የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትስስር

የትምህርት አንዱ አላማ በዕውቀት የታነጸና ብቁ የሆነ አምራች ዜጋን በማፍራት ወደ ሥራ ዓለም መቀላቀል ነው። ለዚህ ደግሞ የትምህርት ተቋማት በሥራቸው ላሉ ተማሪዎችና ሰልጣኞች የሚሰጧቸው የንድፈ ሃሳብ ዕውቀቶች ብቻቸውን በቂ ባለመሆናቸው ከሥራ በፊት የተግባር ልምምድ አስፈላጊ ይሆናል። በዚህ ረገድ የነበረው የልምድና የእውቀት ሽግግር የአንድ ወገን ማለትም ተማሪዎች በወረቀት ሲማሩት የነበረውን በሥራ ላይ ካሉት በተግባር የሚቀስሙበት አካሄድ ብቻ ነበር። በትምህርት ተቋማትና በኢንዱስትሪዎች ወይም ሌሎች የሥራ ቦታዎች ሊኖር የሚችለው የዕውቀት ሽግግር ግን የበለጠ ውጤታማ የሚያደርግ ይሆናል።

የከፍተኛ ትምህርትና ሌሎች ተቋማት ትስስርም ይህንን እውን ለማድረግ የተጀመረ ቅንጅት ነው። ይህም ትስስር ተማሪዎችን ከማብቃት ባለፈ የትምህርት ተቋማቱንና ራሳቸው ኢንዱስትሪዎቹንም ተጠቃሚ የሚያደርግም ነው። ይህ ትስስር ለኢትዮጵያ አዲስ ቢሆንም በአውሮፓና የሩቅ ምስራቅ ሀገራት ብዙ ተሰርቶበት አበረታች ውጤት የተመዘገበበትም ነው። በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ይህንን ትስሰር በተቻለ አቅም በመተግበር እያስመዘገቡ ካሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ይጠቀሳል።

ከአራተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ 7 ዓመታትን ያስቆጠረው ሲሆን፤ የተሰጠውን የመማር ማስተማር፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የህብረተሰብ አገልግሎት ሥራ እየተገበረ ይገኛል። በሶስት ኮሌጆች በ9 የመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር የተቋቋመው ዩኒቨርሲቲው በዚህ ወቅት የመማር ማስተማር ሂደቱን በማስፋፋት በ6 ኮሌጆች እና አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ በ33 የመጀመሪያ ዲግሪ እና 41 ሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች የመማር ማስተማር ተግባሩን እያሳለጠ ይገኛል። ‹‹ጥራትን በጋራ/በጥምረት›› የሚል መሪ ቃል ያለው ዩኒቨርሲቲው ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግም ከመማር ማስተማር ሂደቱ በተጓዳኝ ከሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚገኙ የምርምርና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትስስር ሥራዎቹን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ በዩኒቨርሲቲው መምህርት እንዲሁም የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር የሺመቤት ቦጋለ (ዶክተር) ይገልጻሉ።

ዳይሬክተሯ እንደሚሉት፣ በዚህም ዘርፍ ተጠቃሽ የሆኑ እንቅስቃሴዎች ያሉ ሲሆን፤ የመማር ማስተማር ሂደቱን በማሳለጥ፣ የጥናትና ምርምር አድማስን በማስፋት እንዲሁም የምርምር ውጤቶችን ወደ ማህበረሰቡ ለማውረድ እንዲቻል የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማከናወን ከሚያግዙ ተቋማት ጋር ጥምረት በመፍጠር ነው። ዩኒቨርሲቲው በሀገር ውስጥ ከአቻ የትምህርት ተቋማት ጋር የሚሰራ ሲሆን እንደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያሉ አንጋፋ ተቋማትም በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ አራተኛ ትውልድ እንደመሆኑ ዕውቀትና ልምድ ለመቅሰም፣ አሰራሮችን ለማሻሻል እንዲሁም ዕውቀትን ለማሻገር ያመች ዘንድ በትብብር ይሰራል። ለአብነት ያህልም በጅማ ዩኒቨርሲቲ በስፋት ተግባራዊ የሆነውን ከተማሪዎች ምዘገባ አንስቶ ሌሎች አገልግሎቶችን በአንድ ካርድ ብቻ ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ አሰራር ወደ ተቋሙ ማሻገር ተችሏል። በዚህም በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ማስጀመርን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።

በተመሳሳይ በግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሱ የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ከሆነው ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆንም የባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ረገድ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ ተማሪዎችን በማማከርና በመመዘንና ወዘተ ዘርፎች እየተሰራ ነው። እንደ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም አርሲ ዩኒቨርሲቲ ካሉ ተቋማት ጋርም መሰል የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የልምድ ልውውጥ ላይ በጋራ በመሥራት ላይ ይገኛል።

ከትምህርት ተቋማት ባለፈም ዩኒቨርሲቲው ከመንግሥታዊ ተቋማት ጋር በተለያዩ መስኮች አተኩሮ በመሥራት ላይም ይገኛል። ለዚህም ዳይሬክተሯ በማሳያነት የሚያነሱት የኢትዮጵያ ኢንተርፕሬነር ሺፕ ኢንስቲትዩት ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲውን ሠራተኞች በማሰልጠን፣ ተማሪዎች ሥራ ከመፈለግ ይልቅ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ በማስገንዘብ እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ ይህንኑ እንዲረዳ የማድረግ ተግባር ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው። እንደ ሰበታ የምርምር ማዕከል ያሉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋርም በጥምረት በመሥራት በዕውቀት ልውውጥና ልምድ ሽግግር ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እያገኘም ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አካላት ጋር በትስስር ሲሰራ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ወደመሬት ለማውረድ እገዛ ከማድረጉ ባለፈ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለይቶ በማውጣት በጥናትና ምርምር መፍትሔ ለማግኘትም ረድቶታል። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ተማሪዎች እንዲሁም መምህራን የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ተግባራዊ ሆነው ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ መደርደሪያ ላይ መቀመጥ እጣ ፋንታቸው ነው።

ነገር ግን የትምህርት ተቋማቱ ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎችና ኢንዱስትሪዎች ጋር አብረው መሥራት ቢችሉ መሰል ችግሮች በቀላሉ በተማረ የሰው ኃይልና በሳይንሳዊ አሰራር ሊቀረፉ ይችላሉ። በዚህም የትምህርት ሆኖ ሌሎች ሥራዎች ላይ የተሰማሩት ተቋማት ጥናቱን ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም ችግርን በመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል። በሌላ በኩል ይህንን አሰራር ተግባራዊ በማድረጋቸው ዩኒቨርሲቲው ዓላማ አድርጎ የተነሳውን ጥራት እና ብቁ ዜጋን ከማፍራት ረገድ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑንና ኢንዱስትሪው ላይ ያለውን ችግር ለመለየት እንደሚረዳም ዳይሬክተሯ ያብራራሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን ሁለቱ አካላት በምርምር የተደገፈ የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡበትንም መንገድም ይቀይሳል።

ይኸው አሰራር በከፍተኛ ትምህርት እንዲሁም የምርምር ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ ወጪ ተደርጎባቸው የሚገነቡ የጥናትና ምርምር ቤተ ሙከራዎችንና ማዕከላትንም በጋራ በመጠቀም የሀገር ሀብት እንዳይባክን ለማድረግም ያስችላል። ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ምስረታው ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረ እንደመሆኑ በውድ ዋጋ መሰራት የሚያስፈልጋቸው የቤተሙከራ ሥራዎችን ለማከናወን አቅም ባለማዳበሩ ምክንያት ጥምረት ከፈጠረባቸው የምርምር ተቋማት ቤተሙከራዎች ለመገልገል ዕድል ፈጥሮለታል። ትልልቅ ቤተሙከራ ያላቸው እንደ ሰበታ እና ሆለታ የምርምር ማዕከልን የመሳሰሉ ተቋማትም ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ሁኔታ በየተቋማቱ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ቤተሙከራዎችንና ወርክሾፖችን በመገንባት የሚወጣውን የሀገር ሀብት ከብክነት መታደግ እንዲሁም ውጤታማ ሥራን ለማከናወን እንደተቻለም አሰራሩ ማሳያ ይሆናል። ተግባር ተኮር ትምህርትን ከመስጠት አንጻርም ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ከሚያገኙት የንድፍ ትምህርት ባለፈ በዓይናቸው እየተመለከቱና በተግባር ተሳታፊ ሆነውበት በመማር ክህሎትንም እንዲያዳብሩ ከኢንዱስትሪዎች ጋር በትስስር መሥራት የተሻለ እድልን ይፈጥራል። በተጨማሪም ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን አጠናቀው ከተመረቁ በኋላ ወደ ሥራው ዓለም ሲገቡ ለአሰራሩ አዲስ እንዳይሆኑ ይረዳቸዋል።

በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር መሥራታቸው አስቀድሞ ገበያው የሚፈልጋቸውን ተማሪዎች አውቆ ለማፍራትም ያስችላል። በተደጋጋሚ እየተስተዋለ እንደሚገኘው ኢንዱስትሪዎች የራሳቸውን የትምህርት ሥርዓት በማዘጋጀት ተማሪዎችን ተቀብለው ስለሚያሰለጥኑ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተመራቂዎች ቦታ የሚያጡበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህ እንዳይሆንም የትምህርት ተቋማቱ ከኢንዱስትሪው ጋር መሥራት የሀገሪቱ ገበያ የሚፈልገው ምን ዓይነት ተማሪዎችን ነው የሚለውን ለመለየት ከማስቻሉም ባለፈ ሥራ ከማጣት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ቀውስ ለመቀነስ ይረዳል። በመሆኑም እነዚህ ተቋማት አብረው ከመሥራት ባለፈ በሥርዓተ ትምህርት ቀረጻም ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው።

ከትምህርትና ጥናት በዘለለ ከተጣመራቸው ተቋማት ጋር በመሆን የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችል የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ላይም እየተሳተፈ ነው። በማሳያነት ለማንሳት የሚቻለውም ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ ያላገኙ ወጣቶችን በማሰባሰብ በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ጋር በነበረው ስምምነት መሰረት ምርጥ የወተት ዝርያ ያላቸውን ላሞች የማዳቀል ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በየአካባቢው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግን ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ሀገር በቀል ካልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት እና ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የወተት ዝርያ ያላቸውን ላሞች ለማዳቀል የሚያስችል ዘር ከኮሪያ በማስመጣትና የሰለጠኑትን ወጣቶች በመጠቀም በሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙ 1ሺ አርሶ አደሮች በነፃ አገልግሎቱ እንዲሰጣቸው ተደርጓል። በዚህም ከ1ሺዎቹ መካከል 700 የሚሆኑት ስኬታማ እንደነበሩ በተደረገው ክትትል ማረጋገጥ ተችሏል።

ከአካባቢ ማልማት ጋር በተያያዘም በረሃማ የነበሩ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ረገድ ስትራቴጂ በመንደፍና የሶስትዮሽ ግንኙነት በመፍጠር፤ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የዓባይ በረሃ ከደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ደን ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን የበረሃ ቀርከሃ ችግኝ በማፍላትና በማላመድ የማልማት ሥራ እየተሰራ ነው። ከቀርከሃው በተጨማሪ የቆላ ፍራፍሬዎችን በማልማት ለአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሰራጭም ተደርጓል። በአካባቢው እምብዛም ያልተለመደውን የቡና ተክል ምርታማ ሊሆን በሚችል መልኩ በማላመድ ለማህበረሰቡ ተከፋፍሏል። በዚህም ገላጣና የተራቆተ የነበረውን ስፍራ መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ማሳያ የሆነ ፕሮጀክት ተግባራዊ በመደረግ ላይ እንደሆነም ዳይሬክተሯ ዶክተር የሺመቤት ያስረዳሉ፡፡

‹‹ደረጃ ዶትኮም›› የተባለና የሥራ ፈጠራ ላይ ለተማሪዎች ስልጠና የሚሰጥ ድርጅትም ከዩኒቨርሲቲው ጋር በፈጠረው ቁርኝት ተማሪዎች በሥራ ፍለጋ ክህሎት፣ በሲቪ አጻጻፍ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ላለፉት ዓመታት ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በመሆንም የተቋሙን ሥራዎች ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም የጋዜጠኝነትና የኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ተግባራዊ ልምምድ እንዲያደርጉ በማመቻቸት በኩልም በትስስር ይሰራል። በዩኒቨርሲቲው ስር ያለውን የፊቼ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በመሆንም ለአካባቢው ነዋሪዎች የነፃ ሕክምና እንዲያገኙም ተደርጓል። ከባንኮች ጋር በመተባበር ለተማሪዎች ተግባራዊ ልምምድ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውንም ሆነ ሌላውን ማህበረሰብ ሊጠቅም በሚችሉ ጉዳዮች ላይም በጋር ይሰራል።

ይህንንም በቀጣይ ለማጠናከርና አዳዲስ ቁርኝቶችን ለመፍጠርም ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሰራ ይገኛል። ተቋማት በትስስር የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ መሥራት ተገቢ በመሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በጋራ ቢንቀሳቀሱ ሥራቸው ይበልጥ ውጤታማና ፍሬያማ መሆን ይችላሉ። ሀገርን በመጥቀም እንዲሁም ሀብትን በጋራ መጠቀም እንደሚያስችልም ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You