ብልሹው የግብይት ሥርዓት የገንዘብ ፖሊሲውን እንዳያጨናግፈው

ኮሽ ባለ ቁጥር ዋጋ ለመጨመር በጥፍሩ ቆሞና አሰፍስፎ የሚጠብቀው ስግብግበ ነጋዴ ሰሞነኛውን የገንዘብ ፖሊሲ ለውጥ ወይም የውጭ ምንዛሬ ግብይት በገበያ ይወሰን ማለቱን ተከትሎ ቀደም ብሎ ያስገባውን መሠረታዊ ሸቀጥ መደበቅና ከገበያ ማጥፋት እና ያልተገባ ዋጋ ጭማሬ ላይ ተጠምዶ ገበያውን እያመሰውና እያስራበው ይገኛል። በዚህም ሸማቹ እየተማረረና ለብሶት እየተዳረገ ይገኛል።

በዚህ የተነሳ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል። እስከ ነሐሴ አንድ ቀን ድረስ ያላግባብ ዋጋ በጨመሩና ሸቀጦችን ያከማቹ 42 የንግድ መደብሮች ፍቃዳቸው እንደተነጠቀ አስታውቋል። መንግሥት ተመሳሳይ ጥፋት በፈጸሙ 7 ሺ 312 የንግድ መደብሮች ላይ ደግሞ የማሸግ ርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል። 286 ሕገወጥ የተባሉ ነጋዴዎችም በእስራት እንደተቀጡ ሚኒስቴሩ አመልክቷል::

በተያያዘ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ የምግብ ዘይት ደብቀው ከተገኙ ነጋዴዎች የወረሰውን 800 ሺህ ሊትር ዘይት ለ10 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማከፋፈሉን አስታውቋል። ደጋግሜ እንደምለው የኑሮ ውድነት ፣ የዋጋ ግሽበት ፣ ሥራ አጥነት ፣ ድህነትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ብሔርና ሃይማኖት የላቸውም። አማራ ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ ፣ ሱማሌ ፣ ትግሬ ፣ ወዘተረፈ አይደሉም።

ኦርቶዶክስ፣ እስላም ፣ ክርስቲያን ፣ ዋቄ ፈና ፣ ወዘተረፈ አይደሉም ። ኢትዮጵያዊ ከፍ ሲልም ሰው ናቸው። እነዚህ የኢኮኖሚ መሠረታዊ አላባውያን ማለትም የዋጋ ግሽበቱና የሥራ አጥነቱ ቢያንስ ባለነጠላ አኃዝ እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕድገቱ ጤናማ ከሆነ ሕዝብን በአዎንታ ሳይነጋገር አንድ ያደርጋሉ። ሕዝብን ለድጋፍ ለአንድነትና ለፍቅር ያነሳሳሉ። በተቃራኒው እነዚህ መሠረታውያን ጤናማ ካልሆኑ የዋጋ ግሽበቱ አሻቅቦ የኑሮ ውድነቱ ከተባባሰ፤ የሥራ አጥነቱ ካሻቀበና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ፍትሐዊ ካልሆነ ሕዝብን በአሉታዊ ማለትም ለተቃውሞና ለአመጽ በአንድነት ያነሳሳሉ።

ይህ ኢኮኖሚያዊ ስኬታችንም ሆነ ውድቀታችን ከፖለቲካው በላይ ጉልበት እንዳለው ያስረዳል። ከፖለቲካችን በላይ ለኢኮኖሚያችን ልዩ ትኩረት መስጠት ግድ የሚለው ለዚህ ነው። በተለያዩ ሰበቦችና ምክንያቶች የተቀሰቀሱ ቀውሶች ፖለቲካዊ ካባ ይደረብላቸው እንጂ በውስጠ ታዋቂነት የኢኮኖሚያዊ ብሶትና ተስፋ መቁረጥ ቅርሻዎች ናቸው። የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ የሚደረገው ጥረት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የሚመጥን፣ አጥጋቢና ወጥ አለመሆኑን ለታዘበ ፣ ለዘላቂ መፍትሔ ተጨባጭ ፣ ግልጽና ተፈጻሚ የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ካልተነደፈ፤ የተለያዩ ጥያቄዎች ለማንሳት ያስገድዳል።

የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱ በዚህ ከቀጠለ ከጽንፈኝነትና የሴራ ፖለቲካ በላይ የህልውና አደጋ ፤ የኑሮ ውድነቱ የደህንነትና የጸጥታ ስጋት የመሆን አሉታዊ አቅሙ በቅጡ ግንዛቤ ተይዞበታል !? የኑሮ ውድነት ወላፈኑስ ያለ ልዩነት እኩል ዜጋውን እየተሰማው ነው !? የመንግሥት ባለስልጣናትስ የኑሮ ውድነት እንደ ተራው ሕዝብ ይሰማቸዋል !? ካልተሰማቸው እንዴት የመፍትሔው አካል ይሆናሉ !? እንዴትስ ለመፍትሔው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይችላል!? ሁለት አስር ዓመታትን ያስቆጠረው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የዜጋውን ኑሮ በብርቱ እየፈተነው፤ ከኢኮኖሚያዊ ችግርነት ወደለየለት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስነት እንዳይባባስ እያሰጋ ይገኛል ።

በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ኢኮኖሚው ከለውጡ በፊት ከአቅሙና ከልኩ በላይ በብድርና በእርዳታ መልክ የጎረሰው፤ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተቀሰቀሱ ግጭቶች ብልሹው የግብይት ሥርዓት የገንዘብ ፖሊሲውን እንዳያጨናግፈው ጋር ተጃምሎ የዋጋ ግሽበቱንና የኑሮ ውድነቱ የዜጋውን ኑሮ እየፈተነው ይገኛል። በአናቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የተራዘመ የግብይት ሰንሰለት ፣ ከገበሬ ማሳና ከጉልት እስከ ጅምላ አከፋፋይ የተሰገሰገ ደላላ ፣ የገነገነ ሙስና ፣ በግብይት ሰንሰለቱ የተንሰራፋው ሥርዓት አልበኝነት ፣ ዋጋን በአድማ መወሰን ፣ ምርትን በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር፣ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም፤ የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል በመንግሥት መዋቅር ዘንድ ወጥ የሆነ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለመኖር ፣ የሎጅስቲክስ አገልግሎቱ ቀልጣፋ አለመሆን ፣ ወደብ አልባ በመሆናችን በየዓመቱ ቢሊዮኖችን የምናወጣ እና ስለመብቱ የሚቆረቆርና የሚጠይቅ ጠንካራ ሸማች አለመፈጠሩ እንደ ዚምባብዌና ቬኒዞይላ ባይሆንም በሰዓታት ልዩነት ለሚተኮስ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንዲዳረግ ሆኗል።

የውጭ ምንዛሬ በነጻ ገበያ ይወሰን መባሉን ተከትሎ በፍጆታ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ግሽበትንና የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ይገኛል ። የዓለም አቀፍ በረራ የቲኬት ዋጋንና የፓስፓርት ክፍያን ታሪፍ ማሻሻያ ልብ ይሏል። አምስት ሊትር የምግብ ዘይት ሰሞኑን 1500 ብር መግባቱ ሳያንስ፤ ሲያሻው ከገበያ ይጠፋል። ስንዴን ወደ ውጭ ለመላክ እየተዘጋጀን ባለንበት የስንዴ ፊኖ ዱቀት በኪሎ ወደ 100 ብር ተተኩሷል። ገና ሲቆርሱት ዱቂት የሚሆን ዳቦ 10 ብር ገብቷል ።

ጤፍ እንደዚሁ በኪሎ 155ና ከዚያ በላይ ገብቷል። ቡና በኪሎ ወደ 500 በር አሻቅቧል። ሽንኩርት 80 ፣ ቲማቲም አጠቃላይ አትክልትና ፍራፍሬ አልቀመስ ብሏል። አቡካዶ በኪሎ 70 ብር ፣ ቢጨምቁት ጠብ የማይለው አንድ ኪሎ ሎሚ 180 ብር ገብቷል። እህልና ጥራጥሬውም ብሶበታል። በዚህ ሳቢያ በመዋቅራዊና በተቋማዊ ችግር የተነሳ ጽኑ ታማሚ ሆኖ ለኖረው ኢኮኖሚ ሌላ ራስ ምታት ሆኖበታል።

የለውጡ መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ ያደረገው ጥረት የሚፈለገውን ያህል ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም። አልበርት አነስታይን፤” ችግሩ በፈጠረው አስተሳሰብ፤ ችግር መፍታት አይቻልም:: “እንዳለው ከሳጥኑና ከተለመደው አተያይ ወጣ ብሎ መፍትሔን ማማተር ግድ የሚሉ አሳሳቢ ወቅት ላይ ስለሆን ነው ሰሞነኛው የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ የተደረገው። ሥነ ምግባር የጎደላቸው አንዳንድ የመንግሥት አመራሮች በዚህ ሕገ ወጥ የግብይት ሥርዓት ተሳታፊ ሆነው መገኘታቸው ችግሩን እንዳወሳሰበው በዚያ ሰሞን የጸረ ሙስና ኮሚሽን ባካሄደው መድረክ ይፋ ሆኗል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦቦ ሽመልስ አብዲሳ ባለፈው በተካሄደው ጨፌ ኦሮሚያ ይሄን ሀቅ ደግመውታል። ከዚህ ውይይት በፊት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከሕዝብ በደረሰው ጥቆማና ባደረገው ክትትል መሠረት በየመጋዘኑ ተከዝነውና ተደብቀው የሚገኙ የምግብ ዘይት ፣ የስንዴ ዱቄት ሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦችን ለመያዝ ሲንቀሳቀስ በየአካባቢው ያለ አመራር ለመተባበር እንዴት እግሩን ይጎትትና ለማደናቀፍም ይጥር እንደነበር መግለጹ የኮሚሽኑን ግኝት ተጨባጭ ያደርገዋል።

መንግሥት መዋቅሩን ካላጣራ ችግሩ ተባብሶ የሥርዓቱም የሀገሪቱም አደጋ መሆኑ አይቀርም። ይሄን ሥርዓት አልባ የግብይት አሰራር መንግሥት በማያዳግም ሁኔታ በሕግ አግባብ ሥርዓት ሊያሲዘው ካልቻለ፤ ከማሳና ከጉልት እስከ ጅምላ አከፋፋይ የተሰገሰገውን ደላላ ከግብይት ሰንሰለቱ ካላስወጣ፤ በድጎማ ከውጭ የሚገባን ዘይትና ስንዴ ስርጭትን እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ካልተከታተለ፤ የሶማሌ ክልል ሰሞኑን እንዳደረገው በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ተመንና የትርፍ ሕዳግ ካልተቀመጠ ፤ ገበያውን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ባደረገው መሠረት ኩባንያዎችን አሳምኖና አግባብቶ ማስገባት ካልቻለ፤ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጉያ ወጥቶ ስልጣኑና አደረጃጀቱ ተሻሽሎና ተጠናክሮ እንደገና ካልተደራጀ ፤ በግብይት ሒደቱና ሰንሰለቱ የሚስተዋለው አጉራዘለልነትና ውንብድና በሕግ የበላይነት ሥርዓት እንዲይዝ ካልተደረገ ፤ ችግሩ ተባብሶ ተባብሶ ወደለየለት የጸጥታና የደህንነት ችግር እንዳይባባስ ያሰጋል ።

የዋጋ ግሽበቱ ከ30 በመቶ በላይ ተተኩሶና በየቀኑ እየተባባሰ ባለበት፤ የኑሮ ውድነቱ ከእጅ ወደ አፍ የነበረውን ኑሮ የማይቀመስ ካደረገው፤ የስራ አጡ ቁጥር ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ እንዴት ስለኢኮኖሚያዊ ስኬት ማውራት ይቻላል። እንዴት ስለብልጽግና ማለም ይታሰባል። ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው ይሄን ኢኮኖሚያዊ ትብታብ አሁን ላለው መንግሥት በእዳ የተላለፈለት እንጂ ለብቻው የፈጠረው አይደለም። ሆኖም ይሄን ትብታብ የመፍታት ኃላፊነት ትክሻው ላይ ወድቋል።

የጦርነቱ ጫናም ቀላል አይደለም። ኮቪድና የራሽያ ጦርነት የፈጠረው የዋጋ ግሽበትም ተጽዕኖው ከባድ ነው። በባህሪው ገበያ/ኢኮኖሚ ድንጉጥ ነውና ። አይደለም ጦርነትና የግጭት አዙሪት የተሳሳተ ፖሊሲና የገበያ ትንበያ/speculation/ገበያን ያስበረግጋል። ይሄን ችግር ይበልጥ አሳሳቢ ያደረገው ሸማቹ ሕዝብ የመንግሥት ቁርጠኝነት በሙላት ሲገለጥ አለማየቱ ነው። በዚህ የተነሳ ከዛሬው ነገ እንዳይከፋ አስፈርቶታል። አስጨንቆታል። የኑሮው ጉዳይ ልዩ ትኩረት ይሻል። በተለይ በግብይት ሥርዓቱ የሕግ የበላይነትን የማስፈን ጉዳይ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

ከአቅርቦትና ከፍላጎት አለመመጣጠን ፤ ከኮቪድና ከራሽያ ጦርነት ዳፋ ፤ በሀገራችን ከሚስተዋሉ ቀውሶችና ግጭቶች ባልተናነሰ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ሥርዓት አልባ የሆነው የግብይት ሥርዓት ነው ።ለዚህ ነው በግብይት ሥርዓቱ የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ እየተባለ የሚወተወተው ስርዓት ይበጅ የሚባለው ። መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከብር ለውጥ ጀምሮ ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ ኩታ ገጠም ግብርናን ፣ የቆላ ስንዴን ፣ የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት ፣ የአረንጓዴ አሻራን ለማሳካት ጥረት እያደረገ ነው።

ሆኖም ምርት ማሳደግ ብቻውን መፍትሔ አይሆንም። ብልሹው የግብይት ሥርዓት ካልታረም፣ ደላላው ከገበያው ካልወጣ ፣ የኢኮኖሚ አሻጥረኞችን በሕግ ሥርዓት ማስያዝ ካልተቻለ፤ ማህበራዊ ስብራታችን ካልታጀለ ምርታማነታችን የቱንም ያህል ቢያድግ ከዚህ አዙሪት መቼም ቢሆን ሰብረን መውጣት አንችልም። ይሄ ችግር በመንግሥት የተናጠል ጥረት ብቻ አይፈታም። ዩኒቨርሲቲዎች ፣ እንደ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ያሉ ማህበራት ፣ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፣ የሃይማኖት ተቋማት ፣ እንደ የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተውና ተናበው መስራት ይጠበቅባቸዋል ።

በተለይ ዩኒቨርሲቲዎችና እንደ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ያሉ ተቋማት ይሄን ችግር ለመፍታት ጥናትና ምርምር በማድረግ የፖሊሲ ሃሳብ ማመላከትና ማመንጨት ይጠበቅባቸዋል ። ይሄን ሁሉ ተቋም ተሸክመን የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እንዴት እንደ ስፔስ ሳይንስ እስከ መቼ እንደተወሳሰበብን ይቀጥላል ። በእርግጥ የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ የተፈጠረው በምርት እጥረት ነው ፣ በግብይት ሥርዓት ችግር ፣ እሴት በማይጨምር ደላላ ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ፣ በአልጠግብ ባይ ነጋዴዎች ፣ በዩክሬንና በራሽያ ጦርነት ፣ በኮቪድ 19 የተነሳ የተፈጠረና በቅጡ ያላገገመ የሎጁስቲክ ስብራት፤ ወዘተረፈ ነው!? መልሱን በጥናት ማግኘት የማያዳግም መፍትሔ ለማስቀመጥ ይረዳል። በተረፈ ችግሩንና ተጠያቂነቱን ያለአድራሻ ማስቀመጥና ጣት መቀሳሰር ከተዘፈቅንበት አረንቋ አያወጣንም ። መንግሥት የግብይት ሥርዓቱን ስድ መልቀቁ የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን አባብሶታል። ስለሆነም በሕግና በአደረጃጀት ነገ ዛሬ ሳይል ሥርዓት ሊያሲዘውና የቁጥጥርና የክትትል አሰራር ሊዘረጋ ይገባል። የመኖሪያና የንግድ ቤት ኪራይ የኑሮ ውድነቱን ከሚያባብሱ ችግሮች ዋናው ነውና ተመን ሊወጣለት ይገባል። በመሠረታዊ ሸቀጦች የትርፍ ሕዳግና የዋጋ ተመን ሊወጣ ግድ ይላል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ብርሃኑ ደኑ ሰሞኑን ለአትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ ውስጥ የንግድ ሥርዓቱ ፈር የለቀቀ እንዲሆንና የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው በገበያ ሥርዓቱ ውስጥ የሸቀጦች የትርፍ ህዳግ ገደብ አለመቀመጡ ነው:: በመሆኑም በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት መንግሥት የሸቀጦች የትርፍ ህዳግ ገደብ ሊያስቀምጥ ይገባል ብለዋል::

ሌላው ለሸማቾች ሲል ዘይት ፣ ስንዴና ሌሎች መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ቢያደርግም የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት ስለአልዘረጋ ገበያው ሊረጋጋ አልቻለም። መንግሥት በዚህ ፖሊሲው ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ ቢያጣም ለሸማቹ ጠብ ያለ ነገር የለም። ይህ ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው፤ የሕግ ክፍተት መኖሩን ያሳያል ። ስለሆነም በማያዳግም ሁኔታ ሥርዓት ሊበጅለት ይገባል::

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 / 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You