ጭፍን ከሆኑ አስተሳሰቦች ራቅ !

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ መውጣትን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች ዘንበዋል። ምስጉንና ቅዱስ የሆኑ፤ ጨለማና አስፈሪ ሃሳቦች እንዲሁ ተደምጠዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሀገርንና ሕዝብን በሚጠቅም መልኩ አስደናቂና አስገራሚ ለውጦችን ማምጫ መንገድ ነው። በሂደትም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያበለጽጉ ገጸ በረከቶች ያቀፈ ነው የሚሉና በዚህም ተመሳሳይ ለውጥ በማድረግ ሌሎች የዓለም ሀገራት ከየት ተነስተው የት እንደደረሱ በምሳሌነት አስረግጠው የሚነግሩን ጥቂቶች አይደሉም። ብርሃንን የምናይበት መስመር መሆኑን ጭምር ምለውና ተገዝተው ያስረዱናል። እመኑን ለውጥ እናመጣለን። ለውጡን በጋራ እናጣጥማለን። ይህንንም ማሳለጫ መንገድ ብለው የሚተነትኑ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች በርካታ ናቸው። ይሄ ለማንም ለምንም ሳይሆን ሀገርንና ሕዝብን ይጠቅማል ከሚል ቀና ሃሳብ በመነሳት እና ሳይንሱን በመንተራስ ጭምር ።

አንዳንዱ ደግሞ ምንም ሳይገባው ፖለቲካውን ስለደገፈና ካድሬ ስለሆነ ብቻ በቃ ለሀገር ይጠቅማል! መንግሥት ያወጣው በመሆኑ ብቻ ተቀበሉ ብሎ በድፍኑ ዋጠው ሰልቅጠው አስተሳሰብን የሚያራምዱም እንዲሁ አልጠፋም። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ይነሳል። አንድን ፓርቲ (መሪ) ስለደገፍነውም ስለነቀፍነውም ሳይሆን ሳይንሱ ላይ እውነታው ላይ ተመስርተን መሆን አለበት የሚለው ገዢ ምክንያት ይሆናል። ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት ሀገርን ይጠቅማል ? ሕዝብን ከስደት ፣ ከረሃብና ጥም ያድናል ወይ ? ኢኮኖሚው ላይ ጠብ የሚል የሚታይ ነገር ያተርፋል ወይ ?… የሚለው ነው። ዳዴው ቆሞ ወደ መራመድ ከዛም ሮጦ ድህነትን ወደ ማምለጥ ያሸጋግራል ወይ የሚለው ነው ዋና ጥያቄ መሆን ያለበት።

በሌላ በኩል ደግሞ እድል ሳይሆን ስጋት ይዞ መጥቷል ብለው ሳይቀርቡት የፈሩት፤ መፍራት ብቻ ሳይሆን የደነበሩም አልጠፉም ። በዚህ ላይ ትንታኔ የሚያቀርቡ ምሁራን በተመሳሳይ በርክተዋል። ይሄንንም በሁለት መልኩ ማየት ይገባል። አንዳንዱ ይህን ሥርዓት ለማስጠላት በዚህ በኩል አቋራጭ መንገድ አለ ብሎ ከመነሳት ነጩን ጥቁር ለማድረግ የተሞከረበት ነው። ሌላው ደግሞ ፖሊሲው ቢተገበር ጥቅም አለው ሆኖም ግን አብረው የሚመጡ ስጋቶች አሉ ከሚል ይነሳል።

በአግባቡ መምራት ካልተቻለም በዚህ መንገድ ሄደው ያልተሳካላቸው ሌሎች ሀገሮች ወደገቡበት ቀውስ እንገባለን ከሚል ሙያዊ አስተሳሰብ ይመነጫል። እዚህ ላይ መነሳት ያለበት አስተያየቱ ምንም ይሁን ምን ሀገርን ለመጥቀም ከማሰብ ዕድሉንም ስጋቱንም እንደ አመጣጡ ተቀብሎ ሀገርን ለማሳደግ ካለ ቀናነት ከሆነ እሰይ ይበል የሚያሰኝ ነው። ምክንያቱም ስጋቱን የሚተነትነው አካል እስከ መፍትሄው ያክላል፤ የመውጫ መንገዱን ያመላክታል። ቀዳዳውን የመድፈኛ መላዎችንም ያመጣል። ይተነትናል። ይሄ ገንቢ አስተያየት ነው። መሆንም ያለበት ነው እንደ ምሁር። ነገር ግን አንዳንዶች የሚሰጧቸው አስተያየቶች እውነታውን በመርዝ ለውሰው ይሆናል። ሕዝብ ውስጥ ስጋት መፍጠር፣ በሀገር ላይ መአት የመጣ ያክል በሀገሩ ተስፋን እንዲሰንቅ ሳይሆን ተስፋ እንዲቆርጥ የሚያደርግ ነው።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሲደረግ ዋናው ዓላማ ምንድነው ብሎ በቀናነት መነሳት ያስፈልጋል። ዋናው ዓላማውም በሕጋዊ ምንዛሪና በጥቁር ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብና ሕገወጥነትን ማስቀረት ነው፡፡ ተዘግቶ የነበረውን ኢኮኖሚ በመክፈት ዓለምን መቀላቀል ጭምር ነው።

ሀገራት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። ተኪ ምርት ለሀገራዊ ምርትና ኢኮኖሚ እድገት ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም አንድምታው ውስብስብ እና ዘርፈ ብዙ ነው። ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው እና ወደ ውጭ የምትልከው ምርት መጠን የተመጣጠነ አይደለም። ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት 18 ቢሊዮን ዶላር ስታወጣ ወደ ውጭ በመላክ ደግሞ የሚገኘው ገቢ ከአራት ቢሊዮን ዶላር የዘለለ አይደለም። ይሄንን ወጪና ገቢ ምርትን ወደ ማጠጋጋትና የሚታዩ ክፍተቶችን ለመድፈን መስራት አንድ ጉዳይ ነው።

ሌላው ለሀገርና ሕዝብ ተጠቃሚ የሚሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ደሃን በሚጠቅም መንገድ ሲመራ ነው። ዛሬ በትልቅ ስጋትነት በባለሙያዎች የሚነሳው መንግሥትም የሚያምንበትና ችግሩን ለመከላከል የሚሰራው በተለይ አነስተኛ ገቢ ባላቸው የመንግሥት ሠራተኞችና በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ያሉ ዜጎችን በሪፎርሙ እንዳይጎዱ ከማድረጉ ላይ ነው።

የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረግ አስገዳጅ የሆነበት ሌላው ምክንያት ኢንቨስትመንት በሚፈለገው ደረጃ አለማደግ፣ በቂ መሠረተ ልማት አለመኖር ፣ የተቋማት ተልዕኮ የመፈጸም ውስንነት ነው። ሀገራዊ የእዳ ጫናው የሚፈለገውን ያህል እድገት ማምጣት አላስቻለም። በመሆኑም የፖሊሲ ለውጡ አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ዘግይቶ ሊሆን ይችላል። መታሰብ ያለበት በቀጣይ ለሀገራችን እድገትና ብልጽግና ማረጋገጥ የሚያስችለን እንዲሆን እንዴት አድርገን እንጠቀምበት? የትኛው ቦታ ላይ ምን መሰራት አለበት? መንግሥት ያላየው ክፍተትስ የት ነው ያለው? የሚለውን ወደፊት ማምጣትና በዛ ለመጠቀም መሞከር ነው።

በአሁኑ ወቅት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እንደ አንድ ስጋት ሆኖ የሚቆጠረው መንግሥት ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮችና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጫና ያሳድራል፤ የኑሮ ውድነትን ያባብሳል በሚል ነው። ለዚህ ደግሞ መንግሥት መፍትሔ ያላቸውን ሃሳቦች አቅርቧል። እየሰራበትም ይገኛል።

ሌሎች ሀገሮች ያልተጠቀሙበትን ደሀውን የኅብረተሰብ ክፍል በመደጎም የኑሮ ውድነቱን እንዲሸከመው ማድረግ መሆኑን አሳውቋል። ለዚህም እንደ መንግሥት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በነዳጅ፣ በመድኃኒት፣ በማዳበሪያ የሚያደርጋቸው ድጎማዎች እንዲሁም ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ለሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ ማድረግ ነው ። በከተማ ለሚኖሩ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ዜጎችም በሴፍትኔት የሚደገፉበት ፕሮግራም ይኖራል፡፡ ነዳጅም ማህበረሰቡ ሕይወት ላይ ጫና እንዳያደርስም መንግሥት ለድጎማ 100 ቢሊዮን ብር ለማውጣት ዝግጁነቱን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሥራ ሲሠራ የቆየው በጥቁር ገበያ ነው። ደላላና ጥቁር ገበያ የመሪነትን ቦታ ይዘው ሕገወጥነት ተስፋፍቶ ቆይቷል። የጥቁር ገበያ የዶላር ምንዛሬ በአደባባይ የሚቸበቸብበት ሀገር ተፈጥሯል። አሁን ኢኮኖሚው ከፈት ሲደረግ ብዙ የሚያሳስቡ ፣ ያልተጠበቁና የሚያስደነግጡ ነገሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ይሄንን አስቀድሞ ትንተና በመስራት አደጋው የሚቀንስበትን መንገድ ማስተካከል ይገባል።

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ወጪ ምርትን መጨመርና ተገቢውን የገቢ ግብር መሰብሰብ በእነዚህና በመሳሰሉት ገቢ አመንጪ ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ከተቻለ ስጋቱ ቢያጋጥም እንኳን አስደንጋጭ አደጋ ሆኖ አይቀጥልም። በጊዜ ሂደት እየሳሳና እየመነመነ ሄዶ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው እዳ ሳይሆን ምንዳ ሆኖ ይቀጥላል። ለሁሉም ግን አንድን ነገር በጭፍኑ አይቶ ከማጣጣልና ጭራቅ አድርጎ ከመሳል ይልቅ መልካሙን አስፍቶ ወደፊት በቅንነት መራመድ ይገባል። ጭፍን ከሆነው አስተሳሰብና አመለካከት መውጣት በቀዳሚነት የምናስባትን ሀገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ያግዛል።

አዶኒስ(ከሲኤምሲ)

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You