር ማስተናገድ ማለት ነው። ይህ መሳካት ከቻለ እንደ ሀገር ፖለቲካው መስክ ትልቅ ድል ተገኝቷል ለማለት ይቻላል። እንደ ጋራ ምክር ቤት ለቀጣዩ ትውልድ አመለካከትን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ እንደሚቻልና እንደሚገባ ማስተማር ከቻልን እኛ ከምንም በላይ ውጤታማ መሆን እንደቻልን ነው የሚሰማን። እኛን የሚደግፉ አካላትም ይህንን መሠረት አድርገው መሆን አለበት የሚል አቋም አለን።
አዲስ ዘመን፤- ስለነበረን ጊዜ እናመሰግናለን።
አቶ ደስታ፤- እኔም አመሰግናለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም