ኢትዮ ቴሌኮም ከ900 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የገጠር ቴሌኮም አገልግሎት አስጀመረ

ቦዣባር፦ ኢትዮ ቴሌኮም በመላው ሀገሪቱ 903 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የገጠር ቴሌኮም አገልግሎት አስጀመረ፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ቦዣባር ከተማን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ያስገነባቸውን 100 የገጠር ቴሌኮም ፕሮጀክቶችን አገልግሎት አስጀምሯል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ መሠረተ ልማት ምክትል ቺፍ ኦፊሰር አቶ አለም ኃይለማርያም በወቅቱ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በአራት ምዕራፍ 500 የገጠር ሞባይል ኔትወርክ ሶልሽን ፕሮጀክት ለመገንባት የታቀደ ሲሆን በመጀመሪያው ምዕራፍ 100 የገጠር ቴሌኮም ፕሮጀክቶችን በመገንባት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

የቴሌኮም አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ለማስፋት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ የተመረቁት ፕሮጀክቶች 903 ሺህ ዜጎች ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

ዘርፉን በማጠናከር ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግና የዘርፉን እድገት ለመደገፍ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

አገልግሎት የጀመረውም የኔትወርክ መሠረተ ልማት የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጎች ኔትወርክ እና ተዛማጅ አገልግሎት ለማግኘት በአማካይ እስከ 20 ኪሎ ሜትር የሚያደርጉትን ጉዞ በማሳጠር አካታች የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

አገልግሎቱ በገጠራማ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖረው የማህበረሰብ ክፍል መሠረታዊ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል ሱሉ አቶ አለም ተናግረዋል።

በተጨማሪም በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በሌሎችም ዘርፎች የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ የዜጎችን ሕይወት በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

የቦዣባር ከተማ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ሽምነሳ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በከተማውና በአካባቢው በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ የኔትወርክ አገልግሎት ባለመኖሩ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ መገንባቱ በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ኢኮኖሚያቸውን እንዲያሳልጡ፣ ባንኮች እንዲከፈቱና የቁጠባ ባህል እንዲያድግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢው ማህበረሰብ በቴሌብር አማካኝነት ገንዘብ ከመላክ፣ ከመቀበልና ግብይት ከማከናወን ባሻገር ኑሮውን ለማሻሻል እንደሚረዳው ጠቁመዋል፡፡

ኢፕድ ያነጋገራቸው የቦዣበር ከተማ ነዋሪ የሆኑት መምህር ኑሬ መንገሻ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም የኔትወርክ አገልግሎት ባለመኖሩ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ቆይተዋል፡፡

ነግር ግን አሁን ላይ ፕሮጀክቱ አገልግሎት በመጀመሩ የሞባይል ዳታ እና የስልክ አገልግሎት መጠቀም ችለናል ብለዋል።

ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ሰሚራ ሙሰማ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የቴሌኮም አገልግሎት በከተማው አለመኖሩን ገልጸው በዚህም ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ተዳርገን ቆይተናል ሲሉ አስረድተዋል።

አሁን ላይ የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታችን አውስተው ኢትዮ ቴሌኮምን አመስግነዋል።

አማን ረሺድአ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You